ውሸት ምን ያህል ሀይል እንዳላት አሸባሪው ሕወሓት የኔ ዘመን ባለታሪክ ነው። እኩይ ባለታሪክ። ትላንት ዛሬና ነገ የራሳቸው የሆነ የእውነት የፍትህና የሀቅ ሚዛን አላቸው። በዚህ የጊዜ አብራክ ውስጥ ሙሉ ሆኖ ማለፍ ደግሞ የሁሉም ነፍሶች ግዴታ ነው። ምክንያቱም ሰውነት ለሌሎች መልካም የመሆን ስሪት ነውና። ይሄ እውነት የሌላቸው አንዳንድ ጎደሎ ነፍሶች አሉ። በመኖራቸው ሌሎችን የሚያስጨንቁ፣ በሰውነታቸው ለሌሎች መከራ የሆኑ ነፍሶች። ከነዚህ ነፍሶች ውስጥ አንዱ ደግሞ የአሸባሪው ሕወሓት ነፍስ ነው።
ቡድኑ እንደ ሰው አካልና ነፍስ አለው ግን ይሄንን አካልና ነፍሱን ሌሎችን ከመጥቀም ይልቅ ሌሎችን በመጉዳት ያበለጸገው ነው። ከዚህ ጎደሎ ማንነቱ ውስጥ በውሸትና በማስመሰል የታጀበውን ራቁት ማንነቱን ማንሳት ይቻላል። ከዚህ ጎደሎ ማንነቱ ውስጥ በክፋትና በተንኮል የተራመዳቸውን እኩይ ርምጃዎቹን መጥቀስ ይቻላል። የሰው ልጅ ከሁሉም ትልቁን እውነትን በሰውነቱ ላይ ማንገስ ካልቻለ ሰው የመሆን ተፈጥሮው እዛ ጋ ያበቃል።
ቡድኑ ለአመታት ብዙ ውሸቶችን ነግሮናል። በነዚህ ውሸቶች ውስጥ ደግሞ እንደ ሀገር ከመጠውለግና ከመበላሸት ባለፈ ያፈራነው መልካም ፍሬ አልነበረም። በየትኛውም ዘመን፣ ለየትኛውም ስብዕና ውሸት ትርፍ የለውም። አንዳንዶች ዋሽተው ያስታርቃሉ። እንደ ሕወሓት ያሉ ጨካኞች ግን ዋሽተው ያጣላሉ። የዛሬዋ ኢትዮጵያ በሕወሓት ብዙ ውሸት የተፈጠረች ናት። በሀገርና ህዝብ ላይ የሚደረግ ውሸት የመጨረሻው የጭካኔ ማሳያ ነው። ሀገር ሁልጊዜም እውነት መሆንን ትሻለች።
የአሸባሪው ሕወሓት የሀሰት ጉዞ ስልጣንን ከማፍቀር የጀመረ ጉዞ ነው። በውሸትና በማስመሰል ካልተራመደ ህዝብ ወዶና ፈቅዶ ስልጣን ላይ እንደማያቆየው ያውቃል። በዚህም ውሸት እየፈጠረ ህዝብን ከህዝብ አባልቷል ። ውሸትና ሕወሓት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው። አንዳቸው ያላንዳቸው አይኖሩም ። ውሸት አባትሽ ማነው ቢሏት ሕወሓት እንደምትልና ሕወሓትም ባለውለታህ ማነች ቢሉት ውሸት እንደሚል ተጠራጣሪ ይኖራል ብዬ አላስብም።
ይሄ የሰብዐዊነት ዝቅጠት ነው። በድሀ ሀገርና በህዝብ ላይ መጨከን ምን የሚሉት ፈሊጥ እንደሆነ አልደረስኩበትም። እንዴት አእምሮ ያለው ለዛ ውም መሪ የሆነ ቡድን ሀያ ሰባት አመት ሙሉ ሀገርና ህዝብን ይዋሻል? በሕወሓት ልብ ውስጥ ሀገርና ህዝብ የሉም ። በልቡ ውስጥ ሀገሩን የፈጠረ ሰው ሀገር የሚያጸና እንጂ ሀገር የሚያፈርስ፣ ታሪክ የሚያበላሽ ሀሳብ አይኖረውም። በአእምሮው ውስጥ ህዝብ የፈጠረ ሰው ትውልድ የሚያጀግን እንጂ የሚያሸማቅቅ እሳቤ አይኖረውም።
ውሸት የክህደት የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ሕወሓት በየቀኑ ሀገሩን እንደካዳት ነው። በየቀኑ ህዝቡን እንደ ዋሸ ነው። ዛሬ ላይ ዘለን መሻገር ያቃተን ገደል እንኳን ሕወሓት በውሸት የቆፈረው ገደል ነው። ለቡድኑ እውነት እንጂ ውሸት ምኑም አይደለም። በትንሽ ውሸት ሀገር በጥብጦ ያውቃል። የህዝቦችን የዘመናት ፍቅር በራስ ወዳድነት በጠነሰሳት ትንሽዬ ሀሰት ችግር ውስጥ ከቷል ። እንሆ ዛሬም የውሸት ትርክቶቹን እንደቀጠለበት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ምን አይነት መልክ እንደነበረው በደንብ አውቃለሁ። በኢትዮጵያዊነት ላይ የፍቅርን ዋጋ የቱን ያህል እንደሆነም አውቃለሁ። ከሕወሓት በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ በአባቶቻችን የፍቅርና የሀቅ ሚዛን የተሰፈረች፣ በጽናት የተገመደች ነበረች። ይሄ መልክ ይናፍቀኛል። ይሄ ሀቅ… ይሄ ሰብዕና ይታወሰኛል። ከሕወሓት በኋላ ሁሉም ነገር ሌላ ሆነ።
የአባቶቻችን አደራ ተበላ። አንድነታችንና ህብረታችን በስልጣን ጥመኞች አደፈ። ፍቅራችንና መደጋገፋችን በራስ ወዳድ ቡድኖች እንዳልነበረ ሆነ። በጣም የሚገርመው ደግሞ ዛሬም ድረስ በነዚህ ወሮበሎች መሰቃየታችን ነው። ኢትዮጵያዊ ሆኖ በሕወሓት የሀሰት ጅራፍ ያልተገረፈ የለም። ቡድኑ ከትላንት እስከዛሬ የኢትዮጵያ ጠር ነው። እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ግለሰብ ብዙ ነገር አሳጥቶናል።
የሕወሓት ቡድን በእውቀት ሳይሆን በውሸት፣ በምክንያት ሳይሆን በሸፍጥ ነው ሀገር ሲመራ የነበረው። በዚህም የዛሬዋን ጉስቋላ ሀገር ፈጥሯል። ሀገር በእውቀት ስትመራና በሸፍት ስትመራ አንድ አይደለም። በሸፍጥ ስትመራ እውቀት ሁልጊዜም መዳረሻው ጥፋትና ውድቀት ነው ።
የዛሬ መከራዎቻችን፣ የዛሬ መገፋፋታችን እነዛ የሸፍጥ አስተሳሰቦች በእኔነት ስሜት ያበዱ እሳቤዎች የፈጠሯቸው ናቸው። እኔና እናንተ እንኳን የእነዛ አስተሳሰቦች ውጤቶች ላለመሆናችን መተማመኛ የለንም ። ይሄ አያናድድም ትላላችሁ? ዛሬ ላይ ብልሽትሽታችን የወጣው እኮ ያ እኩይ አስተሳሰብ ስለተጫነብን ነው። ዛሬ ላይ ውጥንቅጣችን የወጣው እኮ ትላንት ላይ በተነገረን የውሸት ወሬ ነው። የሕወሓት የሴራ ፖለቲካ በእያንዳንዳችን ቤት ፍሬውን አፍርቶ አለ…ይሄ ፍሬ አፍርቶ እንዳይባዛ ዛሬ ላይ በእውነት ልናሸንፈው ይገባል። ዛሬ ለሁላችንም መልካም ቀን ነው።
ትላንትን አሸንፈን አዲስ ታሪክና አዲስ ማንነት የምንፈጥርበት ጊዜ ላይ ነን። ሕወሓትንና አስተሳሰቡን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥለን አዲስ ሀገርና አዲስ ትውልድ የምንፈጥርበት ሰሞን ላይ ነን። ሁላችንም ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ስንል ይሄን መልካም የለውጥ ጊዜ መጠቀም ይኖርብናል ።
ሀገር አስተሳሰብ ናት… ሀገር የእውነት ሙዳይ ናት። ውሸት በሆንን ቁጥር እያጐሳቆልናት እንሄዳለን። እውነት በሆንን ቁጥር ደግሞ እያጸናናት እንሄዳለን። ሀገራችንን በእውነት መፍጠር የሁላችንም ግዴታ ነው። በሕወሓት የውሸት ትርክት የቆሸሸችውን ሀገራችንን በእኛ የእውነት ፍቅር ልናነጻት ይገባል።
መርህ አልባ ስሜታዊ እሳቤ ለሀገር እጅግ አደገኛ የሆነ ነገር ነው። ሕወሓት ከትላንት እስከዛሬ ሀገርና ህዝብ ሲመራ የነበረው በዚህ ቁመና ውስጥ ሆኖ ነበር። በጣም የሚገርመው ደግሞ ዛሬም በዚህ ቁመና ውስጥ መሆኑ ነው። ለዚህም ነው በውሸትና በማስመሰል የተካነው። ለዚህም ነው በንጹሀን ሞትና መፈናቀል ስልጣን ለመያዝ የሚታትረው።
ሀገር በውሸት ስትመራ ትውልድ የውሸት ሀይልን ነው የሚያመነጨው። የዘራነውን ስለ ምናጭድ ሌላ ምኞትና ራዕይ አይኖረንም ቢኖረን እንኳን ዋጋ ያስከፍለናል። ዛሬ ላይ በዚህ በጠላት ቡድን በተዘራብን ዘር ነው ከለውጥ ይልቅ ነውጥ፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ ወርሶን ያለቦታችን የቆምነው።
ለዚህም ነው ከመነጋገር ይልቅ ጎራ መፍጠር፣ ከመሞጋገስ ይልቅ መተቻቸት ግብራችን የሆነው። ለዚህም ነው ከይቅርታ ይልቅ በቀል፣ ከእውነት ይልቅ ማስመሰል የገነነብን። ሕወሓት ትውልዱ ላይ መርዝ ነው የረጨበት። ያለፉት ሀያ ሰባት አመታት ለኢትዮጵያውያን የመክሰር ዘመናት ነበሩ።
ትውልዱ ቀና እንዳይል በውሸት ትርክት የተተበተበበት። በተጠናና በተመረመረ መርዛም ሀሳብ ታሪክ የተበላሸበት ዘመነ ፍዳ። ዛሬም በዚህ እውነት ውስጥ ነን። ውሸት ለሕወሓት ምኑም አይደለም። ያደገበትና ጥርሱን የነቀለበት ነው። አንዳንድ ጊዜ የሕወሓትን ውሸት ሳደምጥ የሰው ልጅ በዚህ ልክ መዋሸት መቻሉ ያስደንቀኛል።
በሕወሓት ውሸት ውስጥ የሚገርም ድራማዊ ማስመሰል አለ። የበግ ለምድ ለብሶ እኔ የሰላም ሀዋርያ ነኝ ተከተለኝ ሊልህ ይችላል። ፍጹም እንዳትጠራጠር በሚያደርግ መልኩ ሊያሳምንህ ይችላል። ግን ሁሉም ድርጊቶቹ ከውሸት የዘለለ አንድም እውነትነት የሌላቸው መሆናቸው ነው።
ቡድኑ ስላልኖረበት የእውነትን ዋጋ አያውቀ ውም። በውሸትና በማጭበርበር ምን ያህል እንደተራመደ ያለፉት የስልጣን ዘመኑ በቂ ማስረጃዎች ናቸው ። በዚህ ባሳለፍንው አንድ አመት ውስጥ እንኳን ጉድ የሚያስብል ነጭ ውሸት እየዋሸ ሊያሳምነን ሲሞክር እንደነበር ሁላችንም እናውቀዋለን።
በአሻባሪው ሕወሓት ልብ ውስጥ እውቀትና አመክንዩ ሀሳብ የለም። ሁሌም የሚራመደው በውሸት ነው። ከክፋት ባለፈ ቁም ነገር የማይሰሩ ጸዐዳ እጆች አሉት። ለእውነት የሰነፈ ለማስመሰል የበረታ ረጅም ምላስ አለው። ሰብዐዊነት ምኑም ነው። ብቸኛ ደስታው በሌሎች ሞትና ጉስቁልና ስልጣን መያዝ ነው።
በዚህ አንድ አመት ውስጥ እንኳን በርካታ የውሸት ዜናዎችን ስንሰማ ነበር። ሆን ብሎ ፈጥሮ የሚያወራቸው የሀሰት ወሬዎች በርካታ ናቸው። በአፋርና በአማራ ክልሎች በአደባባይ በንጹሀን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ወንጀል ያልፈጸመው ያህል እንደ ተበዳይ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጮኸው እሱ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ሜዳ ላይ እያሳደረ ተበደልኩ ባዩ እሱ ነው። ህጻናትን ያለርህራሄ እየጨፈጨፈ፣ ወጣት ሴቶችን እየደፈረ ተጠቃሁ የሚለው እሱ ነው።
ቡድኑ ምን አይነት ማንነት እንዳለው ያለፉትን ሀያ ሰባት አመታት ትተን ያለፉትን አስራ ሁለት ወራቶች ማየቱ ብቻ በቂ ነው። በማይካድራና በአፋር የሆነው መቼም የሚረሳ አይደለም። ዜጎች በማንነታቸው እየታደኑ እንደከብት የሚታ ረዱበትን ጊዜ አሳልፈናል። በሰሜን ወሎ፣ በጎንደር በዋግ ህምራ፣ በአፋር ክልሎች እና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉትን የሕወሓት ተጠቂ ንጹሀን ማየቱ ዛሬ ላይ ይሄን ቡድን ለፍርድ ለማቅረብ በቂ ማስረጃ ነው።
አለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን የሕወሓትን የድረሱልኝ ጩኸት እንጂ የህዝቡን የድረሱልኝ ጩኸት ለመስማት ዝግጁ አይደለም። በጣም የሚገርመው ደግሞ አለም ሕወሓት ምን አይነት ማንነት እንዳለው እያወቀች ግን ዛሬም ከውሸትና ከማስመሰል ድራማው ጎን እንደቆመች መሆኗ ነው ።
አሜሪካና መሰል ሀያላኖቹ ቡድኑ ዝም ሲል ዝም የሚሉ ሲጮህ አብረው የሚጮሁ ሆነዋል። ለዚህም በቡድኑ ወደ ስልጣን መም ጣት የሚያተርፉት ብዙ ትርፍ ስለ መኖሩ ብዙም መጠየቅ የሚያስፈልገው ጥያቄ አይደለም። እኛ ግን ለአሻባሪው ሕወሓት የውሸት ዜና ቦታ ሳንሰጥ ሀገራችንን በእውነትና ከዚህ በሚመነጭ ቁርጠኝነት ለማገልገል እንነሳ እላለሁ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2014