<<በህግ አምላክ!>> የሚለው ሀረግ የአገሬ ሰው ካልተገባ ተግባሩ አልያም እርምጃው የሚያስቆመው ጥሩ ልምድ ሆኖ ዘመናት ተሻግሯል፡፡ ይህ ህግ ካልተገባ ድርጊት የሚያቅብ ተገቢ ካልሆነ ተግባር ገቺ መሆኑን አመላካች ነው፡፡
ሰዎች መተዳደሪያቸው ይሆን ዘንድ የሚያወጡት መመሪያ አልያም ህግ ለዘርፈ ብዙ ተግባርና እንቅስቃሴያቸው መከወኛ ሀዲድ ነው፡፡ ያ ሀዲድ ደግሞ ጉዳዮችን በስርዓት መምራት የሚያስችላቸው የተቀነበበ መርህ ነው፡፡ የሚገጥማቸው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳያቸው ሁሉ እንደ አገራዊ ተጨባጭ ሁናቴ ባረቀቁትና አምነው ባፀደቁት ህግ ይመራሉ፡፡ ሁሉም በዚያ ስር ተጠልሎ ስርዓታዊ ተግባሩን ይከውናል፡፡
የህግ የበላይነት መከበሩ ከሁሉ በላቀ የአክባሪው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ደህንነት ያረጋግጣል፡፡ ህዝብ ለህግ ሲገዛ፤ አገር ላይ የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሰላም ይሰፍናል። ሁሉም ሀላፊነትና ግዴታውን በስርዓት ይወጣልና ዝንፈቶች እጅጉን ይቀንሳሉ፡፡ ሰዎች መብታቸውን አስከብረው የሌላውንም መብት አክብረው በሚፈቀድላቸው ተጠቅ መው፤ የተከለከሉትን ከማድረግ ይቆጠባሉ፡፡
በዚህም የህግ ተገዢነታቸው ያረጋግጣሉ። እዚህ ውስጥ ሁሉም በተመሳሳይ መልኩ የተቀመጠና በአገሪቱ የተደነገገ ህግ እኩል ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ለማህበራዊ ስክነት መነሻ፣ ለፖለቲካዊ መረጋጋት ምክንያትና ለኢኮኖሚ ምጥቀት አስተማማኝ ዋስትና ይሰጣል፡፡
ህገ ስርዓት በተከበረበትና ህግ የበላይ በሆነበት ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ስልጣኔ ያብባል፡፡ ዜጎች ከህግ ጥላ ስር ሆነው በዚያ አምነው ባፀደቁት ህግ ይዳኛሉ። ያለ ልዩነት እኩል በሆነ መልኩ ዜጎች ከአገራቸው ሀብት በፍትሀዊነት ይጠቀማሉ፤ ባበረከቱት ልክ ወደ ለውጥ ይቀርባሉ፡፡
ሁሉም ለህግ የሚገዛ ነውና አንዱ ተነስቶ እኔ ስለምችል ሌላውን ልደፍጥጥ አይልም፡፡ መሻቱን በስርዓት ይጠይቃል፤ ፍላጎቱን በተገቢው መልኩ ያንፀባርቃል፡፡ ምክንያቱም ተጠያቂነት እንዳለበት ይረዳል፡፡
የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ማለት የአገርን ህልውና እውን ማድረግ ነው፡፡ ያለ ህግ የበላይነት የሚተገበር ፍትሀዊነት፣ የሚረጋገጥ መብትና የሚጎናፀፉት ሉዓላዊነት ፈፅሞ የለምና። በስርዓትን የሚመራ በህግ የሚተዳደር ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጡ ይፋጠናል፡፡ ምክንያቱም ስርዓት አልበኝነት እና የህግ ጥሰት እዚህ ማህበረሰብ ላይ ከቶም አይኖርምና፡፡ ጉዳዮች የሚመሩት ስርዓት ባለው መንገድ ነውና አይስተጓጎሉም፤ ሰዎች በመብታቸው ረገድ የጎላ ጥሰት አይፈፀምባቸውም፡፡ በመብታቸው ልክ ግዴታቸውም ይወጣሉ፡፡ የራሳቸውን መብት ያስከብራሉ የሌላውን መብት አይፃረሩም፡፡
እኛ የዚህች አገር ዜጎች አገሪቱ ላወጣቻቸው ህጎች ተገዢ መሆን ግድ የሚለን ለዚህ ነው፡፡ የዜጎች ህግ የማክበርና የህግ አስከባሪው አካል ህጋዊነት መረጋገጥ እንደአገር የሚያስገኝልን ትሩፋት ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን በሰከነ መልኩ ይመሩ ዘንድ አገሪቱ ያወጣቻቸው ህጎች በዜጎች ያለማወላወል ሲተገበሩ ነው፡፡
በማን አለብኝነት የራሳችን ፍላጎት ላይ ተመርኩዘን የሌሎችን መብት ከመጣስ እንድንቆጠብ የሚያደርገን ህግ ነው፡፡ እንደ ዜጋ በሚሰጡን መብቶች የመጠቀማችን ያህል አገራዊና አለማቀፋዊ ህጎች የማክበር ልምድ ሊኖረን ይገባል። በዚህች አገር ውስጥ እስከኖርን በአገሪቱ ህግና በሚወጡ መመሪያዎች የመመራት ግዴታ አለብን። ተግባራችን ህጋዊ፣ ጥያቄያችን አግባባዊ፣ ተቃውሞና ድጋፋችን ተገቢው መንገድ በተከተለ መልኩ ሊሆን ግድ ይላል፡፡
ህግ ሲጣስ፣ በማን አለብኝነት ሁሉም ያሻኝን ላድርግ ሲል የህግ ድንበር ሲስት ውጤቱ የከፋ ይሆናል፡፡ ስርዓት አልበኝነት ሲንሰራፋ፣ ሰላምና መረጋጋት ሲርቅ የሰዎች የመኖር ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ያለ ህግ መስከን ያለ ስምምነት ሰላም ያለ መግባባት ማህበራዊ ግንኙነት እውን ማድረግ አይችልም፡፡ ህገወጥ አሰራር መከተል ከተግባቦት ያርቃል፤ ህግን አለማክበር ወደተሳሳተ አቅጣጫ ያደርሳል፡፡
ስርዓት አልበኝነት መንሰራፋት ወይም የህግ የበላይነት አለመከበር ለፍትህ መጓደል ምክንያት፣ ለሰላም እጦት ሰበብ፣ ለሽብርና ሁካታ ዋንኛ መንስዔ ነው፡፡ ሁሉም የሚዳኘውና መብትና ግዴታው የሚቀነበብበት ህግ የበላይነቱ አምኖ መቀበል የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡ ለአንድ አገር ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስርዓት መመሪያ የሆነው ህግ ከተጣሰ፤ ስርዓት ይፋለሳል። በመርህ ደረጃ የሚያስማማና የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያመላክት ምንም ነገር ሊኖር አይችልምና የሰከነ ስርዓት ሊኖር ፈፅሞ አይችልም፡፡
ስለዚህም እያንዳንዳችን የህግ የበላይነት አምነን ተቀብለን ሁላችንም ከህግ በታች መሆናችንን አውቀን በዚያ ጥላ ስር መሆን የውዴታ ግዴታችን ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያዊ ከሆንን ኢትዮጵያ ላወጣቻቸው ህጎች ተገዢ ልንሆን ይገባል፡፡ ከህግ ከፍ ያለ አቋም ከመርህ የወጣ አመለካከት መጣረስና የሌላውን መብት መደፍጠጥ ላይ የሚያደርስ የተሳሳተ መንገድ ነውና ወደ ቦታ መመለስ ይገባል፡፡
በየትኛው የአገሪቱ ክፍል እንገኝ አገሪቱ ያወጣቻቸው ህጎች ይገዙናል፡፡ ከማንኛውም ማህበረሰብ እንገኝ ማህበራዊነት የሚያጣርስና ህገወጥነትን የሚያመላክት ተግባር መፈፀማችን ያስጠይቀናል፡፡ እንደ ዜጋ የተሰጠን መብትና ግዴታ በወጉ ለይተን በመብታችን መጠቀም ግዴታችንን ደግሞ ተገቢ በሆነ መልኩ መወጣት ይኖርብናል፡፡ ስርዓት አልበኝነት በሰፈረበት ምድር መብቴን ብሎ መጠየቅ፤ ህግ ባልተከበረበት አገር በሰላም ልኑር ብሎ ማሰብ እጅጉን የተሳሳተ እሳቤ ነው፡፡
ለማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን ስምረት የህግ የበላይነት መከበር የዜጎች ህግን ማክበር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለንተናዊ ለውጥና ማህበራዊ ብልፅግና እንዲረጋገጥ ሁላችንም እንፈልጋለንና ለዚህ የሚያዳርስ ስርዓት መከተል ይገባል፡፡ ስለዚህም ነው ለህግ ተገዢ መሆን የሚገባን፡፡ እያንዳንዳችን አንዳችን ለሌላችን ለውጥ ብሎም ለአገራችን ህዳሴ መረጋገጥ ሀላፊነት አለብን። የሚጠበቅብን አገራዊ ግዴታና ሀላፊነት በአግባቡ መወጣትና ለአገራዊ ህግ ተገዢ መሆን ደግሞ ለዚህ ዋንኛ መሻገሪያ መንገድ ነው፡፡
ሁላችን ለህግ ተገዢ ስንሆን አገራችን ሰላም ህዝባችን የተረጋጋ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን የሰከኑ ይሆናሉ፡፡ የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ህዝብ ህጋው አካሄድን ሲከተል መንግስት መንግስታዊ ሀላፊነቱን ሲወጣ ዲሞክራሲያችን ይለመልማል፣ ዕድገታችን ይፋጠናል፣ የምናስበው አገራዊ ለውጥ ወደኛ ይቀርባል። አስተማማኝ የሆነ ስርዓት ተፈጥሮ ማየት የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠናክረው መመልከት እንደ ዜጋ እንፈልጋለንና መብትና ግዴታችንን ጠንቅቀን መረዳትና በዚያ መሰረት መንቃቀስ ይጠበቅብናል፡፡
ነገር ግን እንደ ህዝብ ያለብንን ግዴታ መወጣትና የሌላውን መብት አክብረን በዚያ ካልተንቀሳቀስንና የህግ የበላይነት አምነን ካልተቀበልን ሰላማችን መደፍረሱ አይቀሬ ነው፡፡ አሁን ላይ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ምልክቶች ዋንኛ መነሻም የህግ የበላይነት አመኖ መቀበልና በዚያ ውስጥ መንቀሳቀስ አለመቻል ነው። በእርግጥ የብዝሀነታችን ያህል የብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩንና እንዲስተካከሉ የምንፈልጋቸው ጉዳዮች በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ያንን ህግን በሚፃረር መልኩ ማንፀባረቅ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም፡፡
ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን ጤናማ ይሆኑ ዘንድ ለሁሉም ስርዓት መበጀትና በስርዓት መመራት ዋንኛ ጉዳይ ነው፡፡ ህጋዊ ስርዓት ጉዳዮችን በወጉ ይመራል። ስርዓት አልበኝነት በአንፃሩ ስርዓታዊነትን ያጠፋል፡፡ ህግ የሰዎች ፈቃድና ተዓቅቦ መብትና ግዴታ አመላካች መመሪያ ነውና ህግ ማክበር የሁላችንም ሀላፊነት ነው፡፡ እያንዳንዳችን በዚህች አገር ጥላ ስር እስከሆን ድረስ የአገሪቱ ህጎችን ማክበርና ለዚያ ተገዢ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ ማንም መቼም ቢሆን ከህግ በላይ አይደለም፤ አይሆንምም። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014