የ2022 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች መነሻቸውን በኳታር መዲና ዶሃ አድርገው በእንግሊዝ በርሚንግሃም፣ በአሜሪካ ዩጂን፣ በሞሮኮ ራባት፣ በጣሊያን ሮም ከተካሄዱ በኋላ ከትናንት በስቲያ ምሽት ስድስተኛዋ የውድድሩ መዳረሻ ከተማ በሆነችው የኖርዌይ መዲና ኦስሎ በተለያዩ ርቀቶች ፉክክሮችን አስተናግዷል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሳተፉበት በዚህ የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ የአምስት ሺ ሜትር ውድድር በሁለቱም ጾታ ከአንድ እስከ ሶስት ባለው ደረጃ በማጠናቀቅ በርቀቱ ነግሰዋል።
ባለፉት አመታት በመካከለኛ ርቀቶች በተለይም በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ውድድር አስደናቂ ብቃት በማሳየት ትልቅ ተስፋ የተጣለባት ወጣቷ አትሌት ዳዊት ስዩም ልዩ ተሰጥኦ ባሳየችበት ርቀት በውጤታማነቷ ገፍታ በአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናና ኦሊምፒክን በመሳሰሉ መድረኮች ጎልታ መታየት አልቻለችም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህች ድንቅ አትሌት በአዲስ ርቀት ውጤታማ ሆና ብቅ ብላለች። በአምስት ሺ ሜትር ልምድ ባይኖራትም ውጤታማ እየሆነች የምትገኘው አትሌት ዳዊት በኦስሎው ዳይመንድ ሊግ በርቀቱ ብዙ ልምድ ያካበቱና ቁንጮ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ጭምር በማሸነፍ አስደናቂ ውጤት አስመዝግባለች።
በርቀቱ በአለም ላይ ትልቅ ስምና ዝና ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገራት አትሌቶች በተሳተፉበት የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ ውድድር አንድ ሺ ሜትሩን እጅግ በጠንካራ ፉክክር በ2:53:83 ማገባደድ የቻሉት ከዋክብት አትሌቶች ሁለት ሺ ሜትሩንም ፈጣን በሆነ 5:52:33 ሸፍነዋል። በበርካታ ከዋክብት አትሌቶች እስከ መጨረሻው ዙር በአስደናቂ ፉክክር የታጀበውን ውድድር ወጣቷ አትሌት ዳዊት ለማጠናቀቅ አንድ ዙር ሲቀራት አፈትልካ በመውጣት ድሉን ጨብጣለች። በርቀቱ ከአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እስከ ኦሊምፒክ መድረኮች መንገስ የቻሉ እንደ ለተሰንበት ግደይ፣ ጉዳፍ ጸጋይና አልማዝ አያና የመሳሰሉ ድንቅ ድንቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድሩ አንድ ዙር እስኪቀረው ያሳዩት ጠንካራ ፉክክር በመጨረሻም ለዳዊት አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት እጅ ሰጥቷል።
በሪዮ ኦሊምፒክ በ10ና 5ሺ ሜትር የወርቅና የብር ሜዳሊያ ካጠለቀች በኋላ በወሊድና በጉዳት ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከውድድር ርቃ የተመለሰችው አልማዝ አያና በኦስሎው ምሽት ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኗን ዳግም ብታሳይም ከእሷ በኋላ በርቀቱ የነገሱ ኢትዮጵያውያንን መቋቋም አልቻለችም። መጨረሻው ዙር ላይ ከሜዳሊያ ፉክክሩ የወጣችው አልማዝን ወደ ኋላ ትተው የአሸናፊነት ክሩን ለመበጠስ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ያደረጉት የቶኩዮ ኦሊምፒክ የ10ና 5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዎቹ ጉዳፍና ለተሰንበት አዲሷን የርቀቱ ኮከብ ማቆም አልተቻላቸውም። በዚህም ዳዊት 14:25:84 በሆነ ሰአት ጣፋጭ ድል ልታስመዘግብ ችላለች። ዳዊትን ተከትላ ጉዳፍ 14:26:69 በሆነ ሰአት ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ የ10ና 5ሺ ሜትር የአለም ክብረወሰን በእጇ የሚገኘው ለተሰንበት 14:26:92 በሆነ ሰአት ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ፈጽማለች።
በዚህ ውድድር የታየው አስደናቂ ፉክክር የአለም ክብረወሰን እንዲሻሻል በቂ ባይሆንም በርቀቱ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ሰባት አትሌቶች ከ14:35 በታች ማጠናቀቅ የቻሉበት ሆኗል። በተመሳሳይ ስምንት ያህል አትሌቶችም ከ14:40 በታች በማጠናቀቅ የኦስሎን ዳይመንድ ሊግ የማይረሳ አድርገውታል።
የኦስሎው የዳይመንድ ሊግ ምሽት በተመሳሳይ ርቀት በወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በግል ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት በማጠናቀቅ የአረንጓዴውን ጎርፍ ታሪክ ደግመዋል። በሴቶቹ ውድድር በ1500 ሜትር የምትታወቀው አትሌት የ5ሺ ሜትር ቁንጮዎቹን ስታሸንፍ በወንዶቹ ተመሳሳይ ውድድር በተቃራኒው በ5ሺ ሜትር የሚታወቀው አትሌት በ1500 ሜትር ገናና ስም ያለውን አትሌት የረታበት ውጤት ተመዝግቧል።
ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ የመጠባበቅና የመፈራራት ድባብ የተስተዋለበት ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር መጨረሻ ላይ የቻለ እንዲያሸንፍ አትሌቶቹ ፍላጎት እንደነበራቸው ያስታውቅ ነበር። የሁለት ጊዜ የአለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የ1500 ሜትር አሸናፊው ሳሙኤል ተፈራ ፉክክሩን እየመራ 3ሺ ሜትሩን በ7:54:39 አገባዷል። ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ በመመለስ አጨራረስ ላይ ጉልበት ቆጥቦ ለማፈትለክ የሞከረው ሳሙኤል እቅዱ በሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጥላሁን ሀይሌ ከሽፏል። በአምስት ሺ ሜትር ባለፉት አመታት ተስፋ ተጥሎባቸው ከነበሩ አትሌቶች አንዱ የነበረው ጥላሁን በበርካታ ውድድሮች ከአሸናፊነት ርቆ ቢቆይም ኦስሎ ላይ በ13:03:51 ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል አስመዝግቧል። ፉክክሩን በጥሩ መንገድ ሲመራ ቆይቶ አጨራረስ ላይ እቅዱ የከሸፈበት ሳሙኤል ተፈራ 13:04:35 በሆነ ሰአት የሁለተኛነቱን ደረጃ አላጣውም። እሱን ተከትሎም ስኬታማው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ስኬታማው አትሌት ጌትነት ዋለ 13:04:48 በሆነ ሰአት ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በርቀቱ የኢትዮጵያውያን የበላይነት ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም