የዛሬው የዘመን እንግዳችን ከጉልበት ሰራተኝነት ተነስቶ ዓለምአቀፍ ሼፍ መሆን የቻለ ወጣት ነው። ትውልዱም ሆነ እድገቱ አዲስ አበባ በተለምዶ የካ ሚካኤል በግ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው አሁን ላይ በፈረሰው ዘርፈሸዋል ትምህርት ቤት ሲሆን፤ በምስራቅ አጠቃላይ እና በኮከበፅባህ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡
ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የተፈጠረው ይህ ወጣት፤ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በተለይ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በጽዳት ባለሙያነት የሚሰሩትን እናቱን በማገዝ ነው፡፡ እንደ ልጅ መጫወት ሳያምረው ከማጀት እስከ ደጅ የእናቱ ምርኩዝ በመሆን ኑራቸውን ለመለወጥ ሲል የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ ጀምሮ፤ በሸክም እና በሌሎችም የጉልበት ሥራዎች ላይ ከመሣተፍ በተጨማሪ በግለሰቦች ቤት በቤት ሰራተኝነት ሳይቀር ተቀጥሮ በመስራት የእናቱን የኢኮኖሚ ቀዳዳ ለመሸፈን፤ ትምህርቱን ለመማር ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡
ገና በለጋ እድሜው ሕይወት ክፉ ፊቷን የሰጠችው እንግዳችን ከቅርብ ዘመድ አዝማድ ጀምሮ ብዙ መገፋትንና መናቅንን ጭምር እያስተናገደ አድጓል፡፡ በልጅነት ጫንቃው የተሸከማቸው ተደራራቢ ችግሮች በትምህርቱ ዘልቆ እንዳይሄድ ገድበውታል፡፡ በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ፤ ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን ከሰው ያገኙትን 300 ብር ይዘው ዶሮ እርባታ ጀመረ፡፡
ዶሮዎቹ ደህና ማደግ ሲጀምሩ በሌሊት አውሬ በልቶ ጨረሰበት፤ ልፋቱ መና ቀረ፡፡ ለችግር እጅ መስጠት የማያውቀው ይህ ሰው ግለሰቦች ቤት በመቀጠር ምግብ ከማብሰል ጀምሮ ልብስ እስከማጠብ ድረስ እየሰራ በሚያገኛት ገንዘብ እናቱንና ራሱን መደጎም ያዘ፡፡ ኬክ ቤት ተቀጥሮ ዳቦ መጋገር ለመደ፡፡ ቀጠለና አንድ የግል ኮሌጅ በመግባት በምግብ ዝግጅት ዲፕሎማውን አገኘ፡፡ በተማረበት ሙያ ተቀጥሮ ከመሥራት ጀምሮ የራሱን ሬስቶራንት እስከመክፈትና ቀጥሮ እስከማሠራት ደረሰ፡፡
ይሁንና የእንግዳችን ውጣ ውረድ አላበቃም፤ የከፈታት ሬስቶራንት ትርፋማ ሆና መቀጠል አልቻለችም። ህልውናዋን ለማቆየት ሲል ብዙ ተንገታገተ፡፡ በመጨረሻ ግን ለስደት እጁን ሰጠ፡፡ በስፔናውያን ወዳጆቹ የቀረበለትን የጉብኝት ጥያቄ ተቀብሎ ስፔን ዘለቀ፤ ቀጠለናም ወደ ጀርመን አቀና፡፡ መንገዶቹ ግን አሁንም አልጋ በአልጋ አልነበሩም፤ በሰው ሀገር ማደሪያ ከማጣትና በካምፕ አስከፊ ኑሮን በመምራት ጭምር ሕይወቱን ገፋ፡፡
የጀርመን ነዋሪነት መታወቂያውን ካገኘ በኋላ ግን እድል በሯን ከፈተችለት፡፡ ቋንቋቸውን ትምህርት ቤት ገብቶ ተማረ፡፡ በሀገሩ ያገኛትን የምግብ ሥራ ሙያ እስከ ዓለምአቀፍ ሼፍ የሚያደርገውን ዲፕሎማ አገኘ፡፡ አሁን ላይ በጀርመን ስመጥር ከሆኑ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች መካከል በአንደኛው በሼፍነት ተቀጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የዛሬው የዘመን እንግዳችን ኢንተርናሽናል ሼፍ አንተነህ ድፋባቸው ኮረና የሰጠውን የእረፍት ጊዜ በመጠቀም በሕይወት ዘመኑ ያሳለፈው ውጣ ውረድ ፤ ማጣት ማግኘት ለሌሎች ጥሩ አስተማሪ ትሆናለች ብሎ በማሰብ በመፅሃፍ መልኩ ሰንዶ በማዘጋጀት #ስደተኛው ሼፍ$ በሚል ርዕስ ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ በኢትዮጵያ ታላላቅ ሃያሲያን እጅ ያረፈባት ይህችው መፅሃፍ በአንባቢያን ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ጊዜ አልወሰደባትም፡፡ ከጠበቀው ጊዜ ፈጥናም የመጀመሪያው ዙር ህትመት ሙልጭ ብሎ ተሸጠለት፡፡
በቅርቡ ደግሞ ይህችኑ መጽሐፍ በጀርመንኛ ቋንቋ በማስተርጎምና በማሳተም ዓለምአቀፉን የገበያ መረጃ መረብ አማዞንን መቀላቀል ችላለች፡፡ በቅርቡ ደግሞ ወደ እንግሊዝኛ በመተርጎም እንዲሁም በሆቴል ኢንዱስትሪው ዙሪያ የሚያትት ሌላ አዲስ መጽሐፍ በማስተርጎም ለአንባቢያን ለማድረስ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ እንግዳችን በሕይወት ውጣ ውረዱና በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስቲ ስለአስተዳደግህ አጫውተንና ውይይታችን እንጀምር?
ኢንተርናሽናል ሼፍ አንተነህ፡– አባቴ የቀድሞ ሠራዊት አባል የነበረ ሲሆን እናቴ ደግሞ በአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ በጽዳት ሰራተኝነት ታገለግል ነበር። እኔም ያደኩት በጣም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች በመሆኑ ያደኩት በድህነት ነው። በዚህ ምክንያት የልጅነት ሕይወት ለእኔ ቀላል አልነበረም፡፡ ፈተናውና ችግሩ የሚጀምረው ይህችን ዓለም ከተቀላቀልኩበት እለት ጀምሮ ነው፡፡ በተለያዩ መድረኮች ላይ እንደተናገርኩት እንደሰው ለመኖር ስል ብቻ ብዙ ፈተናዎች ገና በጨቅላ እድሜዬ ተጋፍጫለሁ፡፡
የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ብሆንም ወድቆብኝ የነበረው ብዙ ሃላፊነት ነበር፡፡ ብዙ ጊዜዬን የማጠፋው እናቴን በመርዳት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርቴን በአግባቡ መከታተል አልቻልኩም ነበር። እውነቱን ለመናገር አሁን ላይ ያለሁበት ደረጃ ለመድረስ ከእድሜዬ በላይ ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ። ከልጅነቴ ጀምሮ ራሴን ለመቻል ብዙ ዝቅተኛ ሥራዎችን ሞክሪያለሁ፡፡ ይሁንና እነዚህ ሥራዎች እንደኪሣራ ሳይሆን የምቆጥራቸው የሕይወት መንገዴ አድርጌ ነው፡፡ ከቀን ሥራ ጀምሮ ፤ ሰው ቤትም በቤት ሰራተኝነት ተቀጥሬ አውቃለሁ፡፡ በተለይ በቀን ሥራ የሠራሁት ለረጅም ጊዜ ነው፡፡
አያት የመኖሪያ መንደር ሲገነባ በቀን ስድስት ብር እየተከፈለኝ ሰርቻለሁ፡፡ በመቀጠልም ትምህርቴን እማር የነበረው ወተት በመሸከም ነበር፡፡ አስተዳደጌን አሁን ላይ ሳስበው እወደዋለሁ፡፡ ምክንያቱም በዚያ ሁኔታ ባላልፍ አሁን የደረስኩበት ደረጃ አልደርስም ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ የምረዳው ፈጣሪ በፈቀደው መንገድ ማለፌ ግድ እንደሆነ ነው ፡፡
የሚገርመው ቤታችን ለረጅም ጊዜ መብራትም ሆነ ውሃ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ለምግብ መስሪያን ጫካ በመሄድ ማገዶ እለቅማለሁ፤ እንዳውም አብዛኛው ውሎዬ ጫካ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የከብት አዛባ ጠፍጥፌ ለእናቴ ማገዶ አዘጋጅላትም ነበር፡፡ ረጅም ርቀት ተጉዤ የቦኖ ውሃ ካለበት ስፍራ ውሃም አመጣ ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ የምሰራው ግን ለአቅመ ሥራ ገና ባልበቃ የልጅነት ጉልበቴ በመሆኑ የዘወትር ስራዬ ስለነበር መላ አካሌ በጣም ተጎድቶ ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ዋናው ትኩረቴ የእናቴን ድካም መቀነስ ስለነበር፤ አጥር ከመስራት ጀምሮ ቤት ውስጥ በወንድ አይሞከሩም የሚባሉትን ስራዎች ሁሉ አጠናቅቄ እጠብቃት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ያደኩት ራሳችንን የቻልን እንድንሆን ላይ ታች እያልኩ ነው፡፡
ማንኛውንም ስራ አልንቅም፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ስራ እወዳለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ እጥር የነበረው ራሴን ለመሆንና ኑሮን ለማሸነፍ ነበር፡፡ ሰባተኛ እና ስምተኛ ክፍል እያለሁ ትምህርቴን ከፍዬ የተማርኩት የቀን ስራ እየሰራሁ ነው፡፡ አንድ ዓመት እንዳዉም ራሴ ከፍዬ የግል ትምህርት ቤት ተምሪያለሁ፡፡ የተረፈውን ገንዘብ ደግሞ የምሰጠው ለእናቴ ነው። ሁለተኛ ደረጃ ከገባሁም በኋላ በጠዋት ተነስቼ 20 ሊትር ወተት በትከሻዬ ተሸክሜ ከሾላ ገበያ እስከ አራት ኪሎ ድረስ በእግሬ እያመላለስኩኝ በወር 20 ብር አገኝ ነበር። ለትምህርት ቤት 16 ብር ከፍዬ አራት ብሯን ጮርናቄ እበላባታለሁ፡፡ የሚገርምሽ ያንን ስራ በምሰራበት ወቅት ትከሻዬ ተልጦ ሁሉ ነበር፡፡
ይሁንና በነበረብኝ የስራ ጫና ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ማለፍ ስላልቻልኩኝ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመሆን ኮልፌ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ሰዎች 300 ብር ሰጥተውን 30 ዶሮዎች ገዝተን ማርባት ጀመርን። በጥሩ ሁኔታ እያደጉና እንቁላል መጣል ሲጀምሩ አውሬ ይበላቸው ጀመር፡፡ በኋላም በሽታ ገባና ጨረሳቸው። ከዚያ ተስፋ ቆረጥኩና ኬክ ቤት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ተቀጥሬ እሰራ የነበረው ለገሃር አካባቢ በ130 ብር ነበር ፡፡
ዘወትር ከሌሊቱ 11 ሰዓት ተነስቼ የካ ከሚገኘው ቤታችን እስከ ለገሃር ድረስ በእግሬ እየሮጥኩኝ በመሄድ ዳቦ እጋግር ነበር፡፡ ዳቦ መጋገሩን እየለመድኩኝ ከመጣሁኝ በኋላ ግን ኬክ ጋጋሪው ሙያውን ሊያስተምረኝ ባለመፈለጉ እቆጭ ጀመር። ስለሆነም ራሴን ማስተማር እንዳለብኝ ወሰንኩኝ። ግን በወቅቱ ክፍያው ቀላል አልነበረምና በሰዎች ድጋፍ ተማርኩኝ፡፡ በመሃል ትምህርት ቤቱ ዋጋ ጨመረብን፤ የምከፍለው ስላልነበረኝ ግለሰብ ቤት ውስጥ የቤት ሰራተኛ ሆኜ ተቀጠርኩኝ፡፡ ምግብ እሰራለሁ፤ የህፃናት ልብስ አጥባለሁ፤ ሌሎች የቤት ስራቸውን እየሰራሁ 260 ብር በወር ይከፍሉኝ ነበር፡፡
ቤታቸው ሲኤምሲ ስለነበር የምማርበት ትምህርት ቤት ፒያሳ እመላለስ የነበረው በአውቶብስ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ገንዘቡ አይበቃኝም ነበር። በዚያ መልኩ ትምህርቴን እንደምንም ብዬ ከጨረስኩኝ በኋላ፤ አክሱም ሆቴል ለስድስት ወራት በነፃ ሠራሁ፡፡ ከዚያ ደግሞ የተወሰነ ገንዘብ እየከፈሉኝ ለአንድ ዓመት ሠራሁ፡፡ በመቀጠልም የተለያዩ ሬስቶራንቶች እየተዘዋወርኩኝ ሠርቻለሁ፡፡ በዚህ መልኩ ከልጅነት ጀምሮ በውጣ ውረድ ውስጥ ካለፍኩኝ በኋላ ዓለምአቀፍ ሼፍ ለመሆን በቅቻለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ያሳለፍከው ችግር አሁን ላለህበት ደረጃ #ጥንካሬ ሰጥቶኛል$ ብለህ ታምናለህ?
ኢንተርናሽናል ሼፍ፡– ልክ ነው፡፡ እንደነከርኩሽ እናቴ ሌሊት ከጅብ ጋር እየተጋፋች በመሄድ የምትመለሰውም ከምሽቱ 11 ሰዓት ነው፡፡ የሚገርምሽ እንዲህም ሰርታ የሚከፈላት የነበረው 40 ብር ነበር። በመሆኑም እኔ ነበርኩኝ ወፍጮ ቤት እህል ከማስፈጨት ጀምሮ በማብኳትና በመጋገር እናቴን አግዛታለሁ፡፡ እናቴ ማታ ስትመጣ የምጠብቃት ቤቱን አፅድቼና ቡና አፍልቼ ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ገበያ እሄዳለሁ፤ እንጨት እለቅማለሁ፤ እድር መክፈልና ቀብር መሄድ ራሱ የእኔ ሃላፊነቶች ነበሩ።
በዚህም ሌት- ተቀን እኛን ለማሳደግ የምትተጋውን እናቴን አሳርፌያታለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እናቴ ትደሰታለች ሌላ ጊዜ ደግሞ ትቆጣኝ ነበር። በነገራችን ላይ እናቴ በባህሪዋ ሃይለኛ ነበረች፤ በዚያ ላይ ከነበረባት የሕይወት ጉስቁልና እና ልጆችን ለብቻ ማሳደግ ምሬት ውስጥ ከቷት ነበር፡፡ እናቴ ምሬቷን ባለማወቅ የምትወጣ የነበረው እኔ ላይ ነበር፡፡ ያም ቢሆን አናቴ ለልጆቿ ብዙ ዋጋ የከፈለች ጀግና እናት ነበረች። በአጠቃላይ ግን እኔ ያንን የእናቴን ትጋት እያየሁ በማደጌ ትልቅ ጽናትና አቅም ፈጥሮልኛል ብዬ አምናሁ፡፡
እንደተባለው አሁን ላይ ያ ጊዜ እንዴት አለፈ እያልኩ አስባለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ችግሮች ደግሞ ለማመንም የሚከብዱ ነበሩ፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ልጅ ሆኖ የሰው ቤት ተቀጥሮ መስራት ቀላል አይደለም፡፡ እንዳውም እዚህ ጀርመን ያለ ሰው መጽሃፌን ካነበበ በኋላ ‹‹ብዙ ሰዎች በአንተ መንገድ ቢያልፉ ራሳቸውን ያጠፋሉ፤ አንተ ግን እድለኛ ነህ›› አለኝ። እርግጥ ነው እኔም ከፈተናው የተነሳ አንድ ሁለት ጊዜ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር፡፡ ግን አልሳካ ብሎኝ ነው። ይህም የሆነው በልጅነቴ ነው፡፡ በኋላ ላይ ግን ጽናቴ ሃይለኛ ሆነ፡፡ ነገሮች እንደሚቀያየሩ አምን ነበር፡፡ እርግጥ ነው በአቋራጭ መንገድ ባምን ኖሮ ብዙ አማራጮች ነበሩ፡፡ ግን እኔ ይህንን መንገድ አልፈልገውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ተብለጭልጮ፤ ነገ የማዘን ሕይወት ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡
በጥቅሉ የእኔን ሕይወት ልክ እንደወይራ ማየት ይቻላል፡፡ የወይራ ዛፍ ቶሎ አድጎ ፍሬ አይሰጥም፤ ልጅ ሆኖ ግን ይረገጣል፤ ይታሻል፤ ተመልሶ ያቆጠቁጣል። ልክ እንደወይራ እኔም ተረግጬ አውቃለሁ፡፡ እንደሚታወቀው በእኛ ሀገር ደምግባት የሌለውና ድሃ ሰው ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ እኔም በዚህ ምክንያት መገፋትን፤ መናቅን አይቻለሁ። እንዳውም ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ጊዜ በእናት ብቻ የምገናኘው ወንድሜ የአባቱ ቤተሰቦች ሰርግ ጠርተውን አብረን ሄድን፡፡ ግን አለባበሳችንን ላየ የምንመስለው የሀብታምና የድሃ ልጅ ነው ፡፡ ምክንያቱም እሱ ድጋፍ የሚያደርጉለት ቤተሰቦች ስለነበሩት ነው፤ እኔ ደግሞ የለኝም። እናም በዚያ አጎቱ ሰርግ ላይ ድንኳን ውስጥ እናቴና እሱ ሲገቡ፤ እኔ ለሰርጉ የሚመጥን ልብስ ባለመልበሴ አጎትየው እኔን ከበር አስፈንጥሮ አባረረኝ። በኋላ ላይ ከሰፈር ለማኞች ጋር ትርፍራፊ ተሰጥቶኝ ተሻምቼ በላሁ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ዘመድም ያገላል፤ የሚያደሉት ከድሃው ይልቅ ላለው ነው፡፡ እነዚህ መገለሎችና ችግሮች ግን ሜዳ ላይ አላስቀሩኝም፡፡ ወይም ደግሞ በቀለኛ አላደረጉኝም። ይልቁንም ታታሪ አደረጉኝ። አቋራጭ መንገድ ፍለጋም በጭራሽ አልሄድኩም። እዚህ የደረስኩት መስመሯን ጠብቄና የሚገባኝን ያህል ለፍቼ በመሆኑም የምበላው ያገኘሁትን ንጹህ እንጀራ ነው፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ሰዎች ከየት መጡ ሳይባል በድንገት ሊነሱና ሊከብሩ ይችላሉ፡፡ ግን መጨረሻቸው አያምርም፡፡ መስመሩን የጠበቀ እድገት ግን ውጤቱም ደስ ይላል፤ እርካታውም ያን ያህል ትልቅ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኀገር የወጣህበት አጋጣሚ ምን ነበር?
ኢንተርናሽናል ሼፍ አንተነህ፡– በመጀመሪያ ስፔን ባርሴሎና የመሄድ እድል አገኘሁ፡፡ እድሉን ያገኙልኝ በስራ የማውቃቸው ስፔኖች ናቸው፡፡ መጀመሪያ ላይ እኔ እንዳውም አልሄድም ብዬ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የራሴን ሬስቶራንት ከፍቼ ጥሩ ሥራ ነበረኝ። ከዚያ ይልቁንም የምፈልገውን ጎብኝቼ ለመመለስ ነበር። በኋላ ላይ ነገሮች እንደፈለኩት አልሄድ ሲሉኝና ተስፋ ሲያስቆርጡኝ ለመሄድ ወሰንኩኝ፡፡ በተለይ ነገሮች በጣም ሲበዙብኝ በጣም ስለምጨነቅ በልጅነቴ ደምግፊት ጀምሮኝ ነበር፡፡
ሃኪሞች ከጭንቀት ነፃ ካልሆንኩኝ የከፋ ነገር ሊደርስብኝ እንደሚችል ነገሩኝ፡፡ በኋላ ላይ ራሴን ለማዳን ስል እዚህ ያለውን ነገር ሁሉ እርግፍ አድርጌ ትቼ ተሰደድኩ፡፡ በእርግጥ ስደት ብዙ ዋጋ አስከፍሎኛል፤ ያም ቢሆን ውስጤ ጭል ጭል የሚል ተስፋ ስለነበረኝ እጅ ሳልሰጥ ቆየሁኝ። ከስፔን ወደ ጀርመን በመምጣት የጥገኝነት ጥያቄ አቅርቤ፤ እንደማንኛው ስደተኛ ካምፕ ገብቼ፤ የካምፕን ክፉም ደግም ሁኔታ አየሁኝ። ከዚያ በኋላ እንግዲህ ነገሮች እየተቀየሩ መጡ፡፡ በዋናነነት እጅ ሳልሰጥ ቋንቋቸውን በመማር ቶሎ ግንኙነቴን ማጠናከር ጀመርኩ፡፡ በአሁኑ ወቅት በጀርመን ትልቁና አለ በተባለው ሆቴል ውስጥ በሼፍነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሕይወት ታሪክህን ጽፈህ ለማሳተም የተነሳህበት ምክንያት ምን ነበር?
ኢንተርናሽናል ሼፍ አንተነህ፡– እንዳልኩሽ ያሳለ ፍኩት ነገር በመፅሃፍ ደረጃ እንኳን ለመግለፅ በጣም ከባድ ነው። እውነት ለመናገር አሁን የተናገርኩትም በጥቂቱ ነው።፡ ያም ቢሆን ግን ሕይወቴ ለሌሎች በጣም ያስተምራል ብዬ አምናለሁ፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ያሳለፍኩትን ሁሉ ነገር እወደዋለሁ። አንድ ሰው ለሌላ ሰው ለመስጠት የሚያስበው የሚወደውን ነገር ነው፡፡ ያሳለፍኳቸው ነገሮች ቀላል እንዳልሆኑ እኔ ራሴ እረዳለሁ። በተጨማሪም በተለይ ለወጣቶች አስተማሪ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ቶሎ ተስፋ ለሚቆርጡና ምክንያት ለሚሰጡ ሰዎች አስተማሪ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
እርግጥ እኔ ራሴ እጄን አጣጥፌ ለመቀመጥ የምደ ረድራቸው ምክንያቶች ነበሩኝ፡፡ ግን ከሥራ ስባረር እንኳን ለመቀመጥ ምክንያት አልሰጥም፡፡ አንዱ ሲዘጋ ሌላውን በር አንኳኳለሁ፡፡ የማገኛቸውን እድሎች በሙሉ እጠቀማለሁ፡፡ በተለይ በሰው በኩል እድለኛ ነኝ፤ የማገኛቸውን ሰዎች ሁሉ እጠቀማለሁ። አገኘሁ ብዬም አልኮፈስም፤ ስላላገኘሁም ተስፋ አልቆርጥም፡፡ የምፈልገውን ነገር የምጠይቀው በግልፅ ነው፡፡ የምገባው በመጠየቄ ጥሩም ሆነ መጥፎ ምለሽ ሊሰጡኝ እንደሚችሉ አምኜ ነው። መማር ካለብኝ እማራለሁ፡፡ ስለዚህ መጽሐፉን ጽፌ በማሳተም ለአንባቢያን ያደረስኩት፤ እኔ ያለፍኩት ውጣ ውረድ የበዛበት መንገድ ለሌሎች ትልቅ አቅም ይሰጣል ብዬ ስላሰብኩ ነው፡፡
እውነት ለመናገር ከዚህ ከአማርኛው መጽሐፍ በፊት መጽሐፍ ጽፌ አላውቅም፡፡ ግን እንዲሁ ስናደድና ስደሰት ለራሴ መፃፍ እወዳለሁ፡፡ ግን ከፃፍኩኝ በኋላ ቀዳድጄ እጥለዋለሁ፡፡ ተመልሼ አላነበውም፡፡ የምፈልገው ስሜቴ ከእኔ ውስጥ እንዲወጣ ብቻ ነበር፡፡ ወረቀቱ ላይ ካሰፈርኩኝ በኋላ ውስጤ ሰላም ያገኛል፡፡ አንድ ወቅት ላይ ግን ሁልጊዜ እንደዚህ ከማደርግ ለምን አልፅፈውም ብዬ አሰብኩኝ። አንዳንድ ሰዎችም ታሪኬን እንድፅፍ ይመክሩኝ ነበር። ሆኖም ለመፃፍ የሚያስችል ጊዜ አልነበረኝም። በተለይ ኢትዮጵያ እያለሁ እረፍት የሚባል ነገር አልነበረኝም፡፡ የሚገርመው ከሰኞ እስከ አርብ ተቀጥሬ እየሰራሁ ሳለ፤ እሁድና ቅዳሜ ደግሞ ለሰርግና ድግስ ምግብ እሰራ ነበር፡፡ ስለዚህ ቁጭ ብዬ ለመፃፍ የሚያስችል ፋታ አልነበረኝም፡፡ በኋላ ላይ ግን ኮቪድ መጣና ለወራት ቤት ውስጥ ቁጭ ስንል ያለውን ጊዜ ተጠቅሜበት መጽሐፌን ፃፍኩኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ይህ መጽሐፍ ከአማርኛ ወደ ጀርመንኛም ተተርጎሞ በዓለም ገበያ ላይ ውሏል፤ ለመሆኑ ተቀባይነቱ ምን ይመስላል?
ኢንተርናሽናል ሼፍ አንተነህ፡– መጀመሪያም ቢሆን መጽሐፉን የፃፍኩት ሰው ይቀ በለዋል፤ አይቀበለውም ብዬ አይደለም፡፡ ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ የሚፃፈው ለገበያ የሚፃፍ ሲሆን ነው፡፡ የግል ሕይወት ታሪክ ስለሆነ ተቀባይነት ማግኘት እኔን ያ የሚያሳስበኝ አይደለም፡፡ የምጽፈው በሕይወቴ የሆነውን ሳልጨምር ሳልቀንስ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ሲያነብ በእኔ ሕይወት ውስጥ የሚማረው ነገር ይኖራል። መጽሃፌን ያረሙትም በትልልቅ ስራዎቻቸው የሚታወቁ የእነሃይለመለኮት መዋልና የብርሃኑ ሰሙ እጅ አርፎበታል፡፡ እነዚህ ሰዎችም ሆኑ መጽሐፉን ያነበቡ ሰዎች የነገሩኝ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ እንዳለው ደራሲ መፃፌን ነው።
የሰጡኝ ምላሽ ታሪኩም መሳጭ በመሆኑ ለማቆም አይጋብዝም የሚል ነው፡፡ በነገራችን ላይ መጽሐፉ ፊልም እንዲሰራም ሁሉ የጠየቁኝ ሰዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ በጣም ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ እውነት ለመናገር ለማስተዋወቅ እንኳን ገንዘብ አልከፈልኩም፡፡ በሬዲዮ ላይ መጽሐፉ ሲተረክና ሲወያዩበት ሰምቻለሁ፡፡ ሽያጩም ያለቀው ወዲያው ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ሁለተኛ ዙር ይታተማል ብዬ አስባለሁ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በጀርመንኛ ተተርጉሟል። እንዲያውም የተሰራው ከአማርኛው በተሻለ በጣም ጥሩ ተደርጎ ነው፡፡ በትርጉም ስራ በጣም ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የጀርመን ምሁራን ተሳትፈውበታ። የአፄ ኃይለስላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት አልጋወራሽ አስፋወሰን ረድተውኛል፡፡ መጽሐፉ የጀርባ ገጽ ላይ ያለው የእርሳቸው ጽሁፍ ነው፡፡ እኚህ ሰው በጀርመን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የቋንቋና የታሪክ ምሁር ናቸው። እንዳልኩሽ በጀርመንኛ የተተረጎመው መጽሐፍ በጣም የተዋጣለትና በቋንቋ ብቃቱም የጎለበተ ነው፡፡ በአጠቃይ በዚህኛው መጽሐፍ ላይ ስድስት ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡ አሁን ገበያ ላይ ውሏል፤ አማዞን ላይም አለ፡፡
በቀጣይ እንግዲህ በሌላ መጽሐፍ ደግሞ ከአንባቢዎች ጋር እገናኛለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከሙያዬ ጋር በተያየዘ እና ለሆቴል ኢንዱስትሪው እድገት በጣም ጠቃሚ ይዘት ያለው መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ ነኝ። በተለይ እዚህ ሀገር የያኋቸውን ለእኛ ሀገር ሆቴል ኢንዱስትሪ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ የማስባቸውን ነገሮች ሁሉ ለማካተት እየሞከርኩ ነው። በመሆኑ ከዚህኛው መጽሐፍ በተሻለ ቆንጆ መጽሐፍ እንደሚወጣ አልጠራጠርም፡፡ የመጀመሪያውን መጽሐፌን ወደ እንግሊዝኛ ተተርጎሞ በመላው ዓለም እንዲነበብ የማድረግ እቅድም አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነት ለአንተ ምንድን ነው?
ኢንተርናሽናል ሼፍ አንተነህ፡– እኔ ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ደስ ይለኛል፡፡ እውነት ለመናር ግን አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊ በመሆኔ አንገቴን የምደፋበት ነገር ደግሞ አለ። በተለይ አሁን ላይ በሀገራችን የሚታየው ጭካኔ፤ ክፋት፤ አላዋቂነት እጅግ ከመንሰራፋቱ የተነሳ የማፍርበት ሁኔታ አለ፡፡ ሁኔታው እየባሰ በመጣ ቁጥር በጣም ያስፈራኛል፡፡ እንዳውም አሁን ላይ እኔ በበኩሌ ለፈጣሪ እጅ እየሰጠሁኝ የመጣሁ ይመስለኛል፡፡ አንድ ቀን እሱ በፈቀደው ጊዜ ልክ እንደእኔ ሕይወት ያስተካክለዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
እውነት ለመናገር እኔ ያደኩባት የማውቃት ኢትዮጵያ ሁሉን በእኩል አቅፋ፤ ሁሉም በፍቅር የሚኖርባት፤ ለሁላችንም በቂ የነበረችውን ኢትዮጵያ ነው። ለምሳሌ ልጅ ሆነን ስንጫወት ማን ምንድነው? የመጣው ከየትኛው ጎሳ ነው? ተባብለን አናውቅም፡፡ ሰፈራችን ውስጥ በየቀኑ ኳስ እየተራገጥን ስንውል ጓደኝነታችን እንጂ የማንነታችን ጉዳይ ጨርሶ ተነስቶ አያውቅም። በቤተሰብ ደረጃም እናቴ ለምሳሌ ማህበር ፤ እድር ውስጥ ትሳተፋለች፤ እነዚህ ማህበራዊ ተቋም ውስጥ ማን ምን እንደሆነ ተጠይቆ አያውቅም፡፡ ጽንፍ የሚባል ነገር አይቼ አላውቅም። ሕዝቡ ቢጣላ እንኳን ለመታረቅ ቅርብ ነበር። ገንዘብ ባይኖራቸውም በበረከት ይኖሩ የነበሩት ለዚያ ይመስለኛል፡፡
አሁን ያለውን ሁኔታ ግን በጣም ያሳዝናል፡፡ ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን ያስፈራልም፡፡ ለምሳሌ እዚህ ሀገር ከእኛ በላይ በብዙ ችግርና ጦርነት ውስጥ ያለፈ ሕዝብ ነው፡፡ ያሳለፉት ችግር ትምህርት ሆኗቸውና ሰክነው ዘር ወይም ጎሳ የሚባለው ነገር ከህሊና መዝገባቸው እንዲወጣ አድርገዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር እንደሚመስለኝ የእውቀት ችግር ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አወቅን የሚሉ ሰዎች በጣም ነገሮችን ያወሳስባሉ፡፡ ይህንን ስመለከት አደጋ ላይ ነን ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል፡፡
እግዚአብሔር ትልቅ፤ አየሯም ሆነ መሬቷ የተባረከ ሀገር ናት፡፡ ሕዝቡም ቢሆን ያን ያህል ክፉ የሚባል አይደለም። እንዳውም ደንጋጣና ፈጣሪን የሚፈራ ቶሎም የሚመለስ ሕዝብ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ መመራት አይችልም ይባላል እንጂ መሪ ካገኘ በስርዓት የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ በትንሽ ነገር የሚደሰት ሕዝብ ነው። ስለዚህ ትንሽ ነገር የሚያስደስተውን ሕዝብ መምራት ቀላል ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ሰከን ብለው ሀገሪቱን ወደፊት ማሻገር ይጠበቅባቸዋል፡፡
እኔ ኢትዮጵያ ሀብታም ሀገር እንደምትሆን ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ እርስ በርስ ባለመግባባት ከድህነት የምንወጣበትን ጊዜ ልናራዝመው አይገባም፡፡ የምፈራው እንደእስራኤል ሕዝብ እንዳንሆን ነው። የእስራኤል ሕዝብ ወደ በረከት ሀገራቸው በ40 ቀን መድረስ ሲገባቸው በራሳቸው ችግር ምክንያት 40 ዓመት እንደፈጀባቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ እኛም በራሳችን ጥፋት የመከራችንን ጊዜ ማራዘም የለብንም። ችግራችን በአጭሩ እንዲቀጭ በሥርዓት መመራት አለብን። አንዳንድ ጊዜ በፖለቲካ እያሳበቡ ራስ ወዳድነት ጎልቶ ይታያል፡፡ ከፖለቲከኞቹ ባሻገር የቤት አከራዮች፤ ነጋዴዎችና ደላሎች በሕዝቡ ላይ የሚፈጽሙት ግፍና ጭካኔ ካላቆሙ ፈጣሪ ይታረቀናል ብዬ አላምንም፡፡ ይህ ሲባል ግን ጥሩ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፤ አሉ፡፡
አሁን የምናየው የብዙ ጨካኞች ድምር ውጤት ነው። በፊት ሌባ ለመስረቅ ሲል ብቻ ሰው አይገድልም ነበር፡፡ አሁን ግን የሰው ገንዘብ ለመቀማት ሲሉ በጠራራ ፀሃይ ሳይታሰብ ከጀርባ ሰው ደፍተው የሚሄዱ አሉ፡፡ እናም እንዲህ ዓይነት ጭካኔ ውስጥ ከገባን ያለነው አደገኛ ነገር ውስጥ ነው፡፡ አሁን እኮ ማታ ማታ ሰዉ እንደፈለገ ዘና ማለት አይችልም፤ ሁሉም ቤቱ የሚሰበሰበው ሳይወድ በግዱ በጊዜ ነው። ሰው በገዛ ሀገሩ በነፃነት የማይመለስ ከሆነ ጤናማ ሥርዓት አለ ለማለት አይቻልም፡፡ እነዚህ ነገሮች ቀላል አይደሉም፡፡ ያም ቢሆን ይህ ችግር መፈታቱ አይቀርም፡፡ ሁሉም ከተባበረ፤ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ሃላፊነቱን ከተወጣ የማይስተካከል ችግር አይኖርም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንተ የምትኖርባት ጀርመን በታሪክ የምትታወቅበትን ዘረኝነት ላይ መሰረት ያደረገውን የናዚ ጭፍጨፋ ትውልዱ ላይ ጥላቻና በቀል እንዳይሻገር ከሠሩት ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን መማር ይችላል?
ኢንተርናሽናል ሼፍ አንተነህ፡- እጅግ በጣም ብዙ ነገር መማር እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እነሱ ጦርነትን በጣም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ የዓለም ክፋትን ጥግ እነሱ ሀገር ላይ ተፈጽሟል፡፡ ግን አሁን ላይ ያሉት ጀርመኖች ግን በጣም ምርጥ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ሀገራቸውንም ለሁሉም የሰው ልጅ የሚመች አድርገውታል። እኛ ሀገር ለምሳሌ አሁን ላይ የሚሰሩ ሕንፃዎች ሰማይ ጠቀስ ናቸው፡፡ ገንዘብ ያለው በሙሉ የሚውለው ድንጋይ ላይ ነው፡፡ ጀርመኖች ግን ብዙ ገንዘብ ቢኖራቸውም ትልልቅ ህንፃ አይሰሩም። ገንዘባቸውን የሚያውሉት ሰው ላይ ነው። ትውልድ ላይ፤ ትምህርት ላይ ነው፡፡
ትኩረት የሚያደርጉት ለሰው ልጅ የሚመች ነገር ላይ እንጂ ሕንፃ ቢገነቡ ከእኛ 40ና 50ሺ እጥፍ ይገነባሉ፡፡ አንድ ሕፃን ልጅ ከተወለደ ጀምሮ እስከ 18 ዓመቱ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ይወጣበታል። ይህንንም የሚከፍለው መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ ገንዘባቸውን ትውልድ ላይ አድርገውታል፤ እንዲሁ ድንጋይ ላይ አፍሰስው መና እንዲቀር አያደርጉትም፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ በተቃራኒው ነው፡፡ ሰው ላይ የሚሰራ ነገር የለም፤ አብዛኞቹ ፖሊሲዎች ከትውልድ አንፃር ሊስተካከሉ ይገባል፡፡
እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም በነበረው መንግሥት ጥቃቅና አነስተኛ በማደራጀት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ከጥቅሙ ይልቅ መጥፎ ጎኑ በማድላቱ ውጤቱ አመርቂ አልሆነም፡፡ ለምሳሌ ወጣቱን ከማደራጀት በፊት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ይጠበቅ ነበር። ሰዎችን ሳያሰለጥኗቸውና የአመላከከት ለውጥ ሳይመጣ ድንገት አምጥተው ገንዘብ ሲሰጧቸው የባሰ እዳና ሱስ ውስጥ ተዘፈቁበት እንጂ አልተለወጡበትም። አንዳንዶቹ እንደውም ብሩን ካጠፉት በኋላ ከሀገር የተሰደዱ አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደውም መንግሥትም ራሱ ወጣቱን ከሀገር ማባረሪያ ዘዴ አድርጎ የተጠቀመበት ይመስለኛል። መሆን የሚገባውን ግን በአግባቡ ጥናት ተደርጎበት ሥርዓት ተበጅቶለት መሆን ነበረበት፡፡
ጀርመኞች ዘረኞች አይደሉም፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ሆኜ እነሱ ሀገር የምኖረው ሰላምና ደህንነቴ ተጠብቆ ነው። ከኢትዮጵያ ይልቅ ደረቴን ነፍቼ በነፃነት በጨለማ፤ የፈለኩትን ተናግሬና መብቴን አስከብሬ ነው የምኖረው። ሥርዓቱ አስቀድሞም ስለተፈጠረ መብቴ የሚከበረው በቀላሉ ነው፡፡ ስለለበስኩና ሳላለበስኩ፤ ጥቁር ወይም ነጭ ስለሆንኩኝ ሳይሆን መብቴ የሚከበረው የተፃፈ ሕግ ስላለና በተጨባጭም ስለሚከበር ነው፡፡ የሕግ የበላይት በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚከበር ነው፡፡ በተወለድኩባት ኢትዮጵያ ግን የዚህን ያህል ነፃነት የለኝም። እርግጥ ነው አሁንም ጥቂት ዘረኛ ናዚዎች አሁንም አሉ፡፡ ግን የፈለገውን ያህል ዘረኛ ቢሆኑ ከሕግ በላይ አይደሉም፡፡ ሕጉ ስለሚከበር ሁሉም ሰው ተከባብሮ ይኖራል፡፡ እየጠላም ጥላቻውን በአፉ መናገር አይችልም፡፡
ኢትዮጵያም ሕግ አለ፤ ግን አልተከበረም፤ ፍትህም ተዛንፏል፡፡ ሙስኝነትም በጣም ተስፋፍ ቷል። ከፍተኛ የሆነ የጉቦ ሥርዓት ተፈጥሯል፡፡ እሱ አደገኛ ነገር ነው። እርግጥነው የኑሮ ውድነቱም፤ ሌብነቱ መስፋፋት ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ግን የሀገሪቱ መንግሥትና ኢኮኖሚስቶች መፍትሔ መፈለግ አለባቸው፡፡ በፊት ጉቦ ሰጪም ሆነ ተቀባይ በድብቅ ተሳቀው ይቀባበሉ ነበር፡፡ አሁን ሁለቱም የሚያደርጉት በነፃነት ነው፡፡
ሁለተኛ ችግር ደግሞ የህጉ አፈፃፃም መላላት ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ በቅርቡ ቦሌ አካባቢ ሌባ አጋጠመኝና ለፖሊሶች ስነግራቸው እኛ ብናስራቸውም መልሰው ስለሚፈቷቸው ፖሊስ ጣቢያ መውሰድ ትተናል አሉኝ፡፡ እናም እንዲህ አይነት ነገር እያለ ሕግ ማስከበር አይቻልም፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ፖሊስ ይጠብቀኛል የሚል እምነቱን አጥቷል። እርግጥ ነው በጣም ምግባረ ሰናይ የሆኑ የፀጥታ አካላት አሉ። በተቃራኒው ደግሞ ከሌባ ጋር አብረው የሚሰሩ አሉ። የፍትህ አካላቱ ራሱ በሌቦች ከተዘፈቀ ሀገር አደጋ ላይ ነች። እንደሚታየው በየጊዜው መኪና ይጠፋል፤ ሰው ይጠፋል አሁንማ የሰው ሕይወት ቀላል ሆኖብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ኢንተርናሽናል ሼፍ አንተነህ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2014