ታሪካዊ ዳራ፤
የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ፖለቲካ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት መመራት ከጀመረ አንድ ክፍለ ዘመን ሊሞለው የቀረው አሥር ያህል ዓመት ብቻ ነው። ፓርላማው የመቶ ዓመት እድሜ ሻማውን የሚለኩሰው፤ አራት ቀሪ የሥልጣን ዓመታት ከፊቱ የሚጠብቁት የዛሬው “የብልጽግና መንግሥት” ሩጫውን ጨርሶ (ዕድል ከቀናውም በሁለተኛ ተርም የሥልጣን ቤትኛነቱን ሊያስቀጥል ይችላል) እና ከእርሱ በኋላ የሚከተለው መጻኢው ወራሴ መንግሥት አምስት ዓመቱን አጠቃሎ ለተረኛው ሦስተኛ ሸንጎ በሚያስረክብበት የመጨረሻው ዓመት ግድም ነው። 3650 ቀናት ያረገዘው አሥሩ ዓመት ሩቅ መስሎ እንዳያዘናጋን እኛ ተመሪዎችም ሆንን የእኛ መሪዎች “ዕድሜና ቁረንጮ ተበጣጥሶ ማለቁን” ልብ ልንል ይገባል። ወንበረተኞቹም ቢሆኑ “ቀን ሳለ” ለሕዝቡ እንቆቅልሽ መፍትሔ መስጠቱ ላይ ቢረባረቡ ይበጃቸዋል።
የዕድሜን ነገር ከጠቃቀስን ዘንዳ የፓርላማችንን ያለፉትን ዘመናት ዜና መዋዕል በወፍ በረር ቅኝትም ቢሆን አስታውሶ ማለፉ ተገቢነት ይኖረዋል። “የኢትዮጵያ መሬትም፣ ሕዝቡም፣ ሕጉም በጠቅላላው የንጉሠ ነገሥቱ ነው” (ክፍል ሁለት)፤ በሚል ጠቅላይነት ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በችሮታነት “በተሰጠው ሕገ መንግሥት” የቆመው የመጀመሪያው ፓርላማ ሥራውን በይፋ የጀመረው ጥቅምት 23 ቀን 1924 ዓ.ም ነበር።
“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከኢየሩሳሌም ንጉሥ ከሰሎሞንና ንግሥተ ሣባ ከተባለችው ከኢትዮጵያ ንግሥት ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልከ ነገድ ተያይዞ ከመጣው ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘር ከተወለደው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትውልድ እንዳይወጣ ተወስኗል (ክፍል 3)፤ በሚል “በሞአ አንበሳዊ” ውርስ በፀና የብረት ግንብ በታጠረው ሕገ መንግሥት ሥራውን “ሀ” ብሎ የጀመረው ፓርላማ የቆየው እስከ ፋሽስት ወረራ እስከ 1928 ዓ.ም ድረስ ነበር።
ወራሪው የፋሽስት ሠራዊት በሽንፈት ከተባረረ በኋላ ፓርላማው እንደገና አንሰራርቶ ሥራውን የጀመረው በ1935 ዓ.ም ነበር። ለአሥራ አምስት ዓመታት ያህል ተግባሩን ያከናወነው ይህ ፓርላማ በሕገ መንግሥቱ ላይ ክለሳ ተደርጎ “ከሕዝብ በተመረጡ” በተባለላቸው “ተወካዮች” አማካይነት ሥራውን ያስረከበው በ1948 ዓ.ም ሲሆን፤ ሁለተኛው የንጉሡ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ በቆየባቸው 20 ዓመታት ውስጥም አምስት ያህል ጊዜያት የፓርላማ “ምርጫ” ተደርጓል።
የአፄው ሥርዓተ መንግሥት የአርባ ዓመታት ጉዞና የፓርላማው የወንበር ሥልጣን ያከተመው ወታደራዊው ደርግ ሥልጣኑን በተቆጣጠረበት በ1967 ዓ.ም ነበር። የደርግ መንግሥትም በፊናው፤ 835 “የሕዝብ እንደራሴዎችን” ያቀፈውን የፓርላማ ሥርዓት ያቋቋመው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥት የተቋቋመበት ሕገ መንግሥት ጥር 24 ቀን 1979 ዓ.ም ከጸደቀ በኋላ ነበር።
“የዝሆኖች ሸንጎ” በመባል የሚታወቀውና አንዲቱን ተርም አንኳን ለመጨረስ ያልታደለው ያ የኢህዲሪ ፓርላማ የቅጽል ስያሜውን ያገኘው የአሸናፊዎቹ ወንበረተኞች የምርጫ ምልክት በሙሉ “ዝሆን” እንዲሆን ኢሠፓ በወሰነው መሠረት ነበር። በፈጠጠ የድርጅታዊ አሠራር መንበሩን የተቆጣጠረው የዚያ ሸንጎ የምርጫ ሂደት “ተጨፈኑና ላሞኛችሁ” ይሉት ዓይነት አሠራሩን ጊዜው ሲፈቅድ በዝርዝር እንመለስበታለን።
“የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ በሠራተኛውና በገበሬው ኅብረት፣ በምሁሩ፣ በአብዮታዊ ሠራዊት፣ በዕደ ጥበብ ባለሙያውና በሌሎች ዴሞክራሲያዊ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ የሠርቶ አደሩ ሕዝብ መንግሥት ነው (አንቀጽ 1፡1)” የተባለለት አዲሱ ኢሠፓውያን የተሰባሰቡበትና ከደርግ አገዛዝ ወደ ኢሕዴሪ ተለወጠ የተባለለት ሥርዓተ መንግሥት ቆይታው እስከ 1983 ዓ.ም ለአራት ዓመታት ያህል ብቻ ነበር።
በሀገራችን መንግሥታዊ ሥርዓት በሦስተኛነት የፓርላሜንታዊ ሥርዓት የሚጠቀሰው “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ” ፍልስፍና አራማጁ የወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥት ነው። ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የጸደቀውና “ከ550 የማይበልጡ” የወንበረተኞቹን ቁጥር የወሰነው ሕገ መንግሥት (የቁጥሩን ብዛት በተመለከተ ታማኝ ባይሆንም)፤ ለስድስት ያህል ጊዜያት የምክር ቤት አባላት “ስመ ምርጫ” ተካሂዶበታል።
በስድስተኛው ዙር ምርጫም “ድምጻችን ድምጽህ ነው” ብለን የመረጥነው የብልጽግናው ገዢያችን እየመራ ያለው የ27 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው ነባሩ ሕገ መንግሥት ባጎናጸፈው “በትረ ሙሴ” አማካይነት ስለሆነ ደፈር ብለን ለምሥጋና፤ ጨከን ብለንም የሕገ መንግሥቱን ሰነድ ለመተቸት ጊዜው ስላይደለና “የያዘን ስለሚይዘን” ትዝብታችንን አምቀን “በሆድ ይፍጀው” ብሂል ማለፉን መርጠናል። “እንዲህ ያለ ነገር ለወሬም አይመች” ያለው ድምጻዊ ማን ነበር?
የፓርላማችን ክራሞት፤
ከአሁን ቀደም በፓርላማችን አዋዋልና በተከበሩ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ዙሪያ በሕዝብ መካከል የሚያሳዩትን የማይመጥናቸውን ተግባር በተመለከተ በመረጃና በማስረጃ አስደግፌ ተደጋጋሚ ትዝብቴን በዚሁ ጋዜጣ ላይ መግለጼ ይታወሳል – ለምን ቢሉ “ተወካዮቻችን ነበሩዋ!”። “የፓርላማው የሰዓት ደውል” እንኳን ሳይቀር በምን ምክንያት ልሳኑ ሊዘጋ እንደቻለ የዓለም አቀፍ ታሪኮችን ዳራ እያጣቀስኩ “ለሰሚዎቹ ይድረስ!” ማለቴን አስታውሳለሁ።
በዚህ አጋጣሚ በወቅቱ ጽሑፉን ያነበቡት ክብርት የፓርላማው ጽ/ቤት ኃላፊ ስልክ ደውለው ዝምታ ያረበበትን የፓርላማውን የሰዓት ደውል በተመለከተ የችግሩን ምክንያት ካስረዱኝ በኋላ ፈጣን “የጥገና” ምላሽ እንደተሰጠው ገልጸውልኝ ነበር። ክብርት ኃላፊዋን ዛሬም ደግሜ አመሰግናቸዋለሁ። ወደ አራት ኪሎ ብቅ ስል ልብ ተቀልብ ሆኜ ጆሮዬን አልሰጠሁ ከሆነ ይቅርታ አይነፈገኝና ዛሬስ ቢሆን በፓርላማችን የሕንጻ አናት ላይ ተሰቅሎ ከታዳጊነት ዕድሜ እስከ ዛሬው ጉልምስናችን በድምጹና በቀስቃሽነቱ ትዝታው በውስጣችን የተተከለው “የሰዓት ደውል” ሥራውን እየሠራ ይሆን ወይንስ እንደለመደው አሸልቧል?
የበቀደሙ ውሎ…
ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከተከበረው የተወካዮች ሸንጎ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የተገኙበትን ጉባኤ የተከታተልኩት ልቤንም ጆሮዬንም ከፍቼ ነበር። በአጠቃላይ የዕለቱ የውሎ መርሃ ግብር መልካም ነበር ማለት ይቻላል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮቹ ለተነሱት ጥያቄዎችም የሰጧቸው ዝርዝር ምላሾች አጥጋቢና ጊዜውን የዋጁ ነበሩ።
ተጨማሪ እውቀት የሚያስጨብጡት ገለጻዎችም ቦታቸውንና ዐውዱን አገናዝበዋል የሚል ጥቅል አስተያየት አለኝ። በግሌ ከሌሎች ውሎዎች በተለየ አኳኋን ፓርላማው እንደዚያ ተነቃቅቶ በማየቴ የዘራኋት ቅንጣቷ የምርጫ ካርዴ የተመኘሁትን ፍሬ አፍርታለች የሚል ስሜት አጭሮብኛል።
በአንዳንድ የጥያቄዎች ይዘት ላይ ግን ብዥታ ተፈጥሮብኛል። ጉዳዩን እንደማሳነስ አይቆጠርና፤ ፓርላማው የፌዴራል አጀንዳዎች የሚስተናገዱበት መድረክ እንጂ “የእኔ የምርጫ አካባቢ” እየተባለ ከራስ ሰፈር ድልድይ ግንባታ መጓተት እስከ የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገድ ሥራ መዘግየት ድረስ ዝቅ ያሉ ችግሮች የሚተረኩበት ትክክለኛ ቦታ አይመስለኝም (ምሳሌዎቼ ለማሳያነት የተጠቀሱ መሆናቸውን ልብ ይሏል)።
ለመሆኑ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የቀበሌ ወዘተ. እየተባለ የሸንጎ መዋቅሩ ተዘርግቶ የለ? እኒህን መሰል ችግር የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች ወክለው ለተመረጡ “የየአካባቢው ተመራጮች” እስከ ክልል ምክር ቤት ድረስ ጉዳዩን ለማሳወቅ ዕድሉ ወለል ተደርጎ የተከፈተላቸው የፓርላማው እንደራሴዎች ለምን በየደረጃው ካሉ የየክልሉ ሹማምንት ጋር ተነጋግረው ግፊት አያደርጉም? እነዚህን መሰል የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ያልሆኑ ችግሮችን ለማንሳት በርግጡ ፓርላማው ትክክለኛ ቦታ ነው? “ጥያቄ አቅርቤያለሁ መልስ ብትሰጡኝ…” አለ ድምጻዊው።
እስከ ዛሬ ያልገባኝና ሊገባኝ ያልቻለ ወይንም የሚያስረዳኝን ሰው ያላገኘሁለትን አንድ ሁለት ግርታዬን ልፈነጣጥቅ። የተከበሩ የምክር ቤቱ አባላት በሺህና በሚሊዮን የሚቆጠር የመራጮችን ድምጽ ያገኙት ፓርቲያቸው ደጀን ስለሆናቸው ወይንም የዕድል በለስ ስለቀናቸው ብቻ አይመስለኝም። በፓርቲያቸው ግምገማ መሠረት “በንቃትም ሆነ በመሪነታቸው ተሰጥኦ የወከሉትን ሕዝብ ሊመጥኑ ይችላሉ” ተብሎ ታምኖባቸው እንደሆነ እንገምታለን።
እንዲዚያ ከሆነ ዘንዳ ጥያቄያቸውን በሚመለከተው የፓርላማው አካል በኩል አስመዝግበው በተፈቀደላቸው ደቂቆች በአጭሩና በተብራራ ሁኔታ በቃላቸው ከማቅረብ ይልቅ “ጥያቄዎቼንና አስተያየቶቼን በንባብ አሰማለሁ” የሚሉት ባህል በርግጡ ለዘጠና ዓመት አረጋዊ ፓርላማ የሚመጥን ወግ ነው? ሰዓት ለመቆጠብ ይሆን ወይንስ ሃሳብ እንዳይሸራረፍ ለመቆጣጠር? ምንም ሆነ ምን ይህ ባህል፤ “ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ” የሚለውን የሕዝብ እምነት የሚወክል አይመስለንም። ማሳመኛ ካለ ይሞግቱን።
እንደ ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም በገጽ ውሱንነት ብቻ ሃሳቡን ፈንጥቆ ማለፉ ይበጅ ይመስለናል። በንግግር ተሟግቶ መርታትና መረታት እያለ በጽሑፍ፤ ያውም በእንደነገሩ የአነባበብ ዘይቤ ተወካዮቹን መሸበብ በግሌ አዋጭ አይመስለኝም። የጥያቄ አቀራረቡ ለምን እንዲህ እንዲሆን እንደተፈለገም የሚያስረዳን ብናገኝ አንጠላም።
የወንበረተኞቹ የስብሰባ አካሄድ መመሪያ ላይም ማብራሪያ ቢሰጥበት ከውዥንብር ያድነናል። በቀዳሚው የትምህርታችን ሥርዓት በየትምህርት ቤቱ ይካሄድ የነበረው የክርክር ፕሮግራም ክሽፈት ያስከተለው ውጤት ለንግግር አይናፋርነት ዳርጎንም ከሆነ ጉዳዩ በትምህርት ሥርዓቱ መሪ ተቋም በኩል ቢጠና ክፋት የለውም። በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነቱ ልማድ በቀዳሚዎቹ የንጉሡና የኢሠፓ ሁለት ሸንጎዎች ላይ ጎልቶ የሚታይ ባህል አልነበረም።
ከነካካን አይቀር “ዴሞክራሲው ያጎናጸፈንን የመራጭነት መብት” በመጠቀም ደፈር ብለን አንድ ጉዳይ እናንሳ። እያንዳንዱ የሕዝብ ተወካይ አስተያየቱንና ጥያቄዎቹን ከመጀመሩ አስቀድሞ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጥያቄዎቻችንን ለመመለስ በመሃከላችን ስለተገኙ እናመሠግናለን” ብሎ በጅምላ መንደርደር ፋይዳው ምኑ ላይ ነው? “ተወካዮቹ የሚተዳደሩበት የሥነ ምግባር መመሪያ ስለሚያስገድድ ነው!” ቢባል እንኳን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ይሄንን መወድስ ስለመውደዳቸው እርግጠኞች አይደለንም።
በተከበሩት አፈ ጉባዔው በኩል አስቀድሞ ምስጋናው በጅምላ ውክልና ቢቀርብና ቀጥታ ወደ ጉዳዩ መግባቱ አይሻልም? መቼም ይሄ የመረጥንበት ካርድ “የተወካዮቻችንን” ውሎ በሚገባ እንድንፈትሽ ስለሚያበረታታንና ዋስትናም ስለሚሰጠን ያልገባንን መጠየቁ ተገቢነት ይኖረዋል። በዚህ ጸሐፊ እምነት ግን ምሥጋናው አንዴ ከቀረበ በቂና ከበቂ በላይ ስለሆነ በቀጥታ ጥያቄን ወይንም አስተያየትን ማቅረቡ የተሻለ የሚሆን ይመስለናል።
የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን አጥንተውና መርምረው፣ የሀገራቸውን ጉዳይ ጠለቅ አድርገው በመፈትሽ በመረጃ የተደገፈና “ዋው!” የሚያሰኝ የመሟገቻ ሃሳብ ይዘው የሚቀርቡ “ተወካዮችን” ማየት የዚህ ጸሐፊ ምኞትና ናፍቆት ነው። ለምን የሌላውን ሀገር የሸንጎ አባላት አዋዋል እያየንና እያደመጥን በመንፈሳዊ ቅናት እንቃጠላለን? ፈጣሪ ሆይ “እንደ ልባችን” የምንላቸውን ተወካዮች እባክህ አብዝተህ ስጠን!?
የሕግ አውጪነትን ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጠው ይህ የሕዝብ ተወካዮች ሸንጎ “ምክር ቤት” የሚለው ስያሜስ አያንስበትም ይሆን? ፓርላማ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ከምክክርም ከፍ ያለ የወሳኝነት ሥልጣን ስላለው ዛሬም ባይሆን ወደፊት “ሕገ መንግሥታችን” ለሕዝብ ውይይት ቀርቦ ሲፈተሽና ሲበጠር ይህ የስያሜ ጉዳይ ትኩረት እንዳይነፈገው ከወዲሁ ይታሰብበት እንላለን። ታዲያ ምን ይባል? ከተባለም፤ በጊዜው አማራጭ ሃሳቦችን ለማቅረብ የቤት ሥራውን ከወዲሁ እንወስዳለን።
ጽሑፎቼን አዘውትሮ የሚያነብ አድናቂዬ ባፋጠጠኝ አንድ ወሳኝ ጥያቄ ልደምድም። “ለመሆኑ አንድ የሕዝብ እንደራሴ (በተለይም በፓርቲ ጥላ ሥር ተጠልሎ ምክር ቤት የገባ ተወካይ) ወገንተኝነቱ ለማን ነው? ቤተኛ ለሆነበትና ላስመረጠው ፓርቲ ወይንስ ‹አለኝታ ሁነኝ› ብሎ ለመረጠው ሕዝብ?” ጥሬውን ጥያቄ እንዳለ የወረወርኩት ሃሳቡን የሚያበስልልን ያገባኛል ባይ አለሁ እንዲለን ነው። ለጠያቂዬ ብቻም ሳይሆን ለእኔውም ቢሆን ግር ስለሚለኝ ምላሹን የምጠባበቀው በትእግስትና ልብ ተቀልብ ሆኜ በመጓጓት እንደሆነ መሸሸግ አልፈልግም። ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2014