ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በሀገር አቋራጭ ውድድር ባስመዘገቡት ስኬት በቀዳሚነት ከሚዘረዝራቸው ሀገራት መካከል ትገኛለች። በተለይ በዚህ ርቀት በሚካሄደው ዓመታዊ ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በርካታ ሜዳሊያዎችን ሰብስበዋል። በተያዘው ሳምንት በሚካሄደው 43ኛው ሻምፒዮናም እንደ ቀድሞው ሁሉ ውጤት እንደሚመዘገብ ይጠ በቃል። የሻምፒዮናው ዝግጅት የዘንድሮ ተረኛ ሀገር ዴንማርክ ስትሆን፤ አርሁስ በተባለው ከተማ በመጪው ቅዳሜ ይጀመራል። በዚህ ተሳታፊ ለመሆን በዝግጅት ላይ የቆየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ዛሬ ምሽት በአራራት ሆቴል ሽኝት እንደሚደረግለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በዚህ ውድድር ተካፋይ የሚሆኑት አትሌቶች በቅርቡ ከተካሄደው 36ኛው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር ተሳትፎ ባላቸው የተሻለ ውጤት እንዲሁም የእድሜ ተገቢነትን ያሟሉ ተመርጠዋል። የተመራጭ አትሌቶች ልምድ ያላቸው አሰልጣኞችም ብሄራዊ ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ መደረጉን ከፌዴሬሽኑ ይፋዊ ድረገጽ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
አትሌቶቹ ካምፕ ገብተውም ለውድድሩ የሚረዳቸውን ልምምድም በአዲስ አበባ ስታዲየም፣ በጃንሜዳ እና ከከተማ ውጪ ልዩ ልዩ ልምምዶችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ከስፖርታዊ ስልጠናው ባሻገርም በስነ ልቦና፣ በአመጋገብ፣ በእረፍት አጠቃቀም፣ በህክምና፣ በማሳጅና ፊዚዮቴራፒ እንዲሁም በእርስ በርስ መስተጋብር ረገድ በቡድኑ አሰልጣኞች፣ አመራሮችና የህክምናው ዘርፍ ከፍ ያለ ድጋፍና ክትትል የተደረገለትም ነበር።
በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በጥቅሉ 28 አትሌቶችን የምታሳትፍ ሲሆን፤ 14ቱ ሴቶች 14ቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው። ውድድሩ በአምስት ክፍሎች የሚካሄድ ሲሆን፤ ከ20ዓመት በታች 6ኪሎ ሜትር የሴቶች ውድድር፤ ዳግማዊት ገብረእግዚአብሄር፣ አለሚቱ ታሪኩ፣ ጽጌ ገብረሰላማ፣ መሰሉ በርኸ፣ ውዴ ከፋለ እና ሚዛን ዓለም ተሳታ ፊዎች ይሆናሉ። በወንዶች ከ20ዓመት በታች የወንዶች ውድድር ደግሞ፤ ጸጋዬ ኪዳኑ፣ ሚልኬሳ መንገሻ፣ ታደሰ ወርቁ፣ ጌትነት የትዋለ፣ ገብረጊዮርጊስ ተክላይ እና ድንቃለም አየለ ተሰልፈዋል። በአዋቂ ሴቶች 10ኪሎ ሜትር፤ ደራ ዲዳ፣ ለተሰንበት ግደይ፣ ዘነቡ ፍቃዱ፣ ሃዊ ፈይሳ፣ ጸሃይ ገመቹ እና ፎቶን ተስፋይ ተካፋዮች ይሆናሉ።
በአዋቂ ወንዶች የ10ኪሎ ሜትር ቡድን ደግሞ፤ ሞገስ ጥኡማይ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ አንዷምላክ በልሁ፣ እንየው መኮንን፣ ቦንሳ ዲዳ እና አብዲ ፉፋ ተካትተዋል። ሴት እና ወንድ አትሌቶች በጋራ በሚሳተፉበት የድብልቅ ሪሌ 8 ኪሎ ሜትር ውድድርም፤ ፋንቱ ወርቁ፣ ቦኔ ጩሉቃ፣ ታደሰ ለሚ እንዲሁም ከበደ እንዳለ የሚሮጡ ይሆናል። አባጣ ጎባጣ በሚበዛበትና ፈታኝ በሆነው በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ልምዳቸውን ተጠቅመው እንደተ ለመደው ስኬታቸውን እንደሚያበስሩም ይጠበቃል።
በተለይ በረጅም ርቀት እንዲሁም በሀገር አቋራጭ ውድድሮች ብቃቱን በማስመስከር ላይ የሚገኘው ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ አሸናፊ እንደሚሆን ከወዲሁ እየተጠበቀ ነው። ሰለሞን በጃንሜዳው ሻምፒዮና ላይ በ10 ኪሎ ሜትር ሁለተኛ ቢወጣም፤ ርቀቱን የሸፈነው 31ደቂቃ ከ18ደቂቃ ከ36ሰከንድ በመግባት ነበር። ያለፈው ዓመት በስፔን በተካሄደ ሌላ ውድድር ላይም በተመሳሳይ አትሌቱ አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው።
አትሌቱ
ከዚህ ባሻገር በጣሊያን በሚካሄደው ዓመታዊ የሀገር አቋራጭ ውድድር ላይ በመሳተፍ የሀገሩን ልጅ ሃጎስ ገብረህይወትን ተከትሎ በመግባት ነበር ውድድሩን ያጠና ቀቀው። በሚያሸልመው የቡድን ተሳትፎም ኢትዮጵ ያዊያን አትሌቶች በተለይ የበላይነቱን የተላበሱ ሲሆን፤ በዚህ ውድድር ላይም አሸናፊ በመሆን ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል። በዚህ የው ድድር መድረክ በተለይ ባስመዘገባቸው ሜዳሊያዎች ብዛት እስካሁንም አቻ ያልተ ገኘለት ቀነኒሳ በቀለ ለአምስት ጊዜያት በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል።
ከ10ኪሎ ሜትር በተጓዳኝንም በ12ኪሎ ሜትር ለስድስት ጊዜያት ሻምፒዮን በመሆን ወርቃማ ታሪኩን አስመዝግቧል። ቀነኒሳ በዚህ ውድድር አጭር ርቀትም ስኬታማ ሲሆን፤ አምስት የወርቅና አንድ የብር ሜዳሊያዎችን የግሉ በማድረግም ባለ ክብረወሰን ነው። እአአ በ2004 በብራሰልስ በተካሄደው ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ፣ ገብረእግዚአብር ገብረማሪያም እና ስለሺ ስህን በሰከንዶች ልዩነት ተቀዳድመው ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ የወሰዱበት ውድድር እስካሁንም እጅግ ስኬታማው ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
ብርሃን ፈይሳ