ስፖርት በስርዓት የሚመራ ውብ ክዋኔ መሆኑ ለተወዳጅነቱ በምክንያትነት ይጠቀሳል። ከአደረጃጀቱ ጀምሮ የትኛውም ዓይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የራሱ የሆነ ሂደትና ስርዓት አለው። ይህ ስርዓት ተጥሶ በዘፈቀደ ሲከወን ደግሞ የተወዳጅነቱን ያህል በአደገኛ አካሄድ ላይ ሊገኝ ይችላል። በኢትዮጵያ ስፖርት አደረጃጀት የሚስተዋለውም ይኸው ነው። የተቀመጠለትን አቅጣጫ በመሳቱም፤ ስልጠናው፣ ሰልጣኞች፣ ሃብት፣ ጉልበት፣ ጊዜ፣ … ለብክነትና ለአሰራር ድርርቦሽ ተዳርገዋል።
ለውጤት ማጣትም የራሱን ሚና ሲጫወት ቆይቷል። በአገሪቷ ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን፤ የታዳጊ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት፣ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ አካዳሚዎች፣ ክለቦች እንዲሁም ብሄራዊ ቡድን የሚል መስመር በመዘርጋት እየሰራ መሆኑ ይታወ ቃል። ነገር ግን ይህ አሰራር በቅብብሎሽ ከመከናወን ይልቅ ሁሉም በራሱ መንገድና አካሄድ ሲመራው ቆይቷል። ይህም ለብክነት ምክንያት ሲሆን፤ ማሰልጠኛ ማዕከላቱ ሚናቸው ተመሳሳይ በመሆኑ የሰልጣኞች ሽሚያ እና የእርስ በርስ ቅሬታ ውስጥ እንዲገቡ ሲያደርጋቸው ቆይቷል። ይህንን የተመለከተው ኮሚሽኑ አገር አቀፍ ስፖርት ስልጠና ጣቢያዎች፣ ማዕከላትና አካዳ ሚዎች አደረጃጀትና ስርዓት መተግበሪያ ረቂቅ ሰነድ በማዘጋጀት፤ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን በመሰብሰብ ላይ ይገኛል።
ረቂቁ አምስት ክፍ ሎች ያሉት ሲሆን፤ የመጀመሪያው ክፍል በማዕከ ላትና ፕሮጀክቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። ቀጣዩ ክፍል ምዘና እና ውድድርን የሚመለከት ሲሆን፤ ሦስተኛው የሰል ጣኞችን የቅብብሎሽና ዝውውር፣ አራተኛው የባለቤትና ባለድርሻ አካላትን ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም በመጨረሻው ክፍል የክትትል፣ ድጋፍና ግምገማ ስርዓትን የሚያጠቃልል ነው። የሰነዱ አስፈ ላጊነትም፤ በየደረጃው በሚገኙ ፕሮጀክቶች፣ ማሰል ጠኛ ማዕከላት፣ አካዳሚዎችና ክለቦች መካከል ወጥ እና ቅንጅታዊ አሰራርን መዘርጋት ነው። በዚህም መሰረት ለሁሉም የየራሳቸው የሆነ የአሰራር ስርዓት ተበጅቶላቸዋል።
በየአካባቢውና ትምህርት ቤቶች ከ13ዓመት በታች (11እና12) በሆነ ዕድሜ ስልጠናው የሚጀመር ሲሆን፤ በዚህም በርካታ ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎችን በተመሳሳይ ዕድሜ ማግኘት ይቻላል። ሁለት ዓመታትን በሚሸፍነው በዚህ ስልጠናም በዋናነት ሥራው የተሰጥኦ ፍለጋ ይሆናል። በቀጣይም ታዳጊዎቹ በ15 ዓመት በታች (13እና14) የስልጠና ጣቢያዎችን በመቀላቀል ለሁለት ዓመታት ይሰለጥናሉ። በዚህ የተሰጥኦ ልየታ ወቅትም ከአሰልጣኞቻቸው እገዛ ባሻገር በምዘና ያላቸውን ተሰጥኦ ለመለየት ይቻላል።
በ17 ዓመት በታች (15እና16) ወደ ስልጠና ማዕከላት በመግባት የተለየውን ተሰጥኦአቸውን ማልማት የሦስት ዓመታት ሥራ ይሆናል። በዚህ ወቅት የስልጠና ጫናን የመሸከም ብቃታቸው የሚ መዘን ሲሆን፣ በማዕከላት መካከል የሚደረገውን ውድድር ጨምሮ በአገር አቀፍ ሻምፒዮናዎች እንዲሁም በዕድሜ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም ተሳታፊ ይሆናሉ። ይህንን ሲያጠናቅቁ ወደ አካዳሚዎች የሚገቡ ሲሆን፤ ከ3- 4ዓመታት በሚዘልቀው ቆይታቸው ለኦሊምፒክ ብቁ እንደሚሆኑ ስለሚታመን ክለቦችን እንዲሁም ብሄራዊ ቡድኖችን ይቀላቀላሉ።
የዚህ ሂደት ባለቤቶችም የተለዩ ሲሆን፤ ከ13-17ዓመት በሚዘልቀው የስልጠና ወረዳ እና ዞኖች ኃላፊነት አለባቸው። የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላትን በባለቤትነት ክልሎች ሲያስተዳድሩ፤ አካዳሚዎች ደግሞ በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ስር ይገኛሉ። የትምህርት ሚኒስትር፣ የጤና ሚኒስትር፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ወላጅ፣ አሰልጣኝ፣ ክለብ፣… ደግሞ ባለድርሻ አካላት እንደመሆናቸው ሥራውን በቅንጅት ያከናውናሉ። በዚህ ሂደትም ለዓመት ለሦስት ጊዜያት የመስክ ምልከታ፣ የብቃት ምዘና፣ ዓውደ ጥናት፣ ወቅታዊ ሪፖርት እና የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚካሄድም ሰነዱ ይጠቁማል።
ሰነዱ ገለጻ ከተደረገበት በኋላም ከተሳታፊዎች በርካታ አስተያየት ተሰጥቷል። የስልጠና ቁሳቁስ፣ የምግብ አቅርቦትና የላብ መተኪያ ላይ ቢታሰብበት፣ ሰልጣኞች ከክለቦች ብቻም ሳይሆን ከማናጀሮች ጋር በምን መልኩ ይሰራሉ፣ ወደ ውጭ አገራት ክለቦች የሚኖራቸው ዝውውር እንዴት ይሆናል፣ ስልጠናው ሳይጠናቀቅ ወደ ክለቦች የሚያደርጉት ዝውውር፣ በምልመላ ላይ መስፈርት ቢቀመጥ፣ እንደየ ስፖርት ዓይነቱ የምልመላ ዕድሜው ቢቀነስ፣ የስልጠናውን ጊዜ በዕድሜ ከመገደብ ይልቅ በሰዓት ማድረግ ቢቻል፣ ማስተግበሪያውን ወደ ሥራ ለማስገባት መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ማሰልጠኛ ሥፍራዎች አጠቃቀምን በተመለከተ፣ ማዕከላት ትኩረታቸውን በአትሌቲክስ ላይ ያደረጉ እንደመሆኑ የሌሎች እጣፋንታ ምን ይሆናል፣ እንደየ ደረጃው የአሰልጣኞች ደረጃ ቢወሰን፣… የሚሉ ሃሳቦች ተንጸባርቀዋል።
በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር ሲሳይ ሳሙኤል፤ ለሰነዱ ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶችን ማሰባሰቡ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ይጠቁማሉ። ክልሎች፣ ፌዴሬሽኖች እን ዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በአጠቃላይ አስተያየታቸውን በመስጠት ረቂቁ ዳብሮ ወደ ተግባር ይገባል። ይህ ሰነድ በትክክል ወደ ሥራ የሚለወጥ ከሆነም በስልጠናውና በአገሪቷ ውጤት ላይ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም እምነታቸው ነው። ሰነዱ ሲዘጋጅ በአገሪቷ ያሉትን የማሰልጠኛ ማዕከላትና አካዳሚዎች ልምድ እንዲሁም ጠን ካራና ደካማ ጎኖች በመያዝ ነው። ከዚህም ባሻገር በዘርፉ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው አገራት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዕከል እና አካዳሚ ለመባል መስፈርቶች በመነሻነት ተይዘዋል። አሰራሩ በወጥ አደረጃጀት፣ ደረጃ እና በተመሳሳይ አቅርቦት የሚካሄድ እንደመሆኑም በአንድ ቀን አዳር ይሳካል ለማለት እንደማያስደርም ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። ነገር ግን ማዕከላቱ በምን መልኩ መስራት እንደ ሚገባቸው ራሳቸውን ይመለከቱበታል፤ እንዲሁም ከዚህ በኋላ የሚከፈቱ የማሰልጠኛ ማዕከላት እንደ መስፈርት በመሆን የሚያግዛቸው መሆኑን አስረድተዋል። የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚ ሽነር ጌታቸው ባልቻ፤ ሰነዱ በዘርፉ በምን መልኩ ውጤታማ መሆን ይቻላል የሚለውን ለማመላከት የተዘጋጀ መሆኑን ይገልጻሉ።
ከሰነዱ የሚጠበቀውም፤ ማዕከላት ተሳስረው ውጤታማ ሥራ በማከናወን በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት ማግኘት ነው። በስፖርት ላይ በሚሰሩ አካላት 50ሺ እና ከዚያ በላይ የሆኑ ስፖርተኞች ሰልጥነዋል ይባላል፤ የሚታየው ግን ለአብነት ያህል በእግር ኳስ ስፖርት11 ተጫዋቾችን ማፍራት አለመቻሉን ነው። በርካታ የማሰልጠኛ ጣቢያዎችና ማዕከላት ኖሮን ሰልጥነው የሚወጡት ውጤት ማስመዝገብ ካልቻሉ አሰራሩንና አደረጃጀቱን ቆም ብሎ መመልከት አስፈላጊ ይሆናል። ይህ ሰነድ ዳብሮ ወደ ተግባራዊነት እንዲገባም ህግና መመሪያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እንደሚኖሩም ምክትል ኮሚሽነሩ ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
ብርሃን ፈይሳ