አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ በሚሰጠው ልዩ ትኩረት አዳዲስ 12 የዩኒቨርሲቲ ግንባታዎች ተደርጎ አራተኛው ትውልድ እንዲደርስ አስችሎታል፡፡ ከዚህ አንፃር በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ምን ላይ ይገኛል?
ዶክተር ሳሙኤል፡- በአራተኛው የማስፋፊያ ምዕራፍ ቦረና ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ 12 ዩኒቨርሲቲዎች ተካተዋል፡፡ በጥቅሉ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑ 45 ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ሲሆን፤ ሌሎች አምስት ደግሞ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ 170 በላይ የሚሆኑ የግል ተቋማትም መማር ማስተማሩን እየደገፉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የተያዙ የትምህርት ተቋማት ተደምረው አንድ ሚሊየን የሚጠጋ የተማሪ ቁጥርን ያስተናግዳሉ፡፡ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ በመንግሥትም በግልም በዚህ ያክል ደረጃ የተማሪ ቅበላ ማደጉ ትልቅ ዕመርታ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ አፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነቱ ገና ከ15 በመቶ በታች ነው፡፡
በተያያዘ መማር ማስተማሩ ዕድል ማስፋት ብቻ ሳይሆን የአገር ኢኮኖሚ በሚፈልገው ሙያ መስክ መሠማራታቸውንም በየደረጃው ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ወደ ተቋማቱ የገቡት ተማሪዎችም በገቡበት የትምህርት መስኮች በጥራት ተምረው መውጣታቸውን በየጊዜው መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ለማስፋፋትና ቁጥሩን ለሟሟላት ብቻ ማስፋፋት ጥራትን በመጉዳት ሥራ አጥነትን ሊያስከትል ይችላል። ችግሮቹ በአንድ ላይ ከመጡ ደግሞ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናን ይፈጥራል፡፡ ለዚህም ለኢኮኖሚው ማደግ የሚፈለገው የሰው ኃይል ብሎም ቴክኖሎጂ አብሮ ማደግ ይኖርበታል፡፡ የሰው ኃይሉ ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተዘጋጅተው እንዲወጡ ቢጠበቅም ዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል አንዳንዶቹ የሦስት አንዳንዶቹ ደግሞ እስከ 69 ዓመታት ያስቆጠሩ መሆናቸው የራሱን አሉታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡ የዕድሜ ልዩነቱም አንዳንዶቹ መማር ማስተማር ዋናው አጀንዳቸው ሳይሆን የተቋሙ መቀጠልና በሁለት እግሩ መቆም የሚያሳስባቸው ሌሎች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው የትምህርት ጥራት አሳሳቢው ጉዳይ አድርገው እንዲይዙት አድርጓቸዋል፡፡ የአገሪቱ የመማር ማስተማር ሂደት የት ደርሷል የሚለውም በሁለቱ መካከል ይቀመጣል፡፡ ለውጤትም ባለፉት ዓመታት የተሠሩ ስህተቶች መታረም ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ተሠሩ ያሏቸው ስህተቶች ምንድን ናቸው? መፍትሔዎቹስ?
ዶክተር ሳሙኤል፡- ባለፉት ዓመታት የማስፋፋት ዕቅዳችን በሚፈለገው የትምህርት መስኮች መሆን አለመቻሉ ያልተመጣጠነ የሰው ኃይል እንድናመርት አድርጎናል፡፡ ይህም መታረም ያለበት ችግር ነው። ማስፋፊያ ሲደረግ ጥራት ችግር እንደሚገጥመው ይታወቃል፡፡ ለዛም ያደረግነው ዝግጅት፣ የመደብነው ሃብትና የመራንበት አግባብ ክፍተት የነበረበት በመሆኑ እያረምን መሄድ ይገባናል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል የሚፈጠረው ልዩነት ተቋማቱ ያሉበት አካባቢ፣ የአመራር ብቃትና ቁርጠኝነትን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ይኖሩታል። በመሆኑም እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ተቋማቱ በእኩልና በተቀራራቢ ደረጃ እንዲጓዙም አስፈላጊውን ሥራ ይሠራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋማቱ ከግንባታ ባሻገር የመማር ማስተማሩን የሚደግፉ መሠረታዊ ግብዓቶችም እንደሌላቸው ያነሳሉ፡፡ በተለይም የመጽሐፍት ዕጥረት ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ይገለፃልና መንግሥት ይህን አውቆ ለማቃለል እየሄደበት ያለው ርቀት ምን ይመስላል?
ዶክተር ሳሙኤል፡- የመጽሐፍት አቅርቦት ውስንነት እንዳለ ይታወቃል፡፡ ማነቆው በመጽሐፍት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ግብዓቶች ላይም ይታያል፡፡ የሀብት ዕጥረቱ የሚያመጣቸው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ የመምህሩ ጥራት ላይ የሚነሱ ችግሮች መነሻ ምንጫቸውም ከሀብት ዕጥረት የመጣ ነው፡፡ ከመንግሥት የመክፈል አቅም ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጊዜ መለስተኛ አንዳንዴም ደግሞ ከዚህ በከፋ ሁኔታ አጠያያቂ አቅም ያለው መምህርም ተቀጥሮ በሥራ ላይ ይታያል፡፡ ጥሩ የሠራ ሦስት ዕጥፍ የሚያገኝበት ሌላ ዘርፍ እያለ መምህር መሆን እየፈለገ እንኳ በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች መምህር ሆኖ መቀጠርን አይፈልግም፡ ፡ ለዚህም የመምህር ዕጥረት ባለበት የዓለም ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ላይ የሚያስተምሩ የተሻሉ ምሁራን ያስተማሩትን በመውሰድ ተማሪዎች እንዲጠቀሙበት ማድረግም ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ከዓለም ጋር ከተገናኘን የሕትመት ጊዜያቸው የቆዩትን ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ዋጋ ገበያ ላይ ከወጡ በወራት ዕድሜ ያስቆጠሩ መጽሐፍትንም ማቅረብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ማግኘት የሚቻልበት አሰራር መዘርጋት ይገባል፡፡
በላብራቶሪ ላይ የሚታየውንም ዕጥረት የዓለም ቴክኖሎጂ በደረሰበት የተራቀቀ ስልጣኔ ላብራቶሪን መፍጠር ይቻላል፡፡ ይሄ ግን የተከለሰ ዕይታን ይሻል፡፡ መልሶ መመልከትን የሚፈልጉ በርካታ ውሳኔዎችም አሉ፡፡ መጽሐፍትን በተመለከተ በአገር ደረጃ የመጽሐፍ ቅጂዎች ከፍላጎቱ ጋር ተቀራራቢ በሆነ መልኩ ሊኖሩ ይገባል፡፡ የሚያነብ ማሕበረሰብን ለመፍጠርም ይህን መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ምክንያታዊ ትውልድን ለመፍጠር መጽሐፍት ያላቸውና የሚጫወቱት ድርሻ የላቀ እንደሆነ ቢታወቅም በአገር ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅጂዎችን አትመው ማዘጋጀት የሚችሉ ተቋማት አቅም መፍጠር ግን አልተቻለም፡ ፡
በአገር ውስጥ ምሁራኖች የተፃፉ መጽሐፍትም ቁጥራቸው እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ ይታያል፡፡ በመሆኑም ከውጪ እየገዛን በማስገባት የምንቀጥልበት ጊዜ መቋጫ ሊበጅለት ይገባል፡፡ ለዚህ አጠቃላይ መፍትሔ የሚሆነው አገር ሠላም አድርጎ ኢኮኖሚው በፍጥነት ማሳደግ በዚህም አገልግሎቱን በፍትሃዊነት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ቢወጡም አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ግን ብቃታቸው የተረጋገጠና በሰለጠኑበት የትምህርት ዘርፍ ብቁ እንዳልሆኑ ሲነገር ይደመጣል፡፡ በዚህም ተማሪዎቹ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ገበያ ሲወጡ ተቀጣሪ ያለመሆን ችግሮች ይታያሉና ይህን ችግር በምን ዓይነት መልኩ ለማቃለል ታቀደ? ተማሪዎች ሥራ አጥ እንዳይሆኑ አንድም በቅጥር ሌላም ደግሞ በትምህርት ቆይታቸው ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማስቻልስ ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፡- የብቃት ማረጋገጥ የአንድ ምዕራፍ ተግባር ብቻ አይደለም፡፡ ከጤና ጀምሮ ቢታይ የመጀመሪያ አንድ ሺህ ቀናት ላይ ለእናትና ለህፃን የቀረበ የምግብ ዓይነት ለአዕምሮ ጤናማ ዕድገት እጅጉን ወሳኝና የራሱን አስተዋፅዖ የሚያበረክት ነው፡፡ በመቀጠልም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቆይታ አጠቃላይ ትምህርት ሂደት ዩኒቨርሲቲዎቹ የተሟላላቸው መሠረተ ልማት ብሎም የመምህራኑ ብዛትና ጥራት እንዲሁም ልምድ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ብቃት ማረጋገጥም በግብዓት፣ በስርዓትና በአመራር ብቻ የሚመለስ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ብቃት ማረጋገጥ ተብሎ የሚወሰደው መውጫ ላይ ያለ መመዘኛን ነው፡፡ አንድን ተማሪ ለማብቃት ከመውጣቱ በፊት የተሠሩ ሥራዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡
የትምህርት ሥራ የቅብብሎሽና ሁሉም በየደረጃው አሻራውን የሚያሳርፍበት ነው፡፡ ተማሪው በቅቷል የሚባለው በማን ዓይን ነው? ለኢንደስትሪው ወይንስ ለመምህሩ? የሚለው ሊዳሰስ ይገባል፡፡ ኢንደስትሪው የተለየ አልያም የተሻለ ፍላጎት ካለው ኢንደስትሪው ፍላጎት አንፃር የተማሪዎችን ብቃት መቃኘት ይጠይቃል፡፡ ሥራውንም ሰፋ አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ጥራት ማረጋገጥ በሒደት የሚመጣ ሆኖ መፍትሔው የሚሆነው ዋናውን ቁልፍ ለይቶ ማወቅ ነው፡፡
በእኛ ዕምነት ደግሞ መምህር ነው ወሳኙ፡፡ ለአገሪቱ መፃዒ ዕድል ወሳኙ መምህር አቅሙን ከገነባ በበቂና በሚፈለገው ደረጃ የተማረ መምህር ካዘጋጀን ሌሎች ግብዓቶች ጉድለት እንኳ ቢኖር የመምህሩ አቅም ያካክሳል፡፡ በሌላ በኩል ከአንድ ተቋም ተመርቆ የወጣ ተማሪ ምን ላይ እንደደረሰ መፈተሸ የአንድ ጊዜ መረጃ ነው የሚሆነው፡፡ ሥራ መያዝ ሲዳሰስ በተፈጠረ ሥራ ላይ፣ ኢንደስትሪ በሚፈልገው መስክ ማዘጋጀታችን፣ ተማሪው ራሱን ለኢንደስትሪው ማዘጋጀቱ፣ በያዘው ዕውቀትና ክህሎት ብቻ ሳይሆን ኢንደስትሪው በሚፈልገው ቋንቋ የሥራ ቅጥር ማመልከቻ ማዘጋጀትን ለቃለመጠይቅ መቅረብንም ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተቋም ሥራ አማካሪ እንዲኖርና ተማሪዎች ቆይታቸውን ጨርሰው ሲወጡ ምን ዓይነት ኢንደስትሪ እንደሚጠብቃቸው፣ ለዚህ የሚፈለገው ዕውቀት፣ ክህሎትና የሥራ ሥነምግባር ምን መምሰል እንዳለበት ከስር ከስር የሚመክርና መስመር የሚያስይዝ አሰራር መዘርጋት አለበት በሚል በዴሊቨሮሎጂ የተያዘና የሚተገበር ነው።
የሥራ ቅጥር የተደረገው በሰለጠነበት ሙያ መስክ ወይንስ ቸግሮት የዕለት ጉርሱን ለማግኘት በማይመለከተው መስክ ነው የተቀጠረው በሚል የሥራ ጥራቱም መታየት ይኖርበታል፡፡ ይህን በተመለከተም ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ደግሞ በአንድ ላይ በተማከለ ሁኔታ እንዲደረግ ስርዓት ተፈጥሯል፡፡ ወጣቶቹ ያላቸው ሃሳባዊ ዕውቀት ወደ ተግባር ቢቀየር በሚሊየን የሚቆጠር ገቢ ሊያስገኝ ቢችልም ሃሳባቸውን የሚያጎመራባቸው ወደ ተግባር የሚለውጥባቸው የሚያማክሩት ሰውም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የሥራ ፈጣሪነት ማዕከላት በየተቋማቶቹ እንዲፈጠሩ ማድረግና ይህንን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ጋርና ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደግሞ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ማዕከል ጋር በመሆን ሥራው ስምንት በሚደርሱ ተቋማት ተጀምሯል፡፡ ከተጀመረ አራት ዓመታት ገደማ ያስቆጠረው ይህ ሥራ በተወሰነ ተቋማት የሚደረግ በመሆኑ ተሞክሮውን ወስዶ ማስፋትን ይጠይቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፍኖተ ካርታው ላይ በጥናት ከተቀመጡ ችግሮች መካከል አንዱ የመምህራን ጥራት ጉዳይ ነው፡፡ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት መምህራን በመሆናቸው በዚህ ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
ዶክተር ሳሙኤል፡- መምህራን እንዴት ወደ ስርዓት ውስጥ እንደሚገቡ፣ በዛም ውስጥ አቅማቸው እንዴት እንደሚጎለብት አልፎም የማይሆናቸውም ከሆነ ከስርዓቱ የሚሰናበቱበት ስርዓት መጠናከር ይገባዋል፡፡ በዚህ ላይ አቅማቸውን ለማጎልበት በትኩረት ይሠራል። በታችኛው እርከን የሚያስተምሩ መምህራን ቀደም ብለው መምህር እንደሚሆኑ ወስነው የገቡ፣ ሞያው ሥራ ሲጠፋ የሚገባበት ሳይሆን ሁኔታዎች ቢመቹም ባይመቹም አገርና ትውልድ ለመቅረጽ የሚሠራበት በመሆኑ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አምነው በቁርጠኝነት የሚገቡ መምህርን ናቸው የሚፈለጉት፡፡ ዩኒቨርሲቲ ላይ መምህር ሲሆን ደግሞ ጥሩ አፈፃፀም ያሳየ ትምህርቱን ከመስጠት ባሻገር መልካም ሥነምግባር ያለው ሊሆንም ይገባል፡፡
መምህር ባለአደራ አባት ነው ከተባለ በዛ ልክ ለሌሎች የሚሰጠው መልካም ሥነምግባር የተላበሰ መሆን ይኖርበታል፡፡ የተሻለ አፈፃፀም ኖሯቸው ወደ ሙያው ከገቡ በኋላም በቀጣይነት አቅማቸውን ማሳደግ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎም ጥራት ያላቸው መምህራንን የማፍራት ሥራ የአንድ ጀምበር ተግባር አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ስላስተማሩ አልፎም ሕግና ሥርዓት ማዕቀፎች ስለተዘጋጁ ብቻም ችግሮቹ ይቃለላሉ ብሎ መጠበቅ አዳጋች ይሆናል። ሙያው አገር የመቀጠልና ያለመቀጠልን የሚወስን በመሆኑ በዛ ልክ ራስን ማዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ የየኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ቅንጅት አሰራር ላይ ክፍተት እንዳለ ይነሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጉድለቱን የሚሞላ ምን ዓይነት ተግባርን ለማከናወን ታቀደ? ምንስ እየተሠራ ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፡- ዩኒቨርሲቲዎች ከድሮዎቹ የዩኒቨርሲቲ ባህል አልወጡም፡፡ በጣም ትልልቅ ሰው የማይገባበት የተዘጋ ግቢ፣ ፕሮፌሰሮቹ ከግቢያቸው የማይወጡበትና ላብራቶሪዎች ላይ የሚመራመሩ ሌላ ዓለም ፈጥረው ከሚንቀሳቀሱበት ዘመን ጠቅልለው አልወጡም፡፡ ይህም ሊስተካከል የሚገባው በመሆኑ በሩን መክፈትና የሚመራመሩትም የማሕበረሰብ ችግር ለማቃለል መሆን ይኖርበታል፡፡ ትስስሩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያወጡት የሰው ኃይል ኢንደስትሪው የሚፈልገው እንደሆነ ለማረጋገጥ እንዲሁም የሚሰጡት ዕውቀትና ክህሎት ኢንደስትሪው የሚፈልገው ዓይነት መሆኑን ለማረጋገጥ ያስችላቸዋል። ለኢንደስትሪዎች ደግሞ በቀላሉ ሠራተኛ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል፡፡ ምርምር ተሠርቶም ችግሮቻቸው በቀላሉ ይፈቱላቸዋል፡፡ ጥብቅ የሆነ የዩኒቨርሲቲ፣ የኢንደስትሪ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትና የምርምር ተቋማት ትስስር አስፈላጊነት ታምኖ በአገር ደረጃ በ 19 ክላስተር ለመፈፀም ቢታሰብም በሚፈለገው ፍጥነት አልሄደም፡፡ በዚህ ላይ በቀጣይም በስፋት መከናወን የሚገባቸው ተግባራት ይኖራሉ፡፡ በቅርቡም ከዚሁ ጋር በተያያዘ መድረክ ይዘጋጃል፡፡ ይህም የራሱ የሆነ አስተዋፅዖ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውስጥ ሌላው የምርምር ሥራዎችና የሚደረጉ ጥናቶችም የቴክኖሎጂ ሽግግር ተደርጎባቸው ታች ያለው የሕብረተሰብ ችግር በለየና በሚያቃልል መልኩ ማሕበረሰብ አገልግሎት ማቅረብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሚስተዋሉ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸው ይገለፃልና ከዚህ ጋር ተያይዞ ተቋሞቹ ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ዶክተር ሳሙኤል፡- በተቋማቱ ዋናው ሥራና ጊዜውን እየወሰደ ያለው የመማር ማስተማሩ ነው፡፡ በአገሪቱ ሁኔታ ምርምር ባይሠራም የሚመጣበት ጉዳት የለም፡፡ ምሁሩን በሣምንት 12 ሰዓታትን ካስተማረ አልተመራመርክም ብሎ የሚጠይቀው አካል የለም። ስለዚህ ይህንን በሕግና በስርዓት መመለስ ይፈልጋል በሚል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በተጨማሪ ምርምር ይሠራል ቴክኖሎጂ ይወጣል፡፡ ነገር ግን ለማሕበረሰቡ ይጥቀም አይጥቀም የሚያረጋግጥ ስርዓት የለም፡፡ ስለዚህ ይህንን ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖ እየተሠራ ይገኛል፡፡ አንዳንዴ ምርምሮቹ ከመደርደሪያ ያልዘለሉ እንደሆኑ ይነሳል፡፡ ነገር ግን መደርደሪያ ላይ መቀመጣቸውንም መፈተሸ ይጠይቃል፡፡ ቴክኖሎጂዎች ወጥተዋል ወይ? ዕውነትም አሉ ወይ? የተባሉት ቴክኖሎጂዎችስ የኢትዮጵያን አርሶ አደር ሕይወት መቀየር ይችላሉ አይችሉም? በሚል በጥልቀት ሊፈተሽም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያልዳሰሰ ምርምር ግለሰቡን ሊያሳድግ ይችላል፡፡ ነገር ግን የአገሪቱን አርሶ አደር ካለበት ሁኔታ ፈቀቅ የማያደርግ ከሆነ ተደምሮ ውጤት አያመጣም፡፡ በማሕበረሰብ አገልግሎት ላይ የአተያይም ችግር በመኖሩ በተገቢው መንገድ ማረምም ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ ተደርጎ ተይዟል፡፡ በድምሩ ቢታይ በአገር ደረጃ ገና ያልተሠራበትና ብዙ ሺህ ማይሎችን መሄድ የሚጠይቅ ዘርፍ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋማቱ ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲፈፅሙ ሠላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር ማድረግ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ አለመረጋጋትን በሚፈጥሩ አጀንዳዎች ሰለባ ሲሆኑ ይታያል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ዘላቂ ሠላማዊ መማር ማስተማር እንዲሠፍን ምን ይሠራል?
ዶክተር ሳሙኤል፡- ሠላማዊ መማር ማስተማር ከአገራዊ ሁኔታ ጋር በተወሰነ መልኩ ይያያዛል፡፡ ተቋሞች ሠላም የሚያሳጣቸው በተቋሙ የተፈጠሩ ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ ከሌላ ቦታ የሚገቡ ብዙ አጀንዳዎችም ተደማምረው ነው፡፡ በዚህ ውስጥም መንግሥትን በመጥላት የሚደረግ ፖለቲካዊ ትግልንና አገር መጥላትን ለይቶ አለማየት ይስተዋላል፡፡ በተማሪዎች ውስጥ ያልተገባ አስተሳሰብ አቆጥቁጦ በሕዝቦች መካከል ልዩነት እንዲጎላና መቃቃር እንዲፈጠር መሥራት አገር መጥላት ነው፡፡ መንግሥትን በመንቀፍ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ ቢቻልም፤ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት በመፈፀም አገርን መጉዳት ግን ወንጀል ነው፡፡ ዜጎች እንዲጋጩ ሕዝቦች እርስ በእርስ ያላቸው መተማመን ጠፍቶ በውስጣቸው ጥርጣሬ እንዲነግስ፣ ተማሪዎች በብሔራቸው፣ በሐይማኖታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ተከፋፍለው ለአገርም ለተቋማቸውም ስጋት እንዲሆኑ የሚሠሩ አካላት አሉ፡፡ እነዚህን ልብ እንዲገዙና ከተማሪዎች ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ በሚኒስቴሩና በሌሎችም ባለድርሻ አካላት የጋራ ትብብር ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ውጪም በተቋማት ውስጥ ለሠላማዊ መማር ማስተማር ዕጦት መነሻ የሚሆኑ በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡
መንግሥት ሁሉንም ነገር ችሎ የሚያስተምርበት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ነገር ግን በተቋማቱ ደረጃ በተመሳሳይ ተማሪዎችም ኃላፊነት ሲወስዱ አይታይም። ከአገሪቱ የዕድገት ደረጃ አንፃር ይህን ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ኃላፊነቱን የሚሸከም ትውልድ ሊፈራበት ግን ይገባል፡፡ ርዕሰ መዲና የሆነችው አዲስ አበባን ጨምሮ ከተሞች ውሃና መብራት ያጣሉ፤ መቆራረጥም ያጋጥማቸዋል፡፡ ነገር ግን በተቋማቱ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር ሲያጋጥም ተማሪዎች አይታገሱም፡፡ ለዚህም ቁጭ ብሎ መነጋገርን ይጠይቃል፡፡ ትውልዱ ከታች ጀምሮ ኃላፊነትን መውሰድ እንዲለማመድ ወላጆች በዚህ መልኩ ልጆችን አንፆ መቅረጽና ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕብረተሰቡም በዚህ መልኩ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሲኖር ተገቢ አለመሆኑን የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ በዝቅተኛና በከፋ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ሕይወታቸውን ከሚገፉ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዜጎች ጉሮሮ ላይ ተወስዶ ዩኒቨርሲቲ ተገንብቶ የሚቀርብ ምግብን የሚደፋ ተማሪ ምን እንደደፋ ማወቅ መቻል ይኖርበታል፡፡
ስንት ሺህ ሕፃናትና እናቶች ሕክምና እያስፈለጋቸው ብሎም በሚሊየን የሚቆጠሩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ባሉበት አገር ላይ ለእነርሱ ቅድሚያ ሳይሰጥ ከድህነት የመውጫ ቁልፍ የትምህርት ዘርፉ ነው የሚል ዕምነት ተይዞ የቀረበ ሃብት በትልቅ የአደራ ስሜት ከትህትና ጋር ነው መጠቀም ያለባቸው፡፡ ችግሮቹንም ተማሪዎች ወደ ራሳቸው ወስደው መመልከትና መፍትሔ አካልም መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አገሪቱ ካላት በጣም ውስን ከሆነው ሀብት ትልቁን ድርሻ የሚሠጠው ለትምህርት በመሆኑ በጥንቃቄ መጠቀም ካልተቻለ ነገ ችግሩን የሚያስታግስ ወጣት፣ ፈፃሚና አመራር ካላፈራንበት ኢትዮጵያ ከድህነት ጋር መዝለቋ አይቀሬ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የኒቨርሲቲ የገባው ኃይል የልማት ኃይል በመሆን ዕድገቱን አ
ፍጥኖት አገሪቱን ከድህነት አረንቋ ሲያወጣ ጎዳና ላይ የወደቁ ወንድምና እህቶቹን ሊታደግ በሚችልበት መንገድ ሊቀረጽ ይገባል፡፡ ከዜጎች ሕክምና ተቀንሶ የተማረው ይህ ዜጋ ከእንስሳት ጋር ውሃ ተሻምተው የሚጠጡ ዜጎችን መታደጉንም ያረጋግጣል፡፡ ሠላማዊ መማር ማስተማርን ለማስፈን በሚኒስቴሩና አጠቃላይ በመንግሥት ደረጃ ስርዓት መዘርጋትና በዛ ውስጥ ማስተዳደር እንዲሁም ተጠያቂነት ማረጋገጥ ብቻ በቂም አይደለም፡፡ ተቋሙ፣ ሕብረተሰቡ፣ መምህሩና ተማሪውም ለሠላማዊ መማር ማስተማሩ የራሱን ድርሻ ወስዶ ሊወጣ ይገባል፡፡ ይህን ካደረግን የችግሩ መግቢያ ይጠባል፡፡ ሚኒስቴሩ በየጊዜው አንድ የትኩረት አጀንዳው አድርጎ ይንቀሳቀሳል፡፡ ለዚህ የሚረዳ ልዩ ዕቅድ ይዘጋጃል፡፡ ተማሪዎችም በተለያዩ ድርጊቶች ላይ ተሳትፎ ከማድረጋቸው በፊት ነገሮችን መመዘን ይኖርባቸዋል፡ ፡ በምክንያታዊነት የሚያምን ዜጋን መፍጠርም ቁልፍ መፍትሔ ይሆናል፡፡ የሚያስፈልገውም ለሌሎች መኖር የሚችል፣ የሚመራመር፣ በዕውቀት ላይ ተመርኩዞ በክርክርና በሃሳብ ፍጭት የሚያምን ትውልድ ነው፡ ፡ በዕውነትና በተጨባጭ ጉዳይ ላይ ተመስርቶ የሚቃወምና የሚደግፍ ማሕበረሰብ መፍጠር ቀጣይ ሥራ ተደርጎ ይተገበራል፡፡ መንግሥት ይቀየራል የማትቀየረው ግን ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ናቸው። እሷንም በተባበረ ክንድ ከችግር መጠበቅና ማዳን ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ትምህርት ቁልፍ ዘርፍ ነውና በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያጋጠሙ ችግሮችንም ለማቃለል በቀጣይ የተያዙ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ሳሙኤል፡- መንግሥት ለትምህርት ትኩረት ሰጥቷል ስንል በአሁኑ ወቅት ሚኒስቴሩን ለሁለት መክፈሉ እንደ ዓይነተኛ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በሀብት ምደባ ላይም ሲታይ ትልቅ ሀብት የሚመደበው በዚሁ ዘርፍ ላይ ነው፡፡ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ላይ ነው፡፡ ይህን ደግሞ የሚያስፈፅም ሚኒስቴር እንደ አዲስ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በዚህ ውስጥ አምስቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ይገኛሉ፡፡ ተደራሽነትን ማስፋት አንዱ ሲሆን፤ የትምህርት ጥራቱ ችግር ውስጥ በመውደቁ ይህንን ቁልፍ ጉዳይ መፍትሔ ማበጀት ደግሞ ሌላው ይሆናል። በሌላ በኩል በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ላይ ያልተረጋገጠው የትምህርት ፍትሐዊነት ማረጋገጥ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ ተይዟል፡፡ ምርምራችን፣ ቴክኖሎጂ ሽግግራችንና ማሕበረሰብ አገልግሎቱም እንደነገሩ ነው፡፡ ይህንን ማስፋትም ጥራቱንም ተገቢነቱንም ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የተገኘችው ትንሽ ሀብት ለላቀ ውጤት የሚመራበት አግባብ የተቋሙ አመራርና አስተዳደር በልዩ ሁኔታ የሚሠራበት ዋነኛ አቅጣጫ ተደርጎ ይሠራበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑልን እናመሰግናለን!
ዶክተር ሳሙኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011