አሲዮ ብለን፣ የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ ስንል ገጥመን፣ በጥሌ ዜማ፣ በዘሪቱ ጌታሁን እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ፣ በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ ብለን ተምነሽንሸንና የአዲስ ዓመት ብስራታችንን መስከረምን ሸኝተን፣ ከገናና ከፋሲካ፣ ከአረፋና ከረመዳን በረከት ተቋድሰን፣ በኑሮ ውድነትና በኮሮና ስጋት ተይዘን፣ በጦርነትና በሞት ስጋት ተከበን አያልፍ የለ 2014 እየተንገዳገደ አስር ወራትን ቆጥረን እንሆ ሰኔ ላይ ከተምን። ጊዜ ሕይወት ነው.. ጊዜ ስኬት ነው። ጊዜ ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን በጎውን እንድናደርግ እድል የሚሰጠን አጋጣሚ ነው።
እኔም በዚህ የጊዜ ምህዋር ላይ ተረማምጄ የክረምት ሁሉ አባት በሆነው ሰኔ ላይ ቆሜ ክረምትን ለበጎነት ስል መጣሁ። ጊዜ ድር ነው.. ጊዜ እኔና እናተ የተሸመንበት ማግ ነው። ጊዜ ሕዝብ ለሀገር፣ ሀገር ለትውልድ የምትሰጠው የቅብብሎሽ በትር ነው። በጊዜአችን ውስጥ በጎ ነገር ስናጣ፣ ጊዜአችንን ተጠቅመን ለራሳችንም ሆነ ለሌላው መልካም ነገር ማድረግ ሲያቅተን ያኔ ዘመን የሸመነው ሰውነታችን እያረጀና እየጃጀ እንደ ልብስ እናልቃለን ከዛም ከእድሜ አመሻሽ ላይ ቆመን ‹ወይኔ እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ› ብለን እንቆጫለን።
ሰኔ የክረምት መግቢያ በር ነው። ሰኔ ዝርክርክ ብሎ የሚያዝረከርከን የጸጋና የመከራ ጌጣችን ነው። ወፍራም በመልበስና የላመ በመብላት አንሸሸውም ምክንያቱም ወፍራም መልበስ የማይችሉና የላመ ለመብላት አቅም የሌላቸው ወገኖች አሉንና ነው። ሰውነት ስለ ሌላው መታመም ነው። ሰውነት በሌሎች ስቃይ መሰቃየት ነው። ክረምት ደግሞ ስለሌላው እንድንታመምና እንድንሰቃይ የሚያደርግ ጥሩ አጋጣሚያችን ነው። ምክንያቱም በክረምት ቤት የሌላቸው፣ በክረምት መሸሸጊያ ያጡ ነፍሶች ብዙ ናቸውና ነው።
ክረምት እንባና ሳቅ ነው። የሞቀ ቤት ያለን እኔና እናተ እንደምንስቅ ሁሉ ክረምት በመጣ ቁጥር የሚያለቅሱ፣ መግቢያ የሚያጡ ነፍሶች ጥቂቶች አይደሉም። ክረምት ለሀገራችን በጎውን እንድንሰራ እድል ከሚሰጡን አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ ነው። እንጸድቅበት ዘንድ ጥሩ አጋጣሚም ይመስለኛል። በእርግጥ ለመጽደቅም ሆነ ለሀገር መልካም ለመስራት ሁሉም ጊዜአቶች እኩል ቢሆኑም የክረምትን ያክል ሀገር ወገን የሚረዳበት ጊዜ አለ ብዬ አላስብም።
ምክንያቱ ደግሞ ክረምት ሲመጣ ይዟቸው የሚመጣው ብዙ ችግሮች ስላሉ ነው። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ጎርፍ፣ የአካባቢ መጥለቅለቅ፣ የመንገድ መበላሸት፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎች በቂና አስተማማኝ መኖሪያ ስለሌላቸው በክረምቱ መቸገር የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። እንግዲህ ክረምትን ለበጎነት የሚለው መነሻ ሃሳቤ ትርጉም የሚያገኘው እዚህ ጋ ነው።
እንደሚታወቀው ሀገራችን ብዙ ድሆች የሚኖሩባት ሀገር ናት። የእኛን እርዳታ፣ የእኛን ድጋፍ የሚፈልጉ አያሌ የማሕበረሰብ ክፍሎች አሉ። ክረምት ሲሆን ደግሞ ይሄ ማሕበራዊ ምስቅልቅል እጅጉን ይጨምራል። በዚህም መሰረት ለወገናችን የምንደርስለት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን እላለሁ። በጎ መሆን ከኪሳችን የምናወጣው ሳይሆን ከልባችን የምናወጣ ነገር ነው። በዙሪያችን የእኛን በጎ መሆን የሚሹ ብዙ ማሕበራዊ ችግሮች አሉ። ሀገር የምትቆመው የአንዱን ችግር አንዱ የኔ ነው ብሎ ሲነሳ ነው። ዜግነት ትርጉም የሚያገኘው የወገኖቻችንን ስቃይ መሰቃየት ስንችል ነው።
ለራስ ብቻ በማሰብ ውስጥ፣ ለራስ ብቻ በመኖር ውስጥ ዜግነት የለም። ሀገር ማለት ምንድነው ብሎ ለጠየቀ የመልካም ልቦች ሕብረት ነው የሚል መልስ ያገኛል። በእውቀታችን፣ በጉልበታችን፣ በገንዘባችን ለሀገርና ወገን አለኝታ መሆን ካልቻልን እኛ ምንም ነን ማለት ነው። ስለሆነም ክረምት ይዞብን የሚመጣው ማሕበራዊ ቀውስ የታወቀ ነውና ከወዲሁ መረዳዳታችንን ማጠንከር ይኖርብናል። በጎነታችንም በዙሪያችን ካሉ የሚጀምር ነው። በጎነታችን ከሰፈርና ከጎረቤት የሚጀምር ነው።
ክረምቱ ስቃይ እንዳይሆንባቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወገኖቻችንን ችግሮቻቸውን ጠይቆ በመረዳት መፍትሄ መስጠት ሰኔን የምንበቀልበት አንዱ መንገድ ነው እላለሁ። ቤት ለሌላቸው ቤት በመስራት፣ ቤታቸው ያረጀባቸውን ቤታቸውን በማደስ፣ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ወገኖቻችንን ክረምቱን የሚያልፉበትን መንገድ በመፍጠር በተለያየ መልኩ ክረምቱን በበጎ ስራ ማሳለፍ እንችላለን።
በዛው ልክ ከተጠቀምንበት ክረምት ጸጋችን ነው። የሚያዘንብልንን ዝናብ ለበጎ ነገር የመጠቀም አቅሙና ሕብረቱ ካለን ከነበርንበት የድህነት ዝቅታ ከፍ ማለት ይቻለናል። በዓለም ላይ ቀዳሚ ያደረገንን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ያሳካነው እኮ በክረምት ጸጋ ነው። ከራሳችን አልፈን አፍሪካን ያማከለ የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ያደረግነው እኮ በሰኔ ጉርምርምታ ታጅበን ነው። የታላቁ ህዳሴን ሶስተኛ የውሃ ሙሌት ለማስተናገድ የተዘጋጀነው እኮ በክረምት ሃይል ነው። እጆቻችንን ለልማት፣ ልቦቻችንን ለመልካም ስራ ያተጋነው እኮ ክረምት ስለመጣ ነው። ዘንድሮም ብዙ ችግኞችን ለመትከል እቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ያለነው እኮ በክረምት ጸጋ ነው። እንደዚሁም ደግሞ የአቅመ ደካሞችን ቤት አድሰን ለመመረቅና ለመመስገን የተነሳነው እኮ በዚህ ጊዜ ነው።
ከሁሉ በላይ ደግሞ የመኖር ዋስትናችን የሆነው የአርሶ አደሩ መሬት የተሻለ ምርት ይይዝ ዘንድ ክረምት እጅግ አስፈላጊያችን ነው። አብቅለን ለመብላትና እያሰቃየን ካለው የኑሮ ውድነት ተላቀን ጥሩ ኑሮ ለመኖር ክረምት ዋስትናችን ነው። እንዲሁም ደግሞ አዲሱን ዓመት በደስታና በፍቅር እንድንኖር ክረምት ያሻናል እንዴት ላለኝ እንዲህ እለዋለው..ሁሉም አዲስ ዓመት የሀምሌና የነሀሴን ክረምት ጠጥተው ያማሩና የቆነጁ ናቸው። የምንናፍቀው መስከረም እንኳን አምሮና ተውቦ የምናገኘው ከፊቱ ባሉት የክረምት ወራት ተደግፎ ነው።
ዓለም ላይ መለያችን የሆነው፣ ጳጉሜን ተንተርሶ ነፍስ የሚዘራው አደይ አበባ እኮ የሀምሌና የነሀሴ ጽንስ ነው። በዓመት አንድ ጊዜ ብቅ ብላ የምትሰወረው የመስቀል ወፍ እኮ ጎጆዋን የምትቀልሰው በመስከረም ተስፋ ነው.. ተስፋዋን የሰጣት ደግሞ ክረምት ነው። እናም ክረምት ከተጠቀምንበት ጸጋችን ነው ካልተጠቀምንበት ደግሞ መከራችን ይሆናል።
ከእኛ የሚጠበቀው በክረምት ጸጋ እየተጠቀምን ችግሩን በጋራ ማሸነፍ ነው። ክረምት የፍቅር ወቅት ነው። ከመቸውም ጊዜ በላይ በዚህ ወቅት መዋደድና መፋቀር ይኖርብናል። በክረምት ጠብና ቁርሾ የማይታሰብ ነው። በክረምት ሁሉም ጦረኞች ጦር የሚጥሉበት፣ ይቅር ለእግዜር ተባብለው ወደ ስራ የሚገቡበት ጊዜ ነው። በክረምት እልኸኞች እልሃቸውን ትተው ወደ ልማት የሚሰማሩበት ነው። ምክንያቱም የክረምት ጸጋ በዓመት አንዴ ስለሆነ ነው። ቤታችንን በጋራ ሰርተን፣ ፍቅራችንን በጋራ አለምልመን ቀጣዩን የበጋ ወራት በደስታና በአንድነት እናልፍ ዘንድ ዛሬን መረዳዳት ግድ ይለናል።
መንግሥት ይሄን የክረምት ወቅት ለብዙ የልማት ስራዎች መጠቀም አለበት። እኛም ዜጎች በዚህ ክረምት ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች በጎ ስራ በመስራት ሃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል። ክረምትን በጦርነት ያሳለፈ ማሕበረሰብ ቀጣዩ ጊዜው የስቃይ ጊዜ ነው የሚሆነው። በክረምት ያላበቀለ፣ በክረምት ይቅር ያልተባባለ ጠበኛ መጪው ጊዜ ጥሩ አይሆንም። በክረምት ቂማችንን ካልተውን፣ በክረምት ትጥቅ ካልፈታን መጪው ጊዜ ይበረታብናል። እናም ክረምትን ለይቅርታና ለልማት፣ ለመረዳዳትና ለመተጋገዝ እንድናውለው አሳስባለሁ።
ሀገር መውደድ ሰውን መውደድ ነው። የሀገር ፍቅር ስሜት ከሚገለጽባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ አስቸጋሪ ጊዜዎችን በጋራ ማለፍ ነው። ከፊታችን ያሉ ጊዜዎች መልካም የሚሆኑት ዛሬ ላይ በምናደርገው ድርጊት ነውና ከነውር ወጥተን ሊጠቅመን በሚችል በጎ ስራ ላይ ማሳለፍ ይጠበቅብናል። ልባችንን ለበጎ ካስገዛን ክረምት የምንረዳዳበት ትክክለኛ ጊዜ ነው። ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ ከመቸውም ጊዜ በላይ ክረምት ስቃይ የሚሆንባቸው ብዙ የማሕበረሰብ ክፍሎች አሉ። ከመከራው አንጻር ጭራሽ ክረምት ባልመጣ ብለው የሚመኙ ጥቂቶች አይደሉም። ይሄ ደግሞ ክረምት ምን ያክል ችግረኛው ማሕበረሰብ ላይ እንደሚበረታ አንዱ ማሳያ ነው።
በዚህ ጊዜ ነው ለወገናችን ልንደርስለት የሚገባው። በእንዲህ ያለው ወቅት ነው አጋርነታችንን ልናሳይ የሚገባን። በክረምት የሚያለቅሱ አይኖች፣ የሚባቡ ልቦች ጥቂት አይደሉም። ዙሪያችንን ቃኘት ማድረግ ብንችል ብዙ ችግረኛ ሰዎችን ማግኘት እንችላለን። በክረምት ቤታቸው ዝናብ እያስገባ የሚሰቃዩ እናቶች ጥቂት አይደሉም የነሱን እንባ ማበስ ደስታው ምን ያክል እንደሆነ መገመት አይከብድም። በክረምት መጠጊያ አጥተው ጎዳና ላይ እትት የሚሉ ችግረኛ ወገኖች አሉ እነሱን መታደግ በረከቱ ምን ያክል እንደሆነ አይጠፋንም። በክረምት መንገዶች በጎርፍ ይጥለቀለቃሉ፣ ይቦረቦራሉ፣ ጉምና ጭጋግ ስለሚበዛ በዚህም የትራፊክ አደጋ ከፍ ይላል። እኚህ ሁሉ ክረምት ወለድ ሀገራዊና ማሕበራዊ ችግሮቻችን እልባት የሚያገኙት በእኛ መልካም ተግባር ነውና ክረምትን ለበጎነት እንጠቀምበት እላለሁ።
በክረምት የመሬት መንሸራተት አደጋ ያይላል። በከተማም ሆነ በገጠር እንዲህ አይነቱ አደጋ የተለመደ ነው። ይሄን አይነቱን አደጋ ለመቅረፍ ከአሁኑ የእርከን ስራዎች ቢሰሩ መልካም ሆናል። አምና በዚህ ሰአት የክረምትን መግባት ተከትሎ የተከሰቱ በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች አሉ። እነዛን አደጋዎች ለመከላከል ሁላችንም ባለንበት መልፋት ይጠበቅብናል። ክረምትና የትራፊክ አደጋም እንደዚሁ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሆነው ከትናንት ዛሬ የዘለቁ ናቸው። የመሬት መንሸራተት ስለሚኖር በዛው ልክ የትራፊክ አደጋው ይጨምራል። ጉሙና ጭጋጉ ሲጨመርበት ደግሞ ወትሮ ሃይ ባይ ያላገኘው የትራፊክ ችግራችን በእንቅርት ላይ ሆኖ ለአደጋ ተጋላጭ ነው የሚያደርገን። እግረኛም ሆነ አሽከርካሪ መጪውን ጊዜ ግምት ውስጥ በማስገባት ከወዲሁ ለራሱ ዋስትና ቢሰጥ መልካም ነው እላለሁ።
በሁሉም ነገር ለሀገራችን ዘብ የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን። በልማቱም በሰላሙም በእርቁም ለሀገራችን ውለታ የምንውልበት ጊዜ ላይ ነን። ብልህ ሰው ነገውን ዛሬ የሚሰራ ነው። ብልህ ሰው አስቸጋሪ ጊዜዎችን በመተባበር የሚያልፍ ነው። እኛም በቀና ልብ ነጋችንን ዛሬ መስራት ይኖርብናል። አስቸጋሪ ጊዜዎቻችንን በመነጋገርና በመመካከር ማለፍ ግድ ይለናል። መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን በመልካም ልብ የምናከናውናቸው ተግባራት ብዙ ናቸው። ከወዲሁ ተጋግዘን እልባት ካልሰጠናቸው በቀር ክረምትን ተከትለው የሚመጡ ማሕበራዊ ቀውሶች ቀላል የሚባሉ አይደሉም።
ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳኒቱ እንደሚባለው ክረምት ወለድም ሆኑ በጋ ወለድ ችግሮቻችን በአንድነት የሚረቱ ናቸው። ሀገር በመረዳዳት ውስጥ ውብ ናት። ለብቻ ቆመን፣ ለብቻ አስበን የምናሳካው አንዳች ነገር የለም። የኔ ችግር የማሕበረሰቡ ችግር ነው። የአንተ ችግር የኔና የሌላው ችግር ነው። ይሄን እውነት ታሳቢ አድርገን ለጋራ ጥቅም በጋራ መንቀሳቀሳችን ትርፍ እንጂ ጉዳት የለውም። እስካሁን ድረስ ያልተሳካልን ለብቻ ስለቆምን ነው። ይሄ ክረምት አንዱ ለአንዱ አጋርነቱን የሚያሳይበት፣ ያለው ለሌለው አለሁልህ የሚልበት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ችግሮቻችንን በህብረትና በአንድነት ካልሆነ በመለያየት የማንወጣበት ጊዜ ላይ ነን። መለያየት ጥቅም ቢኖረው ኖሮ ከማንም በፊት እኛ እንጠቀም ነበር። ግን ጥቅም የለውም..ተለያይተን ያተረፍነው ነገር የለም። ስለዚህም በዚህ የክረምት ወቅት በዙሪያችን ላሉ ሁሉ መልካም የምንሆንበት ጊዜ ነው። ለጎረቤቶቻችን፣ በአካባቢያችን ላሉ ችግረኞች የምንደርስበት ጊዜ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2014