መገናኛ ብዙሃን ለአንድ አገር ህልውና መሰረት ከሚባሉት የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የገጠሙን ችግሮችን በማራገብም ሆነ መፍትሄ በማፈላለግ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እና ባለሙያዎች የማይተካ ሚና አላቸው የሚል የፀና ዕምነት አለኝ፡፡
መገናኛ ብዙሃን ሀገርን በመገንባት የሚኖራቸው ሚና በቀላሉ አይታይም፡፡ በዚያው ልክ ሀገርን በማፍረስም ያላቸው አሉታዊ ሚና እጅግ የጎላ ነው፡፡ ምዕራባውያን አንድን ሀገር ማፍረስ ሲፈልጉ የመጀመሪያ ሥራቸው በመገናኛ ብዙሃን ነፃ ሃሳብን ማራመድ በሚል ብሂል ሥም የማጥፋት ዘመቻ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ይህን በማድረጋቸውም በርካታ ሀገራትን አፈራርሰዋል፡፡
ለአብነት ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ እና ሌሎች ሀገራትን ለማፈራረስ የመጀመሪያ ሥራቸው የነበረው በሀገራትና በመንግሥታት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ውስጥ መግባት ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ሲ.ኤን.ኤን እና ሌሎች መሰል ሚዲያዎች የሚሰሩት ሥራዎችና ሲሰሩ የቆዩትን ተግባራት ማስታወስና መመልከት በቂ ነው፡፡
የመን የምትባለው ሀገር መንግሥት አልባ የሆነችው በጦርነት ብቻ ሳይሆን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ሌት ተቀን በከፈቱት የፕሮፓጋንዳ እና የሚዲያ ዘመቻ ነው፡፡
ሶማሊያ ጠዋትና ማታ የደም አብዓላ የሚያጥለቀልቃት ራሳቸው በፈጠሩት ችግር ሳይሆን፤ የምዕራባውያን ሚዲያ ሳይታክቱ በዘሩት የጎሳ ልዩነትና የጥላቻ ዘመቻ ነው፡፡ በዚህም ሞቃዲሾ በየቀኑ በአሸባሪዎች እየተናጠች ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ምዕራባውያን ባቀጣጠሉት የውሸት ፕሮፓጋንዳ በሩዋንዳ የዘር ፍጅት እንዲከሰት ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የምዕራባውያን ሚዲያ የጥፋት ቡራኬውን ይጀምሩና፤ መንግሥታቶቻቸው ደግሞ በሠላም ማስከበርና ሌሎች ሰበቦች ወደሚፈልጉት ሀገር ዘው ብለው ይገባሉ፡፡
እነዚህ ፈተናዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያ ላይም በተመሳሳይ መልኩ ፤ከዛም በከፋ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወሳል፡፡ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች በፈጠሩት እና እየፈጠሩት ባለው ችግር ሀገር ስትታመስ እየተመለከትንም ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በዘውጌ አስተሳሰብ የተፈጠሩና እሳቤያቸው ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጋር የተጋጨ የመገናኛ ብዙሃን እየተበራከቱ መምጣታቸው ችግሩን አግዝፎታል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ያልተገባ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት ይገኛል።
የመገናኛ ብዙሃን በአግባቡ እና በሃላፊነት ካልተያዙ ከፍ ያለ ችግር ምንጭ ስለመሆናቸው የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የዲጂታል ሚዲያው ማደግ ችግሩን በእጅጉ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ከምንም በላይ በምጣኔ ሀብት ያላደጉ ሀገራት ፈተናው ይፀናባቸዋል፡፡ ቲውተር፣ ማህበራዊ ሚዲያ (ፌስ ቡክ)፣ ኤሜይል እና ሌሎች የመረጃ መለዋወጫ መንገዶች በአንድ ጎኑ መልካም ቢሆኑም ታዳጊ ሀገራትን ግን ክፉኛ እየተፈታተኗቸው ይገኛሉ፡፡
ችግሩ ለታዳጊ ሀገራት መዘጋትና መክፈት በማይችሉት አሊያም ቁልፉ በሌላ እጅ ያለ ቤት ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በርካቶች ሃሳብን በነፃነት የሚገልጹባቸው ሳይሆን አመፅ ፤ የተበረዙና የተመረዙ መረጃዎችን ተሸካሚ አደገኛ የዘመኑ የጦር መሳሪያ ሆነዋል፡፡ መንግሥታትን በአየር ላይ እስከ መሾምና መሻር የዘለቀ ድፍረትም እየተላበሱ መጥተዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ እውነታ የሀገራችንንም የጋዜጠኛነት ሙያ ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት መፈታተን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። ሀገሪቱ እያጋጠማት ባለው ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ችግር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆነም ይገኛል። በሽርፍራፊ ሳንቲሞች በመደለል የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት ጀምሮ ግለሰቦች መፍጠር ለሚፈልጉት ተራ ጀብድ መሳሪያ በመሆን ላይም ነው።
እስካሁን ባለው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ሀገር አልባ ሕዝብና መንግሥት እየተፈጠረ ያለው ከጦርነት በፊት ሆነ በጦርነት ወቅት በሚሰራጩ መርዘኛ መረጃዎች ነው፡፡ መረጃዎቹ የሚፈጥሩት የተዛባ አስተሳሰብና ከዚህ የሚቀዳው ለጥፋት ዝግጁ የመሆን መነቃቃት ነው ወደ ዋናው ግጭት (ጦርነት) የሚወስደው፡፡
ከዚህ አንጻር በሀገራችን እንደ አሸን እየፈሉ የመጡ የማህበራዊ ሚዲያ ጀግኖች (ፌስ ቡከሮች) እና ዩቱዩበሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል። ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሚል እየሄዱበት ካለው መረን የወጣ መንገድ የሚመለሱበትን አሰራር መፍጠር ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሳይቻል ለሚፈጠረው ጥፋት ከሁሉም በላይ የመንግሥት ተጠያቂነት ከፍ ያለ ይሆናል።
በየትኛውም መልኩ የመንግሥት ሆደ ሰፊነት ሀገረ መንግሥቱንና ሕዝብን አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል መሆን የለበትም። የመንግሥትንም መንግሥትነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆን የለበትም ፤ የተሳሳተን እንዳይሳሳት ማስተማር ሲሳሳት መገሰጽና ማረም እምቢ ሲል በተገቢው የሕግ አግባብ መቅጣትና ችግሮች ሳያድጉና ባህል ሳይሆኑ ማስቆም የአንድ ጤነኛ መንግሥት ባህሪ ነው።
የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 790/ 2008 በመግቢያው እንዲህ ይላል ‹‹በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት እንዲሁም ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች የተረጋገጠውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል….”፡፡
“…ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመገናኛ ብዙሃን መብቶች በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ ሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶችን ለማረጋገጥ ያላቸውን ፋይዳ በመገንዘብ እና በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት የሚደረገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን የሚጫወቱትን የማይተካ ሚና በመረዳት…›› እያለ አዋጁን ማውጣት አስፈላጊ እንደሆነ ያብራራል፡፡
ከዚህ መረዳት የሚቻለው በኢትዮጵያ ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸው ሀገርን በመገንባት፣ ዴሞክራሲን በማስረጽና በማበልጸግ ብሎም ከዘመኑ ጋር የተስማማ ማሕበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ላይ ሚናቸው እጁን የጎላ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ማለት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማሳደግ መገናኛ ብዙሃን የተሰጣቸውን ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ የሚያሳስብም ጭምር ነው፡፡
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች በተለይም ደግሞ ዩቱዩበሮች የኢትዮጵያን ህልውና ጭምር የሚፈታተኑ መረጃዎች በማሰራጨት መጠመዳቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፤ የተወሰኑትን ደግሞ በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ ለማድረግ በሕግ ሂደት ላይ መሆናቸው አብራርቷል፡፡ ይህ መሆን ያለበትና የሚጠበቅም ነው፡፡
ሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃንን ነፃነት ለመጠበቅ ብሎም ሕግን አክብረው እንዲሰሩ ለማድረግ ሲባል በአዋጅ ጭምር የተደገፈ መብትና ግዴታን በግልጽ ማስፈሯን አቅሎ ማየት አይገባም፡፡ የትኛውም የመገናኛ ብዙሃን በሀገር ሉዓላዊነት እና ጥቅም ላይ የመደራደር የሞራል ብቃት ሆነ ሙያዊ ተጠየቅ የለበትም፡፡
በተለይም አሁን ባለንበት ሀገራዊ የፈተና ወቅት መገናኛ ብዙሃን ሀገርና ሕዝብ የማረጋጋት ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው። ሽርፍራፊ ሳንቲም ለመቃረም ከአሉባልታና ከፈጠራ ወሬ ወጥተው ተጨባች በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሚዛናቸውን የጠበቁ ፣ ለሙያው ሥነምግባር የተገዙ ዘገባዎችን ማሰራጨት፤ ለዚህም እራሳቸውንም ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2014