መንገዱ ብዙ የሚየስጉዝ ይመስላል፤ ነገር ግን እጅግ አጭር ነው:: ለአውነት በቀረቡ ትዕይንቶችና ትረካዎች ስለሚታጀብ ብዙዎች ያጎርፋል፤ ነገር ግን መድሻው እሾሀማ ውጤቱ ደግሞ የከፋ ነው:: በተለይ በዚህ ቴክኖሎጂ በተንሰራፋበት አለም ይህ አቋራጭ መንገድ ብዙዎች ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ:: በርካቶች ጅማሮው ላይ ባዩት ተታለው አቋራች ነው ባሉት የተሳሳተው መንገድ ገፍተው ይሄዱበታል::
ምን አልባት ዕድለኛ ሆነው ብዙ ሳይገፉ ከመንገዱ ከሚመለሱት በስተቀር፤ በዚያው ላይመለሱ እስከመጨረሻው የሚሄዱ ይበረክታሉ:: ተጓዦቹ ብቻቸውን ቢሆን መልካም ነበር፤ ነገር ግን ብዙዎችን አሳስተውና የበርካቶችን አመለካከት አዛብተው ማስኬዳቸው ነው ክፋቱ:: እያወራሁ ያለሁት በዚህ በአሁኑ ዘመን በማህበራዊ ሚዲያ ውሸት መነሻቸው አድርገውና እብለትን ተመርኩዘው ለመታወቅ ስለሚሯሯጡ ግለሰቦች ነው:: በርካቶቹ ዩቱዩብ፣ፌስ ቡክና ቲክ ቶክ ላይ መዋያና ማደሪያቸው አድርገዋል:: እነዚህ ተጠቅመው በአቋራጩ መንገድ ብዙዎችን ጠልፈው ያስገባሉ::
በአሁኑ ወቅት እውነት ከሚናገረው ይልቅ የሚሰማው የሚቀጥፈው ሆኗል:: ሀቅ ላይ የቆመው ሳይሆን የሚደመጠው የሚያስመስለው መስሏል:: ሰበቦችና ተጨባጭ ያልሆኑ ምክንያቶች ደርድሮ እንዲህ ሆነ አልያም ደግ እንዲያ ተባለ ብሎ እውቅናን በመቀዳጀትና ወዳጅ ማብዛት ለብዙዎች አቋራጭ መንገድ ሆኗል:: ለእርነሱ ዋንኛ ጉዳይ ተከታይ ማብዛት በሚያገኙት የእይታ መጠን ገንዘብ መሰብሰብ በሚመለከትላቸው ሰው ልክ ንዋይ ማጋበስ ነው:: እኛ ደግሞ መረጃ ለመስማት ጉጉ ነንናወደነሱ እንቃረባለን:: ባልተረጋገጠና ተጨባጭ ላልሆነው ትክታቸው ተገዢ ለተዛባ መረጃቸው ተጠቂ ያደርናል:: እነሱ ለመታወቅ ብለው የጀመሩት አቋራጩ መንግድ እኛን አስጉዞ ከማይበጀን ቦታ ያደርሰናል::
እናንተዬ ኢትዮጵያችን እነሱ ከላይ የጠቀስኩላችሁ ማህበራዊ ሚዲያ እየተጠቀሙ እንደሚገልጹልን አይነት ብትሆን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር:: ደግነቱ እነሱና እውነቱ እጅጉን የተራራቁ ናቸው:: እነሱ በሚወሸክቱት የሚያገኙትን ገቢ ላይ ተመርኩዘው አልያም ይህቺን አገር ለመጉዳት ከሚያሴሩት ጋር አብረው የእኛን አሉታዊ ሁነቶችን ሁሉ አግዝፈው ያቀርባሉ:: የፈካ ገፅታችንን ሸፍነው ያልነውን ያሳዩናል:: አንድነታችን መላላቱን፣ የእርስ በርሳችን መፋጀት፣መጠላላት፣መነቋቆር፣መገፋፋት መለያችን አድርገው በጥቂት መነሻና በብዙ ቅጥፈት እያጎሉ ለእኩይ አላማቸው ያውሉታል:: በአቋራጭ ለመክበርና ለመታወቅ ይጠቀሙበታል::
አሁን ላለንበት አገራዊ ሁኔታ መውጫ ይሆነን ዘንድ ጥበብንና ትዕግስት የእኛ መለያ ሊሆን ይገባል:: እውነትን ለማየት ጥበብ መጠቀምና እውነታው ከሀሰቱ እንዲለይ መታገስ በብርቱ ያስፈልጋል:: የጠቢቡ ሰለሞንን ጥበብ መላበስ የእዮብን ትዕግስት መጎናፀፍ ያሻናል:: ጥበብ መላበስ እውነትን ከሀሰት ያስለያል:: ትዕግስት ደግሞ ከተሳሳተ እርምጃ ይጠብቃል::
አዎ ነገሮችን በጥበብ መለየት ከአሳሳቾች ይጠብቃል:: ጠቢቡ ሰለሞን ሁለት እናቶች አንድን ህፃን ልጅ “የእኔ ነው፤ የእኔ” በሚል ክርክር ገጥመው የህፃኑ ልጅ እናት ማንነት የለየበት ልዩ ጥበብ ያስደንቀኛል:: ወዶቼ አስቡትማ ያቺ የምር ልጅዋን በሌላ “የእኔ ነው” የተባለባት እውነተኛዋ የህፃኑ እናትና የራስዋን ያልሆነን ልጅ “የእኔ ነው” ያለችው እናት መሀል ያለው ልዩነት::
በእርግጥ ሁለቱም እናቶች ልጅ ወልደው ነበር:: አንደኛዋ ወዲያው በሞት ተነጠቀች እንጂ:: አያችሁ ይህ ለጉዳዩ እውነትነት የቀረበ ምክንያት ነው:: ሁለቱም መውለዳቸው:: እናት የወለደችው ልጇን ታቅፋ በተኛችበት በዚያች ወልዳ ልጇ በሞተባት እናት ተሰረቀባት:: እናት የእስዋ ልጅ ፈፅሞ እንዳልሞተና እንደተሰረቀባት ባወቀች ጊዜ ልጄን መልሽልኝ አለቻት:: ነገር ግን ልጅዋን በሞት ያጣችው እናት “አይ ይሄ የእኔ ልጅ ነው፤ የአንቺ ሞቷል” አለች::
ይሄኔ ክርክር ተነሳና አለመግባባቱ ጠነከረ:: ሁለቱም እናቶች ልጁ የእኔ ነው በሚል ሙግት ውስጥ የሚያስታርቃቸው ጠፋ:: በመጨረሻም ንጉሱ ዘንድ ቀረቡ:: ይህ ንጉስ ጥበበኛ ነበርና ሁለቱንም ጎን ለጎን አቁሞ ሀሳባቸውን ጠየቀ:: ሁለቱም ልጄ ነው ያሉበትን ምክንያትና እውነት አስረዱ:: ያቀረቡት ማስረጃ ሁሉ ግን ተመጣጣኝ ነበር:: እውነትና ውሸት ልክ የሚያስመስል ማስረጃ ታውቃላችሁ:: ልክ እንደዚያ ማለት ነው:: ይሄኔ ጥበበኛው ንጉስ አንድ ነገር አሰበና ለወታደሮቹ እንዲህ ብሎ አዘዛቸው::
ጎራዴ አምጡና ልጁን ለሁለት ቦታ ክፈሉት እናም የልጁን አካል ግማሽ ግማሽ ይካፈሉት አላቸው:: ሴቶቹም በዚህ ይስማሙ እንደሆን ጠየቀ:: ይሄን አንደኛዋ እንደተስማማች ተናገረች:: አንደኛዋ ደግሞ በዚህ ሀሳብ ደንግጣ ተብረከረከች:: ልጇ ሊቆረጥ ነውና ፍርሀት ያዛት በሀሳቡም አልተስማማችም:: እያለቀሰች ፤ ልጁ ለሁለት ተከፍሎ ከሚጎዳብኝ እና ከሚሞት እርስዋ ትውሰድ ብላ ተናገረች:: በዚህ ንግግር የህፃኑ እውነተኛ እናትነት ተለየ::
ልክ እነደዚህ ጥበብን መላበስ እውነትን ማጥራት ይጠይቃል:: ለአቋራጭ መንገደኞች ልብን ከፍቶ ከመስጠት ይልቅ ለምን ብሎ መጠየቅ፤ዓላማቸው ጠንቅቆ መረዳት ያሻል:: አዎን የእኛ እውነት ለሌሎች ለመግለጥ የሚያስፈልገን ጥበብ ነው:: እዚያው እውነት ላይ ፀንቶ በመቆም የሚገኝ ዘላቂ የሆነን ድል ማጣጣም ነው ያለብን:: የዚህች ታላቅ አገር እውነት ላይ መፅናት፤ የዚህ ህዝብ በሀቅ ላይ መቆም ፈፅሞ ሳይለዝብ መቀጠል የሚኖርበት ወቅት ላይ ነን:: እውነታችን ተቀምተን የቆምንበት ሃቅ ተወስዶብን ዛሬ ተሸናፊ መስለን ልንታይ እንችል ይሆናል:: ነገር ግን እያደር እውነት ፀሀይ መሞቅዋ አይቀርም::
እርግጥ ነው፤ እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል:: በትዕግስት ውስጥ የሚገኝ ድል ይጥማል:: በጥረት የሚገኝ ስኬት ወደር የሌለው ነው:: እውነት ላይ ፀንቶ የቆመ የቆመለትን ዓላማ ሳያሳካ ቢያልፍ እንኳን በእውነት መዛግብት ውስጥ ጎልቶ ይወሳል:: የያዘው እውነት የቆመበት ሀቅ ውሎ አድሮ ሁሉም ይረዳውና ስለእውነት ብሎ በፈፀመው ታላቅ ተግባር ሲዘከር ይኖራል:: በተፈጥሮው ተሰባሪ የሆነው ሰው የማይሰበረውና ዘላለማዊ የሆነው እውነት ከራሱ በላይ ከፍ አድርጎ ማንገስ የሚገባው ለዚሁ ነው::
ወገን ለእራሳቸው እኩይ ዓላማ እኛ ያለንበት እውነት ሲያዛቡብን ስምን ዝም እንላለን:: እኛ ያለንበት እውነት ከመግለጥ ባለፈ ያላችሁት ውሸት ነውና አቁሙ፤ይልቁንም እውነትን ይዛችሁ መዋደዳችንን አብስሩልን አንድነታችን የሚያጠነክር መተሳሰራችን ከፍ የሚያደርግ ስራ ስሩልን ማለት ይኖርብናል::
እውነት የሚያዘቡትን ተው ብለንና አስቁመን እኛም እንደ ህዝብ እውነት ላይ መቆም ያለብን ለዚህ ነው:: ምድር በሙሉ በሀሰት ትርክት ተገፍቶ እኛ ላይ ቢፈርድ ለእውነት እስከቆምንና እዚያ ላይ እስከፀናን ድረስ አሸናፊዎቹ እኛ ነን:: አበቃሁ፤ ቸር ያሰማን::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014