አዲስ አበባ:- ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ተሳታፊ ሃሳብ በማዋጣት የተሻለ ሀገር ለመፍጠር በጋራ የሚሠራበት መሆን ይኖርበታል ሲል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገለጸ።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ተሳታፊ ሃሳብ በማዋጣት የተሻለ ሀገር ለመፍጠር በጋራ የሚሠራበት መሆን ይኖርበታል።
በኮሚሽኑ እየተሠራ ያለውም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው፤ ምክክሩን አስመልክቶ የተሳሳተ እሳቤም ሆነ እልህ የተጋባው አካሄድን በመቀየር የተገኘውን ዕድል ሃሳባችንን በትክክል በመግለጽ መጠቀም መቻል አለብን ብለዋል።
በመንግሥት በኩል ዕድሉን ከመፍጠር ባለፈ ምክክሩ እውነተኛ እንዲሆን፣ ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ ነገሮች እንዲፈቱ በትክክል መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተክርስቲያን በምክክሩ መታየት ያለባቸው ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቆሙት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ተራና ተጨባጭነት የሌላቸው የተሳሳቱ ታሪኮች እና ትረካዎች አሉ። በተደጋጋሚ በመነገራቸው ምክንያት እንደ እውነት ተወስደው ሰዎች በአደባባይ በድፍረት ሲናገሯቸው ይደመጣል ብለዋል።
የበዓላት ጥያቄዎች ሌሎችም አሉ ግን በመግባባት መካሄድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ቤተክርስቲያኒቱ በሀገር ግንባታ የራሷን ሰፊ አስተዋፅኦ አድርጋለች። በውስጧ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የተለያየ ውግንና ሊኖራቸው ይችላል። ያ ከንቃተ ህሊናቸውና ከነበራቸው እውቀት የሚመነጭ እንጂ ተቋማዊ አይደለም ሲሉም ያስረዳሉ።
የተሳሳቱ ትርክቶች የሌሎች እምነት ተከታዮች ላይ አሉታዊ እሳቤዎች እንዲኖሩ ሊያደርግ ይችላል የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በአንዳንድ አገልግሎቶች ቀደም ባለው ጊዜ በጣም እንደተጠቀመች አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ ጭምር አለ። ይህም ቤተክርስቲያኗን መበደልን እኩልነትን ለማስፈን የሚደረግ እንቅስቃሴ የሚቆጥሩ ሰዎች እንዲኖሩ አድርጓል ብለዋል።
እኩል ዕድል መፍጠር ማለት አንድን ቡድን ወደፊት በመግፋት፣ ሌላውን ደግሞ ወደ ኋላ እንዲቀር ማድረግ አይደለም። ምክክሩ እንዲህ አይነትና መሰል ትርክቶችን ለማረም የሚጠቅም በመሆኑ ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል ሁላችንም እገዛ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም