በሀገር ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረው መርሃ ግብር ውጤታማ እየሆነ ነው

አዲስ አበባ፡- የብልፅግና ፓርቲ በቤተሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል ያስጀመረው መርሃግብር ፍሬ ማፍራት መጀመሩን መመልከት መቻላቸውን አመራሮች ገለጹ።

የፌዴራልና የክልል የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአዳማ ከተማ የተለያዩ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

‘’የህልም ጉልበት ለእምርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የብልፅግና ፓርቲ የከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና ተሳታፊዎች በአዳማ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

ጉብኝቱ የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ በጥቃቅን እና አነስተኛ ዘርፍ የተሠማሩ ኢንተርፕራይዞችን ያካተተ ነው። ከፍተኛ አመራሮቹ የብልፅግና ፓርቲ በቤተሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል ያስጀመረው መርሐ-ግብር ፍሬ ማፍራት መጀመሩን መመልከት መቻላቸውን ገልፀዋል።

የሌማት ትሩፋት ራስን በምግብ ለመቻል እና የሥርዓተ ምግብ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የገለፁት ከፍተኛ አመራሮቹ ፓርቲው ለመርሐ ግብሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ለሌማት ትሩፋት የተሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን በመጠቆም በቤተሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

በሌማት ትሩፋቱ የተመዘገቡ ውጤቶች የይቻላል መንፈስን የፈጠሩ እና የማህበረሰቡን የሥራ ባህል የቀየሩ መሆናቸውን በመጠቆም በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ማስፋት እንደሚገባም ገልፀዋል።

በተለይ በአዳማ ከተማ በሌማት ትሩፋት ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ አበረታች ሥራዎችን መመልከት መቻላቸወን ገልፀዋል። መሰል ተሞክሮዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በአዳማ ከተማ እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠና ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በሚገባ ተረድቶ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ብቁ ሆኖ ለመቆም የሚያስችል አቅም የፈጠረላቸው መሆኑንም አመራሮቹ ገልፀዋል።

ፓርቲው ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋጥ በሚያደርገው ጥረት በተለይ የአመራሩ የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ወሳኝ መሆኑን ከፍተኛ አመራሮቹ ገልጸዋል።

በጉብኝቱ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም የሁለቱ ከተማ ከንቲባዎችን ጨምሮ ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You