196 ሠልጣኞች በዓመቱ ወደ አካዳሚ ይገባሉ

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በአዲስ አበባ ማሠልጠኛው እንዲሁም በአሰላ የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላቱ ለ2017 ዓ/ም ሠልጣኞች ምልመላ አካሄደ፡፡ አካዳሚው ሠልጣኞችን በሳይንሳዊ መንገድ የብቃትና የጤና ምዘና በማድረግ ልየታውን ማከናወኑንም አካዳሚው አስታውቋል፡፡

ታዳጊ ስፖርተኞችን በሀገሪቷ ከሚገኙ ፕሮጀክቶችና የሥልጠና ማዕከላት በመመልመል ለአራት ዓመታት በሳይንሳዊ መንገድ በማሠልጠን ለክለቦችና ለብሄራዊ ቡድኖች ከሚያበቁ ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ነው። አካዳሚው ለ2017 ዓ/ም የሚቀላቀሉትን የአዳዲስ ሠልጣኞች ምልመላ ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ በሁለቱም ጾታ 196 ሠልጣኞች በዓመቱ ሥልጠናቸውን የሚጀምሩ ይሆናል። ምልመላው በተለያዩ ዙሮች ሲከናወን ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተገኙ ተመልማዮች በመጀመርያው ዙር በሴቶች እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌት እና ቦክስ ስፖርቶች በስኬት ማጠናቀቁን አካዳሚው አስታውቋል። ሁለተኛው ዙር ምልመላም በአትሌቲክስ (ሩጫ፣ ዝላይና ውርወራ)፣ በፓራሊምፒክ እንዲሁም ቮሊቦል ስፖርቶች የሚከናወን ይሆናል፡፡

በሳይንሳዊ ዘዴ ሠልጣኖችን ለብቁ ስፖር ተኝነት የሚያበቃው አካዳሚው ምልመላውን የሚያከናውነውም በሳይንሳዊ መንገድ ነው፡፡ መሰል የታዳጊ ሥልጠናዎች ከእድሜ እና ከብቃት ጋር የተያያዙ የተገቢነት ጥያቄዎችን ማስነሳታቸው የተለመደ ነው፡፡ ይህንን ለመቅረፍም በስፖርት ሳይንስ ምሁራን እንዲሁም በዘመናዊ የስፖርት ላቦራቶሪ የተደራጀው አካዳሚው በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ምልመላውን የሚያከናውነው የቴክኒክ፣ የታክቲክ፣ የብቃት አመላካች፣ የላቦራቶሪ ምርመራ፣ የጤና፣ የአካል ብቃት እና የሥነልቦና ምርመራዎች በማካሄድ ነው፡፡ የተመልማዮችን መረጃ በአንድ ቋት በመሰብሰብና እንደየስፖርት ዓይነቱ በተቀመጠው ግልጽ የመመልመያ መስፈርት ውጤታማ የሆኑ 594 እጩዎችን በአዲስ አበባው ማሠልጠኛ በመጥራት የመጨረሻ ዙር ምልመላው ተከናውኗል። ይኸውም ደረጃውን በጠበቀ የማዘውተሪያ ሥፍራ ከሚደረገው የብቃት ምዘና በተጨማሪ በተሟላ የህክምና ምርመራ፣ የተለያዩ ልኬቶችን ለማድረግም ታስቦ ነው፡፡

አካዳሚው የሥልጠና ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት ወደ ክለቦች በማሸጋገር በምትካቸው ሌሎች ሠልጣኞችን በየዓመቱ ይቀበላል፡፡ ለዘንድሮ የሥልጠና ዓመትም ከሃምሌ 25 አንስቶ እስከ ነሃሴ 20/2016 ዓም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች አካዳሚውን ሊቀላቀሉ የሚችሉ ታዳጊዎች ምልመላ በባለሙያዎች ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህም እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን እንደየስፖርት ዓይነቱ በመስፈርቱ መሠረት ልኬት በማድረግ እንዲሁም የጤና እና የሥነልቦና ዝግጁነታቸውን በመፈተሽ ወደ ቀጣዩ ምዘና እንዲያልፉ ይደረጋል፡፡ በዚህም ጥልቅ ምርመራ እና ምዘና በማድረግ የመጨረሻዎቹ እጩዎች የሚለዩ ይሆናል። ሥልጠናውም ለቀጣይ አራት ዓመታት በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቦክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌት፣ ቅርጫት ኳስ እና ፓራሊምፒክ ስፖርቶች የሚከናወን ይሆናል።

የነባር እና የአዳዲስ ሠልጣኞች የዘንድሮ ሥልጠና ከመስከረም 18/2017 ዓ/ም የሚጀምር ሲሆን፤ አካዳሚው በአጠቃላይ 750 ሠልጣኞችም ይኖሩታል፡፡ ከ2005 ዓ/ም አንስቶ ታዳጊዎችን ተቀብሎ ኢትዮጵያን ለማስጠራት የሚችሉ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚተጋው አካዳሚው ከሥልጠናው ባለፈ የማደርያ፣ የምግብ እንዲሁም የመደበኛ ትምህርት አገልግሎት ለሠልጣኞቹ ይሰጣል፡፡

አካዳሚው ያፈራቸው እንዲሁም ሥልጠና ላይ የሚገኙ ታዳጊዎቹ ከሀገር ውስጥ ውድድሮች ባለፈ በዓለም አቀፍ ቻምፒዮናዎች በግልም ሆነ በቡድን ደረጃ ሀገርን በሚያኮራ ደረጃ ወክለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በአትሌቲክስ ስፖርት ለሜቻ ግርማ፣ ያለምዘርፍ የኋላው፣ አብርሃም ስሜ፣ ጌትነት ዋለ፣ ዘርፌ ወንድማገኝ፣ መልኬነህ አዘዘ፣ ኤርሚያስ ግርማ፣ በእግር ኳስ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዷ የሆነችው አረጋሽ ካልሳ በወንዶች ደግሞ የዋሊያዎቹ አባል የሆነው ሱሌማን ሃሚድ፣ በፓራሊምፒክ ገመቹ አመኑ፣ በወርልድ ቴኳንዶ በብቸኝነት ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ የወከለው ሰለሞን ቱፋ፣ በቦክስ ሃና ደረጀ፣ እንዳሻው አላዩ፣ በብስክሌት ሄለን ፍሰሃ የመሳሰሉ ምርጥ ስፖርተኞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You