ዜና ትንታኔ
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ናት። እነዚህ ቅርሶች ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ ይዘታቸው የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ ከመያዝ ባለፈም የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማሳደግ ረገድ አይነተኛ ሚና አላቸው። በ2016 ዓ.ም በዘጠኝ ወራት ብቻ በቱሪዝም ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ሆኗል።
በተለይ በመስከረም ወር የሚከበሩት መስቀል፣ ኢሬቻ፣ ፍቼ ጨንበላላና የተለያዩ ብሔሮች የዘመን መለወጫ በዓላት የቱሪዝም ገቢን ከማሳደግ አኳያ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።
በዓላቱት ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዕድገት ያላቸውን ሚና ከማሳደግ አኳያ ፤ ሁነቶቹን ከማስተዋወቅ ፣ቱሪስቶችን በአግባቡ ከመቀበልና የቆይታ ጊዜያቸውን ከማራዘም አኳያ ምን ያህል አይነት ሥራዎች ያስፈልጋሉ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የቱሪዝም ዘርፍ መሪዎች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አምባሳደር ናኒሴ ጫሊ እንዳሉት፤ የመስከረም ወር የቱሪዝም ወር ተብሎ ሊጠራ የሚችሉ ሁነቶችን የያዘና የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ የሚችል ወር ነው።
ወርሀ መስከረም የኢትዮጵያ የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የአዲስ ዓመት በዓላት በደማቅ ሁኔታ የሚያከብሩበት፣ እንዲሁም ክረምቱ አልፎ አዲስ ዘመን የሚታይበት፤ የተለያዩ ኃይማኖታዊና የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት ወር እንደመሆኑ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚነሱ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ያስረዳሉ።
በተጨማሪ ሶስተኛው ዙር የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ የተደረገበት ወር እንደመሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለአዲስ ዓመትና ለመውሊድ በዓላት መግባታቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይም ለመስቀልና ለኢሬቻ በዓላት የሚገቡ ዜጎች እንደመኖራቸው በተያያዥነት በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስጎብኘት የሚቻልበት አማራጭ መኖሩን ይጠቁማሉ።
ጎብኚዎች ሲመጡ ሀገሪቷን በደንብ ለማስተዋወቅ እንዲቻል ከክልሎች ጋር በመተባበር ዝግጅት መደረጉንም አንስተው፤ አገልግሎት ሰጪዎች የተሻለ ገቢ እንዲገኝ የሚረዱ አሠራሮችን በመከተል ለእራሳቸውም ለሀገራቸውም የሚጠቅም ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅናቸው ይገልጻሉ።
ቱሪዝም ልዩ እንክብካቤና ሳቢ አገልግሎትን ይፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በዓላትን አስታኮ የሚመጡ እንግዶች ከበዓላት በኋላት ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ አስጎብኚዎች፣ ሆቴሎች፣ ሙዚየሞችና የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች እንዲሁም ቅርስ አስተዳዳሪ አካላት በተሻለ የእንግዳ አቀባበር ሥርዓት መስተንግዶ መስጠት ከቻሉ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገቢ ማሳደግ ይቻላል ሲሉ ይጠቁማሉ።
ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩም በወሩ የሚከናወኑ የተለያዩ በዓላት ለቱሪዝም ገቢ ዕድገት ያላቸውን ሰፊ ጠቀሜታ በመረዳትና ከክልሎች ጋር በመነጋጋር የተለያዩ የጉብኝት ጥቅሎችን አዘጋጅቶ እያስተዋወቀ ይገኛል ይላሉ።
በደቡብ የሀገሪቷ ክፍል ያሉ አንዳንድ አካባቢዎች የዘመን መለወጫ በዓላትን በመስከረም ወር እንደሚያከብሩ አመላክተው፤ በዓላቶችን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ እንግዶች ከነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና ከጫሞ ሐይቅ ጋር የተያያዙ የጉብኝት መርሃግብሮች ላይ እንዲሳተፉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይመላክታሉ።
በየአካባቢው የሚገኙ ሌሎች የቱሪስት መስህቦችን በመለየት የማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ ለማድረግ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባም ያስረዳሉ። በዓላቱ በሚከበሩበት ወቅት በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙ፤ በዩኔስኮ የተመዘገቡና አዲስ የለሙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ዜጎች በልዩ ሁኔታ ማስጎብኘት እንደሚገባም ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪስት ቁጥር የምታስተናግድባቸው ወቅቶች የዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁን ያለንበት ወር ደግሞ የሁለተኛው ትውልድ ኢትጵያውያን ሀገሪቷን የሚጎበኙበት ወቅት እንደመሆኑ በርካታ ገቢ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅበት ነው ይላሉ።
የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሲከበሩ በርካታ ሚሊዮን ሕዝቦች አደባባይ ወጥተው በአብሮነት፣ በፍቅርና በአንድነት የሚያከብሯቸው በዓላት ከመሆናቸው ባሻገር ከመላው ዓለም የሚመጡ ቱሪስቶች የሚታደሙባቸው ደማቅ ሥነ-ሥርዓቶች መኖራቸውን ይጠቁማሉ።
አቶ ስለሺ እንደተናገሩት፤ በዓላቶቹ ኃይማኖታዊ እንዲሁም ባህላዊ ትውፊት የሚፈጸሙባቸውን ሁነቶች ይዘዋል። ከኃይማኖታዊና ባህላዊው ሥርዓታቸው ባለፈም ኢኮኖሚውን የማነቃቃት ሚናቸው የጎላ ነው።
የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለመጨመር እንግዶች በሚሄዱበት አካባቢ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ለሆቴል አሰሪና ሠራተኞች፣ ለአስጎብኚዎችና ለተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች ሥልጠና መሰጠቱን ይናገራሉ።
ሥልጠናው ቀጣይነት ያለው ምቹ አገልግሎቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ጎብኚዎች በማቅረብ የቱሪዝም ገቢውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
በተጠናከረ ሁኔታ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያድግ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑ ሚኒስትር ዴኤታው ይገልጻሉ።
ከውጭ ዜጎች በተጨማሪ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ቅርሶችን መጎብኘት እንዳለባቸው የጠቆሙት ኃላፊዎቹ፤ አገልግሎት ሰጪዎችና የክልል ቱሪዝም ቢሮዎች በተጠናከረ ሁኔታ በመሥራት ቱሪስቶች ባህላዊ፣ ኃይማኖታዊና ማህበራዊ ሁነቶችን ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ገቢያቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸውም አጽንኦት ሠጥተዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም