ትራምፕ ከሀሪስ ጋር እንዲከራከሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልቀበልም አሉ

ትራምፕ ከሀሪስ ጋር እንዲከራከሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልቀበልም አሉ።

የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫው በፊት ከካማላ ሀሪስ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ እንዲከራከሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ ከትናንት በስቲያ ውድቅ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንቱ ውድቅ ማድረጋቸውን ያስታወቁት ተቀናቃኛቸው የዲሞክራት ፓርቲ እጩዋ ካማላ ሀሪስ በፈረንጆቹ ጥቅምት 23 በሲኤንኤን ቀርበው ለመከራከር ፍቃደኛ መሆናቸውን ከገለጹ ከሰዓታት በኋላ ነው።

“ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሀሪስ ከትራምፕ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ መድረክ ለመጋራት ዝግጁ ናቸው። ሲኤንኤን ያቀረበውን ግብዣ ተቀብለዋል። ትራምፕ ለዚህ ክርክር ከመስማማት ወደኋ ላ ማለት አልነበረባቸውም” ሲሉ የካማላ ሀሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ኃላፊ ጀን ኦማሊ ዲሎን ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ትራምፕ ከምርጫ በፊት ሌላ ክርክር አይኖርም በሚለው የቀድሞ አቋማቸው ጸንተዋል።

“ሌላ ክርክር ለማድረግ ጊዜው ረፍዷል። ምርጫው እየተካሄደ ነው” ሲሉ የቀድሞው ፕሬዚዳንት በኖርዝ ካሮሊና ዊልሚንግተን ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

ሀሪስ እና ትራምፕ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን በእዚያ ክርክር ሀሪስ ማሸነፋቸውን የሚያሳዩ አስተያየቶች ወጥተው ነበር።

ትራምፕ ባለፈው ሀምሌ ወር ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር ተከራክረዋል። ባይደን በክርክሩ ባሳዩት ደካማ አፈጻጸም ምክንያት ዲሞክራቶች ባልተጠበቀ ሁኔታ እጩ ለመተካት እንዲገደዱ አድርጓቸዋል። ባይደንም በዚሁ ምክንያት ከእጩነት ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ አድርገዋል።

ባይደን ራሳቸውን ማግለላቸውን ባሳወቁበት መግለጫቸው ለሀሪስ ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል ሲል የዘገበው አል ዓይን ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You