በርካቶች አገረ አውስትራሊያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የትራክ እና የፊልድ ጀግኖች ለሆኑ አትሌቶች ፈውስ የሆነውን ባለሙያ አበረከተች ይሏታል። «ፊዚዮ ቴራፒስት» ቤኒ ኦብረሚሌርን። አገሪቷ በስፋት በክረምት ወቅት በሚደረጉ ስፖርቶች እንጂ በአትሌቲክሱ ላይ እምብዛም አትታወቅም።
ነገር ግን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 በተካሄደው የሪዮ ኦሎምፒክ በዲስክ ውርወራ ሉካስ የተባለ ስፖርተኛዋ የስድስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ እንዲሁም በዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የ16 ዓመቷ ሳራ ላገር የመሰናክል ውድድር አሸናፊ ሆናለች። አውስትራሊያ ምንም እንኳን በአትሌቲክሱ ዘርፍ ውጤታማ ባትሆንም በዓለም ታዋቂ የሆኑ አትሌቶችን የሚያክም እና ተመራጭ የሆነ የህክምና ባለሙያ ማፍራት ችላለች።
ይህ የ72 ዓመት አውስትራሊያዊ እራሱን የአካል ብቃት አሰልጣኝ «fitness coach» እያለ ነው የሚጠራው። በታዋቂ አትሌቶችም እጅግ ተፈላጊ እና በወረፋ የሚገኝ ፊዚዮ ቴራፒስት እና የማሳጅ ባለሙያ ነው። በመላው ዓለም በዚህ ዘርፍ በርካታ ባለሙያዎች ቢኖሩም፤ እንደ ቤኒ ግን ተደናቂ እና ተፈላጊ ሰው የለም። በጣም የተጣበበ ጊዜውን አንዴ ጃማይካ አንዴ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ኬኒያ እያለ ነው የሚያሳልፈው። በነዚህ አገራት የሚገኙ አትሌቶች ከእጁ ፈውስን ማግኘት ይፈልጋሉ።
ከእርሱ ጋር ተገናኝተው በምትሀተኛው ጣቶቹ ከደባበሳቸው፤ በሚወዳደሩበት ቦታ ሁሉ የድል ማማ ላይ እንደሚወጡ ምንም ጥርጥር የላቸውም። በተለያዩ የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ በመገኘት ከበርካታ አትሌቶች ጋር ሰርቷል። በግልም ከጃማይካዊያን የአጭር ርቀት ሯጮች አሰፋ ፖል፣ ኤሌኒ ቶምፕሰን እንዲሁም በተመሳሳይ ከደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴሜኒያ ጋር ለረጅም ጊዜ ሰርቷል። በአንድ ወቅት አሰፋ ፖል ስለዚህ ድንቅ ፊዚዮ ቴራፒስት እና ማሳጂስት ሲናገር «ለኔ በጣም ድንቅ ሰው ነው።
ከማንኛውም ሰው በላይ አምነዋለሁ» በማለት በዚህ ሙያ በተለይም በስፖርቱ ውስጥ ተሳትፎ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ከባድ ቢሆንም እርሱ ግን ይህን ማድረግ እንደቻለ ይናገራል። አትሌቶቹ በውድድር ወቅት የሰውነት መተሳሰር ብሎም መደበት ስሜት ሲያጋጥማቸው ዋናው መፍትሄ ቤን ነው።
ለሙያው ከሚሰጠው ክብር ባሻገር ከአትሌቶች ጋር መስራቱን እጅግ ይወደዋል። ሙሉ ጊዜውንም ከስፖርቱ ተሳታፊዎች ጋር ያሳልፋል። ቴራፒስት ቤን እራሱ በአንድ ወቅት ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች ነበር። ሆኖም እግሩ ላይ ጉዳት አጋጠመው እና ከስፖርቱ ለመገለል ተገደደ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ፊዚዮ ቴራፒስት እና ማሳጂስት ለመሆን የሙያ ትምህርት እንዲወስድ ገፋፋው። ያሰበውንም ብዙም ሳይቆይ አሳካው።
ወደ ስፖርቱ እንዲገባ ደግሞ አንድ የ13 ዓመት እድሜ ያላት የረጅም ዝላይ አትሌት ፈር ቀደደችለት። በሙያው እንዲረዳት ጥያቄ አቀረበችለት። ክሪችማንን እየረዳት ለበርካታ ድሎች ባለቤት እንድትሆን አገዛት። በ1993 በዓለም ሻምፒዮና ስቱትጋርት ላይ በረጅም ዝላይ የነሀስ ሜዳሊያ ማግኘቷ ከሚጠቀሰው ድሏ መካከል አንዱ ነው። ወደ አትሌቲክስ ስፖርት በሙያው መቀላቀሉ እና በአጭር ጊዜ ስኬታማ መሆኑ ሌሎችም አይኑን እንዲጥሉበት አደረገው። ይህ ደግሞ ከአገሩ ውጪ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የሚገኝበትን አጋጣሚ ከፈተለት።
የማሰልጠኛ ማእከል ወደ ሆነው «ላዛሮቴ» እንዲገባ ፍራንኪ ፍሬድሪክ እና ኤሪክ ኑል የተባሉ ሁለት ሙያተኞች ገፋፉት። በሙያው በመማረካቸው የቤን ደንበኞች ሆኑ። ቀስ በቀስም በአትሌቲክስ ዘርፉ ላይ ታዋቂነቱ እየሰፋ መጣ። በርካታ አትሌቶች የእርሱን እገዛ ፈልገው መምጣት ጀመሩ። ቤን ይህንን እውቅናውን ተከትሎ እንዲህ በማለት በአንድ ወቅት አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር «በርካቶች ከማሳጅ ጠረጴዛው ላይ ተነስተው ደጋግመው ያመሰግኑኛል።
እኔም ምናልባት ሌሎች የሌላቸው ነገር ኖሮኝ ሊሆን ይችላል በማለት ምስጋናቸውን እቀበላለሁ» በማለት ፈገግ ይላል። ቤን በሙያው ብቃቱ ጫፍ እንዲደርስ እና የብዙዎች ምስጋና እንዲጎርፍለት በተጨማሪ የቻይኖችን የማሳጅ እና የፊዚዮቴራፒ እውቀትን በተጨማሪ መጠቀሙ እንዳገዘው ይናገራል። ቤን በዓለም ዙሪያ ባሉ ታዋቂ አትሌቶች ዘንድ ተመራጭ ያደረገው ሌላ ተጨማሪ ነገር እንዳለ እራሱ ይናገራል። « በማንኛውም ወቅት ከደንበኞቼ ጋር በህክምና ላይ ስሆን መጥፎ አመለካከት አይኖረኝም።
ሁሌም ደስተኛ ነኝ» በማለት ትሁት፣ታማኝ እና በቀላሉ የማይሰለች ሰው በመሆኑ በርካቶች ከእነርሱ ጋር ለመስራት እንደሚፈልጉ ይገልፃል። ቤን በጣም የተጣበበ ጊዜ ነው ያለው። ሆኖም ግን አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ ማናቸውም አትሌቶች እንዳመጣጣቸው ይስተናገዳሉ። ለራሱ ጊዜ የሚባል የለውም። ሁሌም ቢሆን ስራው ላይ ነው። ነገር ግን እርሱ ረድቷቸው ወደ ድል ሲያቀኑ ደስታው ወደር የለውም። ለነዚህ ሁሉ ዓመታት ከየትኞቹ አትሌቶች ጋር እንደሰራ ሲጠየቅ በቀላሉ በጭንቅላቱ የሚመጡለት በርካቶች ናቸው።
የ800 ሜትር ኮኮቧ ማሪያ ማቶላ፣ ጃማይካዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ቬሮኒካ ካምቤል፣ ትውልደ ናይጄሪያዊው እና የፖርቹጋል የመቶ ሜትር ድንቅ አትሌት ፍራንሲስ ኦቢኩሉ፣ ደቡብ አፍሪካዊው የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ሙቡላኒ ሙላዲዚ፣ ጣሊያናዊው የረጅም ዝላይ ኮኮብ ጉሴፔ ጉብሌስኮ፣ አሜሪካዊቷ የመሰናክል ሯጭ ሎላ ጆንስ፣ ጃማይካዊቷ የ100 ሜትር ሯጭ ኬሪኖ ስቲዋርት እና ከሌሎችም አትሌቶች ጋር መስራቱን ይናገራል። ቤን በሙያው እረፍት የለሽ ነው። ያለበትን ሁኔታ ስለሚወደው እና ብቃት ስላለው ብቻ ሳይሆን የአትሌቲክስ ስፖርትን ጠንቅቆ ስለሚያውቀው። በአጠቃላይ ለሁለት ሙያዎች እራሱን ሰጥቷል ማለት ይቻላል። ለዚህም ነው የዝና ደረጃቸው ጫፍ የደረሱ ስፖርተኞች የሱ እጆችን እንዲዳብሷቸው የሚሹት።
ቤን አሁንም እድሜው ሳይገድበው ለረጅም ጊዜ ከነዚህ አትሌቶች ጋር አብሮ መዝለቅ ይፈልጋል። ይህን ህልሙን እውን እንደሚያደርገው በሙሉ ልብ ሲናገር ደግሞ እንዲህ ይላል «አባቴ ለ100 ዓመት ነው የኖረው»
ከትራኩ ጀርባ የሚሮጡ
በአገራችን የአትሌቲክስ ስፖርት ዓለምን ጉድ ያስባሉ አትሌቶች ተፈጥረዋል። ከአበበ ቢቂላ እስከ ምሩፅ ይፍጠር፤ ከአይበገሬው ዋሚ ቢራቱ እስከ ታላቁ የአትሌክስ ጀግና ሀይሌ ገብረ ስላሴ፤ ከደራርቱ ቱሉ እስከ እነ መሰረት ደፋር እና ጥሩነሽ ዲባባ፤ የስፖርቱን አድናቂዎች እጅ አፋቸው እንዲጭኑ የሚያስገድዱ አስገራሚ አትሌቶችን ኢትዮጵያ አፍርታለች።
በሌላ በኩል ከነዚህ ጀግኖች አትሌቶቻችን ጀርባ ያሉ አሰልጣኞችንም ነበሯት። መጠቀስ ካለበትም ከምናነሳቸው መካከል ዶክተር ወልደ መስቀል ኮስትሬ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ሆኖም ግን ከትራኩ ጀርባ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ በተለያየ የህክምና ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ላይ (ይህ ጉዳይ ከስፖርቱ ዘርፍ ውጪ ባሉ የህክምና ሙያ ላይም ያተኩራል) ገና ብዙ ያልሰራነው የቤት ስራ መኖሩ እሙን ነው።
በተለይም በዛሬው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያነሳናቸው የፊዚዮቴራፒ እና የማሳጅ ባለሙያዎች የአትሌቶቻችን ብቃት እና ጤንነት ተጠብቆ እንዲቆይ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ስለዚህ በውድድሮችም ሆነ በልምምድ ጊዜ ሙሉ ሰዓታቸውን ሰጥተው ከአትሌቶች ጋር የሚሰሩ፤ ለስፖርቱም ፍቅር ያላቸው ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባል። የዝግጅት ክፍሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሮች ሲኖሩት እና ለዚያ ብሎ ዝግጅት ሲያደርግ ብቻ የፊዚዮቴራፒ እና ማሳጅ ባለሙያዎችን በማስታወቂያ መጥራት ሳይሆን እንደዛሬው እንግዳችን አይነት ድንቅ ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል እንላለን።
አዲስ ዘመነ መጋቢት 15/2011
በዳግም ከበደ