ከትምህርት መስፋፋትና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ በየአመቱ በርካታ ወጣቶች የስራውን አለም ለመቀላቀል ይደርሳሉ። የስራ እድል አስመልክቶ ያለው አመለካከት አሁንም የመንግስትን እጅ ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተከትሎ በተለይ ወጣቶች የስራ እድል ጥያቄን ሲያነሱ ይስተዋላል። ስራ መፍጠር ብዙም የተሄደበት አይደለም።
ጉዳዩ ትልቅ ነውናም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ተግባሮች መካከል ለዜጎች የስራ እድል መፍጠርን አንዱ ስራው አርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። መንግስት ለሀገሪቱ ወጣቶች ሁሉ የስራ እድል አመቻችቶ ተቀጣሪ ማድረግ ይችላል ተብሎ ባይታሰብም፣ በዋና ዋና ዘርፎች ላይ ዜጎች ተሰማርተው እንዲያገለግሉ የማድረግ ታላቅ ሃላፊነት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የእቅዶቹ ሁሉ አካል አርጎ እየሰራ ነው።
ዜጎች መንግስት ከሚያመቻቸውና የስራ እድል ባሻገር የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላትና የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ ያለባቸው ቢሆንም፣ ከስልጠና፣ ከፋይናንስ ድጋፍና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ የዜጎች በራሳቸው የስራ እድል የመፍጠር ሁኔታ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም። በዚህ በኩል መንግስት ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም፣ የግሉ ዘርፍ ሚናውን እየተወጣ አይደለም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የመሪነት ሚና እንዲወስድ በመንግስት ፖሊሲ ተቀርጸው ማበረታቻዎች እየተደረጉ ይገኛሉ። ዘርፉ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ጉልህ ድርሻ አንዲኖረው ለማድረግ መንግስት እየደገፈ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ግብ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ገቢን መጨመር እንዲሁም የስራ እድል መፍጠር እንደ መሆኑ በዚህ ረገድ የግሉ ዘርፍ ሰፊውን ድርሻ መውሰድ እንደሚኖርበት በመንግስት በኩል ታምኖበታል። በ2014 ተሻሽሎ የወጣው ይህ ማሻሻያ የግሉን ዘርፍ የመሪነት ሚና ማረጋገጥ ዋነኛ ተግባሩ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በተደጋጋሚ የሚገለጽለት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ግብን ለመተግበርም የግሉ ዘርፍ ዋንኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው።
የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እየጨመረ እንዲሁም የሚያስገኘው የስራ እድል በዚያው ልክ እየጨመረ ቢመጣም፣ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ከመደገፍና ለዜጎችም ለባለሀብቱም ለሀገርም እንዲጠቅሙ በማድረግ በኩል ውስንነት እንዳለበት ይገለጻል።
በኢትዮጵያ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥሩ የፈጠራ ሃሳቦች ያላቸው ግለሰቦች በርካታ ናቸው። በተለይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ደግሞ ብዙ ያልተነካ እምቅ አቅም ያለው እንደሆነ ይታመናል። ይሁን እንጂ በዚህ ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተስፋ በተጣለበት ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ የግል ባለሃብቶችም ሆኑ ተቋማት ያላቸው ፍላጎት ደካማ እንደሆነ ይነገራል። በተለይ በግል ተነሳሽነት የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራ ሰርተው ለራሳቸውም ሆነ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ያላቸው ወጣቶች የሚደግፋቸው የግል ባለሃብትም ሆነ መሰል ድርጅት ባለማግኘታቸው ባክነው የሚቀሩበትና ከመንግስት እጅ ስራ የሚጠብቁበት አጋጣሚ በስፋት ይስተዋላል።
አሁን አሁን ይህን ችግር የሚቀርፍ መፍትሄ አመላካች መረጃዎች እየሰማን እንገኛለን። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኘው የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ሚኒስቴርም ሆነ በክልል በቢሮ ደረጃ ያሉ ተመሳሳይ መዋቅሮች ዜጎች ከመንግስት ስራ ከሚጠብቁ ይልቅ ክህሎታቸውን አሳድገውና የፈጠራ ብቃታቸውን ተጠቅመው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መልካም ውጤት እንዲያመጡ የግል ዘርፉን የማነቃቃትና በፖሊሲ በመደገፍ ለማበረታታት እየሰሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የፈጠራ ባለሙያዎችንና ባለሃብቶችን እንዲሁም ባንኮችን የማስተሳሰር ስራ ነው።
የዝግጅት ክፍላችን በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ባዘጋጀው “ሶስተኛው የቴክኖሎጂና ፈጠራ ክህሎት” ውድድር ላይ ተገኝቶ ይህንን ተገንዝቧል። ከዚህ ባሻገር የግል ባለሃብቶች የስራና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ ያላቸው ወጣቶችን የሚደግፉበትና በዚህ ስራ የግሉ ዘርፍ አበርክቶ ጎልቶ የሚወጣበትን መንገድ ለማመቻቸት የሚደረገውን ጥረትም ለመመልከት ችሏል።
ከዚህ ውስጥ ለዛሬ አምዳችን አንድ በግል ባለሃብቶች ጥምረት ከተመሰረተና የወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ሃሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ ድጋፍ ከሚያደርግ የኢንተርፕረነርስ አሶሲዬሽን ጋር ቆይታ አድርገናል። አቶ አለሙ ዘለቀ ይባላሉ። ዋነኛ ትኩረቱን የስራና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎችን የመደገፍና የማብቃት ስራ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የሸገር ኢንተርፕረነርስ ማህበር (አሶስዬሽን) ዋና ስራ አስፈፃሚ ናቸው።
የማህበሩ ዋንኛ ፍልስፍና “በኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ሃብት የሚያፈሩበት መንገድ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ኢኮኖሚው ማደግ ቢችልም እንኳ በዋናነት መፈታት ያለባቸው ማህበራዊ ችግሮች አይፈቱም። ስለዚህ ምን መደረግ አለበት?” የሚል ሃሳብ አንሸራሽሮ የመፍትሄ ሃሳብ የሚጠቁም መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ያብራራሉ። ኢኮኖሚው በተከታታይ ማደጉን ጠቅሰው፣ ለዜጎች ግን በቂ የስራ እድል የፈጠረ አለመሆኑን ያመለክታሉ። ይህ የሆነው የሃብት ማፍራት አካሄዱ እውቀት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ነው ይላሉ።
“ከላይ ያነሳነውን ዳሰሳ ወይም ፍልስፍናዊ እይታ እንደ መነሻ በማድረግ ለመፍትሄው አራት ዋና ዋና ነገሮች ላይ እየሰራን እንገኛለን” የሚሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ አለሙ ይገልጻሉ። በመጀመሪያው ዜጎች በቴክኖሎጂና መሰል የፈጠራ ስራዎች ላይ ብቃት እንዲኖራቸው የሚያስችል የሙያ ስልጠና እንደሚሰጣው ይናገራሉ። ከዚያ ባለፈ ማንኛውም ግለሰብ ለማህበረሰቡ በቂ የስራ እድል የሚፈጥር ሃሳብ ካለው ያንን በምን መልኩ ወደ መሬት አውርዶ እሴት መጨመር እንደሚቻል በስልጠናው ውስጥ እንደሚካተትና በማህበሩ ለተፈፃሚነቱ ድጋፍ እንደሚደረግለት ያስረዳሉ።
እንደ አሶሴሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ገለፃ፣ በሁለተኛ ደረጃ ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ነው። ይሁን እንጂ በዋናነት ለኢንተርፕረነር አሊያም ለስራ እድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ባለሙያ ገንዘብ ቀዳሚው ጉዳይ እንዳልሆነ ማህበሩ ያምናል።
‹‹በኢንተርፕረነር ህይወት ውስጥ ገንዘብ ወሳኝ አይደለም። ግን ደግሞ አስፈላጊ ነው” የሚሉት አቶ አለሙ፤ ወሳኙ ነገር የሰው ልጅ ያለው ክህሎትና የመፍጠር አቅሙን ተጠ ቅሞ ለመወዳደር የሚያስችል ቁመና ላይ መገኘቱ ነው ይላሉ። ይህ ሁሉ በቅድሚያ ከተሟላ በኋላና ገንዘብ የግድ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ራእዩን እና ለአገርና ለወገን መልካም እድል ይዞ የመጣውን ሃሳቡን እውን ማድረግ እንዲችል የሸገር ኢንተርፕረነር አሶሲዬሽን ድጋፍ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ።
አሶሴሽኑ ይህን ፍልስፍና ተከትሎ ለቴክኖሎጂና አዲስ ሃሳብ መፈጠር ምክንያት ለሚሆኑ ወጣትና ታዳጊዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ ይህን የሚያደርግበትን ምክንያት ሲያስረዱም “ገንዘብ ኖሮት ምንም ሃሳብ ሳይኖረው የሚቀር እንደመኖሩ ሁላ ምንም ገንዘብ ሳይኖረው ግን ለአገር የሚጠቅም ሃሳብ ላይ ብዙ የሚተጋ ስላለ ያንን እድል ለመፍጠር በማሰብ ነው” በማለት ምላሻቸውን ይሰጣሉ። እነርሱም ይህንን ባረጋገጡና ለዜጎች ተጨማሪ እሴት እንደሚሆን ሲታወቅ የፈጠራ ባለሙያው የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራ ይናገራሉ።
“ የአሶስዬሽኑ ሁለተኛ አላማ የፋይናንስ ድጋፍ ከማድረጋችን በፊት ሁሉንም አይነት ስልጠናና የማጣራት ስራ በቅድሚያ እንሰራለን” የሚሉት አቶ አለሙ፣ በቁጥር ይህ ነው ብለው ባያስቀምጡትም መሰል ድጋፍ ያተደረገላቸው ኢንተርፕረነሮች መኖራቸውን ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር በመጀመሪያው ግብ ላይ በተቀመጠው መስፈርት መሰረትም ተቋሙን ከተመሰረተበት ከዛሬ ሶስት ዓመት ጀምሮ እስካሁን ድረስ 3ሺህ 700 ለሚደርሱ የቴክኖሎጂ፣ የሳይንስ፣ የዲጂታልና መሰል መስኮች ላይ የፈጠራ ሃሳብ ላላቸው ግለሰቦች አሶሴሽኑ ስልጠና መስጠቱን ይናገራሉ።
“በሶስተኛ ደረጃ እንደ ግብ አስቀምጠን የምንሰራው የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ ነው” የሚሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ይህን ለማድረግና በሙሉ አቅም ለመስራት የወተወሰነበት ምክንያት በሳይንስ ቴክኖሎጂና ሌሎች መሰል መስኮች ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕረነሮች የሙያና መሰል ክህሎት ኖሯቸው ምርት ቢኖራቸውም “እንዴትና የት” ማስተዋወቅም ሆነ መሸጥ ስለሚቸገሩ መሆኑን ይገልፃሉ።
ይህን ችግር አሶሴሽኑ በመረዳቱ በተለይ ወጣቶች ምርቶቻቸውንና የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን በምን መልኩ ወደ ገበያ ማውጣት እንደሚችሉ እናሳያቸዋለን ይላሉ። በዚህ መንገድም የገበያ ትስስር በመፍጠር ኢኮኖሚው ዘላቂ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተና ለብዙዎች የስራ እድል የሚፈጥር እንዲሆን እንሰራለን ሲሉ ያብራራሉ።
“የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ ከገዥዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲዳብር እገዛ እናደርጋለን” የሚሉት አቶ አለሙ፤ ለምሳሌ ያህል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ የሚሰሩ የፈጠራ ባለሙያዎች ገበያቸውን በስፋት ለማህበረሰቡ ለማቅረብ የዋጋ ውድነት ቢፈትናቸውም ያንን መቋቋም እንዲችሉ ዘዴ በመቀየስ ልዩ ልዩ ስራዎችን መስራት እንዲችሉ ዘዴ በመቀየስ እንደሚሰራ ነው የሚያብራሩት። ለምሳሌ ያህልም በተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚመረት አትክልትና ፍራፍሬ ሁሉም ዜጎች ገበያ ላይ ከፍ ያለ ወጪ አውጥተው መግዛት ባይችሉ ምርቱ ከገበያ እንዳይወጣ በቀጥታ የመግዛት አቅም ካላቸው ጋር ስራ ፈጣሪው እንዲገናኝና እንዲበረታታ የማድረግ ሃላፊነት ወስዶ እንደሚሰራም ያስረዳሉ።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ከማህበሩ ዋና ዋና ግቦች ውስጥ አንዱና የመጨረሻ የሆነው ተግባር ጥናትና ምርምር መስራት መሆኑን ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው፣ በተለይ በክህሎትና ስራ ፈጠራ ላይ በእውቀት ላይ በመመስረት ብዙ ስራዎች መሰራት እንደሚቀር ይገልፃሉ።አገሪቱ በዋናነት የሰው ሃይል ቢኖራትም የአለመቀጠር ችግር በስፋት ይታያል በማለትም ይህንን ያመጣው በቂ የሙያ እውቀት አለመኖሩ መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ የሰለጠኑት አገራት በብቁና ጥቂት የሰው ሃይል የዓለምን ትልቁን ኢኖኮሚ መገንባት ችለዋል። ይህን ያደረጉት ደግሞ ለኢንተርፕረነሮች ምቹ አጋጣሚን በመፍጠራቸውና በእውቀት ላይ በመመስረታቸው ነው። በኢትዮጵያም ይህ እንዲፈጠር ዋና ዋና ችግሮችን ነቅሶ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል።
እርሳቸው የሚመሩት አሶሴሽንም በጥናትና ምርምር ዘርፉ ላይ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስና ምሁራንን በማሳተፍ ዋንኛ ማነቆዎች በሳይንሳዊ መንገድ የሚፈቱበትን መንገድ ለመጠቆም እየሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። ይህን የጥናትና ምርምር ውጤትም ማህበሩ ለፖሊሲ አውጪዎችና በመንግስት ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያቀርብም ይናገራሉ።
የኦሮሚያ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ለሶስተኛ ጊዜ ባዘጋጀው “የቴክኖሎጂና ክህሎት ውድድር” ላይ የሸገር ኢንተርፕረነርስ አሶሲየሽን ተሳታፊ ነበር። የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ፣ የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ፣ በቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦች ያሏቸው ወጣቶችን የተቋሙን ድጋፍ እንዲያገኙ እየሰሩ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ነግረውናል። የእነዚህ የፈጠራ ባለሙያዎች ሃሳብና ስራ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍና ለአገር እድገት የሚጠቅም ከሆነ ማህበሩ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠውልናል።
“የቴክኖሎጂና የስራ ፈጠራ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ከዋናው ችሎታቸው በተጨማሪ ልዩ ልዩ ብቃቶችን ማዳበር ይኖርባቸዋል” ሲሉ የኦሮሚያ ስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አደም ከማል ይገልጻሉ። በተለይ የሰሩትን ቴክኖሎጂ በምን መልክ ወደ ገበያ ማውጣትና አቅም መፍጠር እንዳለባቸው፣ ራሳቸውን እንዴት ማስተዋወቅ እንደሚችሉና የግንኙነት አድማሳቸውን ማስፋት እንደሚኖርባቸው ክህሎቱ ሊኖራቸው ይገባል ይላሉ። ለዚህ ደግሞ የኦሮሚያ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ይገልፃሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ እንደ ሸገር ኢንተርፕረነሮች ማህበር ያሉት በግል ባለሃብቶች ጥምረት ለተመሰረቱ ተቋማት የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን ከሚፈጥሩ ወጣቶችና ታዳጊዎች ጋር እንዲገናኙ ቢሮው ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ስንቄ ባንክ ካሉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጥሩና ለስራዎቻቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ድልድይ በመሆን ይሰራል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2014