ለዘመናት ፈተናዎቹን ሁሉ ተቋቁሞ ፤ ከምንም ነገር በላይ ሀገርን አስቀድሞና ህልውናዋን አስቀጥሎ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፈ ያለ ታላቅ ሕዝብ ሚሊየን ጊዜ ቢደነቅ ፣ ቢመሰገንና ቢወደስ ያንስበታል እንጅ አይበዛበትም ። ከጥላቻ ፣ ከልዩነት ፣ ከቂም በቀል ፣ ከሴራና ከደባ ፣ ከሀሰተኛና የተዛባ መረጃ በላይ ከፍታ ላይ ያለ ሕዝብ በቅጽል ጋጋታ ሌት ተቀን ቢሞካሽ ያንስበታል እንጅ አይበዛበትም ። ከርዕዮተ አለም ፣ ከተቋም ፣ ከሀሰተኛ ትርክት ፣ ከታሪክ ምርኮኛነት ፣ ከመደበኛና ከማህበራዊ ሚዲያ በላይ የሆነ ታላቅ ሕዝብ ምስጋናና አድናቆት ቢጎርፍለት ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም። ማንነትን ኢላማ አድርጎ ከተፈጸመ ጭፍጨፋ ፣ ጥቃት፣ ግጭት ፣ መፈናቀልና መዘረፍ በላይ ሆኖ በሰውነት ማማ ላይ የተቀመጠ አስተዋይና አርቆ አሳቢ የሆነ ሕዝብ ለሰዓታት ቆመው እጅ እስኪቃጠል ቢያጨበጭቡለት ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም ።
እየተራበ ፣ እየተራዘና በድህነት እየተጎሳቆለ ለሀገሩ ህልውና ሲል በምንም የማይተመንና የማይገለጽ ውድ ዋጋ እየከፈለ ላለ ሕዝብ ቅኔ ቢቀኙለትና ቢዘፍኑለት ያንሰዋል አንጅ አይበዛበትም ። በተለይ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ የሰሞነኛውን ጨምሮ እርስ በርሱ እንዲጋጭ ፤ ወደለየለት አመጽና ተቃውሞ እንዲገባ ሺህ ጊዜ ቢተነኮስ ፤ ሀሰተኛ መረጃ እንደ ፍላጻ ከየአቅጣጫው ቢንበለበልበት ሀገሬና አብሮነቴ ይበልጥብኛል ብሎ እርፋችሁ ተቀመጡ ያለ ልዩና ታላቅ ሕዝብ በአደባባይ ቢደነቅና ቢሸለም ያንስበትበታል እንጂ አይበዛበትም። የሟርተኞችንና ክፉዋን የሚመኙ ድሞጾችን ሳይሆን የራሱን ድምጽ የሚሰማ የሰከነ ሕዝብ በፍጥረት ሁሉ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ቢደነቅና ቢሞካሽ ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም ። ለዚህ ነው “መኅልዬ መኅልዬ ዘኢትዮጵያ ሕዝብ”ያልሁት ።
መኀልየ መኀልይ ዘሰሎም ከሁሉም የሚበልጥ የሰለሞን መዝሙር ማለት ነው ። የሁለት ፍቅረኛዎች ንግግር ተደርጎም ይወሰዳል ። የፍቅረኞች ንግግር በግጥም ነውና ምት ፣ ዜማ አለው ። ሰለሞን ስለ ሙሽራውና ሙሽሪት ፣ ስለፈጣሪና ስለ ቤተ ክርስቲያን የዘመራቸውን 1005 መዝሙሮችን ይመለከታል ። ሙሽራው ልዑል እግዚአብሔርን ሲወክል ሙሽራይቱ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት። መኅልይ እንደ ለዘብና ወረብ አይናት በፍጥነት የሚዘመር ጥዑም ዜማ ነው ። መዝሙሮቹ በተለያየ ስልት ዜማ ቢደጋገሙም ያው ስለፈጣሪና ቤተ ክርስቲያን ክብር ፣ ቅድስና የሚመስክሩ ናቸው ። ይህ መጣጥፍ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚዘክር ፣ የሚያወድስና የሚያከበር ሆኖ ስለአገኘሁት “ መኅልዬ መኅልዬ “ዘኢትዮጵያ ሕዝብ” ማለትን መርጫለሁ ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት በታላቁ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁራን ስሙ ተደጋግሞ ከመወሳት ይጀምራል ።
የሀገራችን ታሪክ ከካም ይመዘዝ ከኩሽ ወይም ከኢትዮጲስ ይሁን ከሳባ አልያም ከማክዳ ፣ ከቀዳማዊ ምኒልክ ወይም ከሳባውያን ፣ ከሀበሻ ይሁን ከአግዓዚ፣ ወዘተ . መዳረሻው ታላቅነት ነው ። የቀደምት ስልጣኔአችን እርሾ የተጣለው ተቦክቶ የተጋገረው በዚህ የታላቅነት እልፍኝ ነው ። ኢትዮጵያዊነት የተገመደበት ገመድ የተፈተለበት ቃጫ የበቀለው ከዚህ ታላቅ ምድር ነው ። የስነ ህንጻ ፣ የመርከብ ፣ የንግድ ፣ የመጀመሪያው የመገበያያ ገንዘብ ፣ የእርሻ ከፍ ሲልም የስነ መንግስት መሰረታችን የተጣለው ኢትዮጵያም የተቀለሰችው በዚሁ ምድር ነው ። ዛሬ ካስማዋ ድንኳኗ ጠቦ ጦቦ ቀይ ባህርን ሱዳንን ደቡብ አረብያን ባይሻገርም ። የዚህ ሁሉ ከፍታችን ልዕልናችን የማዕዘን ድንጋይ ኢትዮጵያዊነት ነው ።
ከእስክንድርም ይሁን ከፕቶሎሚ አልያም ከግሪክ መናገድ እንዲሁም ዲፕሎማሲ አሀዱ ያልነው በታላቋ ኢትዮጵያ በአዶሊስ ነው። ቀዳሚው የግንብ ቤተ መንግስትም ባኪንግሀም አልያም ኋይት ወይም ብሉ ሀውስ ሳይሆን አክሱም ነው የተገነባው ። በዩኔስኮ በቅርስነት የተመዘገቡት እስከ 33 ሜትር የሚረዛዝሙ ከአንድ ድንጋይ የተቀረፁ ሀውልቶች ፤ በቦና ጊዜ የተገነባው ምን አልባትም የመጀመሪያው የውሃ ማከፋፈያ፤ ዘብን በማቆም ንግድ መናገድ ፤ የፅሕፈት ስርዓት የተጀመረው ፤ ከሁሉም በላይ በተለይ ንጉስ አፍላስ ከሱዳን የተወሰነው ክፍል ፤ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ደቡብ ምዕራብን ቆርሶ ከማስተዳደሩ ባሻገር የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥታዊ አገዛዝ መስራች እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ ። ከእሱ በኋላ የነገሱት ኢላ አሚዳ ፣ ኢዛና እና ካሌብ የአክሱምንና የኢትዮጵያን ስልጣኔ አስቀጥለዋል ። ሶስቱ አብርሀማዊ እምነቶች ክርስትና ፣ አይሁድና እስልምና ወደ ሀገራችን የገቡትም በዚሁ ዘመን በዚሁ በር ነው ።
የመጀመሪያዎቹ የመሐመድ ተከታዮች በነብያቸው ምሪት ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እጁን ዘርግቶ የተቀበላቸው የክርስቲያን ንጉስ ኢትዮጵያዊ ነው። የዛሬው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት አስኳል እንበለው እራስ ወይም ዲ ኤን ኤ አልያም ልብ እንበለው የደም ሰር የሚመዘዘው ከዚህ ታላቅነት ነው። በዘመናት ጅረት ፣ በትውልድ ቅብብሎሾ ፣ በአይዶሎጂ ውርክብ አያረጅም ። አይፈዝም ። አይደበዝዝም ። አይወይብም ። አይጠወልግም ። ለዚህ ነው ወጀቡን ማዕበሉን አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰው ። ሀገርንና አብሮነትን እያስቀጠለ ያለው ።
የጥንታዊ ስልጣኔ ፋና ወጊነት ከሚገለጽባቸው አንዱ በሆነው ስነ ፈለክ ኢትዮጵያውያን ከፊተኛው ረድፍ ነበሩ ። በኪነ ህንጻና በጹሑፍም ቀዳሚ ነበሩ ። ሀገራችን ከ3ና 4ሺህ አመታት በፊት በህዋ ምርምር ዘርፍ የዛሬዎቹን ልዕለ ኃያላን ከፊት ሆና ስትመራ እንደነበር የጥንት ብራና መፅሐፍትና ስንክ ሳሮች ዋቢ ከመሆናቸው ባሻገር አለማቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት በሀገራችን ልዕልት ፣ ንግስትና ንጉስ ስም ሕብረ ከዋክብት constellations መሰየሙን ስንቶቻችን ይሆን የምናውቀው !? ስለ ቀደምት ኢትዮጵያውያን የስነ – ፈለክ / የሕዋ / እውቀትና በዘመን አቆጣጠር ምን ያህል የተራቀቁ እንደነበሩ በማስረጃ የሚተነትነው የሮዳስ ታደሰና ጌትነት ፈለቀ ( ሁሉም ፒ ኤች ዲ ሰርተዋል ) ። በጋራ በደረሱት ፤ “ አንድሮሜዳ “ መፅሐፍ 5ኛ ዕትም ላይ ፤”… ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉ የውጭው አለም ታሪክ ፀሐፊዎች …’ ጥንታዊ ዘር ‘ በመባል የምትታወቀውን ኢትዮጵያን …አውሮፓና እስያ ባልሰለጠኑበት ዘመን …ፍልስፍና ፣ ሥነ ጽሑፍ ፣ ሒሳብ ፣ ግብርና ፣ ሕክምና ፣ የክዋክብት ጥናት …የኢትዮጵያውያን ነባር ሀገር በቀል እውቀቶች እንደነበሩ ተናግረዋል ።… “ ይህ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለስነ ፈለክ የማይናወጥ መሰረት እንደነበራቸው ያረጋግጣል ። የዛሬው ታላቅነቱ ሚስጥር ቋጠሮ ከዚህም ይፈታል ።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን እና ለስነ – ፈለክ ምርምር ወረት ፣ መነሻ እንደነበራት የሚያረጋግጡ የቀደምት ሊቃውንት እማኝነት ከፍ ሲል በተገለፀው መፅሐፍ እንደሚከተለው ተዘግቧል ። “ 60 ዓመት ቅድመ ልደት ክርስቶስ የነበረው ዲዎዶርስ ሴኩለስ የተባለ የተሪክ ሊቅ ‘ አውሮፓውያን ኋላ ቀር እድገት አኗኗር ላይ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ታላቅ ስልጣኔ ላይ የነበረች …ኢትዮጵያውያን ለግብጻውያን ስልጣኔ ያስጀመሩና እስከ ሕንድ ድረስ የገዙ ናቸው ። ‘ …
በ700 ዓ ም የነበረው የቤዛንታይኑ እስቲፋንስ ባካሄደው ጥልቅ ጥናት ‘ ኢትዮጵያ መሬታችን ላይ የተመሰረተች የመጀመሪያ ሀገር ናት ‘ ሲል አርኖልድ ኸርማን ሉድዊግ የተባለ የጀርመናዊ የታሪክ ፀሐፊ ደግሞ ‘ ኢትዮጵያን የመሰለ ጥንታዊ ሀገር ወዴት ይገኛል !? ‘ ሲል ይሞግታል ፤ ከ800 ዓመት ክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ሆሜር አሊያድና እና ኦዲሴይ በተባሉ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹ ኢትዮጵያውያን ‘ እስከ መሬት ጫፍ ድረስ የሚኖሩና ከአምላክ ጋር ቅርበት ያላቸው ‘ በማለት ይገልጻቸዋል ።
የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው ሔሮዶቶስ ኢትዮጵያውያንን ‘ ከሰሐራ በታች የሚኖሩ ፣ ጥቁር ቆዳ ያላቸው …ብልሆች ፣ በዓላቶቻቸውና ሀሴታቸውም ሳይቀር አማልክትን ስለሚያስደስት የአማልክት አምላክ እየሄደ በዓላቱን በደስታ አብሯቸው ያሳልፋል ‘ ብሏል ። … ዲዮዶር የተባለ የሮም ፀሐፊ ደግሞ ‘ ከግብፅ በፊት ስልጡንና ገናና ነበረች ። ግብፅን ቀኝ ገዝታ 18 የኢትዮጵያ ነገስታት ተፈራርቀውባታል ። …’ ይላል ።
“ሲያወጋ ውሎ ቢያድር የማይሰለቸው ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ( በግሌ ከብዕሩ ትዕባት ይልቅ አንደበተ ርቱዕነቱ ስለሚበልጥብኝ ፤ ተመርጎ እንደከረመ የጨፋቂት ጊዎርጊስ የገብስ ጠላ ስለሚያረካኝ “ ደራሲ “ የሚለውን ማዕረጉን በተሰጠኝ ስነ ፀጹሑፋዊ መብቴ poetic license “ አፈ ማር “ ብየዋለሁ ። ) በፍ ት ሕ መፅሔት 2ኛ አመት ቁ 60 ታህሳስ 2012 ዓም ዕትም ፤ “ ከሮኬት ሮክ ወደ ሳተላይት ሀልዮት “ በሚል ርዕስ ‘ ባወጋን ‘ መጣጥፉ “…ከእኛ ይልቅ አባቶቻችን ለሳተላይት ምንጠቃ የሚያበቃ የህዋ እውቀት ነበራቸው ። ህዋውን በአቅጣጫ ፣ ፕላኔቶችን በደረጃ መድበዋል። በጀት ባይኖር ትኩረት ፣ ሙከራ ባያደርጉ ሃልዮት ነበራቸው። ሰማየ ሰማያትን እግዜአብሔርን ባማከለ ዕውቀት ( Theocentric ) ለሰባት ከፍለው አንብረዋል ።
ሰባቱ ዓለማት ( ሰማያት ) መንበረ መንግስታት ፣ ፅርሃ አርያም ፣ ሰማየ ውድድ ፣ ኢዮሪያሌም ሰማያት ፣ ኢዮር ፣ ራማ እና ኤረር ብለው ከፋፍለው አጥንተዋል። …” ብሎናል ። ሀገራችን የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን በአደባባይ ካስመሰከረ በኋላ በአለማቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት የተሰጣትን ቦታ ይተነትናል ። “…ሕብረ ከዋክብት constellations ማለት በሰማይ ላይ የሆነ አይነት ቅርፅ የሚሰራ የከዋክብት ስብስብ ሲሆን ቅርጹም ከማይቶሎጂ ጋር በተያያዘ መልኩ የሰው ፣ የእንስሳት ወይም ሕይወት የሌለው ነገር ሆኖ ሊገለጽ ይችላል ።…አለማቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት በ1930 ዓም ከ88 ሕብራተ ከዋክብት ውስጥ ሶስቱን ማለትም አንድሮሜዳን፣ ካሲዮፕያንና ሴፌውስን በኢትዮጵያውያን ስም መዝግቧል ። … አንድሮሜዳ የኢትዮጵያ ልዕልት ስትሆን ፤ ካሲዮፕያን ደግሞ የኢትዮጵያ ንግስት ናት ። ሴፌውስ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉስ ነው ። …”
በአለት ላይ ስለተመሠረተው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኋላ መነሻ ይሄን ያህል ካልሁ ፤ ይሄን ታላቅ ሕዝብ የማመሰግንበትና የማወድስበት ሚሊዮን ምክንያቶች ቢኖሩኝም ሰሞነኛ መግፍኤዎችን እመለስባቸዋለሁ ። ከዚያ በፊት ግን ይቺ ሀገር ከ3ሺህ በላይ አመታትን ነጻነቷን፣ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን አስከብራና አስጠብቃ ያስቀጠለችው በሀገረ መንግስቷ ፣ በአገዛዟ፣ በተቋማቷ ፣ በመሪዎቿ ሳይሆን በታላቁና ንኡዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ። እንደ ሀገር የገጠሙን ፈተናዎችና ቀውሶች እንደዛሬው ሀገረ መንግስትን ፣ ተቋማትን ፣ መሪዎችንና ልሒቃንን ተሻግረው ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ …ሊያንበረክኩንና ሊረቱን ሳለ የመጨረሻ ምሽግ ሆኖ የታደገን ፤ ወደፊትም የሚታደገን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለመሆኑ ቅንጣት ታክል ስለማልጠራጠር ነው፤ ያለምንም ስስትና ንፍገት ታላቁን የኢትዮጵያን ሕዝብ”መኀልዬ መኀልዬ ዘኢትዮጵያ ሕዝብ ፤”ስል መወድስ የያዝሁለት።
የቀደመውን እናቆየውና ከ66ቱ አብዮት ከነጭና ቀይ ሽብር ማዕት ፤ ከ17ቱ አመታት ዘግናኝ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ፤ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ከተለፈፈውና ከተሰበከው ልዩነት ፣ ጥላቻ ፣ ዘረኝነት ፣ ቂም በቀል ፣ ወዘተረፈ፤ ህወሀት ከሽግግር መንግስቱ አንስቶ ከአገዛዝ እስከተፈነገለባቸው አመታት ንጹሐን በመላው የሀገሪቱ ክፍል በማንነቱ እንዲጠቃና እንዲጨፈጨፍ አድርጓል። በምስራቅ ሐረርጌ በጋራ ሙለታ ፣ በወተር ፣ በበደኖና በድሬደዋ ፤ በምዕራብ ሀረርጌ በገለምሶ ፤ በአሰቦት ገዳም፣ በአርሲ ፣ በአርባ ጉጉ ፣ በአጋሮ ፣ በሸቤ ፣ በጉራ_ ፈርዳ ፣ በወለጋ ፣ በኖኖ ፣ በአማያ ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በከማሺ ፣ በመተከል ፣ በአፋር እና በራሱ ክልል ዘርፈ ብዙ ጥቃት እንዲፈጸም አድርጓል ።
በዚህ የተነሳም ከፍ ብዬ እንደገለፅሁት በበዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል ፣ አካለ ጎደሎ ሆነዋል ፣ ተፈናቅለዋል ፣ ተዘርፈዋል ። በሱማሌ ክልል በተለይ በጅግጅጋ ፤ የአርቲስተት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ፤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ፤ በዩኒቨርሲቲዎች ይቀሰቀሱ የነበሩ ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ግጭቶችም ሆኑ በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ግፎች ሆኑ ከፍ ብለው የተፈጸሙ ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸው ሰቆቃዎች ግብ ሀገሪቱን እንደ ሩዋንዳ ወደለየለት የእርስ በርስ ግጭት ፣ ዘር ማጥፋት መዝፈቅና ሀገሪቱን መበተንና ማፍረስ ነው ። ሆኖም ይህ እኩይ ሴራ በጥበበኛው ፣ በአስተዋዩ ፣ በአርቆ አሳቢውና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ መክኗል ። ከሽፏል ።
የእናት ጡት ነካሾች እንዲሁም ጋላቢዎቻቸውና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ግን እስከመጨረሻዋ ህቅታቸው አልተኙልንም። ባለፉት አራት አመታት ህወሀት በተላላኪዎቹ አማካኝነት በመላ ሀገሪቱ እስፓንሰር እያደረገና ስምሪት እየሰጠ የቀፈቀፋቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ጭፍጨፋዎችና ቀውሶች በዚህ ታላቅ ሕዝብ አስተዋይነት ቢከሽፍበት የመጨረሻ ካርዱን መዘዘ ። በሸረብሁት ሴራ ሀገሪቱ የማትፈርስ የማትበተን ከሆነ እራሴ አፈርሳታለሁ ብሎ ከቡችሎቹና ከጋላቢዎቹ ጋር አብሮና ተማምሎ ተነሳ ። ሰሜን ዕዝን በማጥቃት ጦርነት አወጀ። የአማራንና የትግራይ ሕዝብን ለማቆራረጥ በማይካድራ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጸመ ።
ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ድባቅ ቢመታም አፈር ልሶ በመነሳት ፤ በአማራና በአፋር ክልሎች ተነግሮና ተሰምቶ የማያልቅ ሰቆቃ ፣ ግፍ ፣ ዘረፋና ውድመት ፈጸመ ። በጋሊኮማ ፣ በአጋምሳና በሌሎች አካባቢዎች የተቀነባበረና የታቀደ የዘር ማጥፋት በመፈጸም ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳ አሴረ ። ሸኔንና ሌሎች ተላላኪዎቹን በመጠቀም የእርስ በርስ ግጭት ለመቀስቀስ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ግፍ እያስፈጸመ ቢሆንም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን እንደ ትላንቱ የሀገሩን ህልውና ማስቀጠልና አብሮነትን መርጧል ።
መኀልዬ መኀልዬ ዘኢትዮጵያ ሕዝብ !አሜን።
ከቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳይን )
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2014