የኑሮ ውድነቱን ለማርገብና የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት አዲስ አበባ ከተማ ላይ የእሁድ ገበያ ሲጀመር እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ ደስ ብሎን ነበር። በእርግጥም የመጀመሪያዎቹ ሰሞን የእሁድ ገበያ እንደታሰበው ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ ገበያውን ማረጋጋትና የኑሮ ውድነቱን ጫና በመጠኑም ቢሆን ማቃለል ችሏል። የግብርና ምርቶች በተለይም አትክልት፣ ጥራጥሬ እና የመኸር ሰብል ምርቶች እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶች በተሻለ አቅርቦት እና በተመጣጣኝ የገበያ ዋጋ ለሸማቾች ማድረሱ አስደሳችና ተፈላጊ ነው ። በከተማዋ 50 ቦታዎች ገበያዎቹ መስፋፋታቸው ገበያውን ተደራሽ ስለሚያደርገው በእጅጉ ይበረታታል።
እንደልብና በአቅራቢያ መሸመት ያስችልና መጨናነቅን ይቀንሳል። ኅብረተሰቡ ፓስታና ማኮሮኒውን ጨምሮ፣ዘይቱ ፣ሩዙ፣ ጤፉና ሌሎችም የበሰሉ ምግቦች በተመጣጠነ ዋጋ ቀርበውለት ሲሸምት ቆይቷል። ለአብነት ከበሰሉ ምግቦች አንድ ነጭ ጤፍ ደረቅ እንጀራ በስምንት ብር የቀረበበት ሁኔታም ነበር። ይሄ እነዚህ ምርቶች በእሁድ ገበያ የቀረቡበት ዋጋ ኅብረተሰቡ በሰርኩና በመደበኛው ወቅት ከሚሸምትበት በእጅጉ የተሻለ ነበር።
ከሸማች ማኅበራት ከሚገዛበትም እንዲሁ የተሻለ ሆኖ ቆይቷል። በደምሳሳው የእሁድ ገበያ አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እና በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ያለባቸውን የኑሮ ጫና በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና ሲጫወት ቆይቷል ። አምራቹን እና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት በከተማዋ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እና ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር ማስቻሉ እሰየው ያሰኛል። ሆኖም አሁን ላይ በከተማችን የእሁድ ገበያ ቀድሞ በነበረበት በዚህ ውጤታማነት ቀጥሏል ለማለት የማያስደፍሩ ብዙ ሕጸጾች ይስተዋላሉ።
በሰርክ ቀናት በሸቀጦችና በምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት በእሁድ ገበያ ምርቶች ላይም ጎልቶ እየተንፀባረቀ የመጣበት ሁኔታ ተከስቷል። በሸማቾች ማኅበራት ቀደም ሲል ከ30 ብር እስከ አርባ ብር የነበረው አንድ ኪሎ ሩዝ በአብዛኞቹ የእሁድ ገበያዎች በአንድ ጊዜ ከ48 እስከ 50 ብር ማሻቀብ ችሏል። ማኮሮኒም በኪሎ 51 ብር እየተሸጠ እንዲሁ ቀይ የፈረንጅ ሽንኩርት በአንድ ጊዜ ከ40 እስከ 48 ብር የገባበት ሁኔታ መኖሩንም ታዝቤያለሁ። እንዲህም ሆኖ ሸንኩርት አንድ ኪሎ ብቻ አለመሸጡ ብዙዎቹን አቅመ ደካማ ሸማቾች ማሳዘኑንም ሳልታዘብ አላለፍኩም።
አምስት አንዳንዴም ሦስት ኪሎ እንዲገዙ መገደዱ ከዋጋው ንረት በላይ ሲያስቸግራቸው ማየቴንና ድርጊቱ አግባብ አለመሆኑን ሳልገልፅ ማለፍ አልፈልግም። ይሄው የዋጋ ንረት እያሻቀበ የሚወጣ እንጂ የሚወርድ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የአንዳንድ ምርቶች እጥረት ጭምር መኖሩም ተስተውሏል ለአብነት ያህል አሁንም ቢሆን በነዚህ በአብዛኞቹ አካባቢ በሚገኙ የእሁድ ገበያዎች የዘይት ምርት እንደልብ አይገኝም።
በአቅርቦቱ ላይ ከፍተኛ እጥረት ይታይበታል። ዱቄትም ቢሆን እንዲሁ የአቅርቦት እጥረት አለበት። ሰው በብዛት ይጠቀም የነበረው ሩዝም ቢሆን ጭራሹኑ አቅርቦቱ የለም ። የሳሙናው ዋጋም ከሰማይ ርቆ ሰው ልብሱን አጥቦ መልበስ ቀርቶ ፊቱን በሳሙና እስከመታጠብ እስከማይችል ደረጃ ደርሶ ገዝፏል።
በጥቅሉ በነዚህ በእሁድ ገበያዎች ምግብ ነክም ሆነ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ዋጋ በፍጥነት መጨመሩን ቀጥሏል። ሄዶ ሄዶ የጭማሪው ማቆሚያ የት እንደሆነ አይታወቅም። አሁን አሁን የእሁድ ገበያ ምርት አቅራቢዎችም እንደመደበኛው ገበያ ምርት አቅራቢዎች ሸማቹ ዋጋ ጠይቆ ይሄን ያህል የሚል ምላሽ ሲሰጡት ሲደናገጥና ራሱን ይዞ ሲጮህ ቆይ ኧረ ይሄን ያህል ሲገባ ትገዛለህ በማለት ዋጋውን ዝቅዝቅ አድርገው በመጥራት በሸማቹ ላይ መሳለቅ ሁሉ ጀምረዋል። ስላቃቸው አንድና ሁለት ኪሎ ሽንኩርት ሲጠይቅ አምስትና ሦስት እንጂ አንድና ሁለት እንደሌለ በሚነግሩት ጊዜ ያለውንም ያካትታል።
የእሁድ ገበያ ምርት አቅራቢዎች በመደበኛው ቀንና ገበያ ከሚቀርበው በሳንቲምና ሁለትና ሦስት ብር ልዩነት ምርታቸውን ማቅረባቸው ሳያንሳቸው በሸማቹ ኅብረተሰብ ላይ እንዲህ ማላገጣቸው ቢያሳዝንም ሳያስተዛዝብ የሚያልፍ አይደለም ። የእሁድ ገበያ በሸማቹ አዕምሮ ከሰርኩ ገበያ የሚለይበት ምንድነው የሚል ጥያቄ መፍጠሩ አይቀርም። ዕውነት ለመነጋገር ገበያው የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ እና የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እንጂ ለሸማችና ኅብረት ሥራ ማኅበራት የገበያ ዕድል ለመፍጠር ነው እንዴ የመጣው ማሰኘቱም አይቀሬ ነው። በስፋት የሚሳተፉበት ሸማች ማኅበራት መሆናቸውና በእሁድ ገበያው ሰርክ ሸቀጦቻቸውንና ምርቶቻቸውን በየራሳቸው መደብር ከሚያቀርቡበት ዋጋ በላይ በእሁድ ገበያ ሲያቀርቡ መታየታቸው ሸማቹንም ሆነ በሸማቹና በአቅራቢው መካከል ያለውን ግንኙነትና የገበያ ሁኔታ የታዘበውን ሁሉ ይሄንኑ ለማለት ይጋብዘዋል።
አሁን አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት መንስኤ ብዙዎች እንደሚሉት ዋንኛ መንስኤ መንግሥትም ሆነ የመንግሥት አካል ነንና በንግዱ ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ የንግዱ አመራሮችና ነጋዴዎች እንደሚሉት የአምራች በምርት ላይ ጭማሪ ማድረግ፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረት፣ በምንዛሪው እጥረት ምክንያት ጥሬ ዕቃ አለመኖር ፣የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን፣ የመሠረታዊ ፍጆታዎች ፍላጎት ማደግ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም በዋነኝነት መጥቀስ ይቻላል።
በአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስተባባሪነት አዲስ አበባ ከተማ ላይ የዋጋ ንረትን በማርገብና ገበያ በማረጋጋት ስም ወደ እሁድ ገበያ እንዲወጡ የተደረጉት የሸማችና የተለያዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቢሆኑ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ካልተደረገባቸው የችግሩ በአካል መሆናቸው የማይቀር እንደሆነ ይሰማኛል ።
እነዚህ የሸማችና የኅብረት ሥራ ማኅበራት የዋጋ ንረት በማርገብ ስም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካኝነት ወደ እሁድ ገበያ መግባታቸው አሁን ላይ ከተማ አስተዳደሩ የሚጠብቀውን ያህል ገበያን እያረጋጋ የኑሮ ውድነቱን እያረገበ መሆኑም ቢፈተሽ አይከፋም። እንዴውም በተለያየ መንገድ የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ የራሱን አስተዋፅዖ እያደረገ ነው። ይሄን ያልኩበት ምክንያት በአንድ በኩል እነሱ በምርትና ሸቀጥ ላይ ዋጋ በጨመሩ ቁጥር በመደበኛው ገበያ ተሰማርቶ የሚያቀርበው ነጋዴ የዛኑ ያህል እነሱን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርግበት ሁኔታ ስላለ ነው።
በሌላ በኩል ከነጋዴው ጋር በመመሳጠር የሸቀጥና ሌሎች ምርቶችን አየር በአየር በመሸጥ እጥረት እንዲፈጠር ስለሚያደርጉ ነው ። በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ የእሁድ ገበያን ጠንካራ ጎን ማጠናከር ደካማ ጎኑን ደግሞ መንቀስ በመንቀስ የእሁድ ገበያ በከተማችን ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ይገባዋል እላለሁ!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2014