አሪስጣጣሊስ በግሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ384 ዓ.ዓ እስከ ታህሳስ 7፣ 322 ዓ.ዓ የኖረ ስመ ገናና የግሪክ ፈላስፋ ነው። በምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔም ከፍተኛ ስፍራም የሚሰጠው ነው። ይህ ስመ ገናና የሆነ ፈላስፋ ብዙ መጻሕፍትን እንደ ጻፈ ቢነገርለትም ዘመናትን ተሻግረው ለዚህ ትውልድ የተረፉት መጻሕፍት ጥቂት እንደሆኑ ይነገራል።
አሪስጣጣሊስ በመጻፉ ካሰፈራቸውና ዘመናት ተሻጋሪ ከሆኑ አባባሎቹ መካከል ስለሕግ የበላይነት የተናገረው ‹‹ዜጎችን ማንም ሰው ከሚገዛ ይልቅ፤ ሕግ ሊገዛቸው ይገባል» የሚለው አባባሉ ስለ ሕግ የበላይነት በተነሳ ቁጥር የሚጠቀስ ነው። የህግ የበላይነት ምንኛ ትልቅ ማሕበራዊ እሴት እንደሆነም የሚያመላክት ነው።
በትግሉ ተስፋው የሚባሉ ፀሃፊ ደግሞ፤ “ሕግ የበላይነትን ማስከበር የየትኛውም አገር ተቀዳሚ ተግባር የሚሆነው አገርን እንደ አገር ህልውናዋን አስጠብቆ ለማስቀጠል ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ በመሆኑ ነው ” ይላሉ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ገና በእንጭጭ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ያሉ አገራት የሕግ የበላይነት ጉዳይ ትልቁን ስፍራ ሊይዝ እንደሚገባ ትኩረት ሰጥተው ይናገራሉ።
በተለይ አምባገነን ከሆነ መንግሥት ወደ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት የሚደረገው ወሳኝ ታሪካዊ ጉዞ፤ በሕዝብ ምርጫ ብቻ መከናወን ይኖርበታል። በሕገመንግሥት በተደነገገባት አገር የሕግ የበላይነት ማስከበር በቀጥታ አገርን ከአደጋ መጠበቅ ጭምር ነው። የሕግ የበላይነት ከሌለ አስተማማኝና ዘላቂ የሆነ ሥርዓት መገንባት አይቻልም የሚልም የፀና እምነት አላቸው። የሕግ የበላይት የሚረጋገጠው ደግሞ ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡ ብቻ ነው።
የሕግ የበላይነት በሌለበት ሁሉ አገር የግለሰቦች መፈንጫ፣ ሥልጣን የአምባገነኖች እና የመዝባሪዎች መሸሸጊያ ይሆናል። የሕግ የበላይነት በሌለበት ወይንም ቁጥጥሩ ልል በሆነበት ሁኔታ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳል። የአገር ሠላም ይናጋል፤ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢና አገር ነፃነት ተሰምቷቸው እንዳይኖሩ በማድረግ የዕለት ተዕለት ሕይወትን ሳይቀር ያናጋል።
በርካቶች እንደሚስማሙት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት የነበሩ ችግሮች ምንጫቸው የሕግ የበላይነት ዋጋ በማጣቱ የተከሰቱ ናቸው። ሀገሪቱ ባለፉት 50 ዓመታት የፖለቲካ ፍልስፍና ውስጥ የማወደስና የማውገዝ ስብሰባዎች እና የታጠቁ ኃይሎች የበላይነት ዋነኛ የፖለቲካ የአመራር ዘይቤ ሆኖ ሲያገለግል በጠባብም ሆነ በሰፊው በፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች ማግለልና ማሳደድ፣ ግድያና ማሸማቀቅ ትልቁን ቦታ ነበረው።
በሀገሪቱ በየወቅቱ የሕግ የበላይነት ለማስከበር የተደረጉ ጥረቶች ከፍተኛ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል፤ በአሁኑ ወቅትም በሰፊው እየተስተዋለ ያለው ይኸው እውነታ ነው ነው። በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አመክንዮ ሥፍራ ኖሮት በመነጋጋርና በመደማመጥ መፍትሄ የተገኘቡባቸው አጋጣሚዎች በጣት ሚቆጠሩ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ደም መፋሰስና የከፋ እልቂት ሲከሰት ከታሪካችን ተገንዝበናል፤ አሁንም እያስተዋልን ነው።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የአሸባሪው ሕወሓት ኃይሎች በሀገር መከላከያ ላይ ክህደት በፈፀሙ ጊዜ በርካቶችን ትኩረታቸውን ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል አድርገው ነበር። ታዲያ በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም በርካቶች የሳሳ የመሰለውን ፀጥታ ሁኔታ እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ከመንግሥትም በላይ መንግሥት ነን ለማለት ሲዳዳቸው ተመልክተናል።
ቡድኑ የፈፀመው የሕግ ጥሰት እንዳለ ሆኖ ለሌላ የሕግ ጥሰት ሲኳትኑ የነበሩ ቡድኖችን ለመታዘብ ችለናል። በዚህ ውስጥ መረዳት የሚቻለው ልክ እንደ ሕወሓት የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ትጥቆችን የማግኘት ዕድል ቢኖራቸው ለኢትዮጵያ ከሕወሓት ባልተናነሰ ሁኔታ ፈተና መሆናቸውን ነው።
የሕግ የበላይነትን በመጣስ የራሳቸውን ፍላጎት ማስፈፀምና መፈፀም የሚዳዳቸው በርካቶች መኖራቸውን በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ውስጥ ላለው የሰላም መደፍረስ ዋንኛ ምክንያት ነው።
አመክንዮ ስፍራ ኖሮት በመነጋገርና በመደማመጥ ለመፍትሄው ከመትጋት ይልቅ በስሁት አካሄድ ዓላማቸውን ማሳካት የሚፈልጉ አሁንም በጉያችን ተሸክመናል። የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የጸጥታ ሃይሎች ያልተጠበቁ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ነው።
የፌዴራል ፖሊስ እና ሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንቅስቃሴ በመግታትና በመተናኮል ተልዕኮዎች እንዲከሽፉ የሚያደርጉ መንደራዊ ተግባራትና ኢ-ሕመንግስታዊ አካሄዶች እየተስተዋሉ ይገኛሉ።
ይህ ችግር እያደገ ከሄደ ሀገረ መንግሥቱን ሆነ ሀገሪቱን እንደ ሀገር ከፍ ያለ አደጋ ውስጥ ሊጨምራት እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም። ይህ ደግሞ ለዚህ ትውልድ ላይ ሊያስከትል የሚችለው የታሪክ ተጠያቂነት ከፍ ያለ ነው።
እንደ ዜጋ ጥያቄያችንና አካሄዳችን መናበብ አለበት። የሕግ የበላይነት ይከበር ማለት፤ሕግ የበላይ ይሁን ማለት ነው። ይህ በየትኛውም መልኩ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ወንጀለኞችን በመደበቅ አሊያም ደግሞ ለወንጀለኛች ከለላ በመስጠት የሚፈጠር የሕግ የበላይነት የለም።
ለሕግ የበላይነት መገዛት የሚጀምረው ወንጀልን በመፀየፍ፣ ወንጀለኛን አሳልፎ በመስጠት ብሎም ከወንጀል ፍሬ የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ሳይቀር ጥቅም ላይ እንዳይውል በማድረግና ሕግ ለሚያስከብር አካላት በመተባበር ነው። ወንጀለኛ የትም መቼም ቢሆን በእይ ድርጊት ውስጥ እስከተገኘ ድረስ የእኛ እና የእነርሱ የሚባል ስያሜ ወይንም ከለላ ሊሰጠው አይገባም።
ኢትዮጵያን ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ኩስምን አድርጎ ያስቀራት አንድም ሕግ ባለማክበር አንድም ደግሞ የሕግ በላይነትን ለሚያስከብሩ ድጋፍ ባለመስጠት ነው። ይህ እንደ ሀገር የተጠናወተን አካሄድ ከግለሰባዊ እሳቤና ተንኮል አልፎ ቡድናዊ እና ማሕበረሰባዊ እሳቤ መሆን ዕድሉ የሰፋ ስለመሆኑ ከአሸባሪው ሕወሓት እና ተከታዮቹ መረዳት ይቻላል። የቡድኑ ሰዎች ጥቂት ተጠርጣሪዎችን ለፌዴራል መንግሥት አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ በክልሉ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ መመልከት በቂና ከበቂ በላይ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት በዚህ ደረጃ የወንጀለኞች መናኸሪያ ሊሆን የቻለውና ትግራይ ክልልን ለከፋ አደጋ አሳልፎ የሰጠው ለሕግ የበላይነት የመገዛት ልምድ ባለማዳበሩ፤ ሕግን በሕግ ዓይን ብቻ ዓይቶ ባለመዳኘቱ ነው። የሆነነው ሆኖ ሕግ የሕግ በላይነት ለድርድር መቅረብ ስላነበረበት ሕግ የጣሱት የእጃቸውን ሊያገኙ ግድ ሆኗል።
ታዲያ ከቡድኑ መማር አለመቻል በራሱ አስገራሚ ቢሆንም ሰሞኑን አንዳንድ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ዘመቻ ሲጀመር የእኛ ሰዎች ተነኩ፤ ብሄራችን ተጠቃ፤ ተደፈርን… በሚል ወንጀል እና ወንጀለኛን ለመሸፋፈን እየተደረገ ያለው ጥረትን እየተሰማ ያለው ጩኸት ችግሩ በየወቅቱ መልኩን እየቀየረ መቀጠሉን የሚያመላክት ነው። ይህ አካሄድ ፍትህ እና ርትዕን የሚያሰፍን አይደለም፤ ይልቁንም ያለፉትን ስህተቶችን መደገም ካልሆነ በስተቀር።
ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ ከክርስቶስ ልደት በፊት ስለ ሕግ እና የሕግ የበላይነት ሲናገር የነበረው የሰው ልጅ በሥርዓትና ደንብ እንዲዳኝ እንጂ በዘውጌ የፖለቲካ እሳቤ ውስጥ በመወሸቅ ፍትህ እንዲዳፈን አይደለም። እንኳ አይደለም ዛሬ ጥንትም ቢሆን ፍትህ ምንኛ አስፈላጊ እንደነበር መገንዘብ ተችሏል።
ወንጀል ውስጥ ተዘፍቆ በብሄር አጥር ውስጥ መወሸቅና አልነካም ባይነት፣ መታበይና መንደላቀቅ ለጊዜው ካልሆነ በስቀተር ፈፅሞ ከተጠያቂነት አያድንም። አንዲት ሀገር መንግሥት ካላት ሀገር ደግሞ ሕግን ተግባራዊ በማድረግ ተጠያቂነት ማስፈን የግድ ነው።
መንግሥትም ሕግን ማስከበር ግዴታው መሆኑን ማመን ይገባል። መንግሥት የአንዱና ዋንኛ መገለጫው ሠላማዊ ምህዳር መፍጠርና የሕግ የበላይነትን ሳያወላዳ ማስከበር ነው። ለዚህ ሁሉም ዜጋ የመተባበር ግዴታ አለበት። በሕግና ሥርዓት የሚጸናው ሰላማችን የነገ ተስፋችን መሰረት ጭምር ነው። ከዚህም የተነሳ የሕግ የበላይነት በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ለድርድር መቅረብ የለበትም። መንግሥት ይህ ይሆን ዘንዳ በጽኑ ሊሰራ ይገባል።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2014