ምክንያታዊነት እውነትን ከሀሰት፤ ትክክለኛው ከተሳሳተው መለየት የሚያስችል የአስተሳሰብ አድማስ ነው። በዚህ አስተሳሰብ ከተመራን እያንዳንዱን ጉዳይ የምንመረምረው ምክንያታዊ ና ሚዛናዊ በሆነ አስተሳሰብ ማእቀፍ ውስጥ ሆነን ነው። ፍትሀዊነት መላበስና ከግልብነት መራቅ መነሻው በትክክለኛ አመክንዮ ማመን ነው።
ፍትሀዊነት ላይ ከቆምን አተያያችን የተቃናና ሚዛኑን የጠበቀ ስለሚሆን ጉዳዮች የምናይበት መነፅር የጎደፈ አይሆንም። የእይታ መነፅራችን የፀዳና እውነትን አጥርቶ የሚያሳይ ስለሚሆን ተግባራችን ከስህተት የጠራ ውጤቱም ከውድቀት የራቀ ይሆናል።
በምክንያታዊ አስተሳሰብ ውስጥ እያንዳንዱ ጉዳይ የሚታየው በስክነት ነው። ጉዳይ ከመነሻው እስከ ውጤቱ ተለይቶ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን በተለያየ አተያይ ይመረመራል። በምክንያታዊነት ውስጥ ስሌት የገዘፈ ስፍራውን ይይዛል። ወደዚህ መድረክ የመጡ ጉዳዮች ሁሉ የሚመረመሩት በሰከነ መንፈስና በሰላ አስተሳሰብ ነው። ለምን? የሚል መነሾ ከፊት ስለሚቀድም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ተግባር የሚያመጣ ውጤት ድርጊት የሚያስከትለው ግኝት ቀድሞ ይገመታል፤ ይመረመራልም።
ስለሆነም በምክንያታዊ አስተሳሰብና ተግባር ውስጥ የተሳሳተ ውጤት ቦታ አይኖረውም። ምክንያቱም ቀድሞ ስለ ጉዳዩ ምንነት በእርጋታ ይመረመራል፣ ስለ ተግባሩ መነሻ ይጠናል። እያንዳንዱ ጉዳይ በቂ የሆነ መነሻና መድረሻ ይኖረዋል። ምክንያታዊ መሆን የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። ከስሜት መራቅና ጉዳዮች በስሌት መመልከት የሚገባን ከውድቀትና ከጥፋት እራሳችንን ለመጠበቅ ነው።
በምክንያታዊነት የተመራ ትውልድ በአስተሳሰቡ ሚዛናዊ የሆነ ማህበረሰብ ይፈጥራል። ለዚህ ማህበረሰብ አገራዊ ለውጥና ሁለንተናዊ ከፍታ ላይ መድረስ እጅጉን ይቀለዋል። መግባባትና አንድነቱ ይጠነክራል። እዚህ ጋር በስክነት የሚከወን ስሌት ስላለ ተግባር ብዙን ጊዜ ባማረ ውጤት የታጀበ ድል ያስገኛል።
በአንፃሩ ደግሞ ምክንያት አልባነት ከዚህ የተለየ ውጤት ላይ ያደርሳል። እዚህ ላይ ስሜት እንጂ ስሌት ዋንኛ መሰረት ስለሌለው መድረሻው ጥፋት ውጤቱ ያልታሰበ ይሆናል። በዚህ አስተሳሰብና ተግባር የሚገኘው ውጤት ቀድሞውኑ ያልታሰበበት ስለሚሆን አሉታዊነቱ እሙን ነው። ምክንያት አልባነት የሚያስመለክተው ስሜትን እንጂ እውነት አይደለም። ስሜት ደግሞ በደመነፍስ መነዳት እንጂ በጥበብ አንድም እርምጃ አያራምድም። ለዚህም ነው፤ ምክንያት አልባ ትውልድ ዘመኑን በራሱ የሚበላው።
ምክንያት አልባነት ግልብነት ነውና ውጤቱ አክሳሪ ነው። ላለመግባባትና ግጭት ዋንኛ መንስኤ በመሆኑ ለአብሮነት ትልቁ መሰናክል ይፈጥራል። ከምክንያታዊ አስተሳሰብ መራቅ በትውልድ ዑደት ውስጥ በሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት ችግሮች ይደራረባሉ። ትውልዱ ጥያቄና ተግባሩ የሚጣረስ ፍላጎትና ማሳኪያ መንገዱ የተቃረነ ይሆናል።
በምክንያት የተመራ ጉዳዮችን አመዛዝኖ የሚያይ ትውልድ ከስህተት የራቀና ከውድመት የተረፈ ይሆናል። ምክንያቱም እዚህ ጋር ስሌት ከስሜት ይልቅ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። የሚያደርገውና የሚከውነው ሁሉ ከስሜት በራቀ መልኩ በስክነት አስልቶ ነውና። እያንዳንዱ ሀሳብና ተግባራቱ በስክነት የተሞሉ ይሆናሉ። እዚህ ስክነት ላይ ተቁሞ የነገሮችን ሁሉ መፍትሄ ማሰብ ብሎም መተግበር ይቀላል። በዚህ ውስጥ አገር ትረጋለች በዚህ ውስጥ ለውጥና እድገት ይቀላል።
አገራችን በዘርፈ ብዙ ትግል ውስጥ መሆንዋ ለሁላችን ግልፅና ልንሸፋፍነው የማንችለው ሀቅ ነው። ያሉብንን ማህበራዊና ፖለካዊ ችግሮች መፍቻ ቁልፉ ደግሞ እኛው እጅ ላይ ነው። ይህ በሰከነ መልኩ ለመግባባት እራሳችን ዝግጁ ማድረግ። ይህንን የሁለንተናዊ ችግራችን መፍትሄ የሆነን ቁልፍ በትክክል መጠቀም ደግሞ የእኛው ፋንታ ነው። ለችግራችን መፍትሄ የሚሆኑ ጉዳዮችን በስክነት መለየት ብሎም መተግበር ይገባናል።
ትልቅ አገርና ብዝሀነት መለያው የሆነ ማህበረሰብ ውስጥ የሀሳብ ልዩነት መኖሩን ሀቅ ነው። በሀሳብ ልዩነት ምክንያት የሚቀርቡ ጉዳዮችን በምክንያታዊ አስተሳሰብ ላይ ቆሞ መመርመር ይገባል። የራስን ሀሳብ ከሌላው ጋር ማስታረቅና ሰጥቶ በመቀበል መርህ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።
እንኳን አገራዊ ጉዳይ ግለሰባዊ ጉዳይ በስሜት ከተመራ አቅጣጫውን ይስታል። ለጋራ መፍትሄ ስክነት ለተግባቦት መደማመጥ ያሻል። እያንዳንዳችን አገራዊ አንድነት ተጠናክሮ ለሁላችንም ምቹ የሆነችና በእያንዳንዳችን ላይ የሚታይ ለውጥ መጎናፀፍ እንፈልጋለን። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ የጋራ ለውጥ ላይ መረባረብ አገራዊ እድገት ላይ በአንድነት መስራት ቀዳሚ ተግባር ነው። አንድ ሆኖ ወደፊት ለመራመድ ደግሞ አንድነትን የሚያጠነክሩ መለያየትን የሚያርቁ ጉዳዮች ቀድሞ መፍታት ያስፈልጋል።
ያለችን አንድ አገር ናት። ህልውናዋን አንድ ሆኖ ማስጠበቅ ደግሞ የእኛ የዜጎች ግዴታ ነው። ኢትዮጵያችን ለሁላችንም የምትበቃ በጋራ መቆም አንድነታችን ማጠንከር ካወቅንበት ከራሳችን አልፋ ለሌላው የምትተርፍ ኃያል አገር ናት። በእስዋ ውስጥ አብረን በጋራ ተሳስረን መኖር ግድ ይለናል። አገራችን ለልጆችዋ ምቹ በእድገት ወደፊት የተራመደች፣ በፅኑ መሰረት ላይ የፀና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያረጋገጠችና ዲሞክራሲና ፍትህ የነገሰባት ትሆን ዘንድ የአመለካከት ለውጥ መላበስ ይኖርብናል። ይህ የአመለካከት ለውጥ ደግሞ የተሻለች አገር ለመፍጠር ያስችላል።
በአገር ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ እየተሰራበት ያለው አገራዊ ውይይት ፍሬያማ ይሆን ዘንድ መስራት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ውይይቱ መግባባት ላይ ያደርሰን ዘንድ እንደ ዜጋ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀው ቀና እሳቤና አገራዊ የተቆርቋሪነት ስሜት መላበስ ነው። ለውይይት ስነቀርብ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ተላብሰን ፍትህና አንድነት የጋራ አጀንዳችን አድርገን አገራዊ ለውጥን በመናፈቅ ሊሆን ይገባል።
ከስሜት በራቀ መልኩ በምክንያታዊነት መመራት ለመፍትሄ ያቃርባል። ለመግባባት ከራስ ባለፈ ወገኔ ከግል ጥቅም ባየለ አገሬን ማለት ይኖርብናል። ከሁላችን በላይ ቀድማ መቆም ያለባት ኢትዮጵያ ናትና የእኛ እሳቤና አመለካከት በእርስዋ ውስጥ በተንሰላሰለ መልኩ የሚተገበር ከሌላው ጋር መግባባትና መተሳሰር የሚያስችል መሆን ይኖርበታል። የእኛን ለሌላው መስጠት እንደምንፈልገው ሁሉ መቀበል፤ እንዲከበር እንደምንፈልገው ሁሉ የሌላን እሴትና አመለካከት ማክበርና አብሮነትን ማፅናት ይገባናል፡።
እንደ አገር ወዳድ ዜጋ አገራዊ አንድነት ማፅናትና ፍትሀዊ የሆነ አስተሳሰብ መላበስ የእኛ መቆሚያ ሊሆን ይገባል። የምንጠይቀውን በትክክል ማወቅ የተሰጠንን አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣትና አገራዊ መግባባቱን ውጤት ላይ ለማድረስ ምክንያታዊ አስተሳሰብ መላበስ ለመልካም ውጤት እንደሚያቀርብ መረዳት ያሻል። በአገራዊ መግባባት ውስጥ የሚገኙ መልካም ፍሬዎች መቋደስ እንድንችል የሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ ጠንክረን መስራት፤ በሀሳብ የሚያለያዩን ደግሞ በጥበብ መፍታት ቀዳሚው የቤት ስራችን ነው። ይህ ስራችን ደግሞ የህዝባችን አንድነት የሚያጠነክር የአገራችን ህልውና የሚያስጠብቅና ሰላማችን የሚያረጋግጥ በጥበብ የተመራ ይሁን። አበቃሁ፤ ቸር ይሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014