
መንግሥት ተኪ ምርት በሀገር ውስጥ እንዲመረት በማበረታታት ላይ ይገኛል። ይህም “በአንድ ወንጭፍ ሁለት ወፍ” እንደሚባለው ነገር ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው። ተኪ ምርት ፋብሪካዎች እንዲገነቡ ይረዳል። በእዚህም ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ያገኛሉ። በተጨማሪም በሚገነባው ፋብሪካ ሥራ አጦች ተቀጥረው ለመሥራት የሥራ ዕድል ያገኛሉ። ሀገርም በውጭ ምንዛሪ የሚገባ ምርትን በሀገር በማምረት የውጭ ምንዛሪ ታድናለች። ፋብሪካው በተቋቋመበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ ይከፈታል። የፋብሪካውን ዕቃ ምርት ለመውሰድና የፋብሪካውን ግብዓት ለማራገፍ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ሲበዙ፤ ነዋሪዎች ምግብና መጠጥ ቤት ይከፍታሉ። ወጣቶችም እቃ በመጫንና በማውረድ ገቢ ያገኛሉ።
ወደ ውጭ በጥሬው የሚሸጥ ምርት ተጨማሪ እሴት ተጨምሮበት በሀገር ውስጥ ሲመረት ከላይ እንደጠቀስነው ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው። የሀገር ውስጥ ጥሬ ምርት አምራቾች ሰፊ ገበያ ያገኛሉ። ሥራ አጦች ደግሞ በፋብሪካ ተቀጥረው ለመሥራት ይታደላሉ።
እንደ ምሳሌ ሀገራችን የቅባት እህሎች (ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ተልባ፣ሱፍ የመሳሰሉት) በጥሬው ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ታገኝ እንደነበር ይታወቃል። ተኪ ምርት ለማምረት በምንጣጣርበት በዘመናችን እንኳ በምግብ ዘይት ምርት ራሳችንን መቻል አልቻልንም። አሁንም የቅባት እህሎችን እየላክን ድፍድፍ የዘይት ምርት (የተለያዩ የምግብ ዘይቶችን ምርት ከውጭ እናስገባለን)። ቀደም ሲል በከፊልም ቢሆን አነስተኛ በሆኑ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ለምግብ ዘይትነት ያመርቱበት ነበር።
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ የነበሩ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች የምግብ ዘይት ምርቶች አምርተው በመርካቶ አካባቢ በርሜል ተሞልተው ይሸጡ ነበር። በወቅቱ በመርካቶ ምስር ተራ አካባቢ አልያም ዕጣን ተራ ፊት ለፊት ባለ የገበያ ቦታ የምግብ ዘይት ከበርሜል በእጅ ፓምፕ እየተሳበ በሊትር ይሸጣል። ሰዎች የሚፈልጉትን ያህል ሊትር ዘይት ሲገዙ አስታውሳለሁ። ታዲያ የምግብ ዘይት በርሜሎቹ፤ ቆሻሻ ላያቸው ላይ ተደፍድፎ እና ተለጥፎ ለሚያያቸው ይሄ ነገር የምግብ ዘይት ነው? ወይስ የነዳጅ ዘይት? የሚል ጥያቄ ያጭር ነበር።
በወቅቱ ብዙ ሰዎች እንደሞጆ ዘይት ፋብሪካ የመሳሰሉ የዘይት ፋብሪካ ምርቶች እያሉላቸው ከላይ የጠቀስኩትን ዓይነት ዘይት ምርቶችን በችርቻሮ እየገዙ ለቤትም ለምግብ ቤቶችም መጠቀም ቀዳሚ ምርጫቸው ነበሩ። ይህም ጥቂት ብር ለማውጣት በመሻትና ጥራቱና ንጽህናው የተጠበቀ ምርት ዋጋው ይዋጋል (ይበዛል) ብሎ ከመስጋት በመነጨ እሳቤ ይመስለኛል። ግብይቱን ስታስቡት የታሸገ ምግብና የባልትና ውጤቶችን የመግዛት ባህላችን ደካማ ለመሆኑ ማሳያችን ነው ያስብላል።
በወቅቱ ከነበሩ ድክምክም ካሉ ዘይት ፋብሪካዎች የዘይት ፋጉሎዎችን እንደተረፈ ምርት ወስደው (የኑግ ፋጉሎ የመሳሰሉ) ከአዲስ አበባ ወንዝ ፍሳሾች እየቀዱ የገዙትን ፋጉሎ በጉርድ በርሜል ጨምረው በመቀላቀልና እንደጭቃ በእግራቸው እያቦኩ ዘይት እንዲመስል አድርገው መልሰው በወቅቱ ለነበሩት ጥቃቅን ዘይት ፋብሪካዎች ይሸጡ ነበር። የዘይት ፋብሪካዎቹ ደግሞ የተበከለውን ዘይት መሳይ ነገር ከራሳቸው ዘይት ምርት በመቀላቀል ለገበያው ያቀርባሉ። ዕኩይ ድርጊቱ ተጋለጠና ነጋዴዎቹ ተይዘው በፌዴራል ፖሊስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም መተላለፉን አስታውሳለሁ።
በእዚህም ምክንያት በየመንደሩ የሚመረተውን ዘይት፤ ሕዝብ ባለመግዛትና ከገበያ በማስወጣት “አምራቾችን” አይቀጡ ቅጣት ቀጣቸው። እናም ከላይ የጠቀስኩት ዓይነት የዘይት ምርት ከገበያ እንደወጣ ቀረ።
በተመሳሳይ መርካቶ ሸራ ተራ ከንጋት እስከ ምሽት በርበሬ ፈጭተው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚልኩ ወፍጮ ቤቶች ነበሩ። ወፍጮ ቤቶቹ ቀድሞም የገበያ ችግር የሚባል አልነበረባቸውም። ማለትም የሚፈጭ በርበሬ አጥተው ሥራ የሚያቆሙበት ቀን አልነበረም። የጭነት መኪናዎች ይመጣሉ ጥሬ በርበሬያቸውን ያራግፋሉ። ከእዚያ የተፈጨ በርበሬ ጭነው ደግሞ ይሄዳሉ። ወፍጮ ቤቶቹ ስፋታቸው በራሱ አዳራሽ የሚያስንቁ ነበሩ።
ያ ሁሉ ገበያ አልበቃ ያላቸው ከላይ የጠቀስኳቸው ስግብግብ ነጋዴዎች ውስብስብ ነገር ውስጥ ተዘፍቀው ተገኙ። ወፍጮ ቤቶቹ አጎራባቻቸው ከነበረው ወንበር ተራ እንጨት መላጊያና መሰንጠቂያ ቤቶች ሰጋቱራ ወይም ድቃቂ የእንጨት ጥራጊዎችን ለማገዶ በሚል በጆንያ ወስደው እና ቀይ ሸክላ በአሳቻ ሰዓት እያደቀቁ ከበርበሬው ዱቄት ጋር እየደባለቁ ሲሠሩ ሲያስጭኑ በፖሊስ ተደረሰባቸው። ፕሮግራሙም በፖሊስ ቴሌቪዥን ተላልፎ ነበር።
ፕሮግራሙ በቴሌቪዥን ከተላለፈ በኋላ አንድ ሁለት ዓመት ተዘግተው እንደነበር በአካባቢው በብዛት ስመላለስ አስታውሳለሁ። በወቅቱ በበርበሬ ላይ ባዕድን ነገር ቀላቅሎ በመሸጥ በመርካቶ ከነበሩት 14 ወፍጮ ቤቶች ነፃ ሆነው የተገኙት ሁለቱ ብቻ ነበሩ። ጥፋተኛ የተባሉት ወፍጮ ቤቶች ከሁለት ዓመት በኋላ ቢከፈቱም ቅሉ ቀድሞ ከነበራቸው በማምታታት ከሠሩበት ገበያ ብዛት፤ ኢምንት ማምጣት አልቻሉም። እናም ወፍጮ ቤቶቹ ሲከፈቱ ገበያው ስለጠፋ በብዛት የእንጨትና የቆዳ ጫማ ቁሳቁስ መጋዘን ሆነዋል።
በማምታታት ግብይት ውስ ጥ ያልነበሩት ሁለት ወፍጮ ቤቶች እንኳን ከፍተኛ የገበያ እጥረት አጋጠማቸው። ከላይ እንደ ማሳያ የጠቀስኳቸው የምግብ ዘይትና የበርበሬ ዱቄት የመርካቶ ታሪኮች ራሴ ያየኋቸውና በወቅቱ (ከአስር ዓመት በፊት) በተላለፈው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ከባልደረቦቼ ጋር የሠራኋቸው ነበሩ። ዜጋው እነዚህን መሰል ከባዕድ ነገሮች ጋር ተደባልቀው የሚሸጡ የባልትና ምርቶች ከመግዛት በመታቀቡ የገበያ ድርቅ ተዘፈቁ።
በቅርቡም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጠቅሶ አዲስ ዘመን ባወጣው ዜና፤ ኅብረተሰቡ አገልግሎት ላይ እያዋላቸው ከሚገኙ የወተት ምርቶች ለአደገኛ በሽታዎች የሚያጋልጡ አራት የባክቴሪያ ዓይነቶች ተገኝቶባቸዋል። ዜናው ላይ እንደተገለጸው፤ በወተት ምርቶቹ የተገኙ ባክቴሪያዎቹ የኩላሊት፣ የሽንት መተላለፊያ እና የቆዳ በሽታን የሚያስከትሉ፤ በተጨማሪም የሳምባ ምች፣ የደም ዝውውር እና የቁስል ኢንፌክሽኖች እና ታይፎይድን የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎችን በብዛት የሚፈጥሩ እንደሆነ ተዘግቦ ነበር። ዜናውን በማስተጋባት ብዙ ሚዲያዎች የተረባረቡበት ቢሆንም የዜና ምንጩን ኢፕድ ብሎ ለመጥቀስ ግን አልደፈሩም። ያም ሆነ ይህ ግን ከላይ እንደ መግቢያ ያነሳናቸው የምግብ መበከል ቁንጽል መረጃዎች ለምግብ ደህንነት ስጋት እንደሆኑ ማሳያዎች ናቸው።
የምግብ ደህንነት ችግር የሚከሰተው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። ከእነዚህም በስግብግብነት ወይም በፍቅረ ንዋይ በመታወር፣ በቸልተኝነት በማምረትና በማከማቸትና በማጓጓዝ፣ ለሽያጭ በሚቀርብበት ሂደት ተገቢውን የጥራትና ደህንነት ጥንቃቄ ባለማድረግ እና በመሳሰሉት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው። የምግብ ደህንነት ምግብን ከምርት እስከ ግብይት ከብክለት ተጠብቆ ለተመጋቢው የማድረስ ሂደትን የሚያካትት ነው።
በሀገራችን አብዛኛው ለገበያ የሚቀርብ የምግብ ግብዓት ለብክለት የተጋለጠ ነው። እንደ ወተት፣ እርጎ፣ ቅቤ፣ አይብ፣ ማር፣ በርበሬ፣ ሽሮ፣ እንጀራ የመሳሰሉ የባልትና ምርቶች ለገበያ ሲቀርቡ ከባእድ ነገር ጋር የመቀላቀል ችግር ይታይባቸዋል። አብዛኞቹ ከገጠር እስከ ከተማ ሲጓጓዙ የምግብ ግብዓቶቹ የሚያዙበት ዕቃ ራሱ ለንጽህና ችግር የተጋለጡ ናቸው።
ማርና፣ ቅቤ፣ አይቤ ከገጠር ቦታዎች ሲመጡ በብዛት በስልቻ እና በላስቲክ ተጠቅልለው ነው። ጎጃም በረንዳ ያለውን የማርና የቅቤ የግብይት ቦታ ብታዩት ለማዘመን እና የምግብ ግብዓቶቹን አሽጎ ለማቅረብ ብዙም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አይታይም። በርግጥ የተወሰኑ የታሸጉ ምርቶች አሉ። ማር፣ለውዝ፣ እርጎ፣ ወተት የመሳሰሉት የታሸጉ ምርቶች አሉ። እንዲስፋፉ ሚዲያው ግንዛቤ በመስጠት መሥራት አለበት። ቂቤውን አሽገው ሊሸጡ የሚችሉበትን መንገድ የበለጠ ማስፋፋት ለምግብ ደህንነት ስጋት የሆነው ኋላቀር ግብይት እንዲዳከም የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል።
የዛሬ ሃምሳ ዓመት ሲሸጡበት በነበረ መልኩ ነው አሁንም የተጠቀሱትን የምግብ ግብዓቶች የሚሸጡት። ነጋዴዎቹ በአክሲዮን ተደራጅተው የምግብ ግብዓቶቹ ታሽገው እንዲሸጡ ማድረግ የሚችሉበት መንገድ እንዳለ ቢገነዘቡም፤ ሳይለፉ ትርፍ ማፈሱን ነው የሚያስቡት። ሌላው ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ባሉባቸው አካባቢዎች በገበሬ የሚመረቱና ለከተሞች የሚቀርቡ የምግብ ምርቶች ካሉ ለአቧራ፣ለፀሐይ ፣ለእጅ ሳይጋለጡ ታሽገው ሊሸጡ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል። እርግጥ ነው ገበሬው በእዚህ ረገድ ግንዛቤም አቅምም የለውም። ምርቶቻቸውን በርካሽ ዋጋ ለነጋዴና ለደላላ እየሸጡ ሕይወታቸውን ሊለውጡ ያልቻሉ ገበሬዎችን ቆጥረናቸው አንጨርሳቸውም።
ባንኮችም ለገበሬዎች እንዲደራጁና የሚያመ ርቱትን ምርት በኢንዱስትሪዎች አሽገው ለገበያ ሊያቀርቡ የሚችሉበትን መንገድ ብር በማበደር የድርሻቸውን ይወጡ። የክልል ግብርና ቢሮዎችም በየአካባቢው ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመመካከር የገበሬዎች አቅምን በማየት ከባንክ ተበድረው ጥቃቅን ኢንዱስትሪ መሥርተው የባልትና ውጤቶችን አምርተው ለከተማው ሸማች እነሆ በረከት እንዲሉት መሥራት ቢችሉ መልካም ነው።
ገበሬው፣ ነጋዴውም የከተሜው ሸማችም አትራፊ እንዲሆን ምርቶች በቀላሉ ታሽገው ሸማቹ ጋር ማድረስ ሀገርንና ዜጋን አትራፊ ማድረግ ነው። ይህም ስጋት የሆነውን የምግብ ደህንነት መግታት ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናን ማምጣት ነው። የምግብ ብክለት ለጤንነት ስጋት ቢሆንም ችግሩን ለመቅረፍ የታሸጉ ምርቶችን መግዛት አልያም ምርቱ ከተመረተበት ቦታ ለመገብየት ቢቻል ወይንም ሰዎች የባልትና ውጤቶችን ሲገዙ ከስጋት ነፃ ለመሆን የራሳቸው ደንበኛ ቢይዙ ችግሮች እንኳ ቢከሰቱ ችግር ፈጣሪውን ለሕግ ማቅረብ ይቻላል።
የምግብ ደህንነት ስጋትን ለማስወገድ የምግብ ግብዓቶችን ገበሬዎችና ነጋዴዎች ከምንጩ ለገበያ እንዲያቀርቡ፤ በአክሲዮን ተደራጅተው ምርታቸውን አሽገው ለተገልጋዩ ሊያቀርቡ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል። በእዚህ ረገድ በየአካባቢው ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች በሚፈለገው ልክ ሲንቀሳቀሱ አይታይም፣ አይሰማም።
የምግብ ደህንነት ማለት ከምግብ ወለድ በሽታ እና ጉዳት ለመከላከል ምግብን በማዘጋጀት በማቀነባበር እና በማከማቸት ውስጥ ያሉ የዕለት ተእለት እንቅስቃሴዎችን ያመላክታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2023 የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ ስድስቱ ከምግብ ደህንነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው መሆኑ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
የምግብ ደህንነት ለብዙ የዓለም ሀገሮች ወሳኝ ዘለቄታዊ የልማት ግብ (SDGs) ነው። ይህም አልቦ ረሃብ (ending hunger) ፣ የምግብ ዋስትናን ማሳካት፣ መልካም ጤንነት እና ደህንነት፣ የኢኮኖሚ እድገት እና አጋርነትን ያካትታል። የዓለም ጤና ድርጅት የምግብ ደህንነት አስፈላጊነትን ዕውቅና በመስጠት እና እ.ኤ.አ. 2022 ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ አውጥቷል። የዓለም ጤና ድርጅትና የተመድ የምግብና እርሻ ድርጀት ያለ ምግብ ደህንነት የምግብ ዋስትና አይታሰብም በማለት ሀገራት ለምግብ ደህንነት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ያሳስባሉ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ሚኒስቴር፤ በሀገሪቱ የምግብ ደህንነትን ለማሻሻል ጠንካራ ቁጥጥርና ምቹ አካባቢ መፍጠር እንደሚገባ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ከፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ብሎግ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ውጤታማ የምግብ ደህንነት እና የጥራት ቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት አልሞ እየሠራ ነው። ይህም የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ምግብ መቆጣጠር፣ የኢኮኖሚና ንግድ አማራጮችን ከማስፋት ጎን ለጎን ለኑሮ መሠረት፣ለአካባቢና ለአየር ንብረት አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይህም የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ ይረዳል።
መንግሥት ብሔራዊ የምግብ ደህንነት አስተዳደር ፕላን (ፍኖተ ካርታ) ከ2017 -2021) በማውጣት እና ለመጀመሪያ ደረጃ የግብርና ምርት፣ ብሔራዊ የምግብ ደህንነትና የጥራት ስትራቴጂ በመዘርጋት፣ የምግብ ደህንነት ብሔራዊ ቅድሚያ የሚሰጠው አድርጎታል። የምግብ ደህንነትን በማሻሻል የተሻለ ጤናን ጨምሮ ጠንካራ ገበያና ኢኮኖሚ፣ ለተሻሻለ የምግብ ዋስትናና የአመጋገብ ሥርዓትን በመዘርጋት ለመሥራት መታቀዱ የመንግሥት ጥረት በርካታ ጠቀሜታ እንዲኖረው የሚረዳ ነው። ይህም መንግሥት ለምግብ ደህንነት ብሎም ለዜጎች ሕይወት የሰጠውን ትኩረት ያሳያል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ፤ለአምስት ዓመት የሚቆየው የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ 338 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ እየተሠራበት ነው። የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታው በርካታ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፤ ምግብ ወለድ በሽታዎችን በመቀነስ፣ ውጤታማ የምርት አቅርቦት ሰንሰለት በመዘርጋት እና በክምችትና ትራንስፖርት የሚከሰት የምግብ ብክነትን ለመቀነስ ይረዳል ተብሎ ይታሰባል።
በዓለም በየዓመቱ ከ600 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታዎች ይጠቃሉ። 420 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ይሞታሉ። በአፍሪካ በየዓመቱ በምግብ ወለድ በሽታዎች 137 ሺህ ሰዎች ለሞት እና 91 ሚሊዮን የሚደርሱት ደግሞ ለአጣዳፊ በሽታዎች እንደሚጋለጡ እና ለከባድ በሽታ የሚዳረጉት ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት እንደሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ሚኒስቴር በሀገሪቱ የምግብ ደህንነትን ለማሻሻል ጠንካራ ቁጥጥርና ምቹ አካባቢ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተውታል።
ይህ ዘገባ ሲጠናከር፤ ቻይና የምግብ ደህንነትን ለመጠበቅ ከኢትዮጵያ የምትወስደውን የሥጋ ምርት በሀገሪቱ ባሉ ሥጋ ማቀነባበሪያዎች የሥጋ መቀቀያ ቴክኖሎጂ በማስገባት የሥጋ ምርቱን በመቀቀል ለቻይና ገበያ እንዲያቀርቡ እየተሠራ መሆኑን ሰሞኑን አሀዱ ሬዲዮ ያወጣው ዜና ያሳያል። በእዚህም ቄራዎችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማስገባት ኮምፒውተሮች ተገዝተው ለዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እየተሠራ መሆኑን ነው መረጃው የሚያሳየው። ይህም ለሌሎች ሀገሮችም የሥጋ ምርቶችን ቀቅሎ አሽጎ ለመላክ የሚረዳ ነው። ኢትዮጵያ በያዝነው በጀት ዓመት ስድስት ወር ብቻ ወደ ሞንጎሊያና ቻይና ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ የተቀቀለ ሥጋ በመላክ ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች።
የአትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በዓለም ገበያ በመላክ ይታወቃል። በዘርፉ ከ550 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እየተገኘ ሲሆን፤ ከ200ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው። እርግጥ ነው ማህበሩ የሚታወቀው በአበባ እርሻና ኤክስፖርት ቢሆንም፤ አትክልትና ፍራፍሬም ይልካል። ይህንኑ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በማስፋፋት እያሸገ ቢልክና ዜጎችም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገኙ የሚችሉበትን ሁኔታ ማህበሩ ቢያመቻች እንላለን።
የምግብ ደህንነትና የምግብ መበከል ዓለም አቀፍ ችግር እየሆነ ነው። በሀገራችን የምግብ ምርት ታሽጎ በመሸጥ ረገድ ገና ብዙ ይቀረናል። እያንዳንዱ ቤት ቅቤ ቢያንስ ለበዓል ይገዛል። ግን የታሸገ ቅቤ በብዛት አይገኝም። አይቤ ፣እርጎ የመሳሰሉ የታሸጉ ምርቶችን በመግዛት ረገድ ማፈግፈግ ይታይብናል። ማር ታሽጎ በመሸጥ ገና ይቀረናል። ለየት የሚለው ነገር አብዛኛው ምግብ ለገበያ ሲቀርብ ስጋት የሆነው ፀሐይ ሲፈራረቅበት የዋለ፣ ለአቧሯ የተጋለጠ መሆኑ፤ እንዲሁም ስግብግብ ነጋዴዎች በምግብ ግብዓቶቹ እና የባልትና ውጤቶቹ ላይ ባዕድ ነገር ሲደባልቁበት በተደጋጋሚ የሚሰማበት ሂደት ነው።
በእርግጥ የእኛ ሀገር የምግብ ደህንነት አብዛኛው ስጋት የሆነው የፋብሪካ ምርት ባለመሆኑ ይመስላል። በውጭ ሀገር ምርቶች የታሸጉ ቢሆንም የታሸጉትን አመሳስሎ በመሸጥ፣ ምርቱ የአገልግሎት ዘመኑ የሚያበቃበትን ዓመት በመፋቅ የሚታይ ችግር ነው። በሀገራችን አብዛኛው ምርቶቻችንን አሽጎ ለመሸጥና የምግብ ደህንነትን ለማስጠበቅ መረባረብ ይኖርብናል። እርግጥ በሱፐር ማርኬቶች የታሸጉ የምግብ ምርቶች በብዛት አሉ። የተወሰኑት ከውጭ የገቡ የባልትና ምርቶች ናቸው። ብዙ ሰዎች በሱፐር ማርኬት ገብተው ለመገብየት ዋጋው ይበዛል የሚል ፍርሃት አለባቸው። ደህንነቱ ያልተጠበቀ ምግብ ከመሸመት ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ በመሸመት ለራስና ለቤተሰብ ጤና መቆም ይገባናል።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም