
ዜና ሐተታ
አቶ አሰፋ ገነቱ ይባላሉ።በሙያቸው አስጎብኚ ሲሆኑ ላለፉት 15 ዓመታት በአስጎብኚነት እየሠሩ ነው።በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን አጠቃላይ የከበሩ ማዕድናትን በተመለከተ የሚሰጠውን የአጭር ጊዜ ሥልጠና ወስደዋል፡፡
ሙያቸው እና የወሰዱት ሥልጠና ባይገናኝም፣ የከበሩ ማዕድናትን ለማወቅና ለመለየት ትልቅ ውስጣዊ ፍላጎት ስላላቸው ሥልጠናውን መውሰዳቸውን፤ ስለማዕድናቱ በደንብ ለማወቅ የሚያስችል ሥልጠና ለመውሰድ ብዙ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በስተመጨረሻ እንደተሳካ ላቸውም ይናገራሉ።
በአስጎብኚነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በሚንቀሳ ቀሱበት ወቅት ከከበሩ ማዕድናት ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ እንደነበራቸው፤ በተለይም ሀገሪቷን ለመጎብኘት ከውጭ ሀገር የሚመጡ ጎብኚዎች ለከበሩ ማዕድናት ያላቸው ውስጣዊ ፍላጎትና መነሳሳት፤ ስለ ማዕድናቱ ያላቸው ግንዛቤ እንዲያሰፋና የበለጠ እንዲያወቁ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን ሰሞኑን ስለ ከበሩ ማዕድናት በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ የአስራ አምስት ቀናት ሥልጠና መውሰዳቸውን ሥልጠናው፤ ዓለም ላይ ያሉ የከበሩ ማዕድናት ባሕርያት ለማወቅና ለመለየት እንዲሁም እሴት ጨምሮ በማስዋብ ለጌጣጌጥ እንዴት ማዋል እንደሚቻል በተግባር እውቀትን የጨበጡት እንደሆነ አመልክተዋል።
‹‹ሥልጠናውን ከመጀመሬ በፊት ስለማዕድናቱ የማወቅ ፍላጎት ብቻ ነበረኝ›› የሚሉት አቶ አሰፋ፤ ፍላጎት ደግሞ ወደ እውቀት የሚወስድ መንገድ እንጂ በራሱ እውቀት ስላልሆነ ሥልጠናው ስለከበሩ ማዕድናት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዲያወቁና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል።
የከበሩ ማዕድናትን በደንብ ማወቅና መለየት የሚያ ስችል ሙያ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ አሰፋ፤ ይህም በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች እንዲበረቱና ሥራው እንዲጠናከር ይረዳል፤ ኮርፖሬሽኑ በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ እየሰጠ ያለው ሥልጠና ቀጣይነት ኖሮት ለብዙዎች ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላኛው ሠልጣኝ ሐና ታደሰ ትባላለች።ጂኦሎጂስት ስትሆን ስለከበሩ ማዕድናት በጂኦሎጂ ትምህርት ካገኘችው እውቀት በተጨማሪ ስለከበሩ ማዕድናት በደንብ ለመለየትና ለማወቅ ያስችለኛል በሚል ሥልጠናውን መውሰዷን ትናገራለች፡፡
ሥልጠናው ቀደም ሲል ከነበራት እውቀት በተጨማሪ ብዙ እንድታውቅና ወደዘርፉ በስፋት ለመግባት እንደሚረዳት የምትናገረው ሐና፤ ሥልጠናው ስለማዕድናቱ በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተፈተሸ እውቀት ያገኘችበት እንደሆነ ትገልጻለች።በተለይ ማዕድናቱ ላይ እሴት መጨመርን በተመለከተ የተሻለ እውቀት የገበየችበትም ነው።
ኮርፖሬሽኑ በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ የሚሰጠውን ሥልጠና አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቅሳ፤ ሥልጠናውን ያለምንም ክፍያ በነፃ እንድታገኝ ስለረዳትም ኮርፖሬሽኑን አመስግናለች።
የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን የቢዝነስ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው ስማቸው በበኩላቸው፤ የከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ከሌሎች የማዕድን ዓይነቶች አንዱ መሆኑን፤ በዘርፉም አቅም ለመገንባት ኮርፖሬሽኑ ሥልጠናዎች እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
ሥልጠናው ያስፈለገበት ዋና ዓላማ የከበሩ ማዕድናት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆናቸው አኳያ፤ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ዜጎች እውቀቱ ኖሯቸው እንዲሠሩና ለሌሎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ለማስቻል ነው ብለዋል። የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተሻለ ዕድል መፍጠር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡
ሥልጠናው ለ15 ቀናት የሚቆይ አጭር ሥልጠና ቢሆንም ሠልጣኞች በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ በአጠቃላይ ማወቅ ያለባቸው ነገሮች እንዲያውቁ ፤ ዘርፉ ለሕገወጥ ንግድና ለሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይጋለጥ ግንዛቤን ለመፍጠር፤ ከዛም ባለፈ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ታስቦ በ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ስለመሆኑ ተናግረዋል፤ በሦስት ዙር 59 ያህል ዜጎችን ማሠልጠን መቻሉንም አስታውቀዋል ።
ኮርፖሬሽኑ ሥልጠናውን በተመጣጣኝ ክፍያ እየሰጠ መሆኑን፤ በዘርፉ የሚሠሩ ወይም ፍላጎቱ ያላቸው ዜጎች ሥልጠናውን ሊወሰዱ እንደሚችሉ አመልክተዋል። በቀጣይም ጅምር ሥራዎች በማጠናከር የሥልጠና ማዕከል በመክፈት ዘርፉ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
በወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም