‹‹በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ300 በላይ ፋብሪካዎች ገንብተዋል›› አቶ መሐመድ ዓሊ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ

አዲስ አበባ፡በአፋር ክልላዊ መንግሥት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ከ300 በላይ ፋብሪካዎች መገንባታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ዓሊ አስታወቁ። ክልሉ በነዚህ የለውጥ ዓመታት ውስጥ የሰላም ተጠቃሚ መሆኑን አመለከቱ።

የቢሮ ኃላፊው አቶ መሐመድ ዓሊ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የአፋር ሕዝብ ከብልፅግና መንግሥት በፊት በነበረው ሥርዓት ምንም የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ተሳትፎ ሳይኖረው በሞግዚት አስተዳደር ሲተዳደር ቆይቷል። የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሳይሆን በሀገሩ እንደሁለተኛ ዜጋ ሲቆጠር ከርሟል።

ብልፅግና በሚያስተዳድረው መንግሥት አሁን ላይ በፖለቲካ ሆነ በኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚ መሆን ችሏል፤ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ከሞግዚት አስተዳደር ነፃ በመውጣት ኢትዮጵያን ከሌሎቹ ጋር በመሆን እየመራ ይገኛል ብለዋል።

‘እኔ ነኝ የማውቅልህ፤ እኔ ነኝ የማደርግልህ’ ከሚል አካሄድ ወጥቶ ዛሬ ላይ በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተጎናጸፈበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

አቶ መሐመድ እንደተናገሩት፤ ካለፉት ሰባት ዓመታት በፊት ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት ባለ መኖሩ ምንም ዓይነት የኢንዱስትሪ ፓርክ አልነበረም። በአሁኑ ጊዜ ግን አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቷል። ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥም ከ300 በላይ ፋብሪካዎች በክልሉ ተገንብተው ሥራ ጀምረዋል። ከእነዚህ ከተገነቡ ፋብሪካዎች መካከል የጨው፤ የብሮሚን ማምረቻ ፋብሪካዎች ተጠቃሽ ናቸው።

አፍዴራ ላይ ከ20 በላይ ፋብሪካዎች ይገኛሉ ያሉት አቶ መሐመድ፤ ባለሀብቶች ፋብሪካ በመገንባት ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማስቻሉን ገልጸዋል። ለአካባቢው ማኅበረሰብ ደግሞ እንደ ትምህርት ቤትና ንፁሕ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በመገንባት ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የሥራ ባህል እንዲጠናከር አድርጓል ብለዋል።

የጨው ምርት ካለፉት ሰባት ዓመታት በፊት ለማይገባቸው ሰዎች ተሰጥቶ ሌሎች ሲጠቀሙበት የአፋር ሕዝብ የዳር ተመልካች እንደነበር ያስታወሱት ቢሮ ኃላፊው፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ግን በጥናት በመለየት የአፋር ሕዝብ በራሱ ሀብት መጠቀም እንዲችል መደረጉን ጠቁመዋል።

ክልሉ በቀድሞ ጊዜ የተለያየ የሰላም ስጋት እንደነበረበት ጠቁመው፤ አሁን ላይ በክልሉ ሰላም መስፈኑን፤ አፋር የውስጡን ሰላም ማስጠበቅ መቻሉን አስታውቀዋል። አፋር በግጭቱ ጊዜም ከዚያ በፊትም ሰላም በነበሩት የለውጥ ዓመታት ክልሉ ሰላም እንደነበር ጠቁመዋል።

እርሳቸው እንደገለጹት፤ በእርግጥ ግጭቶችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አይቻልም፤ ነገር ግን ተነጋግሮ መቀነስ ይቻላል። ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የነበረው ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረግ ነው። የነበረው ወንድማማችነትና ኅብረ ብሔራዊነት እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ከዚህ አንጻር በሰላም ላይ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ ናቸው።

አፋር የኢትዮጵያ ገቢ እና ወጭ ምርት የሚተላ ለፍበት መስመር መሆኑን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፣ ከጅቡቲ-ጋላፊ-መተሐራ ድረስ ያለው እንቅስቃሴ ፍጹም ሰላማዊ ነው፤ በቀንም ሆነ በሌሊት የሚደረግ ጉዞ የሚከናወነው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው ብለዋል።

ከአቶ መሐመድ ዓሊ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በተጠየቅ ዓምዳችን ገጽ 6 ላይ ሙሉ መረጃውን ያገኛሉ።

በሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You