
አዲስ አበባ፡– የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ማሠልጠኛ ማዕከል ዘመናዊ ሕንጻን ገንብቶ የመጀመሪያ ርክክብ ማድረጉን የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕ ራይዝ ገለጸ፡፡
የሕንፃ ግንባታው ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደረጀ ኃይለገብርኤል ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ግንባታው በ229 ሚሊዮን ብር፤ በ550 የካላንደር ቀን ተጠናቆ በተያዘለት ጊዜ የመጀመሪያ ርክክብ ተደርጓል፡፡
ሕንፃው በ1ሺ560 ካሬ ሜትር ስፍራ ላይ ያረፈ ባለ ሦስት ወለል መሆኑን ኢንጂነሩ ጠቅሰው፤ የሰላም ማስከበር ሂደትን ለማሳለጥ ወደ ማዕከሉ ለሚመጡ አሠልጣኝ ባለሙያዎች እና ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟላ አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የሕንጻው የአርቴክት ውበቱ፣ የመማሪያ ክፍሎቹ፤ የስብሰባ አዳራሾች እንዲሁም ቤተ መጻሕፍቱ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቁ፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ናቸው።
ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ማስረከብ የተቻለው በርካታ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ በማድረጋቸው ነው ያሉት ኢንጂነር ደረጀ፤ የሰላም ማስከበር ማዕከል አዛዥ እና የበላይ ኃላፊዎች በቅርበት እየተከታተሉ አስፈላጊ እገዛ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን የሠራው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅትም ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን ተወጥቷል፤ በተለይም የግንባታ ግብዓት በማቅረብ ሂደት የመከላከያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት ከፍተኛውን ድርሻ መወጣቱን አመልክተዋል፡፡
የግንባታ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለበርካታ ዜጎች የቋሚ፣ የኮንትራት እና የጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን፤ በግንባታው የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡
ሕንጻው ለመማር ማስተማር እና ለምርምር የሚረዱ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እና የቢሮ መገልገያ ዕቃዎችን ተሟልተውለት በቅርብ የሥልጠና አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ጠቁመዋል።
በስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም