ሰውነት የአምላክ መልክና አምሳል ነው። በመጀመሪያ እግዚአብሄር ሰውን ለመፍጠር ሲነሳ ራሱን ነው የተጠቀመው። የራሱን መልክና አምሳል አርዐያም ነው የወሰደው። ‹ሰውን በአርያና በአምሳላችን እንፍጠር› ሲል። ሰው የፈጣሪ ቤተ መቅደስ ነው። በሀጢዐት ሊረክስ፣ በበደል ሊቆሽሽ አልተፈጠረም። ከዚህ እውነት በመነሳት የሰውነትን ባህሪያት መረዳት እንችላለን ብዬ አስባለው። ሰው ራሱን በሀጢዐት፣ በበደል፣ በነውር ዝቅ እስካላደረገ፤ ሰው ራሱን በክፋት፣ በጭካኔ፣ በመጥፎ ግብር እስካላረከሰ ድረስ አፈጣጠሩ አስደናቂ ነው። ማንነታችን ይሄ ሆኖ ሳለ እኛ ግን ከዚህ ድንቅ ተፈጥሮአችን በተቃራኒ የቆምን ነን። ዘፍጥረት ላይ እግዚአብሄር አምላክ ሰውን በመፍጠሩ የተጸጸተበት ታሪክ አለ።
ይሄ ብቻ አይደለም ሰው ልቡ ክፉና የማይመረመር እንደሆነ ይሄው ምዕራፍ ይናገራል። ይሄን ሁሉ ትተን ኖህና ቤተሰቡ ብቻ የዳኑበትን የጥፋት ዘመን ብናይ በሰው ልጅ ክፋት የመጣ እንደሆነ እንደርስበታለን። ሌላም ሳይንሳዊ እውነት ..አለም ላይ ካሉ አስር እጅግ አደገኛ እንስሳት ውስጥ ቁጥር አንድ ደረጃን የያዘው ሰው ነው። እንግዲህ አስቡት ለክብርና ለሞገስ ተፈጥሮ ሰው አለም ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ በክፋቱ ቀዳሚ ሲሆን። አስቡት ከየትኛውም ፍጥረት ተለይቶ በፈጣሪ አምሳል ተፈጥሮ አውሬነትን ተላብሶ ሲኖር። የሚያስብበት አእምሮ፣ የሚረዳበት ልቦና ተሰጥቶት የሀጢዐት አለቃ ሲሆን።
የአፈጣጠራችን ታሪክ የሚነግረን በጎ አስበን፣ በጎ አድርገን በጎውን እግዚአብሄርን እንድንመስል ነው። ጽድቅ ሰርተን፣ ጽድቅ አውርተን የክብር መንግስት እንድንወርስ ነው። ሰው የሆነው ለሰው ልጅ ሁሉ አስፈላጊዎች እንድንሆን ነው። ሰው የሆነው እንድንራራና እንድናዝን ነው። በእጃችን ሰይፍ እንድንጨብጥ አልተፈጠርን። በእጃችን ደም እንድናፈስ፣ በእጃችን ንጹሀንን እንድንበድል ሰው አልሆንም። በስልጣናችን ሌሎችን እንድናስጨንቅ አልተፈቀደልንም። እንድንበቀልና እንድንፈርድ አልተፈጠርንም። በቀልና ፍርድ የአምላክ ነው።
በታላቁ መጽሀፍ ኤፌሶን 2 ከቁጥር 10 ላይ ስለ ሰውነት የተነገረ አንድ ጥቅስ አለ እንዲህ ይላል ‹መልካሙን ስራ እንድንሰራ በክርስቶስ እየሱስ ተፈጠርን› ይላል። በቃ ሰውነት ይሄ ነው። እኛ ሰው የሆነው በበጎ ሀሳብ በጎ ነገር ለመስራት ብቻ ነው። ስለዚህም ራሳችንን መረዳት ይኖርብናል። ለምን ሰው እንደሆንን፣ ፈጣሪ ለምን እኛን በአርዐያና በአምሳሉ አልቆ እንደፈጠረን መመርመር ይኖርብናል። ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ‹ያልተመረመረ ህይወት ዋጋ የለውም› ይላል እውነት ነው ያልተመረመረ ህይወት ዋጋ የለውም። ራሳችንን መመርመር አለብን። ሀሳባችንን ተግባራችንን መፈተሸ ይኖርብናል።
አሁን ላይ በሰውነታችን እያደረግናቸው ያሉ ነገሮች እኛንም ሆነ ሌሎችን የሚጎዱ ናቸው። አገራችን ላይ የተፈጠሩ አብዛኞቹ መጥፎ ታሪኮች በሰው ልጅ መጥፎ ሀሳብ የተፈጠሩ ናቸው። አሁንም እንኳን ሀሳቦቻችንን መግታት አቅቶን ችግር እየፈጠርን ነው። ሰው ሰውነቱን ሲረዳ በብሄር አይባላም። የኔነት ስሜት አይገዛውም። በዘርና በቀለም አይገፋፋም። ምክንያቱም ይሄ አለም የእኛ አይደለምና። ሰው ሰውነቱን ሲረዳ ሌሎችን ማፍቀር ነው የሚጀምረው። ሰው ሰውነቱን ሲረዳ ጥልና መገፋፋት ሰይጣናዊ እንደሆኑ ነው የሚረዳው። ሰው ሰውነቱን ሲረዳ ተነጋግሮ መግባባትን ነው የሚያስቀድመው። ምክንያቱም ከአምላክ የተማረው ይሄ ነውና። ሰው ሰውነቱን ሲረዳ ለበቀል ድንጋይ አያነሳም፣ ሰይፍ አይመዝም። ሰው ሰውነቱን ሲረዳ ለመገፋፋት አይፈጥንም፣ ለሀጢዐት አይቸኩልም ምክንያቱም የዐጢዐት ደሞዝ ሞት ነውና። ሰው ሰውነቱን ሲረዳ የኔ የሚለው አንዳች ያጣል፣ በብሄርና በጎሳ አይባላም። በቦታና በአካባቢ አይጣላም ምክንያቱም አገሩ በሰማይ እንደሆነ ነው የሚረዳው። መጽሀፍ ቅዱስም አገራችን በሰማይ ነው ይላልና።
ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ሁሉም በሚረዳው ቀላል ቋንቋ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚነኩ በሀሳብ የገዘፉ ግጥሞችን በመጻፍ ይታወቃሉ። ሰውነቱ የጠፋበትን መደዴ ገላ ሸንቆጥ ለማድረግ እንዲሁም ደግሞ ከኩነኔ ጽድቅ፣ ከክፋት ደግነት እጅጉን የሚልቁበትን መንገድ ለማሳየት ‹ጽድቅና ኩነኔ ቢኖሩም ባይኖም፣ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም› ሲሉ ገጥመዋል። እውነት ነው ከክፋት ደግነት እጅጉን ይልቃል። ደግነት የመልካም ነፍሶች ህብስት ነው። በፍርድ ቀን ፈጣሪ የሰውን ልጅ የሚጠይቀው ጥያቄ ‹ምድር ላይ በሰጠሁህ እድሜ ምን በጎ ነገር ሰራህ ብሎ ነው። ፈጣሪ ፊት ስንቆም የሚሟገቱልን በጎ ስራዎቻችን ናቸው። ግንባራችን ላይ ተጽፈው ለፍርድ የሚያበቁን አሁን ላይ እያደረግናቸው ያሉ የጽድቅ ስራዎች ናቸው።
በሰጠኋችሁ እድሜ፣ በሰጠኋችሁ ሰውነት፣ በሰጠኋችሁ ህሊና ምን አደረጋችሁበት ተብለን ስንጠየቅ ሞገስ የሚሆኑን ዛሬ እያደረግናቸው ያሉ በጎ ስራዎች ናቸው። በሰጠኋችሁ እውቀት፣ በሰጠኋችሁ ስልጣን ምን አደረጋችሁበት ተብለን ስንጠየቅ መልስ የሚሆኑን ስራዎቻችን ናቸው። በፍርድ ቀን የምንዋረደውም ሆነ የምንከብረው በሀሳባችን በጉል በሚወጣው ድርጊት ነው። ዛሬ የነገ ቅርስ ነው። የሁላችንም ነገ የሚሰራው በዛሬ ሀሳብና ድርጊት ነው። ሰው በሀሳቡ መልካም ሲሆን በድርጊቱም መልካም ነው የሚሆነው። ድርጊት ህይወት ነው። በህይወታችን ላይ የሚንጸባረቁ እኩይም ይሁኑ በጎ ልማዶቻችን በሀሳብና በድርጊታችን የጸነስናቸው ናቸው።
ሰው በጎ ሲሆን ሰይጣንን ነው የሚያሳፍረው መጥፎ ሲሆን ደግሞ አምላኩን። አምላክ ያፍራል እኮ..የፈጠረን እኛ ህግና ትዕዛዙን ሽረን አውሬ ስንሆንበት ያፍራል። በዚያው ልክ ደግሞ ሰው ፈጣሪውን ማሳቅ ይችላል። አምላክ የሚስቀው በእኛ በጎነት ነው። በዙሪያችን ድሆችን ስንረዳ፣ መከረኞችን ስንታደግ እግዜር ይስቃል። ለበደሉን ይቅርታ ስናደርግ፣ ለጠሉን ትዕግስትን ስናበዛ ሰይጣን ያፍራል እግዜር ይከብራል። በእኛ ክፋት ክብር የሚያገኘው ሰይጣን ብቻ ነው። ሰው በሀሳቡና በድርጊቱ መጥፎ ሲሆን አጋንትን ነው የሚያስደስተው። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እየሰራነው ካለው ስህተት መለየት ይኖርብናል።
በዙሪያችን የእኛን በጎ መሆን የሚሹ በርካታ ነፍሶች አሉ። በዙሪያችን የእኛን እጅ፣ የእኛን እውቀት፣ የእኛን ራሮት የሚሹ እልፍ ሰውነቶች አሉ። አገራችን ያለችበት ሁኔታ ይታወቃል። ብዙ የተፈናቀሉ፣ ብዙ የተጎዱ፣ ብዙ የተራቡ ዜጎች አሉን። ብዙ የታረዙ፣ ብዙ ያዘኑ፣ ብዙ የታመሙ ዜጎች አሉን ለነሱ እንድረስላቸው። መማር እየፈለጉ ግን ደግሞ በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት ያጡ አሉ ለነሱ ትምህርት ቤት እንገንባላቸው። ንጹህ ውሀ የሌላቸው፣ ጤና ጣቢያና የህክምና ቁሳቁሶች ያጡ ሆስፒታሎች አሉ እነሱን እንያቸው። ደግ መሆን ከቻልን ደግ ልንሆንባቸው የሚችሉ በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ድሀ አገርና ድሀ ህዝብ መሀል እየኖርን የእኛ በጎ መሆን ማለት ዋጋው በምንም የማይተመን ነው።
አሁን ላይ በረከቶቻችንን እያራቅን ያለነው ራሳችን ነን። እንደ ዜጋ ጥሩ ብናስብና ጥሩ ብንሰራ ድህነታችን በዚህ ልክ ዘልቆ ባልተሰማን ነበር። እንደ መንግስት፣ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ጥሩ ብናስብና፣ ጥሩ ብንሰራ ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የሚተርፍ የሰላምና የአንድነት ምኩራብ እንገነባ ነበር። አሁን ላይ ከሰውነት የወጣን ብዙዎች ነን። በሰውነት ጭንብል አውሬ ሆነን የምንኖር ሞልተናል። አገር ሰው ነው የሚያስፈልጋት። አገር አስታራቂ፣ ይቅር ባይ ነው የሚያስፈልጋት። አገር እግዚአብሄርን የሚፈራ ትውልድ ነው የሚያስፈልጋት።
አገር ነውር የሚያውቅ፣ የአባቶቹን ስርዐት የሚያከብር ዜጋ ነው የሚያስፈልጋት። በዚህ እውነት ውስጥ ራሳችንን እስካልገነባን ድረስ በተላበስነው የአውሬነት ባህሪያት የባሰ እንጂ የተሻለ ለውጥ አናመጣም። ለራሳችን ስንል ሰው መሆን አለብን። አገራችን አሁን ሰው ነው የሚያስፈልጋት። ሰው ስላችሁ ጭንብል ለባሹን ማለቴ አይደለም። የበግ ለምድ ለብሶ እንደ ተኩላ የሚንቀሳቀሰውን ማለቴ አይደለም። በሀሳቡ አገር የሚፈጥረውን፣ በተግባሩ ትውልድ የሚቀርጸውን እሱን ማለቴ ነው። እውቀትና በምክንያታዊነት የሚራመደውን ማለቴ ነው።
ብዙዎቻችን የሚጠቅመን እያለ የማይጠቅመንን የምናደርግ ነን። ዛሬ የምንሳራቸው ክፉ ነገሮች ሁሉ የነገ መንገዳችንን በእሾህ ከማጠር ባለፈ የሚጠቅሙን አይደሉም። ዛሬ ላይ በክፋት የዘራናቸው ቡቃያዎች ነገ ላይ ዛፍ ሆነው እኛ ላይ ነው የሚወድቁት። ዛሬ ላይ በጥላቻ ያሳደግናቸው ችግኞች ነገ ላይ የሞት ፍሬ ነው የሚያበቅሉት። ዛሬ ላይ ተንከባክበን የያዝናቸው የብሄርና የእኔነት ስሜቶች ነገ ላይ ይዘውን የሚጠፉ ናቸው። የመበላሸትም የመስተካከልም ነጻ ፍቃድ አለን። ታዲያ ሰው መሆን ለምን አቃተን? ራሳችንን መጠበቅ ካልቻልን አለም የውበቷን ያክል ሊያቆሹሹን የሚችሉ በርካታ ጉድፎች አሏት።
የገዛ ሰውነታችን በፈጠራቸው አለማዊ ሀጢዐቶች ተከበን የምንኖር ነን። አሁናችን ውስጥ ብዙ ነገር አለ። እየመረጥን መስማት፣ እየመረጥን ማየት፣ እየመረጥን ማሰብ የእኛ ፈንታ ነው። ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ ሰውን ያቆሸሸው ሀሳቡና ምግባሩ ናቸው። ምድርን ገሀነም ያደረጋት የሰው ልጅ የተዛባ አመለካከት ነው። አጢነን ካየንው ሁሉም ነገር በተፈጥሮው ውብና ማራኪ ነው። የሰው ልጅ ክፋት፣ የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት ግን ይሄን የተፈጥሮ መልክ አወየበው። ሰው ለክብር ተፈጥሮ ለመከራ መኖሩ ይገርመኛል። ለከፍታ ተፈጥሮ ዝቅታን መምረጡ ያስደንቃል።
አለም በሰው ልጅ የተሰቃየችውን ያክል በምንም ተሰቃይታ አታውቅም። ተፈጥሮ በሰው ልጅ የተበላሸችውን ያክል በምንም ተበላሽታ አታውቅም። የሰው ልጅ በራሱ የሰው ልጅ የተጎሳቆለውን ያክል በምንም ተጎሳቁሎ አያውቅም። አብዛኛው የሰው ልጅ መከራ ራስ ወዳድነት የፈጠረው ነው። ከእግዚአብሄር መራቅ የፈጠረው ነው። በአገራችን እየሆነ ያለውም ይሄን እውነት የሚያስረግጥ ነው። አገራችን በራስ ወዳዶች ስትሰቃይ ኖራለች አሁንም እየተሰቃየች ነው። ህዝባችን በራስ ወዳዶች ሀሳብና ምኞት ሲጎሳቆል ነበር አሁንም እየተጎሳቆለ ነው።
አልታወቀንም እንጂ ማንም ሳይደርስብን፣ ማንም ሳይነካን ራሳችንን በራሳችን እየጎዳን ነው። አልገባንም እንጂ ራሳችን ለራሳችን መከራ ሆነን እየኖርን ነው። አልተረዳንም እንጂ የራሳችን ጠላቶች ራሳችን ነን። ከማንም ባልሆነ ከእኛው በሆነ ሀሳብና ድርጊት እየተሰቃየን ነው ያለነው። ሰው የራሱ ጠላት ሲሆን አደገኛ ነው። ሰው የራሱ ጠላት ሲሆን በራሱ ላይ የእሳት ፍም ነው የሚቆልለው። እኛም አሁን የራሳችን ጠላቶች ነን። በዘመነ ሀሳብ፣ በእግዚአብሄራዊ ሰውነት ነውሮቻችንን እስካላጸዳን ድረስ ሁሌም የብሄር፣ ሁሌም የእኔነት በሽተኞች ነው የምንሆነው። ሁሉም የጥላቻ፣ ሁሌም የመገፋፋት ህመምተኞች ነው የሚወጣን። ሁሌም የሀጢዐት፣ ሁሌም የማነስ መንፈስ ነው የሚጎበኘን። ሰው እንሁን..በፈጠርናቸው ችግሮች አንነስ። የፈጠርናቸው ነውሮች አያጥፉን።
ሰው ነን አይደል? በፈጣሪ አርዐያና አምሳል ተፈጥረናል አይደል? እናንተ የእግዚአብሄር ቤተ መቅደሶች ናችሁ ተብለናል አይደል? የሚያስብ አእምሮ ተሰጥቶናል አይደል? እኔን ምሰሉ ሲል ህያው ቃሉ ነግሮናል አይደል? የሀጢዐት ደሞዙ ሞት እንደሆነ እናውቃለን አይደል? በጎነት የህይወት አክሊል እንደሆነ ይሄንንም እናውቃለን አይደል? ታዲያ ሰው መሆን ለምን አቃተን? ‹ቀኑን ሙሉ እግዚአብሄርን በመፍራት እንኑር› ምሳ 23፥17
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2014