የፊታችን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2011 ዓ.ም፤ ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡበትን የአንድ ዓመት የልደት ሻማ ይለኩሳሉ። 180 አባላት ያሉት የኢህአዴግ ምክር ቤት መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም እልህ አስጨራሽ የውስጥ ፍልሚያ በኋላ ከምሽቱ 4፡50 ሰዓት ገደማ በሰጠው መግለጫ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ዓሊን በሊቀመንበርነት መምረጡን ይፋ አደረገ። ዶ/ር ዐብይ ወደፊት እንዲሳቡ የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰዱት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ነበሩ።
የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም በጻፉት ድንገተኛ መልቀቂያቸው ላይ ከተጋጋለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ «የመፍትሔው አካል መሆን አለብኝ» በሚል ራሳቸውን ከፓርቲና ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ማሰናበታቸውን ማሳወቃቸው በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ማማው ሊገፈተር ቋፍ ላይ ለነበረው ለኢህአዴግም ጭምር ትልቅ ውለታ ነበር።
አቶ ኃይለማርያም ይህን ወሳኝ እርምጃ ባይወስዱ ኖሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የወደቀችው አገራችን መጻኢ ዕጣ ፈንታዋ ምን ሊሆን ይችል እንደነበር ማንም መገመት የሚችለው አልነበረም። አቶ ኃይለማርያም በዚያች ታሪካዊ ውሳኔቸው እነዶ/ር ዐብይ ወደፊት እንዲመጡ ብቻም ሳይሆን በአንጻራዊነት ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲካሄድ በተጫወቱት ቁልፍ ሚናም አንዘነጋቸውም። እናም የመጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ቀጣዩን የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ማንነት ያስተዋወቀን ታሪካዊ ዕለትም በመሆን ይታወሳል።
ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር በሆኑ በሳምንቱ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ሹመታቸው ከጸደቀ በኋላ ቃለመሃላ ፈጸሙ። በዕለቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረጉት ንግግር መሳጭና ሕዝቡን ከዳር እስከዳር ለድጋፍ ያነቃነቀ ነበር። የዶ/ር ዐብይን ቃል የሰሙ ሁሉ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ተስፋ አደረጉ። አገሪቱም አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት ታየባት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ተነሳ። ዶ/ር ዐብይ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ያደረጉት ንግግር የሚረሳ ባይሆንም እንኳር ነጥቦቹን ደግሞ ማስታወስ ተገቢ ነው።
«ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደ እና የተዋሃደ ነው፣አማራው በካራ -ማራ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራ-ማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤኒሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያው እና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ ሀገር እንሆናለን። የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን። – ኢትዮጵያ የሁላችን አገር፣ የሁላችን ቤት ናት፤ በአንድ አገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሀሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመስርተን መግባባት ስንችል የሀሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሀሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሄ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም…»
አዎ! ሕዝቡ ነጋ ጠባ ዐብይ፣ ዐብይ አለ። የለውጡ ሐዋርያ ለማ መገርሳንም አልረሳም። ስማቸውን ከፍ አድርጎ አመሰገነ፣ አጀገናቸው፣ ተመካባቸው። ነፍጥ ያነሱ የተቃውሞ ኃይላት ጭምር እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ የዶ/ር ዐብይን የሠላም ጥሪ ያለአንዳች ማወላወል ተቀበሉ። አንዳንዶቹም በፍጥነት ሻንጣቸውን ሸክፈው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የቃሉን እውነታ በገቢር አረጋገጡ። እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያሉ ጎምቱና ቀንደኛ የገዥው ፓርቲ ተቀናቃኝና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሳይቀሩ በእነዶ/ር ዐብይ አህመድ ቃል ተማረኩ። በወቅቱ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ስለዶ/ር ዐብይ እንዲህ አሉ።
«ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ብቻ ሳይሆን ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ በግሉ በነጻነት አስቦ በሀገር ጉዳይ ቁምነገሮች ላይ እንደ ዐብይ አዲስ ነገርና የአስተሳሰብ እንከን የሌለበት ነገር ሲናገሩ አልሰማሁም፤ እኔ የሰማኋቸው ቅንጭብጭቦች የዐቢይ ንግግሮች በሙሉ ሰውዬው የማሰብ ችሎታው የጠራ እንደሆነ ያረጋግጡልኛል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ እንዲህ ያለ ባለሥልጣን ሰምቼ አላውቅም…» ዶ/ር ዐብይ በተሾሙ የመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት እንደተአምር ሊነገሩ የሚችሉ ሥራዎችን ያከናወኑበት ነበር። «የፖለቲካ እስረኛ የለም» ሲባል በኖረበት አገር ከሰባት ሺ በላይ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ አደረጉ።
በተለይ የሞት ፍርድ የሚጠባበቁትና ከየመን ታግተው ለእስር የበቁት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት ዓለምን ጭምር ያስደነቀ ነበር። ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የሆኑ እስረኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት… እየተባሉ ወደማጎሪያ ሲጋዙ የኖሩ ዜጎች ከሁሉም ክልሎች ተፈትተው የነጻነት አየር ለመተንፈስ በቁ። በተለይ የርስ በርስ ሽኩቻና ግጭቶችን በይፋ በማውገዝ ከመከፋፈልና ልዩነት ይልቅ «መደመር» በሚል የሚታወቁበት አብሮነት ቃል ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ሠላምና ኢትዮጵያዊ አንድነት ጥሪያቸው የህዝቡን ቀልብ መሳብ ቻሉ። ሌላው በህዝብ ላይ ላለፉት 27 ዓመታት በደል ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙ የነበሩ አመራሮችን ከሥልጣን ለማሰናበት መድፈራቸውም በሕዝብ ዘንድ ከበሬታን አትርፎላቸዋል።
በውጭ አገር የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች አገር ቤት ገብተው ሠላማዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ በቀረበው ጥሪ መሠረት ከ40 ዓመት በላይ መግባት የተከለከሉ ድርጅቶች መግባት ቻሉ። የተዘጉ ድረገጾች እና መገናኛ ብዙሃን እንዲሁ ተለቀቁ። አዳዲስ የፕሬስ ውጤቶችም ማቆጥቆጥ ጀመሩ። በአገራችን በዛ ያለ ተከታይ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ እና የአሜሪካ ሁለት የተለያዩ ሲኖዶሶች መካከል ለረዥም ዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት በእርቅ እንዲደመደም ሆነ። በተመሳሳይ ሁኔታ በመጅሊስ እና በእስልምና መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መሀል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በእርቅ እና በውይይት በመፍታት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ወደ ፍቅር እና አንድነት እንዲመጣ መንገዱን ጠረጉ።
ላለፉት 18 ዓመታት ሻክሮ የነበረውን እና በኢትዮጵያ ታሪክ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ያለቁበት አስከፊ ደም አፋሳሽ ጦርነት የተካሄደበት፣ የኢትዮጵያና ኤርትራ ሠላም አልባ፣ ጦርነት አልባ የሚባል ግንኙነት እልባት እንዲያገኝ የወሰዱት የሠላም ርምጃ ህዝቡን ካስደሰቱት መካከል ዋነኞቹ ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ እየወሰዷቸው ካሉ በጎ ርምጃዎች በተጨማሪ የዴሞክራሲ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ በተግባር እንደሚረጋገጥ፣ በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ማንም ኢትዮጵያዊ አሳዳጅና ተሰዳጅ እንደማይኖር፣ የዜጎች እኩልነት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የፕሬስ ነፃነት፣ በነፃነት የመሰብሰብና የመደራጀት እንዲሁም የዴሞክራሲ መብቶች እንደሚያረጋገጡ ቃል በመግባት ተግባራዊ ርምጃዎችን መውሰድ መጀመራቸው ህዝቡን አስደሰተ።
ባለፉት ዓመታት ችግር ፀንቶባቸው የነበሩ አካባቢዎችን ቅድሚያ በመስጠት ህዝቡን ለማወያየት ባለፉት እረፍት የለሽ ጉዞዎችን አድርገዋል። በዚህም በደረሱበት ሁሉ የአካባቢውን ቋንቋና ባህል በማንጸባረቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሪ መሆናቸውን በተግባር ለማሳየት ያደረጉት ጥረት ከሕዝብ ጋር ይበልጥ አቆራኝቷቸዋል። ሕዝቡም ይህን ከእነዶ/ር ዐብይ የተሰጠውን ቃል ተማምኖ ለውጡ ግለቱን እንደጠበቀ እንዲጓዝ በማሰብ በተመረጡ በ82 ኛ ቀናቸው ላይ ድብልቅልቅ ያለ የድጋፍ ሰልፍ ወጣ።
ቅዳሜ፤ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም «ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ» በሚል መሪ ቃል በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን መደገፍ እና ማመስገን ዓላማው ያደረገ ሰልፍ ተካሄደ። ሰልፉን ከሌሎች ሰልፎች በጣሙኑ የሚለየው በበጎ ፈቃድና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ የማህበራዊ ድረገጽ አክቲቭስቶች አስተባባሪነት የተጠራና የተካሄደ መሆኑ ነው። በብዙዎች ግምት ከሶስት ሚሊየን ያላነሰ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪ አደባባይ ወጣ። ሰልፉ እየተካሄደ ባለበት ሰዓት ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያነጣጠረ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙ የማይረሳ አሳዛኝ ጠባሳ ጥሎ አለፈ።
ከ135 በላይ ንጹሃን ሰዎች ተጎዱ፣ ሁለት ግለሰቦችም መሞታቸው ተነገረ። ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ ዘጠኝ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረቦችና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ። ሰልፉ ይህን አሳዛኝና አስነዋሪ የሽብር ክስተት አስተናግዶም ሕዝብ መሪውን በአደባባይ ያመሰገነበት፣ ያከበረበት ዕለት ሆኖ በታሪክ ተመዘገበ። እነዶ/ር ዐብይ አህመድ በምርጫ ካርድ ከመመረጥ ያልተናነሰ የሕዝብ ይሁንታን ማግኘታቸው ለቀጣይ ሥራቸው ትልቅ ስንቅ ነበር። ሰልፉ በአዲስ አበባ ብቻ አልቆመም። በተመሳሳይ ሁኔታ በጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ፣ ዱራሜ ከተሞች… የድጋፍ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን፤ እሁድ ሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ በድሬዳዋ፣ ሰመራ፣ አሳይታ እና ጅግጅጋ ከተሞች…ለውጡንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን አካሄድ የሚደግፉ ሰልፎች ተከናውነዋል።
እሾህና ጋሬጣ የበዛበት የለውጥ ጉዞ
አንዳንድ ምሁራን የዶ/ር ዐብይ አህመድ የለውጥ ሒደት በውስጥ በውጪም የሚቃወሙ ኃይሎች መኖራቸው የመጀመሪያው ተግዳሮት ነው ይላሉ። በኢህአዴግ ውስጥ ለለውጥ ሒደቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ደንቃራ የሆኑ አባል ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ከመኖር አልፎ በፍርድ ቤት ማዘዣ ጭምር የወጣባቸውን የወንጀል ተጠርጣሪ ግለሰቦች አሳልፎ ለመስጠት ያለመተባበር ሁኔታ ያሳዩ አባል ድርጅቶች መኖራቸው ምናልባትም ለኢህአዴግ ቀጣይ ሕልውና ጭምር ትልቅ ተግዳሮት አድርገው የሚያዩ ብዙ ናቸው።
ሌላው ትልቁ የአክራሪ ብሔርተኝነት፣ የአስተዳደር ይገባኛል እና የወሰን ማካለል ጥያቄ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጭምር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተደግፎ በስፋት እየተንጸባረቀ፣ እየተስፋፋ የመምጣት ጉዳይ ነው። ይህ መሆኑ እዚህም እዚያም ትንንሽ ጉልበተኞች እንዲቀፈቀፉ ረድቷል። ጥቂት የማይባሉ መገናኛ ብዙሃን (በተለይ ማህበራዊ ድረገ ጾች ) የከፋፋይ አጀንዳ ቀራጭና አራጋቢ ሆኑ። በማህበራዊ ሚዲያዎች የሽብርና የጥላቻ ንግግሮች በተደራጁ ቡድኖችና ራሳቸውን የአንድ ብሔር ጠበቃና ተቆርቋሪ አድርገው ባስቀመጡ ግለሰቦች የሚሰራጩበት ሁኔታ እያደገ መጣ። የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ውስጣቸው የአክራሪ ብሔርተኝነት ዝንባሌ አጥብቀው ባለመዋጋታቸው ምክንያት «የእኔ ነው፣ የእኛ ነው» ጨዋታ ውስጥ ለገቡ ቡድኖችና ግለሰቦች ምቹ ምሽግ ሆኑ። በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም መጨረሻ በሐዋሳ የተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ ይህንኑ ችግር ገምግሞ ተከታዩን አቋም ወስዶ ነበር።
«የፌዴራል ሥርዓት ግንባታችን በጅምር ደረጃ ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን የወሰን አከላለል ጥያቄዎች፣ ማንነትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች፣ የዜጐች ሞትና መፈናቀል፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ በነፃነት የመሥራት ህገ መንግስታዊ መብት ጥሰቶች ይስተዋላሉ። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ከሥር መሠረታቸው መነቀል የሚገባቸው በመሆናቸው የማንነትም ይሁን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች የሚመለከታቸውን ህዝቦች ነፃ ፍላጐት ከግምት ውስጥ ባስገባ፣ በህገመንግስታዊ እና ዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፈቱ፣ የዜጐች የትም ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር፣ የመስራት፣ በቋንቋቸው የመማር፣ የመዳኘት፣ ወግና ባህላቸውን የማሳደግ፣ ተገቢውን ዕውቅናና ውክልና የማግኘት፣ ሀብት የማፍራት፣ ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው እንዲከበር እንዲሁም ብሄራዊ ማንነት እና ሀገራዊ አንድነት ሳይነጣጠሉ እንዲጐለብቱ አበክረን እንሰራለን…»
ይህም ሆኖ ባለፉት ስድስት ወራት በአባል ድርጅቶቹ መካከል ያለው አንድነት ጎልብቶ መታየት አልቻለም። እርስ በርስ መጠራጠሩ፣ መካሰሱ፣ እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ መባባሉ ከኢህአዴግ የቆየ ባህል ባፈነገጠ መልኩ መቀጠሉ ለብዙዎች ግራ አጋቢ ሆኗል። ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአማራ፣ በደቡብ…የታዩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች መንስኤ በአመዛኙ ከአክራሪ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ መንሰራፋት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው። በዚህም ምክንያት ወደ ሶስት ሚሊየን የሚገመት ሕዝብ ከቤት ንብረት ለመፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ለአብነት ያህል ጥቂት ማሳያዎችን ብቻ አለፍ አለፍ ብለን እናስታውሳለን።
ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም፤ ደብረማርቆስ ከተማ
በዕለቱ ጠዋት ረፋዱ ላይ በደብረማርቆስ ከተማ በድንገት ግርግር ተነሳ። የግርግሩ መነሻ ምክንያት ደግሞ የቀድሞ የአዴፓ/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አባል የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን በጎዛምን ሆቴል ታይተዋል መባሉ ነው። በሆቴሉ አቅራቢያ ሰዎች መሰባሰብና ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ። የሰው ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ «አቶ በረከት ከሆቴሉ ይውጣ» የሚሉ ጥያቄዎች ጉልበት አገኙ። የሆቴሉ ባለቤትና ሠራተኞች የተባሉት ግለሰብ በሆቴሉ ውስጥ አለመኖራቸውንና ይህንንም ለማረጋገጥ ተወካዮች ገብተው እንዲያዩ ተማጸኑ። የሰማ ግን አልነበረም። ወዲያውኑ የአቶ በረከት ናት የተባለች አንድ የመስክ ተሽከርካሪ በቆመችበት እሳት ተለቀቀባት። ጎዛምን ሆቴልም በድንጋይ ተወገረ።
ውሎ አድሮ እውነቱ ሲገለጥ ግን የተቃጠለችው ተሽከርካሪ ንብረትነቷ የጣና በለስ ፕሮጀክት የነበረ ሲሆን በዕለቱ አቶ በረከትም አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ቁጭ ብለው የመንጋውን ፍርድ ይከታተሉ እንደነበር መታወቁ ነው።
ነሐሴ 6/2010፤ ሻሸመኔ
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የልዑካን ቡድንን ለመቀበል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሻሸመኔና አካባቢዋ ነዋሪዎች አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ግርግር የአራት ሰዎች ሕይወት አልፏል። አንድን ግለሰብ በድብደባ ህይወቱ ካለፈ በኋላ ቁልቁል ተሰቅሎ የሚታይበት ፎቶግራፍ በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱ ኢትዮጵያውያንን አሳዝኗል፣ አስቆጥቷል። አንድ ወጣት «ቦምብ ይዟል» በሚል ያልተጣራ መረጃ በመንጋ ፍርድ ተደብድቦ በግፍ ከተገደለ በኋላ እንዲሰቀል መደረጉን፤ በኋላም አስከሬኑን በመኪና ለመጎተት ሙከራ መደረጉ ኢ-ሰብዓዊነት የደረሰበትን ጫፍ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ክስተት ነበር ። በአሰቃቂ ግድያው ጋር በተያያዘ ክስ ከቀረበባቸው ስድስት ሰዎች መካከል ሁለቱ የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው፣ የተቀሩት አራት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ምስክሩ በአድራሻው ተፈልጎ ጭምር ባለመገኘቱ ምክንያት በነጻ መለቀቃቸውን፣ ዐቃቤ ሕግ ግን በተለቀቁት ግለሰቦች ጉዳይ ይግባኝ መጠየቁን የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮን ጠቅሶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሰሞኑን መዘገቡ የሚታወስ ነው።
የቡራዩ ግጭት
መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም ለኦነግ አመራሮች በመስቀል አደባባይ ደማቅ አቀባበል ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር። ከዚህ ፕሮግራም መልስ በቡራዩ ያልታሰበ ግጭት ተቀሰቀሰ። ንጹህ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ግፍ በተለያዩ ቦታዎች ከባድ ቁጣን የቀሰቀሰ ነበር። በወቅቱ 15 ሺህ 86 ዜጎች በግጭቱ መፈናቀላቸው፣ በጥቅሉ በቡራዩና በሌሎች አካባቢዎች በዕለቱ ከ23 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን መዘገቡ የሚታወስ ነው። ሰኞ መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዙሪያ የተፈጸመውን ጥቃት በመቃወም ለተቃውሞ ሰልፍ በርካቶች አደባባይ ወጡ። ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው የአምስት ሰዎች ህይወት አለፈ። ብዙ ወጣቶችም በወቅቱ ለእስር ተዳረጉ።
በአጠቃላይ፤ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ከተሞች፣ በኦሮሚያና በአፋር፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በአማራ እና በትግራይ አዋሳኝ ድንበሮች… ሞቅ በረድ በሚሉ ግጭቶች መታመሱን ቀጥሏል። ቀውሱ ሰዎችን ለሞትና ለመፈናቀል አደጋ ዳርጓል። በእነዚህ አካባቢዊ ግጭቶች ጋር በተያያዘ በአገራችን በአጠቃላይ ከሶስት ሚሊየን ያላነሰ ተፈናቃይ ወገን የዕለት ዕርዳታ ጠባቂ ወደመሆን ተሸጋግሯል።
ለእነዚህ ወገኖች የእለት ጉርስ ለማቅረብና ለማቋቋም የሚወጡ ወጪዎች፣ የሚጠፋ ጊዜ፤ የለውጥ አመራሩ በሙሉ አቅሙ ፊቱን ወደኢኮኖሚ ዘርፉ እንዳያዞር እንቅፋት ሆነውበታል። በዚህም ምክንያት የውጪ ምንዛሪ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል። የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ለጥሬ ዕቃ ግዥ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ለወራት እጃቸውን አጣጥፈው እንዲጠብቁ ተገድደዋል። አገራዊ ምርታማነትም አሽቆልቁሏል። የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ከተወሰደው እርምጃ ጋር በተያያዘ የዋጋ ግሽበት ንሯል። የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቷል። ከዚህ ቀውስ መውጫ ስትራቴጂ የሚያስፈልገን ወቅት ላይ ቆመናል።
እንደመውጫ
ጹሑፌን ለመቋጨት ስውተረተር፤ ዶ/ር ዐብይ አህመድ በሳምንቱ መባቻ ላይ የማህበራዊ ሚዲያን አጠቃቀም በተመለከተ የሰጡት ምክር አዘል አስተያየት ቀልቤን ሳበኝ። መግለጫው ውስጥ እንዲህ የሚል ጠንከር ያለ መልዕክት ሰፍሯል።
“…ባለፉት ጥቂት ወራት ሀገራችን ያስመዘገበቻቸው የድል ስኬቶች በመዘርዘርና ከእነርሱም ትይዩ የገባችበትን የፖለቲካ ቀውስ ለእናንተ በማስታወስ ጊዜያችሁን ማባከን አይገባም። አሁን ያለው ትልቅ ቁምነገር ከዚህ ከገባንበት አሳሳቢ ቀውስ ራሳችንንም፣ ሀገራችንንም እንዴት እናውጣት የሚለው ነው። ሁለት የገመድ ጽንፎችን ይዘው የቆሙ ኃያላን በሚያደርጉት ጉተታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አደገኛ ውጥረት ውስጥ የከተቱበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ልበ ስውር ሆኖ ግራና ቀኝ በጥሞና ማስተዋል በተሳነው ጽንፈኛ ቡድን የሀገራችን አየር ምድሯ ሠላምና ተስፋን ከመተንፈስ ይልቅ የስጋትና የውድመት ደመናን አርግዞ የመከራ ዶፉን ሊጥል ከአናታችን በላይ መጣሁ መጣሁ ይላል። መካረር እዚህም እዚያም በርትቷል። ተፈጥሮ ነውና የተወጠረና የተካረረ ጉዳይ ቆይቶ መበጠሱ አይቀርም። የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፣ የአውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ የሚለው የሽፍቶች ፈሊጥ የሠላማዊ ዜጎች መመሪያ አይደለም። በእውነት ኢትዮጵያዊነት የሚፈተንበት ወቅት እየመጣ ነው። ማንም ጣፋጭ ዘር፣ ፍሬ ነኝ ብሎ ሊኮራና ሊመጻደቅ የሚችለው የግንዱ ሥር እስካለ ብቻ ነው።፡ የግንዱ ሥር ቆርጦና ነቅሎ በቅርንጫፉና በዘሩ መኩራት የሞኝ ጨዋታ ይሆናል…” ብለዋል።
አዎ!.. ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት የቀውስ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀናል። ራሳችንንም ሀገራችንንም ከቀውስ ለመታደግ በሀገር ባህል ወግ የሚዳኙን፣ የሚገስጹን የራሳችን ሽማግሌዎች በየአካባቢው ያስፈልጉናል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ምሁራን…ኧረ ወዴት ናችሁ?!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ፍሬው አበበ