በባለፈው ሳምንት ዝግጅታችን ወፈፌው ይልቃል አዲሴ እንደዚህ ቀደሙ በሌሊቱ ተነስቶ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ «ዋጋ እንዳንከፍል እንደማመጥ!» እያለ ሲጮህ ከአራቱም አቅጣጫ የይልቃል አዲሴን ጩኸት እንደ መጽሐፍ ለማንበብ የተሰባሰቡት የሰፈራችን እና የእድራችን ሰዎች የይልቃል እዲሴን ንግግር በጥሞና እያዳመጡ እያለ አብሿሙ ክንፈ ጉደታ የይልቃ አዲሴን ንግግር ማቋረጡን እና የአብሿሙን የክንፈ ጉደታ ጥያቄ እና የወፈፌውን ይልቃል አዲሴን ምላሽ ለቀጣይ ሳምንት ይዘን እንደምንቀርብ ቃል ገብተን ነበር።
እንደሚታወሰው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ የይልቃ አዲሴን ንግግር ያቋረጠው ይልቃል አዲሴ በዋርካው ስር የተሰበሰበውን ሰው «ኧረ ጎበዝ ! አሜሪካ እና መሰል የሰፈራችን እና የእድራችን ታሪካዊ ጠላቶች እኛን ለማባላት እና ለመብላት እየጎነጎኑት ባለው ሴራ እርስ በርስ ተባልተን ሳንጠፋ አሁኑኑ እንደማመጥ። አለበለዚያ ሰፈራችን እና እድራችን «ወደ ነበርነት» መቀየሩ የማይቀር ነው።» እያለ ባለበት ጊዜ ነበር።
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ አብሿም የተባለው ከሰፈራችን እና ከእድራችን ሰዎች አስተሳሰብ ትንሽ ወጣ እና ፈጠን ያለ ባህሪ ስላለው እንጂ የእውነት አብሾ መጠጣቱን ከሰፈራችን ይሁን ከእድራችን አባላት አንድም ያረጋገጠ ሰው የለም ። ያም ሆነ ይህ ! አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ሁለት ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ነበር የወፈፌውን ይልቃል አዲሴ ንግግር ያቋረጠው።
የአብሿሙ ክንፈ ጉደታ አንደኛው ጥያቄ የሰፈራችን እና እድራችን ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ ዐብይ ምክንያት ለይስሙላ ፊደል ቆጥረናል በሚሉ ፤ ሳያውቁ ራሳቸውን በአዋቂዎች መርከብ ያሳፈሩ አንዳንድ የእድራችን አስተዳዳሪዎች ፣ ተፎካካሪ ሃይሎች ፣ ወግ አሳላጮች እና ጡሩምባ ነፊ ሱፍ ለባሾች ነው። እነኚህ አካላት እንዴት ለሰፈራችን እና ለእድራችን ህልውና ስጋት ሊሆኑ ቻሉ? የሚል ሲሆን ፤ ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ እነኚህ አካላት ለምን መደማመጥ ተሳናቸው? የሚል ነው።
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ የይልቃል አዲሴን ንግግር ቢያቋርጠውም ይልቃል አዲሴን በአብሿሙ ክንፈ ጉደታ ሳይበሳጭ ፤ ፈገግታ ከፊቱ ላይ ሳይለየው የተጠየቀውን ጥያቄ ለመመለስ ጉሮሮውን እየጠራረገ…..ንግግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ …. እውነት ነው ! ክንፈ ጉደታ ለመጥቀስ እንደሞከረው ለሰፈራችን እና እድራችን ህልውና ሁነኛ ካንሰሮች እና መድሃኒት የሌላቸው በሽታዎች ለይስሙላ ፊደል ቆጥረናል የሚሉ ፤ ሳያውቁ ራሳቸውን በአዋቂዎች መርከብ ያሳፈሩ አንዳንድ የእድራችን አስተዳዳሪዎች ፣ ተፎካካሪ ሃይሎች ፣ ማን እንደሚከፍላቸው የማይታወቁ ወግ አሳላጮች እና ጡሩምባ ነፊ ሱፍ ለባሾች ናቸው። ሁሉም ሱፍ ለባሾች መጥፎ ናቸው ባይባልም አብዛኛዎቹ በሰፈራችን እና በእድራችን የሚገኙ ሱፍ ለባሾች ግን የንጹሃንን ደም የማፍሰስ ዛር የተዋረሳቸው ፤ የእድራችን እንዲሁም የሰፈራችን ታሪካዊ ጠላቶች በሆኑት አሜሪካ እና መሰል ሀገራት ነዋይ የተገዙ የነዋይ ሴሰኞች ናቸው ።
የሰፈራችንን እና የእድራችንን እያንዳንዷን እርምጃ የሚቆጥሩት አሜሪካ እና መሰል የእድራችን እና የሰፈራችን ታሪካዊ ጠላቶች ለይስሙላ ፊደል ቆጥረናል የሚሉ ፤ ሳያውቁ ራሳቸውን በአዋቂዎች መርከብ ያሳፈሩ ሱፍ ለባሾችን በነዋይ ገዝተው እድራችንን እና ሰፈራችንን እንደፈለጉ ማድረግ እንደሚችሉ ከተረዱ በርካታ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህን ተከትሎም የጥቁሮች ኩራት እና የነጻነት ተምሳሌት የሆነችውን ሰፈራችንን ሆነ ብለው የስም የማጥፋት ዘመቻ (character assassination) አደረጉባት። በዚህም ሆነ ተብሎ በሚደረግ የስም የማጥፋት ዘመቻ (character assassination) ሰፈራችንን እና እድራችንን ስም ከማጠልሸትም አልፈው እንደ ሰፈር እና እድር የመኖር ህልውናችንንም መፈታተን ከጀመሩ በርካታ ጊዜያት ተቆጥረዋል።
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ያላቸው ጥላቻ የቆየ መሆኑን ለመረዳት እ.ኤ.አ በ1927 በባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ የተጻፈው እና በከያኒ ደበበ እሸቱ ወደ አማርኛ የተተረጎመው “Abessinien: Die schwarz Gefahr” ወይም «የባሩድ በርሜል» የተሰኘውን መጽሃፍ ማየት በቂ ነው።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ፤ የባሩድ በርሜል የተሰኘው ጸሃፊው ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ይባላል። ኦስትሪያዊ ሲሆን ፤ ዋነኛ ተግባሩም በሰፈራችን እና በእድራችን መሰብሰቢያ ዋርካ ስር የዲፕሎማሲያዊ ስራ መከወን ነበር ። ይህ ሰው በ1926 ዓ.ም ከዲፕሎማት ሥራው እና ከዲፕሎማቲክ መብቱ ጋር የሚፃረር ተግባር ሲያከናውን በመገኘቱ የእድራችን እና የሰፈራችን መሪዎች ከመሰብሰቢያ ዋርካ ስር በብርሃን ፍጥነት በማባረር ወደ ሀገሩ መለሱት። ቂም አርግዞ ወደሀገሩ የተባረረው ዲፕሎማትም መርዝ ያዘለ መጽሃፍ ጻፈ።
አሜሪካ እና መሰል የእድራችን እና የሰፈራችን ታሪካዊ ጠላቶች ሰፈራችንን እና እድራችንን ለማጥፋት ካላቸው ጉጉት የተነሳ በ1927 ዓ.ም በባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ የተጻፈውን መጽሃፍ በ34 የአውሮፓ ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንዲጻፍ አደረጉ።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተተረጎመውን ያነበቡ ለይስሙላ ፊደል ቆጥረናል የሚሉ ፤ ሳያውቁ ራሳቸውን በአዋቂዎች መርከብ ያሳፈሩ አንዳንድ የእድራችን አስተዳዳሪዎች ፣ ተፎካካሪ ሃይሎች ፣ ማን እንደሚከፍላቸው የማይታወቁ ወግ አሳላጮች እና ጡሩምባ ነፊ ሱፍ ለባሾች ፤ የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ የጠላች ንግግሮች ፖለቲካ ማኒፌስቶአቸው አድርገውት አረፉ።
ከእነኝህ መካከል አንዱ የሆነው እና ሰፈራችንን እና እድራችንን ለሶስት አስርት ዓመታት የመራው በአይተ ጭሬ ልድፋው የሚመራው ሱፍ ለባሽ ቡድን በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው ። ለይስሙላ ፊደል ቆጥረናል የሚሉ ፤ ሳያውቁ ራሳቸውን በአዋቂዎች መርከብ ያሳፈሩ አንዳንድ
የእድራችን አስተዳዳሪዎች ፣ ተፎካከሪ ሃይሎች ፣ ማን እንደሚከፍላቸው የማይታወቁ ወግ አሳላጮች እና ጡርምባ ነፊ ሱፍ ለባሾች የምዕራባውያን የሴራ ማሳለጫ ፈረስ ከሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እየተባለ ከሚጠራው ድርጅት ጋር በመተባበር ሰፈራችን እና እድራችንን ለማፍረስ የሚሮጡት የጥፋት ሩጫ በሰፈራችን እና እድራችን ላይ እያሳደሩት ያለውን ተፅዕኖ ለመረዳት በባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ የተጻፈውን መጽሃፍ በወፍ በረር ማየቱ ተገቢ ነው ። ስለሆነም ስለመጽሃፉ ትንሽ ልበላችሁ! አለና .. ይልቃል አዲሴ ለአፍታ ንግግሩን ገታ ካደረገ በኋላ ንግግሩን እንዲህ ሲል ቀጠለ….
መጽሃፉ ምዕራፍ አንድ ላይ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ምንድን ነው? ” የሚል ርዕስ የያዘ ነው ። በዚህ ርዕስ ተነስቶ በሀገሪቱ ስለሚካሄዱ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ይዳስሳል። መጽሃፉ ስለ ሀገሪቱ መልክዓ ምድራዊ፣ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩነት ያትታል ፣ ቅኝ ተገዥ ከሆነው ከሌላው ዓለም ህዝብ የሚያገኙትን ክብርና ታዛዥነት ኢትዮጵያ ውስጥ ማጣታቸውን ሳይደብቅ ይነግረናል። ይህንን የኢትዮጵያውያን ኩራት ማኮስመን ካልተቻለ እና በቸልተኝነት ከታለፈ ወደ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ተሸጋግሮ ዋጋ ያስከፍለናል ሲል ይመክራል።
የኢትዮጵያውያን ኩራት እና የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ማኮስመን እንደሚገባ ለአውሮፓውያን ይመክራል። ኢትዮጵያውያን በተለይም አንደኛው ብሔር ለውጭ ሃይሎች ያላቸው ጥላቻ ለሁሉም የውጭ መንግሥታትና ዜጎች አሳሳቢ በመሆኑ ፤ ይህንን ብሄርን ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በማጋጨት ኢትዮጵያን እንዳትነሳ አድርጎ ማጥፋት እንደሚቻል ይገልጻል።
በ1968 ዓ.ም በእጅ የጻፈው አይተ ጭሬ ልድፋው ማኒፌስቶው መነሻው የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ መጽሃፍ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ መገንዘብ ይቻላል ። የእነ አይተ ጭሬ ልድፋው ቡድን ማኒፌስቶን ከባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ መጽሃፍ ጋር መስመር በመስመር ብታስተያዩት ለሶስት አስርት ዓመታት ሰፈራችን እና እድራችን ሲያስተዳድረው የቆየው ሱፍ ለባሽ ከፍጥረቱ ጀምሮ የምዕራባውያን የጥፋት አሽከር መሆኑን በቀላሉ እንድንገነዘብ ያስችለናል። አሁን ላይ የሚታዩ አንዳንድ በብሄር ጥላቻ የሰከሩ ሱፍ ለባሾችም የፖለቲካ እውቀት መነሻው የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ መጽሃፍ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ ያስገነዝበናል።
የዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ ሁለት “ጥቁር መጽሐፍ የኢትዮጵያውያን የጥቃት ስንዘራ” የሚል ርዕስ ያዘለ ነው። በዚህም ነጮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመጡ የሚገጥማቸውን መከራና ሰቆቃ ይዘረዝራል። ለውጭው ዓለምም ለጥቁር አሜሪካውያን ሳይቀር ኢትዮጵያ ማለት ለእንግዳ ክብር የማትሰጥ የምድር ሲዖል እንደሆነች አድርጎ ያለግብሯ ግብር እና ያለታሪኳ ታሪክ ለመስጠት ይሞክራል።
ይህን የኢትዮጵያን ክብር ለማውረድ ሲጣጣር የሚመለከት ማንኛም ሰው የአሸባሪው አይተ ጭሬ ልድፋው እና ግብረ አበሮቹ ሱፍ ለባሾች በሰፈራችን እና እድራችን ታሪክ የ100 ዓመት ነው ብለው ታሪካችንን ለማሳነስ የጀመሩት እሩጫ መነሻው የባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ጹህፍ መሆኑን ለመረዳት ያስችላል ። ለመጀመሪያው ጥያቄህ ይህን ያህል ካብራራሁ ጊዜ ስሌለን ለሁለተኛው ጥያቄህ መልስ ብሰጥ ይሻላል በማለት የሁለተኛውን ጥያቄ ምን እንደነበር ለማስታወስ በብጫቂ ወረቀት ላይ የጻፋትን ማስታወሻ አነበበ።
ካልተሳሳትኩ ክንፈ ጉደታ ሁለተኛው ጥያቄህ ሰፈራችን እና እድራችን በብዙ ችግሮች ተተብትበው ተይዘው መላወሻ ባጡበት ሰዓት ሰፈራችንን እና እድራችን የሚመሩት እና ተፎካካሪዎቻቸው እንዲሁም ወግ አሳላጭ እና ጡሩምባ ነፊ ሱፍ ለባሾች እንዴት መደማመጥ ተሳናቸው ? የሚል ነው .. ብሎ ፤ ይልቃል አዲሴ አብሿሙን ክንፈ ጉደታ ተመለከተ ። አብሿሙ ክንፈ ጉደታ በአወንታ ጭንቅላቱን ነቀነቀ።
ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ቀጠለ…. አንዳንዴ ቆም ብየ ሳስብ ሱፍ የተባለ ልብስ ሰዎች መደማመጥ እንዳይችሉ እና ከራሳቸው ውጭ ማንንም እንዳይሰሙ የሚያደርግ ዛር የሰፈረበት ይመስለኛል። ፖለቲከኞቻችን እንተውና የሃይማኖት አባቶች እንኳን ብንመለከት ሱፍ ሲለብሱ ሁሉ ነገራቸው ይቀየራል። በምዕመኑ አንቱታን አትርፈው ይኖሩ የነበሩ ቄስ ፣ ሼክ ወይም የሌላ ሃይማኖት መሪ ሱፍ ሲለብሱ ጨርሰው ግብዝ መሆን ይጀምራሉ።
ይህንን አባባል መቶ በመቶ እውነት ነው ባልላችሁም አብዛኛውን ጊዜ ግን ያየሁት እውነት ነው። እናም ይህን ስመለከት ሱፍ ውስጥ የሰፈረው ያለመደማመጥ ዛር ምንድን ነው ብየ እንድጨነቅ ከማድረጉም ባለፈ ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግም ስለማስብ ብዙ አንቅልፍ መተኛት ካቆምኩ ዘመናት ተቆጥረዋል።
በሰፈራችን ያሉ ሱፍ ለባሾች ለምን መደማመጥ ተሳናቸው ወደሚለው ጥያቄ ማብራሪያ ስመለስ በሰፈራችን ያሉ ሱፍ ለባሾች አብዛኛዎቹ የባህር ዛፍ ፖለቲካ መርህን ስለሚከተሉ ነው። ከእኔ ውጭ ማንንም አላስኖርም የሚል የግብዞች ፖለቲካ ! የእድር መሪዎች የሚመሩት እድር ህልውና በጸና መሰረት ላይ እንዲቀመጥ ከፈለጉ በመጀመሪያ ደረጃ እድሩ ሁነኛ ዓላማ ሊኖረው ይገባል። ዓላማውም በመርህ የተገራ እና በመርህ ሊመራ ግድ ነው። መርህ ደግሞ ዓላማን ለማሳካት መራራም ሊሆን ይችላል። የብዙ እድሮች ተሞክሮ ይሄንን በግልጽ የሚያሳይ ነው። መርህ ደግሞ ለአንድ አድር መሪ «ሀሁ» ነው።
እንደሚታወቀው የእኛ ሰፈር እድር በብዙ ነገሩ ከሰፈራችንም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪም ነው። በዚህ ሳቢያ የሰፈራችን ሰዎች እንደ እይናቸው ብሌን ቢጠብቁትም የውጭው ዓለም እና የሰፈራችን አንዳንድ እኩይ ተልኮ ይዘው ሚንቀሳቀሱ ሱፍ ለባሾች የእድራችንን ህልውና ሲፈታተኑት እያየን ነው።
በነገራችን ላይ አምባ ገነኖች መርህ አያውቁም። በትቢት ሲወጠሩ ህሊናቸው ግራ እና ቀኙን ፤ ፊት እና የኋላውን ማየት ስለሚያቆም ምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሃይል ያለእነርሱ ፈቃድ መኖር እንደማይችል አድርገው ማሰብ ጀምራሉ። በእኔ ልክ የተቀደዱ ለብሶችን ልበስ ! ብለው ማስገደድ ይጀምራሉ። ከዜጎቻቸውም አልፈው የጎረቤት ሀገራትን ሰላም ያውካሉ። ከማወክም አልፈው ወረራ ይፈጽማሉ። ከእነኚህ አይነት ሰዎች መካከለል ናፖሊዮን ቦናፓርት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ናፖሊዮን ቦና ፓርት መላ አውሮፓን መግዛት አለብኝ ብሎ ቆርጦ ተነሳ። የሚችለውንም ያህል ወረረ። በዚህ ጊዜ አውሮፓን ናፖሊዮ ቦና ፓርትን ከፈጣሪ በታች ያለ ፈጣሪያቸው እስኪመስላቸው ድረስ አግዝፈው አዩት። ናፖሊዮን ቦናፓርት በበኩሉ ራሱን ከፈጣሪው ጋር አስተካክሎ ተመለከተ። የትኛውም ምድራዊ ሃይል ሊገዳደረኝ አይችልም ሲል ለራሱ ነገረ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደዚህ አይነት መርህ አልባ ግብዝነት ለይስሙላ ፊደል ቆጥረናል የሚሉ ፤ ሳያውቁ ራሳቸውን በአዋቂዎች መርከብ ያሳፈሩ አንዳንድ የእድራችን አስተዳዳሪዎች ፣ ተፎካከሪ ሃይሎች ፣ ማን እንደሚከፍላቸው የማይታወቁ ወግ አሳላጮች እና ጡርምባ ነፊ ሱፍ ለባሾች በከፍተኛ ደረጃ እያስተዋል ነው ። ለዚህም ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በሰፈራችን ሱፍ ለባሾች መካከል መደማመጥ የጠፋው ለመደማመጥ ከመዘጋጀት ይልቅ የባህርዛፍን ፖለቲካ መርህ በማድረጋቸው ነው ያልኩት ።
በድሮ ጊዜ አንዱን ፈላስፋ እንደህ ሲሉ ሰዎች ጠየቁት «ሊያዝኑለት የማያስፈልግ እና የማይገባው ነገር ምንድን ነው?» ፈላስፋውም «የክፉ ሰዎች መሞት!» አለ። በነገራችን ላይ የእድራችን እና የሰፈራችን ሰዎች ሊያዝኑላቸው ከማይችሉት ሰዎች መካከል እድራችን እና ሰፈራችንን በክፍት እያወኩት ያሉትን ሱፍ ለባሾች በሞቱ ጊዜ ስለመሆኑ በአስር ጣቴ እፈርማለሁ ! ብሎ እየተናገረ እያለ ዛሬም አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፤ ይልቃል አዲሴ እንዲመልስለት የፈለገው ጥያቄ አዘጋጅቶ ኖሮ ያዘጋጀውን ጥያቄ ለመጠየቅ እጁን በማውጣት ይልቃል አዲሴን በተመስጦ እያደረገው ንግግሩ ላይ አቋረጠው።
የአብሿሙን ክንፈ ጉደታ ጥያቄ እና የይልቃል አዲሴን መልስ በሚቀጥለው ዝግጅታችን ይዘን እንቀርባለን። እስከዚያው አለመደማመጥ ከወለዳቸው የጥፋት ጋሬጣዎች ፈጣሪ ይጠብቀን።
ሰላም!!!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2014