እንደማንኛውም ሕዝብና አገር ብዙ ያልተዘጉና ለውሳኔ በእንጥልጥል ያሉ ዶሴዎች አሉን። አንዳንዶች በይፋ ባንነጋገርባቸውም በጥቅሻ ተግባብተን በይደር ያቆየናቸው ናቸው። ሌሎቹ ብንከፍታቸው እንደ ፓንዶራ ሙዳይ በውስጣቸው ተዘግተው የነበሩ የክፋት ጣኦታት ሁሉ እያፈተለኩ ወጥተው በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ ይሆኑብናል። አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ አሸባሪው ትህነግ/ ሕወሓት ስድ የለቀቅናቸው ይገኙበታል።
ወደድንም ጠላንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕወሓት አማራጭ እያሳጣን ነው። ስለሆነም የቀረን አማራጭ የማያዳግም መውጫችንን ማማተር ነው። አዎ ! የሕወሓትን የዳጎሰ ዶሴ የመዝጋትን ሒደት የጀመርን ቢሆንም ውጫዊም ውስጣዊ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት በማያዳግም ሁኔታ እየዘጋነው አይደለም። እያደር አዳዲስ ገጾችን እየጨመረብን ነው።
ግልጽ የሆነ የመውጫ ስትራቴጂም ያለን አይመስልም። በዘገየን ቁጥር የሚያስከፍለን ዋጋ እየጨመረ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። ላለፉት 50 አመታት ቢያንስ ሁለት ትውልድ በምንም ሊተመንና ሊገለጽ የማይችል ለዛውም አዋጭ ላልሆነ አላማ ውድ ዋጋ ከፍሏል። በእኛ ይለፍ ወይም ይብቃ ብለን ለሶስተኛ ትውልድ እንዳይተላለፍ ተቀናጅተን ሌት ተቀን መስራት ይጠበቅብናል። ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት ካልቻልን ነገ ትውልድም ታሪክም ይወቅሰናል። አገርም ትከሰናለች። ከዚህ ያልተዘጋ ዶሴ አንድ አንድ ጥቋቁር ገጾችን ስለ ግንቦት 20 በአለፍ ገደም እንግለጥ።
ግንቦት 20 በግልብ ትንተናና በፈጠራ ትርክት ድቡሽት ላይ የተመሰረት አማጺና አንጋች ለገዥነት ያበቃ የቀን ጎዶሎና ጥቁር ገጽ ነው። አገራችን ዛሬ ለምትገኝባቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች መባቻም ነው። እንደ አገር እንደ ሕዝብ የገባንበት ቅርቃር አሀዱ፣ ክለቱ፣ …የተባለበት ቀን ነው ማለት ይቻላል። አምባገነናዊውን የጊዜያዊ ወታደራዊ አገዛዝ /ደርግ/ን ገርስሶ በሌላ ዘራፊ፣ አምባገነንና አፋኝ አገዛዝ በመተካት አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት ዕለት ነው። የተማሪዎችን አብዮት ቀምቶ ስልጣን የጨበጠ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ 70ሺ የሚጠጉ ታጋዮች የተሰውለትን፣ ከ120ሺህ በላይ አካል ጉዳተኛ የሆኑለትን የነጻነት አብዮት ቤተሰባዊ በሆነ ቡድን ጠልፎና አግቶ ስልጣን በመዳፉ ያደረገበት ክፉ ቀን ነው።
የ3ሺህ አመትና ከዚያ በላይ ታሪካችን ወደ 100 አመት የወረደበት፣ ጥንታዊው የአገረ መንግስት ታሪካችን የተካደበት፣ ስንቶች በዱር በገደሉ የተዋደቁለት ሰንደቅ ጨርቅ ተብሎ ዱቄት የተቋጠረበት፣ ጥላቻና ልዩነት የተቀነቀነበት፤ የጋራ ታሪክ፣ ብሔራዊ ጀግናና ምልክት /አይከን/ እንዳይኖረን የታወጀበት፤ አገራዊና ሕዝባዊ አንድነት የተወገዘበት ጥቁር ቀን ነው።
ግንቦት 20 የአገር ሀብት በጥቂቶች እጅ የገባበት፣ እንደ ኤፈርት ያሉ ድርጅቶችና ቡድኖች እንዳሻቸው እንዲዘርፉ ካዘና የተከፈተበት፣ ለዘመናት የተገነቡ ተቋማትና እሴቶች እንዲወድሙ ደማሚት የተቀበረበት፣ ዜጎች እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚሰራ ተቋም የተመሰረተበት፤ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ሕዝብ በጎሳ፣ በሃይማኖትና በሌሎች ማንነቶች እንዲከፋፈል የተሴረበት፣ በጎሳና በቋንቋ ብቻ የተመሰረተው የልዩነትና የጥል የባቢሎን ግንብ /ክልል/ መሰረተ ድንጋይ የተጣለበት፣ አገር ለብተና የታጨችበት፣ አገር በደም ካሳና በእዳ የተያዘችበትና የታገተችበት፣ አናሳዎችና ህዳጣን በአፈሙዝ ብዙኃኑን ቀጥቅጠው የገዙበት፣ አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ የተፈጠረበት፣ ወዘተረፈ የሀዘን ቀን ነው። ታሪክ የአሸናፊው ነው እንዲሉ ይህ ሁሉ ቀውስ ውድቀት መወገዝ ሲገባው እንደ ድል በዓል የሚከበረበት ቀን ነው። የሚያሳዝነው ዛሬም ከቀን መቁጠሪያው አለመፋቁ ነው።
ቀኑ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ተስፋ ሳይውል ሳያድር ወደ ቀቢጸ ተስፋነት የቀየረ መናጢ ቀን ነው ማለት ይቻላል። ለ17 አመታት በተካሄደ የእርስበርስ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች አምራቹና ወጣቱ የሰው ኃይል በግዳጅና በወዶ ገብነት ለጦርነቱ ተማግዷል። የአገር ሀብት፣ ጥሪት፣ ኢኮኖሚና መሰረተ ልማቶች ወድመዋል። የአገሪቱ እድገት አሽቆልቁላል። ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ማህበራዊ ቀውስ ተንሰራፍቷል።
የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለት “ትግል” ገና ከጅምሩ መጨንገፉ ነው። ነጻነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ እኩልነትንና ዴሞክራሲያዊነትን ያዋልዳል ተብሎ የተጠበቀው ጽንስ ውርዴ ሆኖ ቀርቷል። በተለይ ከ1987 ዓ.ም ወዲህ እስከ ለውጡ ዋዜማ በፅኑ ሕሙማን ማቆያ/ICU/ በጠመንጃ በአፈና እና በከፋፍለህ ግዛ የቅኝ ገዥዎች መርህ ቆዬ እንጂ የተነሳለትን አላማ ገና ከመነሻው የዘነጋ ስለነበር ህልውና አልነበረም።
በግንቦት 20፣ ለቀደሙት 27 አመታት ስልጣን ላይ የነበረው ገዥ ፓርቲ ሕወሓት /ኢህአዴግ መመጻደቂያዎች ቀዳሚው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እኩልነት አረጋግጫለሁ፤ በማንነታቸው እንዲኮሩ አድርጌያለሁ የሚል ቢሆንም የግንባሩ አስኳል የሆነው ትህነግ በሚመራው የትግራይ ክልል በዞኖች እንኳን እኩልነት አልነበረም።
ሕዝቡም በአንድ ለአምስት ተጠርንፎ ዛሬ ድረስ ከኢትዮጵያውያን ተለይቶ በጭቆና ፍዳውን እየበላ ይገኛል። ልጆቹን ገብሮ ያለጧሪ ቀባሪ ቀርቶ ለስልጣን ያበቃው ቤተሰባዊ ቡድን ዛሬም ከትክሻው የመውረድ ፍላጎት የሌለውና ይህ አልበቃ ብሎት ኢኮኖሚውን ከጅምላ ንግድ እስከ ጉልት ተቆጣጥሮ፤ መሬቱን፣ የተፈጥሮ ሀብቱንና ጉልበቱን እየዘረፈ ለምሬትና ለብሶት ዳርጎታል።
ለ44 አመታት ማለትም 17 አመታት በትጥቅ ትግል 27 አመታት በገዢ ፓርቲነት በአገር፣ በትውልድና በተቋማት ላይ የተከለው መርዛማ ሰንኮፍ ሳይነቀልና ሳይሽር፤ ከማዕከላዊ መንግስት በሕዝባዊ አመጽና ከውስጡ በወጡ የለውጥ ኃይሎች በልክህ ሁን ተብሎ ሲሰፋ ድምጹን አጥፍቶ ኮሽታ ሳያሰማና ጭራውን ቆልፎ ወደ መማጸኛ ከተማው መቀሌ በመመሸግ፤ በአራቱ የአገሪቱ ማዕዘናት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ግጭቶችንና ቀውሶችን በመቀፍቀፍ በሰንኮፉ ሌላ ሰንኮፍ፣ በእባጩ ላይ ሌላ እባጭ መጨመሩን በጀ ብሎ ተያያዘው። በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀሉ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን በግፍ ተጨፈጨፉ፤ ሀብት ንብረታቸው ተዘረፈ። በስንት ላብና ሀብት ለአመታት የተገነቡ ከተሞች በእሳት ጋዩ። ለመስማት የሚሰቀጥጡ፣ ለማየት የሚዘገንኑ አረመኔያዊ ድርጊቶች ተፈጸሙ። እንደሀገር ይዘነው የመጣነውን የልቦና ውቅር መለስ ብለን እንድንመረምር አስገደደን።
ሕወሓት ይሄን ሁሉ ሰቆቃ የሚፈጽመው በአምሳሉ በቀፈቀፋቸው ተላላኪዎቹና ቡችሎቹ እየታገዘ ነው። በአናቱ በዩኒቨርሲቲዎች ማንነት ላይ የተመሠረቱ ግጭቶችን በመጎንቆል አገሪቱን ወደማያባራ የእርስ በእርስ ግጭትና ብጥብጥ ለመዝፈቅ ሌት ተቀን ይሰራል። ለዚህ እኩይ አላማው ስኬት እንደ ግብጽ ካሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል። ከዚች አገር በዘረፈው ሀብት ከምዕራባውያን ሚዲያዎች፣ ከሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነኝ ባይ ተቋማትና ከቀድሞ አጋር ፖለቲከኞችና አንቂ ተብየዎች ጋርም የሰመረ ሊባል የሚችል ግንኙነት ፈጥሯል።
ይህ የጥፋት ዕቅዱ የማይሳካ ከሆነም ፕላን ቢ(ው)ላይ አበክሮ መስራቱን ተያይዞታል። በመቶ ሺህዎች ልዩ ኃይል እያሰለጠነና እያስታጠቀ ሲሆን በክልሉ ያለውን ሚሊሻም እንደ አዲስ ማደራጀቱንና ማስታጠቁን ገፍቶበታል። ከዚህ ጀርባ ደግሞ የሰሜን ዕዝን በቀላሉ እንዴት እንደሚያጠቃና በአዲስ አበባና በአስመራ የመንግስት ለውጥ እንደሚያደርግ በአረጠ ዘግቶ ያሴራል።
ሕወሓት ፕላን ኤ(ው) የትም እንደማያደርሰውና የፈለገውን ውጤት እንደማያመጣለት ሲረዳ ፕላን ቢ(ው)ን ከመደርደሪያው ሳበ። በሰሜን ዕዝ ላይ ታሪክም ትውልድም ይቅር የማይለውንና የማይረሳውን ክህደትና ጭፍጨፋ ፈጸመ። ሰራዊቱንና አገሪቱን ውድ ዋጋ ቢያስከፍልም እኩይ አላማው ቅዠት ሆኖ ቀረ። የቆሰለ አውሬ ሆኖ የቀረው ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ በማለት በሕዝባዊ ማዕበል ጦርነት ከፈተ።
በዚህም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ትግራዋይን ማገደ፤ በአማራና በአፋር ክልሎች ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ግፎች፣ ውድመቶችና ዘረፋዎች ፈጽሞም ቢሆን ድባቅ ተመቶ ቢመለስም ዛሬም ለሌላ ዙር ጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል። እንግዲህ ይሄን እፉኝት ለአገዛዝ ያበቃውን ቀን ነው ዛሬም በካሌንደር ዘግተን “እያከበርን” ያለነው። እንደ ዓድዋ እንደ ሚያዝያ 27ቱ የአርበኞች/የድል በዓል። በተለይ ባለፉት አራት አመታት እንደ አገርም ሆነ ዜጋ የተፈጸመብንን ግፍ ስናስብ ዛሬም የግንቦት 20 መከበር ያማል። ያሳዝናል።
በልጆቹ አጥንትና ደም ተረማምዶ ለስልጣን የበቃበትን ሕዝብ ልጆች ዛሬም ከጉያው እየነጠቀ የሚማግድ በላዔ ሰብዕ፤ በአውራጃና በጎጥ የሚከፋፍል፣ ወላጅና ልጅ፣ ባልና ሚስትን በጥርጣሬ የሚያተያይ፤ የሚያፍን፣ የሚያግትና የቁም እስረኛ የሚያደርግ ነጻ አውጭ አስኳል የሆነበት ድርጅት በምን ተጠየቅና አመክንዮ ነው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልነት የሚያረጋግጠው? በእርግጥ የይስሙላና በእሱ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረት አስመሳይ እኩልነት አልነበረም ማለት አይደለም። በመናጆዎቹ በእነ ደኢህዴግ፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና በአጋር ፓርቲዎች መካከልና እኩልነትንና ውስጠ ድርጅታዊ ዴሞክራሲና ነጻነትን ሳያረጋግጥ በየት አልፎ ነው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እኩልነት አረጋግጫለሁ የሚለው !?
ሌላው መመጻደቂያው በግንቦት 20 አገሪቱ ህግ መንግስታዊ፣ ፌደራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሪፐብሊካዊ በሆነ ስርአት እንድትመራ ጥርጊያውን ማመቻቸት ተችሏል የሚለው ነው። በቀደሙት 27 የግፍ አመታት ሕገ መንግስቱ ምሰሶ ያደረጋቸው የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት፣ የሕዝቡ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆኑን፣ የክልሎችን ራስን የማስተዳደር ስልጣን፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን፣ ወዘተረፈ የሚደነግጉ ድንጋጌዎቹም ሆነ ሌሎች አንቀጾች የኢህአዴግ አዛዥና ናዛዥ የነበረው ትህነግ በአደባባይ ሲጥሳቸው ስለነበር፤ “ሕገ መንግስት የታተመበትን ወረቀት ያህል እንኳ ዋጋ አጣ፤” እስከማለት ተደርሶ ነበር።
በአምስቱም የይስሟላ ምርጫዎች ኮሮጆ በመገልበጥ፣ በማጭበርበርና በአፈ ሙዝ የሕዝቡ ድምጽ በጠራራ በመዘረፉ የሕዝቡን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት በተደጋጋሚ በመጣስ ሲከሰስ መኖሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ሌላው በአገሪቱ ታሪክ ዴሞክራሲያዊ ነኝ የሚል መንግስት በገዛ ዜጋው ላይ ዘግናኝና ተቋማዊ በሆነ አሰራር የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን እየረገጠ፣ እየጣሰና እየገፈፈ ከፍ ሲልም ሲገድል፣ ዘቅዝቆ ሲገርፍ፣ ጥፍር ሲነቅል፣ ወሲባዊ ጥቃት ሲፈፅምና ሲያንኮላሽ የነበረ ቡድን ስለ ሕገ መንግስትና ሕገ መንግስታዊነት የማውራት ሕጋዊም ሞራላዊም ልዕልና የለውም።
ግንቦት 20 የራስን አስተዳደር በራስ የመወሰን መብት፣ እኩል የመልማት እድል የፈጠረ እና ሁሉም ክልሎች በአገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል እንዲወስኑ ያስቻለ ስለ መሆኑን ተደጋግሞ ይነገራል። ሆኖም እኔ አውቅላችኋለሁ እያለ የሞግዚት አስተዳደር በአምሳሉ አቁሞ፤ ክልሎች መሪያቸውን የመምረጥ መብት የገፈፈና በጀታቸውንና እንዳሻው ሲሸነሽን የኖረ አሰራርና አደረጃጀት በነበረበት አግባብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አጎናጽፏል ቢባል ከልግጫ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። ለዚህ ነው አገዛዙ ፌደራላዊም፣ ዴሞክራሲያዊም፣ ሪፐብሊክም አልነበረም የሚል የሰላ ትችት የሚሰነዘርበት።
ለውጡ ካበተ ጀምሮ ግንቦት 20 ይከበር አይከበር የሚለው ሙግትና እሰጥ አገባ ገፍቶ የመጣው። ወንድም ወንድሙን ገድሎ ሥልጣን የያዘበት፤ ሌላ አምባገነን በመንበሩ የተተካበት ሆኖ እንዴት የድል በዓል ይሆናል የሚል ክርክር የተነሳበት፤ መስከረም 2 በግንቦት 20 ተተካ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ እስከ ማለት የተደረሰበት። ለዚህ ነው ዶሴው ይዘጋ፤ የመውጫ ስትራቴጂ እንትለም የምለው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2014