ሰላም እንዴት ሰነበታችሁ ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ ለመሆኑ ሳምንቱ እንዴት አለፈ፤ በተለይ የእግር ኳስ አፍቃሪ ወዳጆቼ ሰሞኑን በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው መሰንበታቸውን ታዝቤአለሁ። ሊቨርፑል እና ሪያል ማድሪድ ያደረጉት የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ውድድር ብዙዎችን ትኩረት ስቦ ሰንብቷል።
ስለአውሮፓ ቻፒዮንስ ሊግ ሳነሳ በዚህ ዙሪያ ትንታኔ አልያም ሃሳብ ለመስጠት ፈልጌ እንዳልሆነ ከወዲሁ ተረዱልኝ። ለዚህ የሚሆን ብቃቱ የለኝም። ነገር ግን ከዚህ ጋር የተገናኘ ትዝብት ስላለኝ ነው ብዕሬን ከወረቀት ያዋደድኩት። እንደው ግን ጎበዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ እግር ኳስን ምን ያህል ይወዳል? የራሱ ጠንካራ ክለብ ወይም ቡድን ቢያገኝና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ቢሆን ስንቱ በደስታ ራሱን ይስት ይሆን? ለማኛውም የኔ ትዝብት ከእግር ኳስ ስታዲየሞች ግንባታ ላይ ያተኮረ ነውና እንካችሁ።
በቅርቡ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ስታዲየሞች መስፈርን ማሟላት ስለማይችሉ ውድድር ማስተናገድ አይችሉም የሚል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምታደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ከሀገሯ ውጭ እንዲካሄድ መወሰኑን ሰምተን ብዙዎቻችን ማዘናችን የሚታወስ ነው። የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ለሆነች ሀገር ደግሞ ይህ ትልቅ ተቃርኖ ነው። ጨዋታ እንኳ ለማስተናገድ አትችልም መባሉ ምን ያህል እንደሚያም መገመት አይከብድም።
በአንጻሩ ከኢትዮጵያ በብዙ ጊዜ ዘግይተው እግር ኳስን የጀመሩና በሥልጣኔና ታሪካዊ እድገትም በብዙ እጥፍ ከኢትዮጵያ የሚያንሱ ሀገራት በእግር ኳሱም ሆነ በእግር ኳስ ማዘውተሪያ ስፍራዎቻቸው ጥለውን ሲሄዱ ማየት እጅግ የሚያም ነው። እንደው ግን እና የአፍሪካ እግር ኳስ መስራች ሆነን ቢያንስ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት እንኳን ከበደን ብንል እንዴት ጨዋታ ማስተናገድ የሚችል መጫወቻ ሜዳ እንጣ?
በጣም አሳዛኙና አሁንም መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ደግሞ ሀገሪቷ ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ከካዝናዋ ማውጣቷ ነው። ይህ ሁለት ሃሳብ አይጋጭም ወይ ለምትሉ ደግሞ መረጃውን በጥቂቱ እንካችሁ።
ከኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘሁት መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 16 ስታዲየሞች በግንባታ ላይ ይገኛሉ። ከፊሎቹም በእድሳትና ጥገና ሥራ ላይ ይገኛሉ። ለነዚህ ስታዲየሞች ግንባታ ደግሞ በአጠቃላይ 18 ቢሊዮን 450 ሚሊዮን ብር በጀት ወጪ ተደርጎባቸዋል። ከዚህ ውጭ ደግሞ ለመገንባት ለታቀዱት ስታዲየሞች በድምሩ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞላቸዋል። ይህ እግዲህ በአጠቃላይ ለስታዲየሞች ግንባታ 23 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መያዙን ነው።
ሀገራችን አሁን ካለችበት የኢኮኖሚ ችግር እና እንደሀገር ከገጠመን የበጀት እጥረት አንጻር ይህ ገንዘብ ከልክ በላይ ብዙ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ታዲያ እኛ ከሁሉም መሆን ያቃተን መሆኑ ደግሞ ትልቅ ህመም የሚፈጥር ነው። አንድም ገንዘባችንን ለሌላ ኢኮኖሚያዊ ችግራችን አላዋልን፤ አልያም የምንመኘውን ስታዲየም ገንብተን በሜዳችን ውድድር ለማድረግ አልቻልንም።
ለመሆኑ በሌሎች ሀገራት ያሉ እና የካፍን መስፈርት የሚያሟሉ ስታዲየሞች ምን ያህል ወጪ ተደርጎባቸዋል ብለን ብጠይቅ የማንገኘው መረጃ እጅጉን የሚገርም ነው። ምክንያቱያም እኛ ከያዝነው ገንዘብ በብዙ ያነሰ ሆኖ እናገኘዋለንና። ለምሳሌ ለአፍሪካ ዋንጫ ብቁ ነው የተባለው የማላዊ ቢንጉ ስታዲየም 78 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ነው። ይህ በኢትዮጵያ ገንዘብ ብንመነዝረው አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እንኳን አራት ቢሊዮን ብር ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት እኛ ለስታዲየሞች ግንባታ የመደብነው ገንዘብ ይህንን የማላዊ አይነት በትንሹ አምስት ስታዲየሞችን ገንብቶ ሌላ ተጨማሪ ለስፖርተኞች ማጠናከሪያ በጀት ይኖረን ነበር ማለት ነው።
ወደሌሎች የአፍሪካ ስታዲየሞች ስንመጣ የካፍን መስፈርት ማሟላት የሚችለው የትሪፖሊ ስታዲየም የተገነባው በ2 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ነው። በአጠቃላይ አፍሪካ ውስጥ የተገነቡት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ግንባታ የወጣባቸው ገንዘብ ሲታይ ኢትዮጵያ ለስታዲየሞች ግንባታ ብላ ካፈሰሰችው ገንዘብ በብዙ መጠን የሚያንስ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም። ታላላቆቹ የአውሮፓ ስታዲየሞችም ቢሆኑ የወጣባቸው ገንዘብ ሲታይ አሁን ኢትዮጵያ ከያዘችው ገንዘብ የሚስተካከሉ እንጂ የሚበልጡ እንዳልሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ የሳንቲያጎ በርናባው ስታዲየም የወጣበት ገንዘብ 500 ሚሊዮን ዩሮ ነው።
የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ የሀገራችን ስታዲየሞች አብዛኞቹ ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቁ መፈራረስ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ነው። ለአብነትም በአፋር ሰመራ ከተማ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ስታዲየም ሳይጠናቀቅ በመቆሙ በአሁኑ ወቅት በመፈራረስ ላይ ይገኛል። ስታዲየሙ የተገነባበት ስፍራ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት ቢሆንም ግንባው ይህንን ከግምት ያስገባ ባለመሆኑም መስታወቶቹ ረጋግፈው እና ግንቡም ተሰነጣጥቆ ይታያል። ከዚህም አልፎ ስታዲየሙ ጨዋታ የማይደረግበት በመሆኑ ያን ያህል ገንዘብ የወጣበት ስታዲየም ከጥቅም ውጭ እየሆነ ነው።
ልክ እንዲሁ ሌሎቹም በተለያዩ ምክንያቶች የቆሙ አልያም ለመፈራረስ በቋፍ ላይ ያሉ ናቸው። ለዚህ ደግሞ በአብዛኛው የሚነሳው ችግር አንድም የበጀት እጥረት ሲሆን በሌላም በኩል ኮንትራክተሮቹ ጥለው በመሄዳቸው እንደሆነ ይነሳል።
በአጠቃላይ ግን እኛ ከሁለት ያጣን ሆነን መቅረታችን የሚያሳዝን ነው። ወይ ገንዘባችንን ለሌላ ዓላማ አልተጠቀምን፤ አልያም ስታዲየም ገንብተን ለስፖርታዊ ፍላጎታችን ማርኪያ አላዋልን።
እነዚህ ለስፖርት ትኩረት የነፈጉ አካላት እንዲረዱት የምሻው ነገር ስፖርት በራሱ ከመዝናኛነትም ባለፈ የእድገት ምንጭ መሆኑን ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አይነት በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪ ባለባት አገር ይህንን የስፖርት ዘርፍ በአግባቡ መደገፍ ከስፖርቱም ባሻገር ለሀገራዊ እድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ የጣልያኗ ናፖሊ ያደገችው በማራዶና የኳስ ጥበብ የተነሳ እንደሆነ አይዘነጋም። በአውሮፓም እግር ኳስ በጀት ምን ያህል ከራሳቸው አልፎ በዓለም ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ እንገነዘባለን።
እኛ ደግሞ ስፖርቱን ቀድመን የተቀበልን፤ ነገር ግን ቶሎ ብለን ለመግደል የሮጥን እንዳንሆን ዛሬም እድሉ በእጃችን አለና ትኩረት ባንነፍገው መልካም ነው። ዛሬ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም እነዚህ በብዙ ቢሊዮን የወጣባቸው ስታዲየሞች ግንባታ የት ደረሰ ብሎ ተከታትሎ ቢያስጨርስ እና ለሀገራችን ስፖርት እድገት የራሱን አስተዋፅኦ ቢያበረክት ነገ ከሚመጣ የሞራልም ሆነ የትውልድ ተጠያቂነት ይድናልና ቢታሰብበት መልካም ነው።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2014