ዓለማችን በግለሰቦች የመፍጠር አቅምና ብቃት አያሌ የስልጣኔ በሮች ተከፍተውላታል። አሁን የደረሰችበት ስፍራ እንድትገኝ የእነዚህ ባለ ብሩህ አእምሮዎች አበርክቶ ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል። አገራት ሃያልነታቸውንና የምጣኔ ሃብት ጡንቻቸውን ያፈረጠሙት በእነዚህ ብርቅዬ ልጆቻቸው ድንቅ የመፍጠር አቅምና ያላሰለሰ ጥረት ነው። ለዚህም ነው ጥቂት ሆነው ግን ታላቅ አቅም ያላቸው ታዳጊዎች ላይ ጊዜ፣ ጉልበትና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማውጣት ጭምር ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና ትርጉም ወዳለው መንገድ እንዲቀይሩት እድሉን የሚያመቻቹላቸው።
በአፍሪካ የፈጠራና ልዩ ልዩ ክህሎት ያላቸው አያሌ ታዳጊዎች ቢኖሩም፣ አስፈላጊውን ድጋፍ ስለማያገኙና እምቅ ችሎታቸውን እንዲያወጡ ምቹ ሁኔታ ስላልተፈጠረላቸው ባክነው ይቀራሉ። በዚህ ምክንያትም አፍሪካውያን የድህነት ቁንጮና የምእራባውያኑ የቴክኖሎጂ ውጤት ተጠቃሚ የመሆን ግዴታ ተደቅኖባቸዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂና ልዩ ልዩ የፈጠራ ውጤቶች ጋር በተያያዘ በርካታ ክፍተቶች እንዳሉ ይታመናል። በዋናነት ደግሞ ብሩህና የመፍጠር አቅም ያላቸው ታዳጊዎችን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ደካማ እንደሆነ ነው እየተገለጸ ያለው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ለስራ ፈጠራና መሰል ዘርፎች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ይህን ተከትሎ ታዳጊዎችና ወጣቶች ክህሎታቸውን የሚያዳብሩባቸውንና እውቀታቸውን ለማህበረሰባቸው ችግር መፍቻ መሳሪያነት የሚያውሉባቸውን ተቋማት የመገንባትና ምቹ አጋጣሚዎችን የመፍጠር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ በተጨማሪ በግል ጥረታቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን የሚሰሩ ወጣቶች ስራዎቻቸውን የሚያስተዋውቁበትን እድልም እያመቻቸ ይገኛል።
ለዛሬ በሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን ዘርፉን ለማሳደግ፣ የአገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እድገት ለማረጋገጥ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ውስጥ አንዱ የሆነውን ጉዳይ ወደናንተ ይዘንላችሁ መጥተናል። በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ወጣት ስራ ፈጣሪዎችንና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶችን ለማበረታታት፣ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎች በአገር ልጆች እንዲፈጠሩ ለማድረግ የሚያደርገውን ጅምር ጥረት ልናስቃኛችሁ ወድደናል።
የኦሮሚያ ክልል የስራ እድል ፈጠራ ክህሎት ቢሮ “የክህሎትና ቴክኖሎጂ ውድድር” አሸናፊዎች እውቅናና ልዩ የሽልማት ዝግጅት መድረክ በቅርቡ አካሂዷል። መድረኩ በክልል ደረጃ ወጣት የቴክኖሎጂና ክህሎት አቅም ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣት ምሁራን ማበረታታትን ያለመ ነው፡፡
በልዩ ልዩ ዘርፎች የተቀመጠውን መስፈርት ያሟሉ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን በአውደ ርእይ የማስተዋወቅ እድል ከማግኘታቸውም ባሻገር እርስ በእርስ ተወዳድረው ተሸላሚ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥሮላቸዋል። በዋናነት ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር ለማህበረሰቡ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥሩና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የሚያሳድጉ የፈጠራ ሃሳቦች እውቅና ተሰጥቷቸዋል፤ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ታዳጊና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታትና ክህሎታቸውን ወደ ገበያ ለመቀየር እንዲችሉ የሚያደርግ የክህሎት ስልጠና፣ እውቅናና ሽልማት ለመስጠት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል። በገልማ አባገዳ አዳራሽ በተካሄደው በእዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት እንዳታመጣ የራስን እውቀትና ክህሎት አለመደገፍና ማጣጣል እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት የፈጠራ ባለሙያዎችም እንዳይበረታቱና ተስፋ እንዲቆርጡ ሆነዋል። ይህ ተገቢ ያልሆነ ተግባር እየቀረ መምጣቱን በማንሳትም የፈጠራ ባለሙያዎችና የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት ያላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች ለአገር እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
“የአዳማ ከተማም ለዚህ ምቹ ከመሆን ባሻገር ግለሰቦችና ኢንተርፕራይዞች በስራና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረች ትገኛለች” የሚሉት የከተማዋ ከንቲባ፤ ለሶስተኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል መንግስት የተካሄደው የክህሎትና ቴክኖሎጂ ውድድር ለእዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ ታዳጊዎችን በዚህ መልኩ ማበረታታት ከተቻለ ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋ ሰጪ መሰረቶችን መጣል እንደሚቻል ነው ከንቲባው ያመለከቱት።
በውድድርና እውቅና አሰጣጥ ስነስርዓቱ ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምክትል ፕሬዚዳንት ማእረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው እነ ጃፓን፣ ቻይናና ሌሎች መሰል አገሮች ለቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ምርምር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸው አሁን ለደረሱበት እድገትና ታላቅነት በቅተዋል ይላሉ።
እንደ አገርም ሆነ እንደ ኦሮሚያ ክልል ይህንን ልምድ መውሰድና ውጤት ማምጣት እንደሚያስፈልግም ነው አቶ አዲሱ የተናገሩት። ለዚህ ደግሞ ለስራና ቴክኖሎጂ ውጤት ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። ለስራና ቴክኖሎጂ እድል ፈጣሪዎች የፋይናንስ የስልጠናና የገበያ ትስስር ለመፍጠርም ክልሉ በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
የመድረኩ የክብር እንግዳ የስራ ፈጠራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ የኢትዮጵያ ቀጣይነት ማረጋገጫ የቴክኖሎጂ ፈጠራና ክህሎት ያላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች ወርቅ እጆች ናቸው ሲሉ አስገንዝበዋል። ለኢትዮጵያ ከዚህ በሁዋላ የሚያስፈልጋት እንደቀደሙት አባቶች የህይወት መስዋእትነት መክፈል ሳይሆን እውቀትና የፈጠራ ክህሎት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሙያና እውቀት ክብርና እውቅና ስንሰጥ ሌሎች መሰል ወጣቶች እንደሚበረታቱ አስታውቀዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ሰፊ ወጣት ባለበት በኦሮሚያ ክልልም የስራ እድል ፈጠራንና ቴክኖሎጂን ለመደገፍ የክልሉ መንግስት ላሳየው ቁርጠኝነት አመስግነዋል። የፌደራል መንግስትም ክህሎትን እንደ መግቢያ በር ወስዶ ተወዳዳሪነትን በአህጉርም ሆነ በአለም ላይ ለማሳደግ እየሰራ ሲሆን፣ ለዚህም ከፖሊሲ ጀምሮ ማሻሻያ እየተደረገ ነው። የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን እያሻሻለና በልዩ ሁኔታ እየደገፈ ነው።
አሸናፊዎቹና የስራ ፈጠራ ባለሙያዎቹ ከስንቄ ባንክ ጋር ትስስር ተፈጥሮላቸው የፈጠራ ስራቸውን እውን እንዲያደርጉና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙበት እድል እንዲመቻች እንደሚደረግ የክልሉ መንግስት ቃል ገብቷል። ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ ተሸላሚዎች የወርቅ የብርና የነሃስ ተሸላሚ ሆነዋል፤ እንደየደረጃቸውም የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የጉጂ ዞን የ11ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ናዝራዊ ከበደ በፈጠራ ዘርፍ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን (ዲሽቃ፣ ስናይፐር፣ ሮኬት፣ የፖሊስ ዱላና ፈንጂ) በመስራት ተወዳድሮ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል። ተማሪ ናዝራዊ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ “ታላላቅ የሚባሉ አገሮች ዋንኛ የእድገታቸው ሞተር የሆነው በቴክኖሎጂ ማደጋቸው መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ኋላ ቀር አገራት ደግሞ በዘርፉ ደክመው በመገኘታቸው ምክንያት በእነዚህ ሃያላን አገራት ተፅእኖ ስር ወድቀዋል ሲል ገልጾ፣ ቴክኖሎጂ የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን መረዳት እንደሚገባ አስገንዝቧል።
ታዳጊው የፈጠራ ባለሙያ ከዚህ በመነሳት የራሱን ድርሻ ለአገሩ ለማበርከትና ኢትዮጵያ በወታደራዊ ሳይንስ ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትሸጋገር በማሰብ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂዎቹን ለመስራት መነሳሳቱን ይናገራል።
ተማሪው እንደሚለው፤ ዲሽቃውን ለመስራት 230 ብር ወጪ ብቻ አድርጓል፤ የፈጠረው ቴክኖሎጂ ከ2 እስከ 7 ኪሎ ሜትር ባለ ርቀት ውስጥ አነጣጥሮ ጠላትን መምታት ይችላል፡፡ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑትን የመሳሪያው ግብአት የሚሆኑ አካላት ከወዳደቁ ቁሶች ተጠቅሞ ነው የሰራው፡፡
በሁለተኛ ደረጃም “ስናይፐር” አሊያም አነጣጥሮ መተኮስ የሚችል መሳሪያ ተማሪው በራሱ አቅም ሰርቷል፡፡ ይህም እስከ 50 ሜትር አነጣጥሮ የመምታት አቅም እንዳለውም ይገልፃል። ሌላው ነጭ ሰልፈርና ብረት በመጠቀም የሰራው ፈንጂ (ቦምብ) ሲሆን፣ ይሄም ጠላትን ለማዳከምና አስፈላጊውን ውጤት ለማምጣት እንደሚጠቅም ነው ያመለከተው።
“መንግስት የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ታዳጊዎች ያለምንም ችግር ስራቸውን እንዲሰሩና አገራቸውን እንዲያግዙ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ይገባል” በማለት የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው ተማሪ ናዝራዊ፣ እንደ እርሱ አይነቶቹና በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ታዳጊዎች ክህሎታቸውን ተጠቅመው የፈጠራ ስራ እንዲያከናውኑ ሊታገዙ እንደሚገባ ያስገነዝባል። የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ታዳጊዎችም አገራቸውን ሃያል የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ ተስፋ ሳይቆርጡ መሳተፍ እንደሚኖርባቸው መልእክቱን ያስተላልፋል።
አቶ አደም ከማል የኦሮሚያ ስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ናቸው። በሶስተኛው ዙር የቴክኖሎጂና ክህሎት ውድድር ላይ ለወጣቶችና በፈጠራ ስራ በክልሉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ስለ “ስራና ክህሎት” አጭር ገለፃና ስልጠና ሰጥተዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የክህሎት ልማት የስራ እድል መፍጠር ይችላል። ቢሮው ይህን ታሳቢ በማድረግ የመፍጠር አቅም ያላቸው ባለሙያዎችን በማፍራትና በርከት ያሉ ሙያዎችን (በተለይ ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ) እንዲያውቁ በማድረግ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ዜጎችን ለማፍራት እየሰሩ ነው።
“ክህሎት ስራዎችን በእጅ የመስራት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ጥሩ አስተሳሰብ በራሱ ክህሎት ነው” የሚሉት ምክትል የቢሮ ሃላፊው፤ ስራዎች ሁሉ መጀመሪያ በአእምሯችን ውስጥ ነው የሚያልቁት ይላሉ፡፡ የለማ ክህሎት እጅን ማዘዝ የሚችል አስተሳሰብን የሚቀይር መሆኑንም ይገልፃሉ። ከዚህ አንፃር በኦሮሚያ ክልል ብቃቱ ኖሯቸው ይህን እድል ያላገኙ ወጣቶችን በማሰባሰብና የፈጠራ ስራዎቻቸውን በማቀናጀት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መፍትሄ የሚጡ ስራዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የገበያ ትስስር እንዲያገኙ፣ ብድር እንዲመቻችላቸው መንገዱን ለመጥረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
“ባለፉት ቀናት በ16 የሙያ ዘርፎች ትልቅ ውድድር አዘጋጅተናል። ከዚህ ውስጥ ሰባቱ በተለያዩ ቴክኖሎጂ አይነቶች ናቸው” ያሉት አቶ አደም፤ ከቀደሙት ሁለት ዓመታት አንፃር ሲታይ በዚህ ውድድር ትልቅ ለውጥ መታየቱን ይናገራሉ። ባለሃብቶች፣ ባንኮችና የተለያዩ ድርጅቶችም ከኢንተርፕረነሮቹ ጋር ተቀናጅተው ለመስራትና ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን ይገልጻሉ። የሙያ ልማት አገርን እንደሚቀይር ሁሉም መግባባት ላይ በመድረሱ አሁን በክልሉ መልካም ጅምሮች እየታዩ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
“የቴክኖሎጂና የስራ ፈጠራ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ከዋናው ችሎታቸው በተጨማሪ ልዩ ልዩ ብቃቶችን ማዳበር ይኖርባቸዋል” የሚሉት የቢሮ ሃላፊው፤ በተለይ የሰሩትን ቴክኖሎጂ በምን መልክ ወደ ገበያ ማውጣትና አቅም መፍጠር እንዳለባቸው፣ ራሳቸውን እንዴት ማስተዋወቅ እንደሚችሉና የግንኙነት አድማሳቸውን ማስፋት እንደሚኖርባቸው ክህሎቱ ሊኖራቸው ይገባል ይላሉ። ለዚህ ደግሞ የኦሮሚያ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ይገልፃሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኦሮሚያ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ላለፉት ሶስት ዓመታት የፈጠራ ባለሙያዎችን፣ አሰልጣኞችን፣ ኢንተርፕራይዞችንና የተለያዩ ተቋማትን በመለየት “የክህሎትና ስራ ፈጠራ” ስልጠናዎችን ከመስጠት አልፎ ውድድሮችን እያዘጋጀ እውቅና እየሰጠ ይገኛል። እንደ ሸገር ኢንተርፕራይዝ ለተሰኙና በግል ባለሃብቶች ጥምረት ለተመሰረቱ ተቋማት የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን ከሚፈጥሩ ወጣቶችና ታዳጊዎች ጋር እንዲገናኙ ያመቻቻል። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ስንቄ ባንክ ካሉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጥሩና ለስራዎቻቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ድልድይ በመሆን ይሰራል።
በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡ ተሸላሚዎች የወርቅ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል፤ እንደየደረጃቸውም የገንዘብ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014