በአሁኑ ሰአት ጉዳዬ ተብለው፣ በአግባቡ፣ በአጀንዳነት ከሚንሸራሸሩት ሀሳቦች አንዱ ”ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለው ሲሆን፤ ”ምን?” ብለን የመጠየቃችን ጉዳይም ይህንኑ ከመጠየቅና እንዲብራራም ከመፈለግ እንጂ በአጀንዳው ለመራቀቅ አይደለም። ለዛሬው የመረጥኩት ርእሰ ጉዳይ ምን መነሻ ይሄው ”ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለው ሲሆን፤ ጉዳያችን በርእሳችን ”ምን?” በማለት ያነሳነውን በመጠየቅ ላይ የሚያተኩር ነው።
”ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እማይመረት ነገር አለና ነው ’ምን?’ ተብሎ የሚጠየቀው” የሚል ቆራጥ መልስን የያዘ ቆራጥ ጥያቄ ቢነሳ ትክክል መሆኑን ከመቀበል ጋር ”ምንም” ብሎ ከመመለስ በስተቀር ምርጫ የለም። አዎ፣ ልስራ፣ ላምርት፣ ላትርፍ … ብሎ ለተነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም የማይመረት ምርት አይነት የለም።
ኢትዮጵያ እኮ ሁሌም የምትወቀሰው ባለማምረት እንጂ በሚመረት ምርት ማጣት አይደለም። ሁሌም ንትርኩ ”አትሰሩም፤ ብትሰሩ እኮ …” የሚል ነው። ”ካናዳ ይዝነብ እንጂ …” ተብሎ ሁሉ እስኪቀለድብን ድረስ በስንፍናችን ያልተሳለቀ የለም። ሌላው ቀርቶ ”ኢትዮጵያ ብትሰራ ኖሮ ከቱሪዝም በምታገኘው ሀብቷ ብቻ የአፍሪካን ህዝብ መቀለብ ትችላለች” የሚል ጥናት አደባባይ ከበቃና እጅን ከንፈር ላይ አስጭኖ ካስደመመ እድሜው አንድ አስር ሊሞላው የቀረው ጥቂት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስንዴ ሰብል ጉብኝታቸው ወቅት “ሰፊ የሚለማ መሬት፣ የሰው ጉልበትና እንዲሁም ውሃ እያለን ከውጭ አገራት ስንዴ ሸማች መሆን ልንቀጥል አይገባም” ማለታቸው ያው ”ኢትዮጵያ ታምርት” ማለታቸው ሲሆን፤ ሰፊ የሚለማ መሬት፣ የሰው ኃይል/ጉልበት፣ ውሃ … የሚሉትን ከስራቸው አስምረን ወደ ሌላው እንሂድ። (ምናልባት ለትህትና ሲባል ”ስንዴ ሸማች” ይበሉ እንጂ ”ስንዴ ለማኝ” አይደለንም ማለት አይደለምና ከዚሁ ለመውጣት ከሚያግዙት መንገዶች አንዱ ”ኢትዮጵያ ታምርት”ን እንደ መርህ ይዞ መጓዝ መሆኑን መያዝ ያስፈልጋል።)
ግብርና ሚኒስቴርም ”የስንዴን ምርታማነት በ2011 ካለው 2ነጥብ7 ሜትሪክ ቶን በሄክታር መጠን በ2015 ወደ 4 ሜትሪክ ቶን በሄክታር ለማሳደግ፤ እንዲሁም በ2011 ወደ አገር ውስጥ የገባውን 1ነጥብ7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በ2015 ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።
እንዲሁም፣ ባለፈው ወር “በአማራ ክልል በዘንድሮው በጋ በመስኖ የለማውን 41 ሺህ ሄክታር መሬት በቀጣይ ዓመት ወደ 150 ሺህ ሄክታር በማሳደግ ለአገራዊ የስንዴ ልማት ግብ መሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ” መነገሩን፤ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ እርስቱ ይርዳው “ኢትዮጵያ በስንዴ ልመና የምትኖር ሳይሆን ከራሷ ተርፋ ለሌሎች የምትሸጥ አገር መሆን እንደምትችል በተግባር ማሳየት ይገባል” ማለታቸውን አስምረንበት ከግብርናው ዘርፍ እንውጣና እንደገና ”ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እማይመረት ነገር አለ” ወደ’ሚለው እንዝለቅ።
”ሁሉም አካባቢውን ቢያፀዳ ፓሪስ በአንድ ቀን ትፀዳ ነበር” የሚል ነገር ስንሰማ ነው የኖርነው። ስንሰማ የመኖራችንን ያህል ግን ለሙከራ ያክል እንኳን ተግባራዊ ልናደርገው አልቻልንም። ምን ለማለት ነው፣ ሁሉም አካባቢውን ቢያለማ (ለነገሩ የፌደራሊዝም ስርአት ዋና አላማው ይህ ነበር) ነገሩ ከዛሬው ”ኢትዮጵያ ታምርት” ገና ድሮ ባለፈ ነበር።
ከተሰራ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይመረት ምንም ነገር የለም። ማእድኑ መች ተነካ፤ አገር በቀል እውቀቱ መች በሻይ ማንኪያ እንኳን ተጨለፈ፤ የእንስሳት ሀብታችን በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ መች ዋለ? ዓሣውን ማእበል እያንገላታው አይደል እንዴ? ባለሙያዎቹ ”Human capital” የሚሉት የሰው ሀብት/ኃይላችን ስራ ላይ ውሏል ወይስ እየባከነ፣ ባክኖም እያባከነ ይገኛል? ተፈጥሮ ያደለችንን የአየር ንብረትስ ተጠቅመንበታል? (ይህ ጸሐፊ ለስራ ጉዳይ ያነጋገራቸውና ከቻይና የልማት እንቅስቃሴ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው አንድ የስራ ኃላፊ ”ቻይና እንደ ኢትዮጵያ ያለ የአየር ንብረት ቢኖራት ኖሮ (አመቱን ሙሉ የሚያሰራ ማለታቸው ነው) የት በደረሰች ነበር” ያሉትን እዚህ ጋ ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል።) የኤኮቱሪዝም ሀብታችንስ እየለማ ነው፣ ወይስ እየወደመ? ባህላዊ ህክምናችን የቱ ጋ ነው ያለው?
ወደ ከተሞቻችን ስንመጣስ፣ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች አሉን እንዴ? በውድ የተገዙ መኪኖች እንጂ በዝቅተኛ ካፒታል እንኳን የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች አሉን? ”ርካሽ” የሰው ሃይል እንጂ ባለሙያዎችን እያፈራን ነው? ከሚወድመውና ከሚለማው፣ ማለትም ከሚመረተውና ከማይመረተው የቱ ይበልጣል? መጠየቅ ”ቀላል” ከሆነ ብዙ መጠየቅ ይቻላልና ጉዳዩን አፍሪካዊ እናድርገው።
እዚህ ላይ ነገሮችን ጠቅለል አድርጎ ለማየት የአፍሪካ ህብረት ጥናትና ድምዳሜን መጥቀሱ ተገቢ ነው። የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት ያስችለው ዘንድ ሊታደግባቸው የሚቻሉትን ዘርፎች በሁለት ከፍሎ ያየ ሲሆን፤ እነሱም ”Hard power” እና ”Soft power” ናቸው።
የመጀመሪያው ግብርናን ጨምሮ ተያያዥ የሆኑትን የሚያካትት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በባህል ዘርፉ፣ በተለይም በኪነጥበቡና ሥነጥበቡ ዘርፍ ያሉት ናቸው። እንደ ድርጅቱ ማጠቃለያ ይህ ሁለተኛው ዘርፍ (Soft power) አፍሪካ ውስጥ ጭራሽ ያልተነካ ዘርፍ ሲሆን፤ የውጪ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ቢሰማሩ እጅግ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ለአህጉሪቱም ከፍተኛ ሀብትና ሰፊ የስራ እድል እንደሚያስገኙ ያስረዳል።
ማጠቃለያችንን ግብርና ሚኒስቴር ስትራተጂክ እቅዱን ለማሳካት ”የግብርና እና የገጠር ልማት ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ ተግዳሮቶቹ፣ አበረታች ሁኔታዎች እና አስፈላጊ የማሻሻያ እርምጃዎች” በሚል ርእስ ባስጠናው (አጥኚው ጌታቸው ዲሪባ (ዶ/ር) ናቸው) ሰነድ ላይ መግቢያ ያደረገውን ጥቅስ በማድረግ በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ላይ ያተኮረውን ጽሑፋችንን እናጠቃልል፤
ትክክለኛውን መንገድ ካገኘነው ራዕያችንን ማሳካት እንችላለን። ከዕውቀት ማነስ በስተቀር ወደፊት ለመጓዝ የሚያግደን መሰናክል በጭራሽ አይኖርም። ድንገተኛ አደጋም ሆነ ድርቅ ተአምራዊ አይደሉም፤ በቁጥጥራችን ስር ሊውሉ የሚችሉ ናቸው። ለወደፊት ብሩህ ተስፋ ያልታደልን ፍጡሮችም አይደልንም፤ ሰላም በእጃችን ነው። ከሞት በኋላ ያለውን ገነት ብቻ ማለም አይኖርብንም፣፤ በቴክኖሎጂ ኋላ ቀርነትን አስወግደን አገራችንን ምድራዊ ገነት በማድረግ ኑሮን ማጣጣም ይቻለናል”። (ዩቫል ኖሃ ሀራሪ፣ ሆሞ ደስ፡ የነገ አጭር ታሪክ፣ 2007፡ 200)። ለዛሬው አበቃው፤ ሰላም!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014