ታላቁ የዓለም ዋንጫ በተመረጡ የዓለማችን ከተሞች እየዞረ ይገኛል። ጥቂቶች ብቻ ለመሳም የታደሉት ይህን ታላቅ የስፖርቱ ዓለም ዋንጫ ለማየትም ይሁን ለመሳም ያልታደሉ ዓለማት ውስጥ የሚገኙ የስፖርቱ አፍቃሪዎች እንዲመለከቱትና አብረውትም የማስታወሻ ፎቶ ግራፍ እንዲያስቀሩ በተመረጡ የዓለማችን ከተሞች በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ጉዞ ያደርጋል። በኳታር ከሚስተናገደው የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ አስቀድሞ ይህ ታላቅ ዋንጫ ከሚዘዋወርበት አምስት የአፍሪካ ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ በመሆን በታሪክ ለሦስተኛ ጊዜ መዳረሻ ሆናለች። በኮካ ኮላ አማካኝነትም ይህ ታላቅ ዋንጫ የዓለም ዋንጫን ለማንሳት ከበቁ ታሪካዊ ኮከቦች አንዱ ከሆነው ብራዚላዊው ጁሊያኖ ቤሌቲ ጋር ባለፈው ማክሰኞ አዲስ አበባ ደርሶ ሐሙስና አርብ በመስቀል አደባባይ ለሕዝብ እይታ ይፋ ተደርጓል። ቀደም ሲል ይህን ዋንጫ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል የተባለው ግን ፈረንሳዊው ዴቪድ ትሬዝጌት ነበር። ሆኖም ባልተገለፀ ምክንያት ቀርቷል። እኛ ግን ቀደም ብሎ የስፖርት ቤተሰቡ ይጠብቀው የነበረው ትሬዝጌትና የዓለም ዋንጫ ትዝታዎቹን በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ከብዙ በጥቂቱ የሚቃኝ ይሆናል።
ከፈረንሳይ ከሚመዘዝ የዘር ሃረግ ከተገኙት የቀድሞ የአርጀንቲና እግር ኳስ ተጫዋች አባቱ ጆርጅ ትሬዝጌት በፈረንሳይ ሩይን ኖርማንዲ የተወለደው ዴቪድ ትሬዝጌት የልጅነት ሕይወቱን ያሳለፈው በአርጀንቲናዋ መዲና ቦነስአይረስ ነው። የእግር ኳስ ሕይወትን አንድ ብሎ የጀመረውም ገና የስምንት አመት ታዳጊ እያለ በክለብ አትሌቲኮ ፕላቴንሴ ነው። የለጋነት ዕድሜውን በበርካታ ስልጠናዎች አልፎም እኤአ በ1994 በአንደኛ ዲቪዚዮን ለሚሳተፈው ክለቡ ተጫውቷል። ከአንድ አመት ቆይታ በኋላም ራሱን በፈረንሳዩ ሊግ በሚሳተፈው ሞናኮ ክለብ ራሱን አገኘ። የብሔራዊ ቡድን አጋሩንና ታሪካዊውን ፈረንሳዊ አጥቂ ቴሪ ሆንሪን የተዋወቀውም በሞናኮ አብሮ የመሰለፍ ዕድሉን ሲያገኝ ነው። ትሬዝጌት ከሞናኮ ጋር በነበረው ቆይታ የሊጉን ዋንጫ እኤአ በ1996/97 ካነሳ በኋላ 2000 ላይ በእግር ኳስ ሕይወቱ ትልልቅ ታሪኮችን ወደሠራበት የጣሊያኑ ክለብ ዩቬንቱስ በ20ሚሊዮን ፓውንድ ተዘዋውሯል። በሞናኮ በነበረው ቆይታ በ93 ጨዋታ 52 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ትሬዝጌት ከሞናኮ ጋር ሁለት የሊግና ሌሎች ክብሮችን መጎናጸፍ ችሏል።
በአዲሱ ክለቡ ዩቬንቱስ አስደናቂ ብቃቱን ማሳየት የቀጠለው ትሬዝጌት እኤአ በ2001/2002 የውድድር አመት ሃያ አራት ግቦችን በማስቆጠር ክለቡ የሴሪ ኤውን ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የኮከብ ግብ አግቢ ሽልማትን ማሸነፍ ችሏል። ይህም ብቻ ሳይሆን በውድድር አመቱ አሮጊቷ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የሁለተኛው ዙር ተፋላሚ ለመሆን ስትበቃ ትሬዝጌት በአስር ጨዋታ ስምንት ግቦችን በማስቆጠር አስደናቂ ታሪክ መስራት ችሏል።
ትሬዝጌት በቀጣይ የውድድር አመት ከጉዳት ጋር እየታገለ ክለቡን ባገለገለባቸው ጥቂት ጨዋታዎች የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻለ ሲሆን፣ ዩቬንቱስ በቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ ለመሆን ሲበቃ በአስር ጨዋታዎች አራት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። በአጠቃላይ ትልቅ ስም በገነባበት ዩቬንቱስ በ245 ጨዋታዎች ተሰልፎ 138 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ይህም በክለቡ ታሪክ አራተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አድርጎታል። ትሬዝጌት ዩቬንቱስን ከተሰናበተ በኋላም በስፔን፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ አርጀንቲናና ሕንድ በማምራት ለተለያዩ ክለቦች መጫወት ችሏል።
የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን እኤአ ከ1998 እስከ 2008 ባገለገለባቸው አስር አመታት በሰባ አንድ ጨዋታዎች ሰላሳ አራት ግቦችን ከመረብ ያዋሃደው ትሬዝጌት በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ደረጃዎች ከ18፣20፣21 አመት በታች በተለያየ ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል። በተለይም እኤአ በ1997 የፊፋ ወጣቶች ዓለም ዋንጫ ላይ አገሩን መወከሉ በቀጣዩ አመት 1998 ላይ የያኔውን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ወርቃማ ስብስብ እንዲቀላቀል መንገዶችን የጠረገለት ሲሆን በዚያ የውድድር አመት በትልቁ የዓለም ዋንጫ ትልቁን ታሪክ ለመጋራት አብቅቶታል።
ከምን ጊዜም የእግር ኳስ ታሪካዊ ኮከቦች ዚነዲን ዚዳን፣ ቴሪ ሆንሪ፣ ፓትሪክ ቬራ፣ ዲዲየር ዴሾ፣ ሊሊያን ቱራም፣ ኢማኑኤል ፔቲት፣ ቢዜንቴ ሊዛራዙና ሌሎችም የዚያን ዘመን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ወርቃማ ትውልድ ጋር የ1998 የዓለም ዋንጫን ያነሳው ትሬዝጌት ሌላም አስደናቂ ታሪክ አለው። በተለይም በ2000 የአውሮፓ ዋንጫ ፈረንሳይ ቻምፒዮን በነበረችበት የፍጻሜ ፍልሚያ ጣልያንን በጭማሪ ሰዓት ሁለት ለአንድ ስትረታ የማሸነፊያዋን ወርቃማ ግብ በማስቆጠር የሠራው ታሪክ ዛሬም ድረስ ይታወሳል። ትሬዝጌት ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ጋር የዓለምና የአውሮፓ ዋንጫ ክብሮችን ካሳካ በኋላም በ2002 እና 2006 የዓለም ዋንጫ፣በ2004 አውሮፓ ዋንጫ ለብሔራዊ ቡድኑ መሰለፍ ችሏል። ትሬዝጌት በ2000 የአውሮፓ ዋንጫ ፈረንሳይ ጣልያንን በጭማሪ ሰዓት በወርቃማ ግብ ሕግ ስታሸንፍ ታሪክ የመስራቱን ያህል ከስድስት አመት በኋላ በ2006 የዓለም ዋንጫ መጥፎ ትዝታ አለው። የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ወርቃማ ስብስብ የጉብዝናው ዘመናት እየደበዘዘ በሄደበት ወቅት በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ስብስቡ የመጨረሻውን የዓለም ዋንጫ ለመሳም እስከ ፍጻሜ የደረሰ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል። ከስድስት አመት በፊት በአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ በወርቃማው ግብ ጉድ ያደረጋት ጣልያን በጀርመኑ ዓለም ዋንጫ ፍጻሜም ከፈረንሳይ ጋር ተገናኝታለች። አስደናቂው አጥቂ ዚዳን የጣልያናዊውን ተከላካይ ማታራዚን ደረት በግንባሩ ሆን ብሎ በመነረት ሜዳ ላይ የዘረረበት የማይረሳ ታሪክ በታየበት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ቻምፒዮኑን ለመለየት ተጨማሪ ሰላሳ ደቂቃ በቂ አልነበረም። ሁለቱ ቡድኖች ታላቁን ዋንጫ ለመሳም ወደ መለያ ምት አመሩ። በአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ወርቃማ ግቡ ፈረንሳውያንን ጮቤ ያስረገጠው ትሬዝጌት በዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ጣልያንን ዳግም ጉድ መሥራት አልቻለም። የመለያ ምቱን ሳተ። ጣልያንም ቻምፒዮን በመሆን ትሬዝጌት ከስምንት አመት በኋላ ዳግም የዓለም ዋንጫን የሚስምበት ዕድል መከነ።
ትሬዝጌት ፊፋ በሕይወት ካሉ 100 የምንጊዜም ምርጥ ኮከቦች ዝርዝር ውስጥ ያካተተው ታሪካዊ ተጫዋች ሲሆን በ2015 ታሪካዊ ኮከብ ተብሎ የወርቅ ጫማ ለመሸለም በቅቷል።
ቦጋለ አበበ