ግባችንን ሰላም እና ዴሞክራሲ አድርገን ስንነሳ፤ መንገዳችን ሰላማዊ፣ አካሄዳችን ዴሞክራሲያዊ ይሆናል። መዳረሻችን ሁሉን አቀፍ ነጻነት ሆኖ ስንነሳ፤ መንገዳችን የሃሳብ ልዕልና የሚናኝበት የአዋቂዎች መተላለፊያ ይሆናል። የጉዟችን ፍጻሜ ሁሉን አቀፍ ከሆነ ብልጽግና ከፍታ ላይ ማረፍ ከሆነም፤ ርምጃችን በጥንቃቄና በማስተዋል የተሞላ፣ አካሄዳችንም ጅምሮችን በማፍረስ ሳይሆን መሰረቱን እያጸኑ ከፍ አድርጎ መገንባት ላይ ያተኮረ ይሆናል። እነዚህ ሁሉ ግን መነሻችን እውነት፤ ምልከታችን አገርና ሕዝብ፤ ማረፊያችን ከፍታ ሲሆን ብቻ የሚገለጡ ሃቆች ናቸው። ከዚህ በተቃራኒው ሲሆን ግን ከሀገርና ሕዝብ ይልቅ ቡድንና ግለሰብ ይነግሳሉ፤ ከእውነትና ሰላም ይልቅ ቅጥፈትና ሴራ ይገዝፋሉ።
በዚህ ረገድ ተነጋግሮ ከመግባባት ይልቅ ነፍጥ አንግቶ መሸፈትን፤ ከሰላም ይልቅ ኹከትን፤ ከወንድማማችነትና አብሮነት ይልቅ የመሳሪያ ምላጭ ስቦ መግደል መገዳደልን፤… ምርጫው አድርጎ ጫካ የገባው የሕወሓት ቡድን፤ በ17 ዓመታት የሽፍትነት ጉዞው አያሌ ግፎች፣ ጭፍጨፋና አሰቃቂ የግጭት አውዶችን ፈጥሮ ብዙዎችን ለመከራ ዳርጓል። ከደደቢት በረሃ እስከ መሃል ሸዋ አዲስ አበባ እልፍ በደሎችን እየፈጸመ፣ የበዙ የሰብዓዊ ቀውሶችን እያስከተለ፣ ለትውልድ ክፉ አሸራን ያኖሩ የጥፋት መንገዶችን መርጦ ተጉዟል።
ከ17 ዓመታት የግጭት፣ የውድመትና የጥፋት ጉዞው ማግስት በውጪው ኃይል ድጋፍና እገዛ ላይ ተንጠልጥሎ ለመንግሥትነት የበቃው ይህ የሕወሓት የጥፋት ቡድን፤ የሚመራትን ሀገር ሳይወድ፣ የሚመራውን ሕዝብ ሳያከብር 27 ዓመታትን በሥልጣን ላይ ቆየ። እነዚህ 27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ግን በሽምቅም፣ በግንባርም ሲፈጽመው ከቆየባቸው የ17 ዓመታት የጫካ ሕይወቱ የከፋ የሴራ እና የሰብዓዊ ቀውስ ዓመታት ሆነው ያለፉ ነበሩ። ምክንያቱም ሀገር ሳያውቅ ሀገር እንዲያፈርስ በውጪ ኃይሎች ድጋፍ ለስልጣን የበቃ ቡድን ዓላማውም ግቡም ሀገር ማፍረስ ስለነበር ሀገር ለማፍረስ ያስችሉኛል ያላቸውን የጋላቢዎቹን የቀደመ ሴራ ወደመተግበር ገባ።
ለዚህ ደግሞ ቀድሞ ሀገራዊ ስሜትን ማጥፋትና የብሔር ማንነትን ማግነን ዋናው ሥራ አደረገ። ይሄ በፈጠነ መልኩ እንዲጓዝለትም በሕዝቦች መካከል የኖረው አብሮነትና ወንድማማችነት በቂምና ቁርሾ እንዲተካ የሚያስችለውን ተረክ ከፍ አድርጎ ማስረጽ፤ አብሮነትና ወንድማማችነት በመጠራጠርና በመገፋፋት እንዲተካ ክፉ ዘር መዝራት የሥራው ሁሉ ቀዳሚ ሆነ። ይሄን የተቀበሉ ወዳጅ፤ ይሄን እንቢኝ ብለው የቀደመ አንድነትና ወንድማማችነትን እናጽና ያሉ “የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፣ ጽንፈኛ፣ አሸባሪ፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣…” በሚል ተቀጽላ መሳደድ፣ መታሰር፣ መንገላታት፣ መፈናቀል፣ መገደል፣… እጣ ፈንታቸው ሆነ።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አንዴ በብሔር፤ ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ካባ በተሽሞነሞኑ ሴራዎች እዚህም እዚያም ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ በሕዝቦች ግጭት የራስ ፍላጎትን የማሳካት መንግሥታዊ አቅሙን ለጥሩ ትወና ተጠቀመበት። አማራውን ከኦሮሞ፣ ጉራጌውን ከስልጤ፣ ሲዳማውን ከወላይታ፣ አፋሩን ከሶማሌ፣… እርስ በእርሱ እንዳይተማመን እና እንዲጋጭ አደረገው። ጨርሶ እንዳይጣላም የመንግሥትነት በትሩን ተጠቅሞ የሰላም ማስከበር ጣልቃ ገብነትን ይተገብራል። ይሄ የብሔር ቅብ ግጭት ፋታ ሲያገኝ፣ ነገር ግን የሰላም ነፋስ ሳይነፍስና ሕዝቡ ለምን ብሎ መጠየቅ ሳይጀምር ሌላ የብሔር ወይም የሃይማኖት ጥግ ይዞ ግጭት የሚፈጥር ክብሪት ይጭራል። ይሄም ገፍቶ ወደለየለት ግጭት ሳያመራ የተለመደው የአስታራቂነት ድራማው ይቀጥልና፤ ይሄን ችግር ማርገቢያ በሚል የሀብት ማሰባሰብ ይከወናል። እግረ መንገድም የሚፈለጉ ተቀናቃኝ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተለቀሙ ወደ ዘብጥያ እንዲወርዱ ይደረጋል።
በዚህ መልኩ ያዝ ለቀቅ እያለ ከግጭት የማትረፍና በግጭት ውስጥ እየኖሩ ዓላማን የማሳለጥ መንገድ በሂደት ለዘብ ማለት እንደጀመረ የሕዝቡን አንድነት ወደ ቀደመው አብሮነቱ መራመድ ጀመረ። ይሄ ጅምር ወደ መናበብ ሲሸጋገር የእኔ የሚሉትን አማራጭ ማማተር ጀመሩ። ይህ ወቅት ምርጫ 1997 ዓ.ም የሚከወንበት ነበርና ሕዝቡ የሴራና ግጭት ጉዞው እንዲያበቃ የመናፈቁን ውሳኔ ያሳየበትን ምርጫ ከወነ። ይህ ግን በሕወሓት ቡድን ውስጥ ያልተጠበቀ ነበርና ድንጋጤን ፈጠረ፤ ድንጋጤውም የቡድኑን ግጭት የኑረቱ መሰረት አንኳር አውድ መሆኑን ተገንዝቦ በዚሁ ላይ የበለጠ እንዲሰራ አደረገው። እናም ከምርጫ 97 ማግስት ግጭቶች በረከቱ፤ ሞት፣ መፈናቀል፣ አካል መጉደል፣ አፈና፣ እስርና እንግልት መዋቅራዊ አውድ የተፈጠረላቸው እስኪመስል እንደ ሰደድ ተቀጣጠሉ።
በዚህ መልኩ ግጭት፣ ሞት፣ አካል ጉዳት፣ መፈናቀል፣ የከፋ ሰብዓዊ እንግልት፣ እስርና ቶርቸር፣… ልኩን አልፎ የሕዝብን ትዕግስት እስኪፈታተት ለአስር ዓመት ዘለቀ። ሆኖም ሞት ሞትን እንዲጋፈጥ፤ መገፋት መግፋትን እንዲለማመድ፤ መሰቃየት ስቃይንና አሰቃይን አሽቀንትሮ እንዲጥል የግድ ያለውን ሕዝባዊ እንቢተኝነት በመላው ኢትዮጵያ እንዲገለጥ፤ እንቢተኝነቱም ለውጥ እንዲወለድ አደረገ። ይህ ለውጥ ደግሞ የቡድኑን በግጭት ውስጥ ተደላድሎ የመኖር የጥፋት ጉዞውን የሚገታ ነበር።
ሆኖም የሕወሓት የጥፋት ኃይል በለውጡ ማግስት በተላላኪዎቹም በራሱም አቅም ታግዞ ንፁሃን ዜጎች በግፍ እንዲገደሉ በማድረግ በጅምላ በመቅበር አገራዊ ስጋት ለመፍጠር ሰፊ ጥረት ያደረገበት ወቅት ሆነ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ያረጋገጡትም ይሄንኑ እውነት ነበር።
ለምሳሌ፣ ዓርማ የሌለውን ሰንደቅ ዓላማም እንዲሁ ንጹሃን ዜጎችን ለማጥፋትና ለማሳቀቅ ሲጠቀምበት የነበረው የሕወሓት የጥፋት ቡድን፤ ከለውጡ በፊት የነበረውን የሕዝብ ማዕበል ለማፈን ሲያደርገው በነበረው ሴራ የኦነግን ዓርማ በገፍ በማሳተምና ዓርማውን የያዙ ሰዎችን የኢሬቻና መሰል በዓላት በሚከበሩበት ስፍራ በማስገባት ጭምር ንጹኃን ዜጎችን ለማፈን ተጠቅሞበታል። በለውጡ ሂደትም በመሪዎች ላይ ክትትል ማድረግ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም እስከ የእስር ማዘዣ ማውጣት የደረሰ አስጨናቂ የደህንነት ክትትል ሲያደርግ ነበር።
ይሄንኑ ሴራውን ከለውጡ በኋላም በማስቀጠል ቂም፣ በቀልና ጥላቻን በመተው በይቅርታ የመሻገርን ጉዞ፤ አቃፊ አገረ መንግስት የመገንባትን ትልም፤ የተሻለ ሃሳብ ይዞ ለአሸናፊነት የመብቃትን ፍላጎት በመግፋት የኖረውን የአውዳሚ ግጭት ጉዞውን የሙጥኝ ማለትን መረጠ። በዚህም በወቅቱ በጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ ላይ እንደተመላከተው፤ ቡድኑ ሕልውናው በግጭቶች ውስጥ የተመሰረተና አትራፊነቱም በዚሁ ላይ እንደመሆኑ ከመጋቢት 2010 እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም እስከፈጸመው የአገር ክህደት ተግባሩ ድረስ 113 ግጭቶችን በመላ ኢትዮጵያ ላይ አስነስቷል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንዳመላከተው ደግሞ፤ የሕወሓት የጠፋት ኃይል ለዘመናት ሲሰራው የነበረውን ጸረ-ህዝብና ጸረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባሮቹ በኢትዮጵያ ህዝቦች ፊት በተጋለጡበት ለውጥ ማግስት ከአፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ድርጊቱ ከመጋቢት 2010 እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ምየሀገር ክህደት ተግባሩ ድረስ 113 ግጭቶችን በመላ ኢትዮጵያ ላይ አስነስቷል። በእነዚህ ግጭቶች ብሔርን ከብሔር፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት፣ መንግሥትን ከሕዝብ፣…ወዘተ ለማቃቃር በፕሮፖዳንዳ፣ በፋይናንስ፣ በሎጀስቲክስና በሥልጠና የተደገፉ አውዳሚ ግጭቶችን ፈጥሯል። በግብሩ ልክ የቀረጻቸውን ‹ሳተላይት አሸባሪዎች› በአራቱም ማዕዘናት ለጥፋት ተልዕኮው አሰማርቶ መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችን ወግቷል። ረፍት ነስቷል። በትህነግ እኩይ ሴራ ደም ያልፈሰሰበት የኢትዮጵያ ግዛት አካል የለም።
በዚህ መልኩ የግጭት ማዕከል ካደረጋቸው አውዶች አንዱ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው። ለምሳሌ፣ በ2012 የትምህርት ዓመት በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶችን እና ያደረሱትን ጉዳት አስመልክቶ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የተባለ ተቋም ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ በየዩኒቨርሲቲዎች በተነሱ ግጭቶች 12 ተማሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ58 ተማሪዎች በላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህ በተጓዳኝ በ28 ዩኒቨርሲቲዎች ቀላል እና ከባድ ግጭቶች በመስተዋላቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ መስተጓጎል ፈጥሮ ነበር።
ለምሳሌ፣ ጥቅምት 30 ቀን 2012 በወልዲያ በተከሰተ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በሕዳር ወር 16 በሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶች ተስተውለዋል። ግጭቶቹም የብሔር መልክ ያላቸው ሲሆን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሐሰተኛ መረጃዎች ግጭቶቹን የማቀጣጠል ሚና እንደተጫወቱም ተመላክቷል።
ይሄን መሰል የብሔር ግጭቶችን እዚህም እዚያም በመቀስቀስና ከግጭቶቹ ትርፉን በማስላት ሌላ የግጭት አውድ እየፈጠረ መኖር ልዩ ባህሪው የሆነው የሕወሓት የጥፋት ቡድን፤ ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉት በሁሉም የኢትዮጵያ አከባቢዎች ላይ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ አድርጓል። በዚህም ንጹሃን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል እንዲሁም ሃብት ንብረታቸውን ለማጣት ተዳርገዋል። ይሄንንም፤ “113 ግጭቶች ሲፈጠር በሁሉም ክልሎች ግጭት አለ፤ በሁሉም ክልሎች መጋደል አለ፤ በትግራይ ክልል ግን የለም። እነርሱም አያፍሩም እኛ ብቻ ነን ሰላም ይላሉ ። እዚህ ያለውን የሚያደፈርሱት እነርሱ ስለሆኑ ሁሌ የኛን ቁስል ፤ የሌሎችን ቁስል እየቆሰቆሱ በከፍተኛ ደረጃ ህዝቡን አባሉት፤” ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሳይቀር የተናገሩትም ለዚሁ ነው።
ይሄን የሕወሓት የግጭት ነጋዴነት ተግባር በተመለከተ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ከለውጡ ማግስት በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ብቻ ከተከሰቱ 113 ደም አፋሳሽ ግጭቶች መካከል፤ በኦሮሚያ 37 ደም ያፋሰሱ፣ ያፈናቀሉ እና ንብረት ያወደሙ ግጭቶች ነበሩ። በተመሳሳይ በአማራ 23 ደም ያፋሰሱ ግጭቶች የደረሱ ሲሆን፤ በቤኒሻን ጉልጉሙዝ ክልልም በተለይ የሚጠቀሱትን የመተከልና ዳንጉር ግጭቶችን ጨምሮ 15 ግጭቶች ተከስተዋል።፡
በጋምቤላ የስደተኞችን ካምፕ ጨምሮ 7 ግጭቶች ሲከሰቱ፤ በደቡብ ክልል በኮንሶ፣ በጌድዮ በጉራ ፈርዳ ንጹሀን እንዲገደሉ ንብረት እንዲወድም ያደረጉ ግጭቶች ተስተውለዋል። በሶማሌ ክልል ጅጅጋ፣ አበፋር፣ በድሬዳዋ፣ሲበዳማ እና በሀረሪ ክልሎችም መሰል ግጭቶች ነበሩ። አዲስ አበባም ብትሆን 14 ግጭቶች ተከስተውባታል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድም ቀን በትግራይ ክልል ግጭት ተከስቶ አለማወቁ ነው የተመላከተው። ይህም በእርግጥም የሕወሓት የጥፋት ቡድን የራሱን ሕልውና ባስጠበቀ መልኩ የሚፈጽማቸው ግጭቶች በሌሎች ሞትና ስቃይ የማትረፍ ግልጽ ተግባራቱ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
በዚህ ሁሉ ግጭትና ጥፋት ውስጥ የሚፈልገውን ትርፍ ማግኘት ያልቻለው የሕወሓት የጥፋት ቡድን የመጨረሻ አማራጭ አድርጎ የያዘውን ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ያሳካልኛል ወዳለው ርምጃ ነው የገባው። ይሄም በተላላኪዎቹ በኩል አልሆን ያለውን በራሱ ወደመፈጸም እና ይሄንንም የአገር አጥር የሆነውን ኃይል በመናድ ማሳካት ነበር። እናም ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አባላት ላይ በተኙበት ጥቃት ፈጸመ። በዚህም ግጭቶችን በመፍጠር ትርፍ ማግኘትን ብቻ ሳይሆን፤ ከዛ ከፍ ያለ አገር አፍርሶ የዘመናት ቅዠቱን እውን በማድረግ ውስጥ የሚገኝ ትርፍን ከፍ አድርጎ ማጣጣምን ምን ያህል ጥሙንና የባንዳነት ገጹን አደባባይ አወጣ። ተግባሩም ከግጭት ፈጣሪነት ከፍ ብሎ አገርን ወደ የጦር አውድነት የቀየረ ሆነ። መንግሥትም በመጀመሪያ ሕግ ለማስከበር ጦሩን አሰማርቶና እስከ መቐለ አዝልቆ የቡድኑን ሴል እንዲበጣጥስ ግድ አለው።
በዚህ ሂደት ግን አሸባሪው ሕወሓት የበቀል በትሩን በንጹሃን ላይ በማሳረፍ ነበር ወደዋሻው የፈረጠጠው። ለዚህ ትልቁ ማሳያ የማይካድራው በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ሲሆን፤ መከላከያ ሰራዊቱ እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ጭምር እግር በእግር እየተከታተሉ ድባቅ ባይመቱት ኖሮ በሌሎችም አከባቢዎች ከማካድራው የባሰ ጭፍጨፋ ይፈጽም እንደነበር ጥሏቸው ያለፋቸው የግፍ ዱላዎቹ ምስክር ሆነዋል። ይህ አልበቃ ያለው የግጭት ነጋዴው ሕወሓት መከላከያ ሰራዊት ድሉን ተጎናጽፎ ለሰብዓዊነት ሲባል ከመቐሌ እንዲወጣ በተደረገ ማግስት ለሌላ ጥፋት ራሱን አደራጅቶ በመሰማራት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ፈጸመ።
በዚይ ወቅትም ሌላ ከሕዝቦች ሞትና ስቃይ የማትረፍ አረመኔያዊ ተግባሩን አስመሰከረ። ከቆቦ እስከ አንፆኪያና ገምዛ፤ ከንፋስ መውጫ እስከ ባቲ፤ ከጋሊኮማ እስከ ካሳ ጊታ፤ በሁሉም በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው ሥፍራዎች ንጹሃንን በጅምላ ጨፍጭፏል፤ ሴቶችን በቡድን ደፍሯል፤ በወንዶች ላይም ግብረሶዶም ፈጽሟል፤ ብዙዎችን ለከፋ የአካል ጉዳት ዳርጓል፤ ሥነልቡናዊ ስብራትም ፈጽሟል፤ በመቶ ቢሊዬኖች የሚቆጠር ሃብት ንብረት ዘርፎና አውድሞ ኢኮኖሚያዊ መሰረቶቻቸውን አናግቷል፤ ዛሬም ድረስ በአስር ሚሊዬን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ዳርጎ የሰው እጅ ጠባቂ አድርጓል።
በ1960ዎቹ ማገባደጃ ላይ ጣታቸውን ምላጭ ላይ አሳርፈው ጫካ የገቡት እነዚህ ከግጭት አትራፊ ኃይሎች፤ ግማሽ ምዕተ ዓመት የሚሆነውን ዘመናቸውን በዚሁ ተግባራቸው ተጉዘዋል። በዚህም አያሌ ወገኖችን ለሞት፣ በርካቶችን ለዘላቂ አካላዊና ስነልቡናዊ ጉዳት፣ በርካታ የሃገር ሃብት ለውድመት ሲዳርጉ፤ በአንጻሩ እነሱ ከግጭቶቹ ጀርባ ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም ግላዊ ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ ኖረዋል። ይህ ግማሽ ምዕተዓመት የዘለቀው ግጭት እየጫሩ ከሚነደው እሳት የመሞቅ አካሄድ፤ ዛሬም በእድሜያቸው መጨረሻ ላይም ፀሐይ እየጠለቀችባቸው መሆኑን ሲያውቁ እንኳን ሊታገስላቸውና ፊታቸውን ለጸጸትና ንሰሃ ሊመልሰው አልቻለም። ይልቁንም የመጨረሻ አማራጮቻቸውን አንጠፍጥፈው በመጠቀም የብሔር እንቢ ሲላቸው የሃይማኖት ግጭቶችን ደግማው ደጋግመው እየሞከሩ ሲከሽፍባቸው ማየታችን የተለመደ ሆኗል።
ከሰሞኑ ፍትህ ሚኒስቴር በጥናት ተረጋገጠ ባለው መረጃ እንዳሳወቀውም፤ አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች ጀርባ የአሸባሪው ሕወሓት እጅ እንዳለበት አረጋግጧል። በመረጃው እንደተመላከተውም፤ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የግጭትና አለመረጋጋት ክስተቶች ተስተውለዋል። በተለያዩ ምክንያቶች በተከሰቱት ግጭቶች የበርካታ ወገኖች ህይወት ሲያልፍ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል ተከስቷል። በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ከፊት ሆነው ተሳታፊ የነበሩ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙም ተደርጓል። ሆኖም በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶችን መንስኤ ለማጣራትና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በተደረገው ምርመራ የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት እጆች መኖራቸው፤ የሽብር ቡድኑም ግጭቶቹን በጦር መሳሪያና በበጀት በመደገፍ እና ስምሪት በመስጠት ስለመሳተፉ ተረጋግጧል።
ይህ የሚያሳየው ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት ትናንት በጫካ፤ በኋላም በመንግስትነት ሥልጣኑ፣ ዛሬም በሽብር ተግባሩ ሀገር እንዳትረጋጋ፣ ሕዝብም በግጭት ውስጥ ሆኖ እረፍት እንዳያገኝ በማድረግ ከግጭቱ ጀርባ የራሱን ሕልውና ማቆየት ላይ ተጠምዶ የኖረና ያለ መሆኑን ነው። ይሁን እንጂ ይሄን አይነት ሕልውናን በግጭት ውስጥ የማቆየት እና በአገር፣ በሕዝብ ብሎም በአገር ሃብት ጭዳነት የመቆመር ጉዞ ሊበቃው፤ ለዚህም መላው ኢትዮጵያውያን እውነቱን ተገንዝበው ሊታገሉት፤ የትግራይ ሕዝብም ይሄን የሞት ጠማቂ ኃይል ነጥሎ ሊያወጣው ይገባል። ይህ ሲሆን ሀገር ትረጋጋለች፤ ሕዝቦች ሰላም አግኝተው በፍቅርና በወንድማማችነት አብረው መኖር ችላሉ። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን፤ ሰላም!
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2014