አገራችን ኢትዮጵያ ልብ አጥታለች። ልብ ስላችሁ ደረታችን ስር ያለውን ማለቴ አይደለም ቀናውን የሚያይ ልብ እንጂ። ይህን አይነቱ ልብ ደግሞ ለሰዎች አስፈላጊ ነው። ለምን ቢሉ፣ ልብ የርህራሄ ምልክት ነው። ልብ የእውነትና የፍቅር ማደሪያ ነው። ልብ ከአእምሮ የላቀ የፍቅር ስፍራ ነው። ልብ በፍቅር፣ አእምሮ ደግሞ በሀሳብ እስካልተሞሉ ድረስ አገር ታታሪ ነፍሶች አይበቅልባትም። አእምሮ እና ልብ ድርና ማግ ናቸው። ልብ ማፍቀር ሲሳነው አእምሮ ማሰብ ያቆማል። ልብ ጥላቻን ሲማር አእምሮ ክፉ ሀሳብን ይማራል። እኛ የልብ እና የአእምሯችን ጥንስሶች ነን። በነዚህ ሁለት ሀይሎች ተደምረን ነው ሰው የሆነው። ሰውነታቸውን ለአገራቸው ገብረው ታረክ የጻፉ አያሌ ነፍሶች በዙሪያችን አሉ። በዚያው ልክ ደግሞ ከእውነትና ከሰውነት ሸሽተው ልባቸውን የክፋት ማደሪያ ያደረጉም አይጠፉም።
እኛስ ምን አይነት ነን? በልባችንና በአእምሯችን ውስጥ ምንድነው ያለው? አገራችን የምትፈልገን ነን ወይስ ሌላ ነን? ራሳችንን ለአገራችን የተገባን አድርገን መፍጠር አለብን። በአእምሯችን ክፉ ሀሳብ እጆቻችን ነውር የሚሰሩ ከሆነ፣ በልባችን ክፉ ምኞት እግሮቻችን ወደ ክፉ የሚሮጡ ከሆነ፣ ጆሮዎቻችን መጥፎ፣ አይኖቻችን እኩይ የሚያዩ ከሆነ ገና አልበቃንም። ገና አልሰለጠንም። አይደለም ለአገራችን ለራሳችንም ያልበቃን ነንና ራሳችንን አፍርሰን መስራት ይኖርብናል። ምክንያቱም አገር የዜጎች እጅ ስራ ናት። አንድ ጥበበኛ ሰዓሊ እውቀቱንና ምናቡን ተጠቅሞ አንድ ውብ ስዕል እንደሚሰራ ሁሉ አገራችንን ውብ አድርገን የምንሰራውም እኛ ነን።
አገራችንን እንደምንፈልገው አድርገን ለመስራት መዶሻውም ሚስማሩም እኛው ጋ ነው ያለው። መዶሻና ሚሰማራችን ሀሳብና እውቀት፣ ፍቅርና አንድነት ናቸው። መዶሻና ሚስማራችን ይቅርታና ወንድማማችነት ናቸው። መዶሻና ሚስማራችን ትህትናና እግዚአብሔርን መፍራት ናቸው። ብዙ አይነት መዶሻና ሚስማር እያለን በህብረት ቤት መስራት ሳናውቅበት በከንቱ ኖረናል። አሁን ጊዜው ቤት የመስራት ነው። አሁን ጊዜው ለሁላችን የምትበቃን ኢትዮጵያ አምጦ መውለድ ነው። አሁን ጊዜው የመተቃቀፍ ነው። በመነቋቆር የብቻ ቤት የምንሰራበት ሳይሆን በመነጋገር የጋራ ታሪክ የምናበጅበት ነው። ለትውልድ የተገለጡ አእምሮና ልብ ያስፈልጉናል። እውነት የተጻፈባቸው፣ ፍትህ የደመቀባቸው የሰውነት ብራናዎች ያስፈልጉናል። ፍቅርን የሚሰብኩ፣ መቻቻልን የሚዘምሩ አንደበቶች ያስፈልጉናል። ነውርን የሚጸየፉ፣ ጨዋነትን የሚናገሩ አንደበቶች ግድ ይሉናል። በደልን የማይቆጥሩ ይቅር የሚሉ ልቦች ያሹናል። በእውቀት የሚራመድ፣ በምክንያት ከፍ የሚል አእምሮ ያስፈልገናል። ይቅር ለእግዜርን የሚያውቁ አስታራቂ ሽማግሌዎች እንዲበዙልን እንፈልጋለን።
አገር በአእምሮ ተጠንስሳ፣ በልብ የምትፈጠር፣ በተግባር የምትጸና የሁላችን የቤት ስራ ናት። በዚህ መነሻና መድረሻ ውስጥ አገርን ከነሙሉ ክብሯና፣ ነጻነቷ ጋር የሚፈጥሩልን በልባችንና በአእምሯችን ውስጥ ያስቀመጥናቸው በጎ መንፈሶች ናቸው። በጎ መንፈስ ሁልጊዜም የበጎ አእምሮና ልብ ነጸብራቅ ነው። ሰው ለራሱ በጎ ሲሆን በዙሪያው ላሉ ሁሉ በጎ ነው የሚሆነው። በጎ መሆን ማለት ራስን ወዶ ሌሎችን መውደድ ማለት ነው። በጎ መሆን ማለት ራስን አፍቅሮ ሌሎችን ማፍቀር ማለት ነው። በጎ መሆን ማለት ራስን አክብሮ ሌሎችን ማክበር ማለት ነው። በዚህ ሁሉ የጋራ በጎነት ውስጥ አገር ነው የምንፈጥረው። ትውልድ ነው የምንቀርጸው። ልብ እንዲወድ፣ እንዲምር፣ ቸርነትን እንዲያደርግ የተፈጠረ ነው። ልብ ለሌሎች ደስታ እንዲሆን፣ ለሌሎች በረከት እንዲሆን የተሰራ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ በጎ ማሰብና በጎ ማድረግ ተስኗቸው ራሳቸውን በመርዘኛ ሀሳብ መርዘው ሰውነታቸውን አውሬ ያደረጉ አሉ። ሰው ፍቅርን ካልተማረ በራሱ ላይም በሌሎች ላይም አውሬ መሆን ይችላል። ሰው አውሬ ሲሆን ጥፋቱ ብዙ ነው። ሰው አውሬ ሲሆን ፍቅር ምን እንደሆነ አያውቅም። ሀይሉ ጥላቻና በቀል ይሆናል። ማሸነፊያው እልህና ማንአለብኝነት ይሆናል። ሰው አውሬ ሲሆን ሌሎችን ለማሸነፍ የሚሮጠው በሀይልና በጉልበቱ ነው የሚሆነው። ሰው አውሬ ሲሆን እኔ ያልኩት ብቻ አመለካከት ውስጥ ነው የሚቆመው።
ልብ ፍቅርን ሲያውቅ እንደ እየሱስ ነው። ልብ ጥላቻን ሲማር እንደ ዲያቢሎስ ነው። እኛ ምርጫችንን ነን። እኛ ራሳችንን ያደረግንውን ነን። በሀሳባችንና በድርጊታችን አውሬም ሰውም መሆን ይቻለናል። አሁን ላይ አገራችንን እያሰቃየናት ያለው በልባችን ውስጥ ባጨቅንው ክፉ ሀሳብ ነው። እየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ ሰላሳ ሶስት አመት ሲኖር ፍቅርን ብቻ ነበር ሲያስተምር የነበረው። ፍቅርን የማያውቁ ክፉ ሰዎች ሲያሳድዱት በምህረት እያሸነፈ፣ በይቅርታ እየረታ ነበር አምላካዊ ሰውነቱን የጨረሰው። እኛስ ጥሩ አስበን እንደ እየሱስ ባለማዕረግ መሆን ለምን አቃተን? በመልካም ልብ ፍቅርን አውርተን፣ ፍቅርን ተናግረን ሰው መሆን ለምን ተሳነን? በክፉ ሀሳባችን ራሳችንን አውሬ ማድረግ የለብንም። ለማፍቀር ነው የተፈጠርነው። በዙሪያችን ያሉትን ለማቀፍ ነው ሰው የሆንነው። ሰው ፍቅርን ካወቀ ምንም ባይገባው ጠቢብ ነው። ልብ ፍቅር ካለው ምንም ቢጎድለው ሙሉ ነው። እኛም በፍቅር ጽዋ እንሞላ። በእውነት ጸጋ እንትረፍረፍ።
የአገር ስቃይ የትውልድ ስቃይ ነው። የአገር ስቃይ የዜጎች ስቃይ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ለነፍሳቸው ኩነኔን፣ ለልባቸው ሀጢአትን፣ ለሰውነታቸው አረመኔነትን ባስተማሩ ባንዳ ሀይሎች ስትጎዳ ኖራለች። እኚህ ነፍሶች፣ እኚህ ልቦች፣ እኚህ ሰውነቶች አገርን ከማስነወር፣ ህዝብን ከማስጨነቅ ሌላ ትርፍ የላቸውም። እኛ ትርፋችን ያለው መዋደድ ውስጥ ነው። ፍቅራችን ያለው መቻቻል ውስጥ ነው። ደም ባልነኩ፣ ጥላቻ ባላስነወራቸው ጸዐዳ ጣቶቻችን ልቦቻችን ላይ ወንድማማችነትን እንጻፍ። ይሄ የታሪክ ድርሳን በልጆቻችን እየተገለጠ ሲነበብ የት ቦታ ምን እየሰራን እንደነበር አስረጂ ይሆናል። ፍቅር እኮ መድኃኒት ነው። ምን ያክል ጥያቄ፣ ምንም ያክል ቅሬታ ቢኖርብንም በፍቅር መድረክ ላይ በመልካም አንደበት መነጋገር እንችላለን። ልቦቻችንን ለፍቅር እንግለጥ። ለአንድነት እንክፈት።
የተገለጡ ልቦች….
የተገለጡ ልቦች ክፉ ሀሳቦችን፣ ክፉ ምኞቶችን፣ ክፉ ተግባራትን ማንበርከኪያ ጥበብ ናቸው። የተገለጡ ልቦች ክፉ ሰውነትን፣ እኩይ ስብዕናዎችን መርቻ መንገድ ናቸው። ኢትዮጵያ አገራችን ከትላንት እስከዛሬ በዚህ ግልጥ ማንነት ጠላቶቿን ስታንበረክክ ኖራለች፤ አሁንም የተነሱባትን የውስጥና የውጭ ጠላቶቿን በዚህ መንገድ እንደምታሸንፍ ስነግራችሁ ከልቤ ነው። የተገለጡ ልቦች ሰብዓ ሰገል የጌታን መወለድ ሊያዩ ከሩቅ ምስራቅ እንደመጡ ሁሉ የኢትዮጵያ ልጆችም አገራቸው ኢትዮጵያን ሊያርሱ፣ ኢትዮጵያዊነትን ሊቀልሙ እንደ ሰብዐ ሰገል ትንሳኤዋን ብለው ከሩቅና ከቅርብ ሲሰባሰቡ ነው። ልብ ማረፊያውን ሲያገኝ ደስ ይላል፤ ነፍስ ከእትብቷ ውቅያኖስ ስትቀዝፍ ያኔ ሰውነት ያብባል። እንደ አገርና ወገን ማን አለ? ነፍሶች ስውር ሀቃቸውን የሚገልጡት በአገር ነው፣ ልብ የነጻነት ድሉን የሚቀዳጀው ከወገኑ አጠገብ ሲቆም ነው። ያለ አገርና ህዝብ ሰውነት ምንም ነው። ይሄ ሊገባን ይገባል። የልብ መገለጥ ለአገር ጥሪ፣ ለወገን መከራ ምላሽ መስጠት ነው።
ልብ ስለ አገር ሲያዜም ደስ ይላል፣ ቀልብ እናት አገር ላይ ሲያርፍ ደስ ይላል። የሁሉም የሰው ልጅ የነፍሱ ማረፊያ አገርና ህዝብ ነው። በበጎ ሀሳባችን ተገልጠን ሰላም ላጣችው አገራችን ሰላም እንሁናት። የተገለጡ ልቦች ነውር አያውቁም፣ ለወገን የተገለጡ ልቦች ፍትህ አያጓድሉም። ለኢትዮጵያ መገለጥ ስቃይዋን መሰቃየት፣ ችግሯን መቸገር ነው። ለኢትዮጵያ መሰቃየት በደስታዋ መደሰት፣ በትንሳኤዋ እልልታ ማሰማት ነው። ዳር ቆሞ ማጨብጨብ፣ ወደነፈሰበት መንፈስ ለኢትዮጵያ መገለጥ አይደለም። ለአገር በመኖር ውስጥ ያለውን ክብር፣ ለወገን በመቆም ውስጥ ያለውን ፍሰሀ ልባችሁን ገልጣችሁ እዩት። በምንም የማይገኙ ትላልቅ ደስታዎች በልብ መገለጥ ውስጥ የተደበቁ ናቸው። በምንም የማይተኩ የነፍስ ፈንጠዝያዎች በልብ መገለጥ ውስጥ የተቀመጡ ናቸው። የአገር መገለጥ የትውልድ መገለጥ ነው። የአገር መነሳት የእኔና የእናንተ ብርሃናዊ ነገ ነው። ይሄ ሁሉ እንዲሆን ግን ከሁሉ በፊት እኛ ስለአገራችን ልቦቻችንን መግለጥ ይኖርብናል። ስለኢትዮጵያ ክፉ አላይም፣ ክፉ አልሰማም፣ ክፉም አልናገርም ስንል ልባችንን በክፉዎች ላይ እናጽና።
አገር ስትታመም እኛ ነን የምንታመመው፣ አገር ስትስቅ ህዝቦቿ ናቸው የሚስቁት። እኛ የአገር ደስታ ማረፊያዎች ነን። የአገር ታሪክ በትውልዱ ላይ የሚያርፍ ነው። መገፋፋት ያበላሸውን ኢትዮጵያዊነት ማደስ ይኖርብናል። ጥላቻ የመረዘውን ታሪካችንን ማስተካከል ግዳችን ነው። ባለመነጋገር የራቀንን ሰላም መመለስ ቀሪ የቤት ስራችን ይሆናል። እኛ ለአገራችን ስር ግንድና ቅርንጫፎች ነን። አገራችንን ዋርካ የምናደርጋት እኛ ነን። የምዕራባውያኑን የተንኮል ሩጫ ጥሰን፣ የብሄር ካባ የለበሰ ፖለቲካችንን አስተካክለን፣ ወንድማማችነትን አግንነን፣ በተባበረ ክንድ የጋራ ቤታችንን መስራት ይኖርብናል።
ስለ አገራችን ልባችንን እንግለጥና በአገራችን በኩል ለራሳችን እንኑር። ለአገር መልፋት ለራስ መልፋት ነውና። ለአገር መድከም ለራስ መድከም ነውና። ለአገራችሁ የምትሰስቱት አንዳች ነገር እንዳይኖር ሆናችሁ ተነሱ። ልብን መግለጥ ራስን መግለጥ ነው። ስለ አገርና ህዝብ ልብን መግለጥ ራስን መስጠት ነው። ራስን ለአገር እንደመስጠት ያለ ስጦታ የለም። አገር አርነት የምትወጣው ራሳችንን ስንሰጥ ነው። ራሳችንን ሰስተን የምንፈጥረው አገርና ህዝብ የለም። በሀሳብና በምክክር እስካልተወጣነው ድረስ የአገራችን አሁናዊ ችግር ዳር ቆመን የምንወጣው አይደለም። ልብን መግለጥ ያስፈልጋል።
ራሳችሁን ለአገራችሁ ስጡ፤ ራስን ለአገር መስጠት ራስን ከባዕድ አስተሳሰብ ነጻ ማውጣት ነው። አሁናዊ ችግሮቻችን እልባት የሚያገኙት ራሳችንን ለውይይትና ለአንድነት ስንገልጥ ነው። የተገለጠ ልብ የአንድነት ክንድ ነው። የተገለጠ ልብ አገሬን ለማንም አሳልፌ አልሰጥም የሚል ወኔ የነቀነቀው ነው። ልባችንን በመግለጥ መርህ ወደፊት ልንሄድ ይገባል። ከመቼውም ጊዜ በላይ ልባችንን የምንገልጥበት ጊዜ ላይ ነን። ከገንዘባችን፣ ከእውቀታችን፣ ከጊዜያችን ለአገራችን የምናዋጣበት ጊዜ ላይ ነን። ያለንን ሁሉ እየሰጠን አገራችንን ወደፊት የምናራምድበት ሰሞን ላይ ነን። አላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሰራዊት በአንድ ልብ የምንቆምበት የፈተና ጊዜ ላይ ነን።
በእኛ የአንድነት ግፊት ከፊታችን ያለውን ዳገት እንሻገር። ምርኩዛችን ደግሞ ሰላም ነው። ፍቅር ነው። አንድነት ነው። ጦርና ጎራዴ ሳንመዝ በተከፈተ ልብ ብቻ ወደረኞቻችንን መርታት እንችላለን። አገራችንን የምናፈቅር ከሆነ ልባችንን እንክፈትላት። የመለያየት ጉድፋችንን እያጸዳን ከሰላም ውጭ ምንም አማራጭ እንዳይኖረን ሆነን እንኑር። ህዝባችን በሚፈልገን ቦታ ላይ ሁሉ መገኘት አለብን። ኢትዮጵያ በምትፈልገን ስፍራ ላይ ሁሉ መቆም ግዴታችን ይሆናል። በዚህ የአብሮነት መንፈስ ውስጥ የምትፈጠረውን ኢትዮጵያ ሁላችንም እንናፍቃታለን።
ትላልቅ አገራት በትላልቅ ሀሳብ የተፈጠሩ ናቸው። ዘመናዊና ስልጡን ህዝቦች በዘመናዊና ተራማጅ አስተሳሰብ የተፈጠሩ ናቸው። እኚህ ሁሉ ስፍራቸው ክፍት አእምሮና ልብ ነው። ክፍት አእምሮና ልብ የዘመናዊነት መፈጠሪያ ቦታ ነው። ሰው ሌሎችን ለመፍጠር ከመሞከሩ በፊት መጀመሪያ ራሱን በበጎ ሀሳብ መፍጠር አለበት። ራሳችንን በበጎ ሀሳብ መፍጠር ከቻልን በጎ ቤተሰብ፣ በጎ ጓደኛ መፍጠር አያቅተንም። በጎ ቤተሰብ ደግሞ የበጎ ማህበረሰብ መነሻ ነው። በጎ ማህበረሰብ ደግሞ አገር ነው። በአሁኑ ሰዓት አገራችን የሚያስፈልጋት በጎ ሀሳብ ብቻ ነው። የበጎ ሀሳብ መብቀያ ማሳ ደግሞ በጎ ልብ ነው። በበጎ ልብ አገራችንን እናብቅል ስል ላብቃ። ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2014