ጊዜው ከባድ ነው። አገራችን ያለችበት ሁኔታ ህዝብን ለተለያየ አይነት ችግሮች ያጋለጠ ሆኗል። ጦርነት ፤ ኮሮና ፤ ድርቅ ፤ የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ መወደድ ፤ ስራ አጥነት ፤ ስርአት አልበኝነት እና ሌሎችም ችግሮች በአገር ደረጃ የተከሰቱ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች ዜጎችን ለብዙ አይነት ቀውስ እያጋለጡም ነው። ጦርነቱ መላው ኢትዮጵያዊን ነክቷል ማለት ይቻላል። የጦርነቱ ዳፋ ለኢኮኖሚው ተርፎ ኢኮኖሚው እየተንገዳገደ ነው። ቀድሞውንም ኮሮና ጎድቶት የነበረው ኢኮኖሚ ላይ ጦርነት ሲደመር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው የሆነው። ይባስ ብሎ በ40 አመታት ውስጥ ያላጋጠመ ድርቅ ተጨምሯል። የኑሮ ውድነት ከቁጥጥር በላይ የሆነ ይመስላል። እነ ኦነግ ሸኔም የህዝብን ኑሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እያረጉት ነው።
ይህ ሁሉ ችግር በህዝብ ስነ ልቡና ላይ ጫና እንደሚኖረው ግልጽ ነው። ጥናቶችም ለዚህ ብዙ ማስረጃ ያቀርባሉ። ከመሰል ክስተቶች መፈጠር በኋላ ድብርት ፤ ጭንቀት ፤ የስሜት መዋዠቅ እና ሌሎች ስነ ልቡናዊ ችግሮች አሁን ላይ የሚጠበቁ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ነገሮች እንዳሉ ሆነው አሁን ደግሞ ህዝብን ለሌላ ራስ ምታት የሚያጋልጡ ይዘቶች ተበራክተዋል። ከነዚህ ዋነኛው ደግሞ የዩቲዩብ መረጃዎች ናቸው።
ዩቲዩብ ቀድሞም ቢሆን በኛ አገር አለአግባብ ከተጠቀምንባቸው የቴክኖሎጂ ግኝቶች መሀከል አንዱ ነው። ለጥቂቶች የስራ እድል እና የሀብት ምንጭ መሆን ቢችልም ለብዙዎች ግን የራስ ምታት መንስኤ ሆኖ ነው የቆየው። ማንኛውም ዜና ዩቲዩብ ላይ ሲቀርብ ጥቂት መረጃ ከብዙ ፈጠራ እና ብዙ ማጋነን ጋር ተደርጎ ነው። በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ ሰለባ ሆነው ኖረዋል።
በሌላው ጎን ከስርአት ባፈነገጠ መልኩ የግለሰቦች ኑሮ ሲበለት የሚውለበትም ቦታ ዩቲዩብ ነው። አሁን ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አዲስ የማይጠቅም ይዘት እየተበራከተ ነው። ይህም ግለሰባዊ ያፈነገጡ የወሲብ ክስተቶችን በቃለ መጠይቅ ማቅረብ ነው።
እስኪ እነዚህን ርእሶች ተመልከቷቸው።
“ወንድ ስትሪፐሮችን ማሰልጠን ስራዬ ነበር”
“በጥቅም ተታልዬ የኢሉሚናንቲ ማህበር ውስጥ ገብቼ አሁን መውጣት ብሞክር ስቃዬን አበዙብኝ”
“ሆቴል ውስጥ ተዋውቄው የወደድኩት ሰው ወደቤቱ ከወሰደኝ በኋላ ወደ ሰው ጅብ ተቀየረብኝ”
“የገዛ ፍቅረኛዬ በጓደኞቹ አስደፈረኝ!”
“ባለቤቴ ነው ያልኩት ሰው በውድቅት ሌሊት ወደ ሰው ጅብ ተቀይሮ ከቤት ሲወጣ አየሁት”
“ፍቅረኛዬ ያልኩት ሰው ከገዛ እናቴ ጋር አንሶላ ሲጋፈፍ እጅ ከፍንጅ ያዝኩት”
እንግዲህ አሁን ላይ በዚህ መልኩ የሚቀርቡ ብዙ ከዚህ በላይ አሰቃቂ እና አስጨናቂ ርእስ የተሰጣቸው ይዘቶች ዩቲዩብ ላይ በብዙ ሰዎች በብዙ መልኩ ተበራክተው እየቀረቡ ያሉት። አዘጋጆቹ እንደሚሉት እንዲህ አይነት ፕሮግራሞች የሚቀርቡት ህብረተሰቡ እንዲማር እና እንዲጠነቀቅ ሲሆን አብዛኞቹ ጉዳዮች ግልጽ ወንጀል በመሆናቸው አንዳንዶች አዘጋጆች ጥፋት ፈጻሚውን ወደ ፖሊስ ተጠቂውን ደግሞ እርዳታ ወደሚያገኝበት እንደሚያደርሱ ይናገራሉ።
በእርግጥም ሰዎቹ እንደሚሉት አድርገው ከሆነ ጥሩ ነው። ህብረተሰብም ከዚህ ትምህርት ወስዶ ከሆነ መልካም ነው። በማይካድ መልኩ ፕሮግራሞቹ ብዙ ተመልካች አላቸው። ነገር ግን በነገሩ ከሚማሩ ይልቅ የሚደነግጠው እና ስነ ልቡናዊ ጫና ውስጥ የሚገባው ሰው እንደሚበረክት ከስር የሚሰጡት ኮመንቶች ምስክር ናቸው።
“አኡዙቢላህ የማይሰማ ጉድ የለም ዘንድሮ”
“ወይ ዘንድሮ ምንድነው የምሰማው ኧረ ኡኡኡ አምላከ እስራኤል ማረን ይቅር በለን”
“ዘመኑ የአራዊት የእንስሳ ዘመን ነው:: እግዚአብሔር ይፍረድባቸው::”
ጠቅላላ አስተያየቶቹ እንዲህ አይነት ናቸው። ብዙው ሰው የሰማውን ነገር ከዚህ ቀደም እንኳን ሊሰማ ሊደረግ ይችላል ብሎ እንኳን የማያስባቸው የነበሩ ነገሮች ስለሆኑ ብዙዎቹ አስተያየቶች በድንጋጤ የተሰጡ ናቸው። ይህም ማለት እነዚህ የዩቲዩብ ይዘቶች አሁን ላይ ካላቸው የማስተማር እሴት ይልቅ የማስደንገጥ አቅማቸው አይሏል ማለት ነው። እንግዲህ አሁን ላይ በጦርነትም፤ በረሀብም፤ በኑሮ ውድነት፤ በስርአት አልበኝነትም በሌላም ለምትታመስ አገር እና በነዚህ ችግሮች ከፍተኛ ጭንቀት
ውስጥ ላለ ህዝብ እንዲህ አይነት ሌላ ራስ ምታት የሚፈጥር ግለሰባዊ ችግር መጨመር ፋይዳው ምን ይሆን?
እርግጥ ጥቂቶች በዚህ መልኩ ደፍረው ወጥተው በመናገራቸው መፍትሄ አግኝተው ሊሆን ይችላል። ህዝብ ታሪካቸውን ሰምቶ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ነገሮች እንዳይስፋፋም አድርጎ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአብዛኛው አዬ ጉድ እንዲል፤ ዘመኑን እንዲጠላ፤ ሰውን ሁሉ እንዲጠራጠር፤ ለካ እንዲህም ይደረጋል ብሎ እንዲገረም እና ለወሬ ፍጆታ የሚሆነው ነገር እንዲያገኝ፤ በህብረተሰብ ደረጃ ጸያፍ (taboo) የሆነ ነገር የአደባባይ ምስጢር እንዲሆን ብሎም ብዙዎች እንዲለምዱት የማድረግ ያልታሰበ ውጤትም ይዞ ሊመጣ ይችላል። አንዳንዴ አንዳንድ ነገሮች ከመወራት ይልቅ አለመወራት ይጠቅማቸዋል። እርግጥ የምንኖርበት ዓለም የሰዎችን የመናገር ነጻነት ያለገደብ የሚፈቅድ ነው። ማህበራዊ ሚዲያውም ሙሉ ለሙሉም ባይሆን በአብዛኛው ይህን ገደብ የለሽ መብት ማስከበርን ታሳቢ አድርጎ የተፈጠረ ነው። ነገር ግን እኛ መጠየቅ አለብን። ይህ ጉዳይ በአደባባይ ለመወራት የሚበቃ ነው ወይ፤ አሁን ላይ መወራትስ አለበት ወይ፤ ቢወራ ተጠቃሚው ይበልጣል ተጎጂው፤ ወዘተ…እያልን መጠየቅ ይገባናል።
በተለይም በዚህ ጊዜ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ወሬ ለመስማት ዝግጁ አይደለም። በአድካሚ እና ተስፋ አስቆራጭ ወሬዎች ተሰላችቷል። ታዲያ ለዚህ ህዝብ የሚያስፈልገው የተስፋ ቃል ፤ ነገ የተሻለ ቀን እንደሚሆን የሚመክር ይዘት ፤ ዘመኑ ጥሩ ይሆናል የሚል ማበረታቻ እንጂ ሌላ ተስፋ አስቆራጭ መልእክት መሆን የለበትም። ስለዚህም እንዲህ አይነት ይዘት የምታዘጋጁ ሰዎች ይህ አስቸጋሪ ጊዜ እስኪያልፍ ሌሎች አገራዊ ይዘት ያላቸው፤ የሚያበረታቱ፤ መተማመንን የሚፈጥሩ አንድነትን የሚያመጡ ይዘቶችን ብታዘጋጁልን አይሻልምን?
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2014