በየጊዜው ስልትና አይነቱን እየቀያየረ የሚከሰተው ኮንትሮ ባንድ እና ሕገወጥ ንግድ፤ ጥቂቶች ባቋራጭ የሚከብሩበት ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ በብዙ የምትከስርበት፣ ኢትዮጵያውያንም ክፉኛ የሚጎዱበት ተግባር ነው።በየዓመቱ በቢሊዬን የሚቆጠር ሃብት የሚንቀሳቀስበት ይሕ የሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ተግባር፤ የአገርን ኢኮኖሚ የሚያናጋ ክፉ በሽታ ብቻ ሳይሆን፤ የሕዝቦችን ኑሮ የሚፈታተን፣ የአገርን ሰላምና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል የአደገኞች መክበሪያ አደገኛ መንገድ ነው፡፡
ይሄን እውነት ለመገንዘብ በዘመነ ሕወሓት/ኢህአዴግ የሆነውን መመልከቱ በቂ ነው።የሕወሓት/ኢህአዴግ 27 የሥልጣን ዘመናት ከአገር ይልቅ ቡድን፤ ከሕዝብ ይልቅ ግለሰቦች ከፍ ብለው የሚገለጡበት፣ ልቀው ሃብቱንም ሥልጣኑንም የተቆጣጠሩበት ዘመን ነበር።በዚህም ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን ግብርና ቀረጥ አልባ የንግድ ጉዞ በሴራ ታግዞ ሲያስኬድ፤ ተቆጣጣሪ የሌለው የኮንትሮባንድ መስመር ዘርግቶ የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያን ጨምሮ የወጪና ገቢ ሸቀጦችን እንዳሻው ሲያመላልስ ኖሯል።ይህ ደግሞ አገር ማግኘት ያለባትን ገቢ ያሳጣ ብቻ ሳይሆን፤ በዜጎች ሕይወት ላይ መታየት የሚገባውን ለውጥና እድገት እንዳይታይ፣ የጋራ ተጠቃሚነት እንዳይሰፍን፤ የአንድ ቡድን የሃብት ልዕልና እንዲሰፍን አድርጎታል፡፡
በዚህ መልኩ ስር ሰድዶ የኖረው የሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ታዲያ የኋላ ኋላ ከፍ ያለ አገራዊ አደጋን መጋበዙ አልቀረም።በዚህ መልኩ ሥር ሰድዶ አገርን የገፋ፣ ህዝብን የከፋፈለና የተጠቃሚነት ቦታውን ያሳጣው ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፤ በሕዝቡ ውስጥ በፈጠረው ከፍ ያለ ተቃውሞ የሕወሓት ቡድንና ጀሌው ከሥልጣኑም፣ ከኔትዎርኩም እንዲፋታ ባደረገው ጊዜ፤ ቡድኑና ግብረአበሮቹ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት መፍጨርጨር አሳይተው ነበር፡፡
ምክንያቱም በሕዝብ ብሶት እውን የሆነው ለውጥ ሕዝቦችን ለጋራ ተጠቃሚነትና አብሮነት ሲያንደረድር፤ ኮንትሮባንዲስቶችንና ሕገወጦችን አገር የማጥፋት ጉዟችሁ፣ ሕዝብ የመዝረፍ መንገዳችሁ ይብቃ ያለ ነበር።ሆኖም ዘርፎ መክበር የለመደ በአንድ ጊዜ በቃህ ሲባል እሺ ብሎ ሊቀበል ይቸግረዋልና የሕገ ወጥ ንግዱን ለማስቀጠል፣ የኮንትሮባንድ መስመሩን ለማጽናት ሰፊ ትግል አደረገ።ምንም እንኳን ችግሩ በአጭሩ ሊገታና የባሰ አደጋ ሳይፈጠር በቁጥጥር ስር መዋል ቢችልም፤ ከለውጥ ማግስት በሶማሌ ክልል የተፈጠረው ችግርም ዋናው መንስኤ ይሄው ነበር።
እንደ ሕወሓት/ኢህአዴግ ዘመን የከፋ አይሁን እንጂ፤ ዛሬም እዚህም እዚያም የሚታዩ ጥቁር ገበያን ጨምሮ ሕገወጥ ተግባራትና ኮንትሮባንዶች የአገር ችግር፣ የህዝብ ፈተና ሆነው መቀጠላቸው አልቀረም።ዓሣ ከበሃር ወጥቶ መኖር እንደማይችል ሁሉ፤ እነዚህ ሕገወጦችና ኮንትሮባንዲስቶችም ከዚህ ተግባራቸው ወጥተው መኖር የሚችሉ አይመስላቸውም።ምክንያቱም በሕገወጥ መልኩ በገፍ የተለመደ ሃብት የማግበስበስ ልምድ፤ በሕጋዊ መንገድ ተጉዞና ከሕጋዊ ነጋዴዎች ጋር ተወዳድሮ የሚገኝ አይሆንላቸውም።እናም በዚህ ተግባራቸው ለመቀጠል የተለያዩ ስልቶችና መንገዶችን በመጠቀም እዛው ሲዳክሩ መኖርን ይመርጣሉ፡፡
ለዚህም ነው ዛሬም ከአገር ይልቅ ቡድንን፣ ከሕዝብ ይልቅ ግለሰቦችን በማስቀደም ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ተግባራቸውን የቀጠሉት።የዚህ ውጤትም ነው አገርን ለውጭ ምንዛሪ ችግር፤ ህዝቦችም ለኑሮ ውድነትና ለዋጋ ንረት ተጋልጠው አሳር እያዩ ያሉት።በየቀኑ በሚሊዬኖች የሚቆጠሩ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸው፤ በየእለቱ የሕገወጥ ነጋዴዎች ያልተገባ የሸቀጦች የንግድ ልውውጥ በገበያው ላይ ጫና መፍጠራቸው የየመገናኛ ብዙሃኑ የወሬ አጀንዳ ሆኖ መዝለቁ፡፡
ከሰሞኑም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫም ይሄንኑ እውነት ያረጋገጠ ነበር።በዚህ መግለጫ እንደተመላከተው፤ የንግድ ህግና ደንብ በመተላለፍ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ለሀገራችን ኢኮኖሚ እና ህጋዊ ለሆነው የግብይት ሥርዓት ፈተና ሆኗል።ያለንግድ ፈቃድመነገድ፣ ከተፈቀድ መጠንና ኮታ በላይ ምርትን ማዘዋወርና ማከማቸት፤ እጥረትን ለመፍጠር ምርት አከማችቶ መያዝ፤ ያለበቂ ምክንያት በምርቶች ላይ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ፤ ምርቶችን አለአግባብ መሰብሰብ፣ ማከማቸትና ማዟዟር፤ የንግድ ፍቃድን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት መነገድ እንዲሁም የባንክ መላኪያ ፍቃድ ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በማዳከም ለልማትና ለዕድገት የሚደረገውን ርብርብ እየተፈታተኑ የሚገኙ ህገ- ወጥ ድርጊቶች ናቸው፡፡
ይህ ህገ-ወጥነት ደግሞ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት፣የኑሮውድነትን በማባባስ እና የሀገርን ሀብት ለጎረቤት አገራት ሲሳይ በማድረግ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል። የጥራጥሬ ምርቶች እና የቅባት እህሎችን አላግባብ በክምችት በመያዝ ሀገሪቱ በወቅቱ ከወጪ ንግድ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ከማሳጣቱም ባሻገር ምርቶች በህገ ወጥ ንግድ እና በኮንትሮባንድ መንገድ ወደ ኬንያ በመውጣት በሀገሪቱ የምግብ ሰብሎች ላይ የዋጋ ንረት እያስከተለ ይገኛል።እንደሌሎች ምርቶች ሁሉ የቁም እንስሳት ግብይትም ለህገ-ወጥነት የተጋለጠ በመሆኑ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እያገኘች አይደለም፡፡
ከወጪ ኮንትሮባንድ ንግድ በተጓዳኝ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይም መሰል ሕገወጥ ተግባራት እየተስተዋሉ ይገኛል።ለምሳሌ፣ መንግሥት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አውጥቶ በማስገባት ዓለም አቀፍ ዋጋው ላይ ድጎማ በማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ እያቀረባቸው ካሉ ምርቶች ውስጥ ነዳጅ አንዱ ሲሆን፤ መንግሥት ምርቱን ከውጭ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እና እያሰራጨ ቢሆንም በአንዳንድ የድንበር ከተሞች ከመጠን ያለፈ የነዳጅ ማደያዎች በመክፈት በውጭ ምንዛሪ የገባው የነዳጅ ምርት ለሌላ ሀገር ተሽከርካሪዎች በህገ-ወጥ መንገድ በማሰራጭት የሀገሪቱን ጥቅም እያሳጣ ነው፡፡
የሚስተዋለውን ህገ-ወጥነት እና ኮንትሮባንድ ለመከላከል ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ቢያደርግም በችግሩ ውስብስብነት ምክንያት ሊፈታ ያለመቻሉን የጠቆመው መግለጫው፤ ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት ህጋዊ ንግድን ለማጠናከርና የሀገርን ተጠቃሚነትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ የሁሉንም የሀገራችን ዜጋ፣የንግድ ተዋንያን እና የመንግሥት መዋቅር አካላትን ቁርጠኝነትና ርብርብ ይጠይቃል።በመሆኑም መግለጫው ለኅብረተሰቡ ከተገለፀበት ዕለት አንስቶ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕግ- አስፈጻሚና የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በህገ-ወጥ ተግባራት ላይ እጃቸው ያለበት ተሳታፊ እና ተባባሪ አካላት ላይ ተገቢውን ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል።
የችግሩ ተዋንያኖች ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ፣ በየደረጃው ያለው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትም ሚናቸውን በጽኑ በመወጣት የሀገርን ሀብትና ጥቅም የማስጠበቅ ግዴታቸውን እንዲወጡ አስገንዝቧል።በዚህ መልኩ ችግሩን በወጉ ተገንዝቦ ለማረም ለመስራት አቋም መያዙ መልካም ውሳኔ ነው።ይሁን እንጂ ተግባሩ ከቃል ማሳሰቢያ የዘለለ ተግባር የሚጠይቅ፤ ራስን ከችግሩ ነጻ አድርጎ እስከመጨረሻው መታገልን፤ ሕግ አክብሮ ማስከበርን፣ ላመኑበትና ለቆሙለት ዓላማ መከፈል ያለበትን ሁሉ ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል።ይህ ሲሆንም ነው ተቋም እንደ ተቋም መኖሩንም፤ ሕገ ወጥነትን የሚጠየፍና ችግሩን ለመፍታትም ቁርጠኛ መሆኑን የሚያረጋግጠው፡፡
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2014