አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ እየጨመረ ከመጣው የኮንትሮባንድ ዝውውር ጋር በተያያዘ ባለፉት ስምንት ወራት 715 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ንብረቶችን እና የውጭ አገራት ገንዘቦችን መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ።
ተጠሪነቱ ለገቢዎች ሚኒስቴር ሆኖ በቅርቡ የተቋቋመው የጉምሩክ ኮሚሽን በተለይ ለአዲስ ዘመን በላከው መረጃ እንደገለፀው፣ በ2011 በጀት ዓመት እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ በወጪ እና ገቢ ኮንትሮባንድ ግምታዊ ዋጋቸው 715 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ንብረቶች ተይዘዋል።
እንደ ጉምሩክ ኮሚሽን ጽህፈት ቤቱ መረጃ ከሆነ፤ በከፍተኛ መጠን ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከተያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች አንፃር ባለፉት 8 ወራት ገቢ ኮንትሮባንድ ግምታዊ የብር ዋጋቸው ብር 528 ነጥብ 5ሚሊዮን ብር በላይ ነው። በተመሳሳይ ከአገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙ ንብረቶች ግምታዊ ዋጋቸው 186 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል።
ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ በከፍተኛ መጠን ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል አዳዲስ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ሲጋራና የትምባሆ ውጤቶች፣ ምግብና መጠጦች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ መድኃኒቶች እና የጦር መሳሪያዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ።
በተለይ በስድስት ወራት ውስጥ 12 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ተይዘዋል። 57 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የሲጋራ እና የትምባሆ ውጤቶችም በተመሳሳይ ወደ መንግሥት መጋዘኖች ገቢ እንዲሆኑ መደረጉን መረጃው አመልክቷል።
በሌላ በኩል በኮሚሽን ጽህፈት ቤቱ መረጃ መሰረት፤ ከአገር ሊወጡ ሲሉ ከተያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል ህገወጥ ገንዘብ፣ ማዕድናት፣ ጫት እና አደንዛዥ ዕጾች ዋነኞቹና ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበባቸው ናቸው። በተለይም የጥር እና የካቲት ወራትን ሳይጨምር በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 89 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር የሆኑ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በጥር እና የካቲት ወራትም የተለያዩ የውጭ አገራት ገንዘቦች የተያዙ ሲሆን፣ በተለይ በጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በኩል ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የተለያዩ አገራት ገንዘቦች መያዛቸውን በኮሚሽኑ መረጃ ተገልጿል።
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በገቢም ሆነ በወጪ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የኮንትሮባንድ መጠን ጭማሪ ማሳየቱ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ያሳያል። ከህግ አካላት ክትትል በተጨማሪ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥቆማ መጠናከሩ የህገወጥ ተግባሩን ለማጋለጥ እየረዳ እንደሚገኝ መረጃው ጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ጌትነት ተስፋማርያም