የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አዋጆች እየተዘጋጁ ነው

አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ ባለፉት ዘመናት የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ያደረሱትን በደልና ቁርሾ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሰጥቶ ዘላቂ ሠላምን በማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የወጣውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ አምስት አዋጆች እየተዘጋጁ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የሽግግር ፍትሕ ተቋማትና ቅንጅታዊ አመራር ቢሮ ሴክሬተሪያል ጊዜያዊ ኃላፊ አቶ አወል ሡልጣን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈጠሩና አሁን ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲደረግ በመንግሥት አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ለተግባራዊነቱም ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲያስተባብር ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ በዚህም ሂደትም አምስት አዋጆችን የማዘጋጀት ሥራ ተጀምሯል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ትግበራው የመጀመሪያው ሥራ የባለሙያዎች ቡድን ማዋቀር እንደነበረ የጠቆሙት ኃላፊው፤ በፖሊሲው ትግበራ ውስጥ በማን፤ ከማን፤ እንዴት ይከናወናሉ፤ ምን ያህል በጀት ያስፈልጋቸዋል እና መሰል ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ተደርጎ ግብዓቶችን በመያዝ ረቂቅ ሰነዶችን የማዘጋጀቱ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ተግባሩን እውን የሚያደርጉ ገለልተኛና ነፃ የሆኑ ተቋማት ማቋቋም የሚያስችል አዋጅና የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱ ቀጣዩ ሥራ እንደነበር አቶ አወል ጠቅሰው፤ እየተዘጋጁ ባሉ አዋጆች ከተቋቋሙ ተቋማት መካከል ልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ሚና ጉልህ በሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ከፍተኛ የወንጀል ተሳትፎ ባላቸው ሰዎች ላይ ብቻ ምርመራ በማካሄድ፤ ክስ በመመስረት፤ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ሌላው ልዩ ዓቃቤ ሕጉ ያጠናቀረውን ምርመራና ክስ ተቀብሎ በማከራከር ፍርድ የሚሰጥ ነፃና ገለልተኛ ልዩ የሽግግር ፍትሕ ችሎት ሲሆን፤ ችሎቱን ሊያቋቁም የሚችል አዋጅ እየተዘጋጀ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

እውነትን ማፈላለግ፤ ማውጣትና እርቅ ማምጣት የሚያስችለውን ተግባር የሚያከናውነው የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽንን ለማቋቋም የሚያስችለው አዋጅ ዝግጅት ሌላኛው ተግባር ነው፡፡

ይህ ኮሚሽን የጊዜ ገደብ ሳይወስነው ማስረጃና መረጃ እስከተገኘ ድረስ በሀገሪቱ የተፈጸሙትን ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እውነትነት ሊያጣራ፤ ሊያፈላልግ፤ ስፋቱን፤ ተደጋጋሚነቱን፤ ጉዳቱንና በማን ላይ እንደደረሰ ሊያመላክት የሚችል ነው፡፡ የጉዳቱን ልክ በሚገባ ለይቶ ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠውም ነው ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነት ከዚህም የላቀ እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው፤ የደረሰውን ጉዳት እውቅና እንዲሰጠው በማድረግ ፤ በሕዝቦች መካከል እርቅ እንዲሰፍን ለማስቻል፤ ከፍተኛ የወንጀል ተሳትፎ የሌላቸውን ሰዎች በአዋጁ መሠረት ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ሲገኙ ጉዳያቸው በምሕረት እንዲታይ ለማድረግ፤ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች በማካካሻ ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ እንዲሁም ወደማገገሙ እስኪገቡ ድረስም ድጋፍ እንዲያገኙ መደላደልን እንዲፈጥር የሚያደርግ በመሆኑም ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ በሚያስችል መልኩ አዋጁ እየተዘጋጀ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

ሌላውና የተቋማት ማሻሻያ ኮሚሽንን ለማቋቋም ተብሎ የሚዘጋጀው አዋጅ እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው፤ የኮሚሽኑ ሥራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስጥ ሚና የነበራቸው ወይም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲደርስ ያደረጉ ተቋማትን ለማሻሻልና ባለሙያዎችን የመለየት ተግባራትን ማከናወን ነው፤ ይህንኑ በአግባቡ መፈጸም የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

እየተዘጋጁ ያሉት አዋጆች ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግን ታሳቢ ማድረጋቸውን አመልክተው፤ በእነዚህ አምስቱ የሕግ ማዕቀፎች (አዋጆች) ላይ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ መካሄዱን አስረድተዋል፡፡

በመዘጋጀት ላይ ከሚገኙት የሕግ ማዕቀፎች ጎን ለጎን ሌሎች ተግባራትም እየተከናወኑ እንደሆነ የሚገልጹት ኃላፊው፤ አንዱ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስትራቴጂ ዝግጅት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሌላው ደግሞ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን በሚመለከት መረጃ የሚሰጠውን አካል ለማሳተፍ የሚያስችል የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በጣም ብዙ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ሀገር የሚያደርገው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ዓለም አቀፍ ተቋማትንም ለማሳተፍ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ላይ መሳተፍ ከሚፈልጉ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሠራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ በሀገር ደረጃም ይህንን ሥራ በሚገባ ከሚያጠናክረው ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You