‹‹ የሕዳሴ ግድብ 97 ነጥብ 6 በመቶ አፈጻጸም ላይ ደርሷል›› – አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) የሕዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር

ከሕወሓት የምስረታ ታሪክ ጀምሮ ትልቅ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አላቸው፡፡ በቅርቡም የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ፖለቲካዊ ታሪክ ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም የሚል መፅሃፍ ለአንባቢያን አቅርበዋል፡፡ የቀድሞ የሕወሓት ታጋይ እና የአሁኑ የሕዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፤ የትግራይ ትብብር ሊቀመንበርም ሆነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡

አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)ን አሁን ካለው ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በማያያዝ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ቆይታ አድርጓል፡፡ በዋናነት ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እየሔደችበት ያለውን የዲፕሎማሲ መንገድ በተመለከተ፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያደረገችውን ስምምነት እና የሕዳሴው ግድብ የደረሰበት ደረጃ በሚመለከት ቆይታ አድርገናል፡፡

በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ጠመንጃ ይዘው ጦርነት ውስጥ የገቡ ቡድኖችን በተመለከተ እና ብሔራዊ ምክክሩ ላይ በማተኮር በመጨረሻም በትግራይ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ ያላቸውን አስተያየት እንዲገልፁልን ጠይቀን ያገኘነውን ምላሽ በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡-

 አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መንግስት የባሕር በርን በተመለከተ ያለውን ሃሳብ ከገለፀ በኋላ በርካታ ሀገራት ኢትዮጵያ የባሕር በር የሚያስፈልጋት መሆኑን አቋማቸውን እየገለፁ ነው:: ይህ ለውጥ እንዴት ሊመጣ ቻለ?

አረጋዊ ዶ/ር ፡– ይህ ዲፕሎማሲ ስኬቶቻችን አንዱ ማሳያ ነው:: በመጀመሪያ አገሪቷ ከነባሕሯ ስሟ ኢትዮጵያ የሚባል ነበር:: በታሪክ ሂደት ባዕዳን ወራሪዎች በተለይ ጣሊያን እና አጋሮቿ ኤርትራን በቀኝ ግዛት እንደፈጠሩ ይታወቃል:: ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችውም ሆነ ውዝግብ መፈጠር የጀመረው ከዛ በኋላ ነው:: ይህ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተፈጠረ ሁኔታ የቅርብ ጊዜ ጉዳይ ነው:: ስለዚህ ወደ ሌላ ሳንሔድ፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችው የባሕር በር ነበራት:: በዛም የባሕር በር ለዘመናት ስትጠቀም ኖራለች:: አሁንም ሆነ ወደ ፊት የራሷ የባሕር በር ሊኖራት ይገባል የሚል አቋም ብዙዎች ዘንድ አለ::

ወደ ሕግ እና ታሪክም ከተገባ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል:: ወደብ የነበረው ትልቅ አገር፤ በመቶ ሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ ያለው ሀገር ያለወደብ እና ያለባሕር በር መኖር እንደሌለበት ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ሕጎች ይጠቅሳሉ::

በሌላ በኩል የባሕር በር ያስፈልገናል ስንል እንደ ጦርነት ፈላጊዎች እና በጉልበት ማግኘት እንደምንፈልግ አድርገው የሚያስቡ አሉ:: ይህ ስህተት ነው፤ ኢትዮጵያ ጥያቄውን እያንሸራሸረች ያለችውም ሆነ የባሕር በር ማግኘት የምትፈልገው በሰላም፤ በሕግ፤ በስምምነት ነው:: አሁን አንዳንድ የገባቸው መሪዎች ለምሳሌ የፈረንሳዩ መሪም ሆነ የቱርኩ መሪ ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ እና ኢትዮጵያ የባሕር በር መፈለግ መብቷ መሆኑን እየደገፉ ነው::

ኢትዮጵያ የባሕር በር መጠየቋ ጸብ አጫሪ ስለሆነች አይደለም:: እያስከበረችም ሆነ እየጠየቀች ያለችው መብቷን ነው:: ማንም ሕዝብ መብቱን ማስከበር ይችላል:: ይህ ደግሞ ተገቢ ነው:: ይህንን ጦርነት ናፋቂ ወይም አመፅ ፈላጊ አስመስለው የሚያቀርቡ አንዳንድ ሀገራት የተሳሳቱ መሆናቸውን ቢያዩ ይመረጣል::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እየሔደችበት ያለውን የዲፕሎማሲ መንገድ እንዴት ያዩታል?

አረጋዊ ዶ/ር ፡– ኢትዮጵያ እስከ አሁን በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየሔደች ነው:: ምንም ዓይነት የጠብ አጫሪነት እና የጦርነት ፈላጊነት ሁኔታ አልታየባትም:: ሁሉም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ፣ በስምምነት እና በመግባባት እየተካሔደ ነው:: በኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ የሚታየው ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባሕል ነው:: ይህ ሁልጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያውያን መገለጫ ሆኖ የኖረ ነው::

የባሕር በርን በተመለከተም የምትሔድበት መንገድም ሰላማዊ እንደሚሆን ግልፅ አድርጋለች፤ ምናልባትም አንዳንድ የጎረቤት ሀገራት መሪዎች ያልወደዱት ይህ ይሆናል:: ሰላም የማይመቻቸው ሀገራት በዙርያችን እንዳሉ የሚታወቅ ነው:: ይህ ችግሮችን በሠላም የመፍታት አቋም ደግሞ በአንድ ወገን ብቻ የሚሳካ አይደለም:: ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ያለባትንም ግጭት በሰላም እንድትፈታ ጥረት አድርጋለች::

ሀገር ውስጥ ያሉ የትጥቅ ትግል ውስጥ የገቡ ሰዎችም ወደ ሰላም እንዲመጡ እየጠየቀች ነው:: ስለዚህ ይህ ሁሉም ነገር በሰላም እንዲፈታ ጥረት እያደረገች ያለችበት መንገድ የአገሪቷ አቋም ነው:: ኢትዮጵያ ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ ጥረት ማድረጓ ሊያስመሰግናት ይገባል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ ምስጋና ይገባቸዋል::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያደረገችውን ስምምነት እና ከባሕር በር ጋር ተያይዞ እየሄደችበት ያለውን መንገድ በተመለከተ ምን ይላሉ?

አረጋዊ ዶ/ር ፡- ከላይ እንደገለጽኩት የባሕር በር ጥያቄ የዘመናት የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው:: ሆኖም አሁን ያለው መንግስት ይህንን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ጥረት እያደረገ ነው:: ቀጣይነት ባለው መልኩ ችግሮችን በዲፕሎማሲያዊ እና በሰላም መንገድ ለመፍታትም እየሞከረ ነው:: ሶማሊያዎች በአንድ ወቅት አፈንግጠው በግብፅ አገናኝነት ወደ ኤርትራ ሔደው፤ በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ጀምረው ነበር:: ያ የተሳሳተ አካሄድ ነበር:: አሁን ከሶማሊያ ጋር ወደ ውይይት ሲገባ፤ ምንም የሚያጣላ ነገር እንደሌለ እና ችግሮች ካሉም በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል መግባባት ላይ ተደርሷል::

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የቀረበ መሆኑ፤ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት እየገባቸው ሲመጣ በሰላም መፍታት እንደሚቻል አምነው ለስምምነት ፈቃደኛ ሆነዋል:: ይህ ደግሞ ትልቅ እርምጃ ነው:: ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው ችግሮችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የመፍታት መንገድ ትክክለኛ እና ውጤታማ እንደሆነ የሚያሳይ ነው::

አዲስ ዘመን፡- የሕዳሴው ግድብ ምን ደረጃ ላይ ነው?

አረጋዊ ዶ/ር ፡– ለኢትዮጵያውያን አንዱ እና ትልቁ ስኬት ብለን ካነሳን ዋነኛው የሕዳሴ ግድብ ነው:: ግድቡ 97 ነጥብ 6 ከመቶ ሥራዎቹ ተጠናቀዋል:: ይህ ሲባል በተለይ የግድቡ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ወይም የግድቡ ግንባታ ተጠናቋል ማለት ይቻላል:: አሁን የቀረው የኤሌክትሮኒክ እና መካኒካል የሚባሉ ውስጥ የሚገጠሙ ሥራዎች ናቸው:: እነዚህ ሥራዎች ቀላል አይደሉም፤ እንዲያውም በጣም ከባድ ናቸው::

ከ13ቱ ተርባይኖች 4ቱ ሥራ ላይ ናቸው:: ገና 9ኙ ተርባይኖች መገጠም አለባቸው:: ዕቃዎቹ ከባድ እና ውድ ናቸው:: በታላቅ ጭነት በአንድ መቶ ጎማ በሚሽከረከሩ ጭነት አውቶሞቢሎች ወይም ትራኮች የሚጫኑ በመሆናቸው ይህንን ሁሉ ለመሥራት ሕዝቡ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል:: ነገር ግን በአጠቃላይ ሲታይ 97 ነጥብ 6 ከመቶ መድረሱ እና 4ቱ ተርባይኖች ሥራ ጀምረው ለሕብረተሰቡ እና ለጎረቤት አገሮች የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲካፈል መደረጉ ትልቅ ድል ነው::

በእርግጥ ብዙ እንቅፋቶች ነበሩ:: ግብፆችም ሆኑ የግብፅ ተባባሪዎች የውጪ ጠላቶች የማደናቀፍ ሙከራ አድርገው ነበር:: ነገር ግን መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ተባብሮ ሙከራዎቹ እንዲከሽፉ በማድረግ፤ የግድቡ ግንባታ በታቀደለት መንገድ እንዲሔድ እና የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ በሙሉ አቅሙ ተባብሮ ከዚህም በኋላ ፍፃሜ ላይ ማድረስ እንዳለበት ለማሳሰብ እወዳለሁ::

አዲስ ዘመን፡- የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ እና የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳታል?

አረጋዊ ዶ/ር ፡- እነዚህ ትልቅ ስኬቶች ናቸው:: የባሕር በሩ ጉዳይ ከተሳካልን፤ ደግሞም በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ስለሚካሔድ ይሳካል:: የዓለም ሕዝብ ሁሉም መብቱን ያስከብራል:: እኛም መብታችንን እናስከብራለን:: ይህ ከተሳካ የውጭ ንግድ ሥራዎች በተቀላጠፈ ሁኔታ ማስኬድ ያስችላል::

የባሕር በሩ ከተከፈተ ኢትዮጵያ ንግዷን በማቀላጠፍ ወደ ኋላ የቀረችበትን ሁኔታ ተሻግራ፤ ሌሎች ያደጉ አገሮች ተርታ መድረስ ትችላለች ማለት ነው:: አሁንም 80 በመቶ የሚሆነው የገጠሩ ሕዝብ ወጣት ወደ  ኢንዱስትሪ መግባት አለበት:: የኤሌክትሪክ ኃይል በስፋት መኖር ደግሞ የገጠር ከባድ እና ቀላል ኢንደስትሪዎችን ያስፋፋል:: ስለዚህ የኤሌክትሪክ ኃይል በብዛት ማመንጨት እና የባሕር በር ማግኘት የተያያዘ ውጤት ያመጣል::

የግድቡ መጠናቀቅን ተከትሎ 5ሺህ 500 ሜጋዋት ማመንጨት ይቻላል:: ይህ ኃይል አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ ከበቂ በላይ ስለሚሆን፤ ለጎረቤት አገሮችም ይተርፋል:: ከጎረቤት አገሮች ጋር መገናኘቱ ደግሞ ሌላ የሚያስገኘው ጥቅም አለ:: የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት ባለፈ፤ ተባብሮ እና ተደጋግፎ ለመሥራት በር ይከፍታል::

ይህ ትብብር ከተነሳ ኢትዮጵያ ወደ አስራ አንድ የሚደርሱ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አሏት:: በእነዚህ ወንዞች ላይ ብዙ የልማት ሥራዎችን መሥራት ይቻላል:: አገርን የሚመግቡ ሰፋፊ እርሻዎችን ማከናወን ይቻላል:: ስለዚህ የግድቡ መሳካት ለኢትዮጵያ ጥቅም ከማስገኘት በተጨማሪ ጎረቤት አገሮችም እንዲጠቀሙ፤ አብረን እንድንሠራ እና አብረን እንድናድግ ያደርጋል:: የሥራ ፈጠራን በማበረታታት ትልቅ የኢኮኖሚ ዕድገት ያመጣል::

አዲስ ዘመን፡- በክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ጠመንጃ ይዘው ጦርነት ውስጥ የገቡ ቡድኖችን በተመለከተ ምን ይላሉ?

አረጋዊ ዶ/ር ፡- ይሔ ከባድ ጉዳይ ነው:: ችግሮችን በጦር መሳሪያ እፈታለሁ ብሎ መነሳት ምንም አልጠቀመንም:: እስከ አሁን ድረስ ብዙ ጠመንጃ ተመዟል፤ ብዙ ጦርነት ተካሂዷል:: ብዙ ሕዝብ አልቋል:: ብዙ ንብረት ወድሟል:: በልማት ላይ መዋል ይችል የነበረ ብዙ ሃብት ተቃጥሎ በኖ ቀርቷል:: ነገር ግን ምንም ውጤት አልመጣም:: ይህንን የምናገረው ከተሞክሮ ነው::

መሳሪያ ይዞ መዋጋት የቅርቡም ሆነ የሩቁ ታሪካችን እንደሚያሳየው ያለ እልቂት ያመጣው ምንም ነገር የለም:: ጦርነት መግደል ወይም መሞት ነው:: ይህ በምርጫነት መቅረብ የለበትም:: ለመሞትም ሆነ ለመግደል ከመምረጥ ሰላምን መፈለግ ይሻላል::

ሌሎች አገሮች ችግር የለባቸውም ማለት አይደለም:: እያደጉ ያሉት ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እየፈቱ ነው:: ስለዚህ አሁን ጦር የመዘዙ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ፍለጋ ቢገቡ ለራሳቸውም ሆነ ለወገኖቻቸው በአጠቃላይ ለአገራቸው ጠቃሚ በመሆኑ ሰላምን መምረጥ ይኖርባቸዋል::

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ሠላም ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ ምን ይላሉ?

አረጋዊ ዶ/ር ፡- መንግሥት ለሕዝቡ ሰላም የማምጣት ሕገመንግሥታዊ ኃላፊነት እንዳለበት ማወቅ አለብን:: ሰላምን ማስከበር የየትኛውም መንግሥት ግዴታ ነው:: ከዚህ በመለስ አሁን ያለው መንግሥት ለሰላም ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል:: ከሰሜኑ፣ ከአማራውም፣ ከትግራዩም ሆነ ከኦሮሚያ ብዙ ትንኮሳዎች ቢኖሩም ችግራችንን በሰላም እንፍታ በማለት ከሚገባው በላይ እየተንቀሳቀሰ ነው::

ይህ የሰላም እንቅስቃሴው የበለጠ ትርጉም ሊያመጣ በሚችል መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:: ነገር ግን በአንድ እጅ ማጨብጨብ ስለማይቻል ጦር ያነገቱ ወገኖች ለሕዝብ እና ለአገር ካሉ የሠላም አማራጩን ሊጠቀሙበት ይገባል:: መንግሥት የሰላም ጥሪ ሲያደርግ ለመደራደር ፈቃደኛ ሆነው በሰላማዊ መንገድ መንግሥትን ፈትነው ወደ መፍትሔ መምጣት አለባቸው::

የድርድራቸውን መንገድ ለሕዝብ ገልፀው በሰላማዊ መንገድ መንግሥት ላይ ጫና መፍጠር ይችላሉ:: ከዚህ ውጪ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ልብ ብለው አይተው ሕዝባዊ አቋም ካላቸው ያንኑ በሰላም እያስረዱ ቢንቀሳቀሱ ሰላም ፈላጊ በሙሉ ይደግፋቸዋል የሚል እምነት አለኝ:: መንግሥትም በዚህ ላይ አጠንክሮ ቢገፋበት እና ሁሉም ቢተባበር ትልቅ ድምፅ ሊፈጠር እና መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ብዬ አምናለሁ::

አዲስ ዘመን፡- ብሔራዊ ምክክሩን በተመለከተ ምን ይላሉ?

አረጋዊ ዶ/ር ፡- በብሔራዊ ምክክሩ በኩል ትልቅ ሥራ እየተሠራ ነው:: በእርግጥ የመዘግየት አዝማሚያዎች ይታያሉ:: ምናልባትም ይህን እያልን ያለነው ቶሎ መፍትሔ እንዲመጣ በመፈለጋችን ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ኮሚሽነሮቹ እየሠሩ እንደሆነ እናውቃለን:: ጅማሮዎች ቢኖሩም ሕዝቡ ወደ ጅማሮ ትኩረት እያደረገ፤ ያለውን የጦርነት አዝማሚያ ሊያቀዘቅዘው ይችል ይሆናል የሚል አመለካከት አለኝ::

አገራዊ ምክክር መደረጉ በጣም አስፈላጊ ነው:: ብዙ ምክክር ያልተደረገባቸው ጉዳዮች አሉ:: በሕዝብ ዘንድ ሙሉ ስምምነት እንኳ መፈጠር ባይችል መግባባት ይቻላል:: የአቋም ልዩነት ቢኖርም በሰላም ለመኖር የሚያስችል አሠራር ይዞ መቀጠል ይቻላል:: በእዚህ በኩል አገራዊ ምክክሩ ትልቅ ፋይዳ አለው:: ይህ ወደ ትልቅ እይታ እንዲወርድ እና ሕዝቡ ምን እየተደረገ እንዳለ በግልጽ መገንዘብ አለበት:: ለሕዝቡ መለስተኛ አጀንዳዎች ተሰጥተውት፤ በዛ ላይ ትኩረት አድርጎ ወደ ውይይት እንዲሄድ የሚያደርግ ሁኔታ መጨመር አለበት::

በአጠቃላይ ግን አገራዊ ውይይት በጣም አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው:: የማያግባቡ ትርክቶች አሉ:: የማያግባቡት የትኞቹ ናቸው ? ትክክለኛ የትኞቹ ናቸው? የውሸት ትርክት የትኞቹ ናቸው? የሚሉት የሚለዩልን የምክክር መድረኩ ላይ መጥተው ውይይት ሲደረግባቸው ነው:: ይሔ ያሉብንን ልዩነቶች ሊፈታልን የሚችል አካሄድ እና አሠራር በመሆኑ አገራዊ ምክክሩ በዚህ ላይ ጎላ አድርጎ ወደ ሕዝብ እንዲያቀርበው እና በሕዝቡ ዘንድ እንዲያስተጋባ ያስፈልጋል::

አዲስ ዘመን፡- በትግራይ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተስ ምን ይላሉ?

አረጋዊ ዶ/ር ፡– አንዱ ትልቁ ኢትዮጵያ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ እየተፈጠረ ያለው እዛ አካባቢ ባለው ችግር ነው:: የችግሩ ባለቤቶች የትግራይ ሕዝብ እና አጠቃላይ ሕወሓት ሳይሆን የሕወሓት አመራሮች ናቸው:: ይህንን ያልኩበት ምክንያት አለኝ:: የትግራይ ሕዝብ እና ሕወሓት የተለያዩ ናቸው:: አጠቃላይ ሕወሓት እና የሕወሓት አመራር የተለያዩ ናቸው:: እነርሱ ግን የትግራይ ሕዝብን፣ የሕወሓት ድርጅትን እና የሕወሓት አመራሮችን አንድ ላይ ጨፍልቀው እየተናገሩ መጥተዋል::

ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ለአመራሩ የማይጥም ከሆነ ፀረ ሕወሓት እና ፀረ ሕዝብ እያሉ ሕዝቡን በዚህ ውዥንብር ውስጥ ከተውት ነበር:: አሁን ግን መልካሙ ነገር ሕዝቡ ከዚህ ውዥንብር እየወጣ ነው:: ሕዝቡ ‹‹የሕዝብ ጥያቄ እና የድርጅት ጥያቄ የተለያየ ነው:: የድርጅት ጥያቄ እና የአመራር ጥያቄ ራሱ የተለያየ ነው:: ስለዚህ እንደድሮ አታታልሉንም:: እንደ ድሮ ልጆቻችንን ሂዱ ተዋጉ ብለን አንልክም›› እያላቸው ነው::

‹‹እስከ አንድ ሚሊዮን ወጣት በቅርቡ እስከ ደብረሲና ሔዳችሁ አስጨረሳችሁ፤ ጦርነት ምንም ዋጋ የለውም:: የእስከ አሁኑ ጦርነትም ምንም ዋጋ አላመጣም፤ እሳት እንደበላው ገለባ ሆኗል:: ስለዚህ ከአሁን በኋላ በዚህ መልክ አንሔድም:: እስከ አሁን የፈጠራችሁት ችግር እንጂ መፍትሔ አላመጣችሁም:: 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ሆናችሁ:: አሁን ለስድስት ዓመታት ደግሞ በትግራይ ስልጣን ላይ ሆናችሁ ሕዝቡ ላይ በችግር ላይ ችግር ከማምጣት አልቦዘናችሁም:: ስለዚህ እኛን አትወክሉንም::›› ማለት ጀምሯል ::

በሌላ በኩል በሕወሓት በኩል ሆነው ሆ የሚሉ ሌሎችም ድርጅቶች አሉ:: በተቃራኒው ደግሞ የተሰለፈ የነቃ ወጣት ደግሞ አለ:: ‹‹ ከዚህ በኋላ አንጭበረበርም:: ኢትዮጵያዊነታችንን አስከብረን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ጋር በሰላም እንኖራለን፤ እስከአሁንም የሕወሓት አመራር የሚያቀርበው የመነጠል ጥያቄ አይጠቅመንም አልጠቀመንም:: ›› የሚል ሌላ ወገን እየተፈጠረ ነው:: ይህ ወደ ተሻለ መፍትሔ ያደርሰናል የሚል እምነት አለኝ::

አሁን የትግራይ ሁኔታ በዚህ ውዥንብር መካከል ነው:: ሕዝቡ ከውዥንብሩ የሚወጣበት አቅጣጫ እየያዘ ነው:: የፌዴራል መንግስት በዚህ ላይ ጥረት እያደረገ ነው:: እያወያየ እና መፍትሔ ፍለጋ እየጣረ ነው:: በእርግጥ ጥረቱ እስከ ፕሪቶሪያ ስምምነት ደርሶ አይተነዋል:: አተገባበሩ ላይ ግን ጎዶሎነት አለው:: ለምሳሌ በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀፅ 10 አካታች የሆነ ጊዚያዊ አስተዳደር ይመስረት ይላል:: የተመሰረተው ግን አካታች ያልሆነ ጊዚያዊ አስተዳደር ነው:: ይህ እንግዲህ መንግሥት ሰላም ለማስፈን ካለው ቁርጠኝነት የተነሳ ውክልናውን ሁሉ አሳልፎ ሰጥቷል:: ይህ ሊያስመሰግነው የሚገባ ነው::

ሆኖም በቀጣይ መንግሥትም ጣልቃ ገብቶ አካታች የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት ግፊት ማድረግ ይጠበቅበታል:: ይህ የመደማመጥ ሁኔታ ከተፈጠረ እና አሁን ያለው የለውጥ አዝማሚያ ከተደገፈ በትግራይ ውስጥ ሰላም ሊወርድ ይችላል::

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ::

አረጋዊ ዶ/ር ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ::

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You