ምዕመናን በልደት በዓል ላይ እንዲገኙ የቅዱስ ላሊበላ ደብር ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፡- ምዕመናን በቅዱስ ላሊበላ በደማቅ ሁኔታ በሚከበረው የልደት በዓል ላይ እንዲገኙ ሲል የቅዱስ ላሊበላ ደብር ጥሪ አቅርቧል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ደብር ዋና አስተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ፀጋዬ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ምዕመናን በቅዱስ ላሊበላ ደብር በስፍራው ተገኝተው የልደት በዓልን ሊያከብሩ ይገባል፡፡

የልደት በዓል የእርቅ በዓል ነው ያሉት አባ ሕርያቆስ፤ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሏት ታላላቅ በዓላት አንዱ እና የነፃነት በዓል ብላ ቅድሚያ የምትሰጠው ነው ብለዋል፡፡ ምዕመናን ለተለያየ ዓላማ ታስበው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሐሰተኛ ወሬዎችን ሰምተው በረከት ሳያገኙ እንዳይቀሩ አሳስበዋል፡፡

በላሊበላ ደብር የልደት በዓል ለ800 ዓመታት ያህል ሲከበር አንድም ጊዜ ተቋርጦ እንደማያውቅ ጠቅሰው፤ ኮቪድ 19 ከተከሰተ በኋላ ግን ወደ ስፍራው የሚመጣው ሰው ቁጥር አሽቆልቁሏል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በአካባቢው የሚስተዋለው የፀጥታ ችግርም በክብረ በዓሎችና በቱሪስቶች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጥላ ማጥላቱን ተናግረው፤ ይሁንና ከጊዜ ወደጊዜ አንጻራዊ ሠላም እየተገኘ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

አምና በዓሉን ሊያከብሩ የመጡ ሰዎች ቁጥር የተሻለ እንደነበር አስታውሰው፤ በዓሉን በሠላም አክብረው ያለምንም የፀጥታ ችግር ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል ብለዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመትም ከአምናው በተሻለ ዝግጅት በመኖሩ በርከት ያለ ሰው ይታደማል ተብሎ እንደሚገመት አመላክተዋል፡፡ ምዕመኑ የሠላምና ፀጥታ ችግር እንዳለ አስመስለው ለሚያወሩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጆሮውን ሳይሰጥ ወደ ቅዱስ ስፍራው መጥቶ የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆን ሲሉ አባ ሕርያቆስ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ደብር እና የአካባቢው ማኅበረሰብ በአመዛኙ የሚደጎመው ከቱሪስት በሚገኝ ገቢ እንደሆነ የጠቀሱት አስተዳዳሪው፤ የቱሪስቶች እንቅስቃሴ መዳከም በአካባቢው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡

ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ሰው ከተለያዩ ቦታዎች መጥቶ በዓሉን ማክበሩም የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ለማነቃቃት በእጅጉ የሚረዳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ክብረ-በዓሉ በሰላም እንዲከናወን ደብሩ ዝግጅት ስለማድረጉም ጠቅሰዋል፤ በዓሉ መንፈሳዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ እንዲከበር፤ እንግዶች ምንም አይነት ችግር ሳይገጥማቸው በሥርዓት ተስተናግደው እንዲሄዱ፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ካህናት እና ወጣቶች መንፈሳዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ እና የሚመጡትን እንግዶች እንደቤተክርስቲያን ሥርዓት እንዲያስተናግዱ ቅድመ-ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ቀደም ሲልም ይደረግ እንደነበረው ወጣቶች እግር የማጠብ፣ ማረፊያ ቦታ የማሳየት እና እንግዶች ተመችቷቸው እንዲሄዱ የሚያስችሉ ማናቸውንም መልካም ሥራዎች እንዲያከናውኑ ስለመደረጉ ጠቁመዋል፡፡

እንግዶች በቅዱስ ላሊበላ ደብር እና በአካባቢው ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት እንደሌለ አውቀው በቅዱስ ስፍራው በመገኘት በረከት እንዲያገኙ ሲሉ የደብሩ አስተዳዳሪ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ወንድምነው ወዳጄ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በከተማው የገና በዓል ለማክበር ለሚመጡ ቱሪስቶች መቀበል የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በዓሉ በድምቀት ለማክበር ከክልል እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ ያሉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡

በዓሉን ለማክበር ስምንት ልዩ ልዩ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የወጣቶች ኅብረት በጋራ በመሆን ለበዓሉ ዝግጅት እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በዓሉ የተቀዛቀዘው የቱሪስት ፍሰትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመጨመር ካለው ፋይዳ ጎን ለጎን ለከተማው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አቶ ወንድምነው ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ወንድምነው ገለጻ፤ አሁን ላይ በከተማው ያለው አንጻራዊ ሠላም መጪው በዓል ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንዲከበር የሚያደርግ ነው፡፡ የዘንድሮ የገና በዓል ሲከበርም ባለፉት ዓመታት በፀጥታ ችግር ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በሚያሳድግ መልኩ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

አቶ ወንድምነው እንዳሉት፤ ማኅበረሰቡ የበዓሉ ባለቤት በመሆኑ በበዓሉ ወቅት የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር ከፀጥታ መዋቅሩ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ለሠላም ቅድሚያ እንዲሰጥ የተለያዩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተሠርተዋል፡፡

በዓሉ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ከተደረጉ ዝግጅቶች በተጨማሪ መንገድ፣ ኤሌክትሪክና ውሃ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ችግር እንዳይፈጠር መሠራቱን ጠቅሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ በረራ እንዲያደርግና የበረራ ቁጥር እንዲጨምር ከአየር መንገዱ ጋር ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል ፡፡

በከተማው ከ45 በላይ ትላልቅ ሆቴሎችና ሌሎች የእንግዳ ማረፊያዎች አሉ፤ እነዚህም ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍና ክትትል ሥራዎች መሠራታቸውን አብራርተዋል፡፡

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በየትኛውም አገልግሎት ዘርፍ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ወንድምነው፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከዚህ በፊት በነበረው መልካም የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች እንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You