አዝጋሚው የኤቲኤም (ፈክሳ) አገልግሎት

ኤቲኤም የባንኮች ፈጣን የክፍያ ሳጥን ምህፃረ ቃል ነው:: እኛ አዳዲስ ዕቃዎች ሲመረቱ ዕቃዎቹም ሲገቡ ዕቃዎች ባናመርትም ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡት እቃዎች የፈረንጆችን ስም መዋስ የተለመደ ነው:: ሆኖም እንዳለ ከመጠቀም ወደራሳችን አምጥተን ብንጠቀም ግን የተሻለ ይሆን ነበር::

ሞባይልን ተንቀሳቃሽ አልያም የኪስ ስልክ፣ ዲሽን የጣራ አክንባሎ ብለን ብንጠራው የሚከለክለን አልነበረም:: አሁንም ኤቲኤም ከነስሙ ከመጣ ከአስርት ዓመታት በኋላ በእኔ አማርኛ ምህፃረ ቃል ብያኔ ፈጣን ክፍያ ሳጥን (ፈክሳ) ብዬዋለው:: ስለዚህ ስለ ፈክሳ ላወጋችሁ ስለሆነ በፈገግታ ወደ ንባቡ እንድትገቡ እጋብዛለሁ::

አንድ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ የመጡን ሰው ወዳጅ ዘመድ ሊቀበላቸው መርካቶ አውቶቡስ ተራ መናኸሪያ ተገኝተዋል:: ከዘመዶቻቸው ጋር ተገናኝተው ተሳስመው ሲያበቁ አንደኛው ዘመዳቸው ሊያግዝ የሚችለውን ዕቃ ተቀብሎ ብር ለማውጣት ባንክ ሄደ:: ወደ በር ከመድረሳቸው በፊት አፋቸውን እንዲያሟሹ ሊጋብዛቸው አስቦ ወደ ባንኩ አቀና:: ባንክ ሄዶ ኤቲኤም ወደ ምንለው ፈክሳ ተጠግቶ ካርዱን ከቶ ብሩን አወጣ:: ከገጠር የመጡት ሽማግሌው ተደነቁ፤ የሰይጣንም ሥራ መሰላቸው:: ሆኖም በአግርሞት እየሳቁም ታድላችሁ የእናንተ ሀገር ግድግዳ ብር ያመነጫል አሉ ተብሎ ሲቀለድ ሰምቻለሁ ብለው አግራሞታቸውን ተናገሩ::

ሰውየውን የገረማቸው ግድግዳ ከመሰለው ፈጣን ክፍያ ማሽን አገልግሎት ብር መዥረጥ ብሎ መውጣቱ ነው:: ሆኖም ለእኛ ለከተሜዎቹ ከአስር ዓመት በላይ ልምድ ስላለን ብዙም ጉዳዩ አያስገርመንም:: እንዲያውም የሚጠበቅበትን አገልግሎት ባለመስጠቱ ብዙዎቻችንን ወደ ማማረሩ ደርሷል:: ኤቲኤም ማሽኑ አገልግሎት ተማረሩ አንዳንድ ሰዎች በአንዳንድ ባንኮች ያለው የፈጣን ክፍያ ማሽን አገልግሎት ያረረ እና የመረረ ነው ይሉታል::

እዚህ ላይ በተለምዶ ኤቲኤም (ፈክሳ) ሳጥኖች በአንዳንድ ባንኮች አምስት ስድስት ሆነው ግርግዳው ላይ ተደርድረው ብዙ ግዜ አንዱም የማይሰራበት አጋጣሚ የሰፋ ነው:: አንዳንድ ግዜ ተወራርዶ ለሄደ ሰው አንዱም ከሠራና ብር ካወጣ እንደ እድለኛ ሊቆጠር ይችላል:: በአንዳንድ ቦታ የፈጣን ክፍያው ማሽኖቹ አገልግሎት እንደ ስማቸው ፈጣን ቀልጣፋ ሳይሆን ቀርፋፋ ነው:: አሁን አሁን በእነዚህ ማሽኖች ሰዎች ከመማረራቸው የተነሳ የድሮው ማንዋል አሰራር የተሻለ ነው እስከማለት አድርሷቸዋል::

በተለይ በዓላት እና የእረፍት ቀናት ሲመጡ ችግሩ የጎላ ይሆናል:: በእነዚህ ቀናት ሰዎች ለተለያዩ ወጨዎች ገንዘብ የሚፈልጉበት ቢሆን የእኛዎቹ ባንኮች ኤቲኤም ማሽኖችን ባዶ አድርገው ሰዎችን ለእንግልት መዳረግ የተለመደ ነው:: በእነዚህ ቀናት ደግሞ በፈጣን ክፍያ ማሽኖቹ ውስጥ የሚኖረውን ብር ሰዎች ስለሚያወጡት፤ እርስዎ ተረጋግተው ወደ ባንኮች ፈክሳ ሄደው ሊያወጡ ቢሞክሩ ብር የማግኘት ዕድሎት ከመርፌ ቀዳዳ የጠበበ ነው:: አማራጮት ወደ ሌሎች ቅርንጫፎች ሄደው ፈክሳማሽኖችን መሞከር ይሆናል:: አንዳንዴ ማሽኖቹ ብር ለማዘዋወርና ለማውጣት አልሠራ ሲልዋችሁ፤ ይሄ ነገር የፈጣን ክፍያ ማሽን ነው ወይስ ሀውልት? ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም:: በአካልም በምስልም የፈጣን ክፍያ ማሽን የሚመስል፤ ግን የማይናገር የማይጋገር ዓይነት ነገር (የማይሠራ የማያሠራ) ይሆንባችኋል::

በበዓላት እና በእረፍት ቀናት እንደ አጋጣሚ ሆኖ የሚሰራ አንድ ማሽን ከተገኘ ሰዎች በብዛት ተሰልፈው ይመለከታሉ:: ምንድን ነው ብለው ሲጠይቁ ሰዎች ከኤቲኤም ብር ለማውጣት መሰለፋቸው ይሰማሉ:: በሁኔታው ተገርመው ‹‹ለዚህ ለዚህማ እንደተለመደው ባንክ ቤት ሄዶ ብር ማውጣጡ አይሻልም ወይ:: ኤቲኤም እኮ የመጣው ወረፋን ለማስቀረት መስሎኝ ››የሚል ጥያቄ ራስዎ ለራስዎ ያቀርባሉ:: ሆኖም አማራጭ ስለሌለዎት እረጅሙን ሰልፍ መቀላቀል የግድ ይሆንቦታል::

በአራት ኪሎ እና በአምስት ኪሎ አካባቢ ካሉት የባንክ ፈጣን ክፍያ ማሽኖች (ፈክሳ) የተወሰኑት በአንድ ቅርንጫፋቸው ደጃፍ ላይ አምስትና ስድስት ተደርድረው ሰው ገንዘብ ለማውጣት ተሰልፎ ብታዩ አትገረሙ:: ከተደረደሩት ፈክሳዎች መካከል እድለኛ ከሆናችሁ አንዱ ሊሠራላችሁ ይችላል:: አብዛኛው እንደማይሠራ ስትረዱትና ክስተቱም የቆየ መሆኑን ስትገነዘቡት ደጃፋቸው ላይ የተለጠፈውን ፈክሳን ‹‹ ምናልባት ባንኮቹ ተለጣፊ ሱቅ አድርገው ሊያከራዩት ፈልገው ይሆን እንዴ ? ›› ብላችሁ ታስባላችሁ::

እንመራመር ካላችሁም፤ የፈጣን ክፍያ ማሽኑ፤ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥን በሚመለከት የተገልጋዮች ሃሳብ መስጫ ሳጥንም ነው፤ ልትሉ ትችላላችሁ:: ደግ ደጉን ካሰባችሁ ማለት ነው:: እንደዚህ ዓይነት የሃሳብ መስጫ ሳጥኖች በመርካቶ መሳለሚያ ፖሊስ ጣቢያ ደጃፍ አይቻለሁ:: ሰዎችም በወረቀት የጻፉትን ሲከቱ ጭምር ::

ሰው ብር የሚያወጣው ለብዙ ነገር ነው:: በተለይ አጣዳፊ ጉዳይ የገጠመው ሰው ገንዘብ ቶሎ አገኝቶ ከችግሩ መገላገልን ይመኛል:: ሆኖም እንደ ጅብራ የተገተሩት እነዚሁ ማሽኖች ባዶዋቸውን ቆመው የእርስዎን ችግር ከመፍታት ይልቅ የባሰውኑ ሆድ እንዲብስዎት የሚያደርጉ ናቸው:: በተለይም በድንገት እንግዳ የመጣባቸው ሰዎች፤ ሰው የታመመባቸው እና ሀኪም ቤት ለመውሰድ እየተጣደፉ ላሉ ሰዎች፤ ለቤተሰቦቻቸው እቃ ገዝተው ለመውሰድም ሆነ ሌላ አጣዳፊ ለሆነ ጉዳይ ገንዘብ ለሚፈልጉ ሰዎች የኤቲኤም ማሽኖች መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም:: ገንዘብ ደግሞ በሚፈለግበት ጊዜና ቦታ ካልተገኘ ፈክሳ በባንኮች ደጃፎች መሰንቀሩ ፋይዳ አልባ ይሆንብናል:: እንደውም ከጥቅማቸው ጉዳታቸው አመዝኖ አለኝ ያሉት ገንዘብ የቅርብ ሩቅ ሆኖ እጆዎትን ለብድር እንዲዘረጉ ይገደዳሉ::

ይህንን ሃሳብ ሳነሳ መቼም ሁሉም ፈክሳዎች አይሠሩም እያልኩ እንዳልሆነ ትረዱኛላችሁ:: ገሚሶቹ ገንዘብ ቶሎ ይጨርሱና በሚፈለገው ፍጥነት ብር ስለማይተካባቸው፤ ከፊሎቹም ደግሞ ገንዘብ እያላቸው በቴክኒክ ብልሽት ካርዳችሁን ፈጣን ክፍያ ማሽኑ ውስጥ ከታችሁ ስታበቁ ፈረንጆቹ No money no funny እንደሚሉት በእኔ ግርድፍ ትርጉም ‹‹ዕሴት የለም ሀሴት የለም›› ብሎ ብሩን ከልክሎ ካርዳችሁን ይመልስላችኋል:: ይባስ ብሎም አንዳንድ የኢቴኤም ማሽኖች ሌላቦታ ሄዳችሁ እንዳትሞክሩ ጭምር ካርዳችሁን ወስደው የሚያስቀሩም አሉ:: ስለዚህም ካርዳችሁ ከተመለሰላችሁም በአራዳ ቋንቋ እናውራና ቻንሰኛ (ዕድለኛ) ናችሁ:: ሌላ ፈክሳ ላይ ሄዳችሁ ትሞክራላችሁ::

የቸኮለ አፍሶ ለቀመ እንዲሉ ስትቸኩሉ እነዚህ የኢቴኤም ማሽኖች ነገር ያላቸው ይመስላል:: ብር ልታወጡ ካርዳችሁን ከታችሁበት፤ ብሩንም ካርዱንም ሳይሰጣችሁ ከሁለት ያጣ ትሆናላችሁ:: ያው ካርዱን እንኳ ቢመልስላችሁ ሌላ ፈክሳ ላይ በካርዱ ብር ለማውጣት ትሞክሩ ነበር:: ይህን ያልኩት በተለይ በምሽት በእረፍትና በበዓል ቀን ሲሆን ነው:: በአዘቦት ቀን ከሆነ የባንክ ደብተራችሁን አልያም የሂሳብ ቁጥሩን ይዛችሁ ብራችሁን ለማውጣት የምትችሉበት ዕድል ሰፊ ነው::

እዚህ ላይ በእሁድ የመርካቶ ሰንበት ቀን ሰፊ ንግድ ስላለ ብዙ ሰዎች ለግብይት ይመጣሉ:: እናም በባንኮች ፈክሳ ብር ለማውጣት ወረፋው ብዙ ይሆንና የታክሲ ሰልፍ ሊመስላችሁ ይችላል:: አንድ ባንክ ግን በመኪና የሚዘዋወር ተለጣፊ ፈክሳ በመርካቶ ሰንበት ገበያ ከአውቶቡስ ተራ፣ አመዴ፣ አዳራሽ ገበያ፣ ምናለሽ ተራ ሲዘዋወር በተደጋጋሚ አይቻለሁ:: ሰዎች ገንዘብ ሲያወጡ ጭምር:: ስሙን ብጠራው ጥሩ ነበር ተፎካካሪ ባንኮች ግን ቅር ሊላቸው ይችላል:: ብቻ ዋናው ነገር መፎካከር ካለብን በፈጠርነው የደንበኛ እርካታ እንጂ፤ ዓመቱን ጠብቀን ይሄን ያህል አተረፍን በሚል የነጋዴ ውድድር መሆን የለበትም::

ወዳጄ ለሥራ ጉዳይ ወደ ጅማ ሄደ፤ በእጁ የያዘው ብር አነስተኛ መሆኑን ተረድቷል:: ሆኖም በኪሱ የኤቴኤም ካርድ ስላለ ብዙም ስጋት አልገባውም:: ስለዚህም የኤቴኤም ካርዱን ተማምኖ ጅማ ገብቶ አደረ:: እሁድ ጠዋት ቁርስ ሊበላ እና ለቀን መንቀሳቀሻ ብር ፈልጎ ወደ ፈክሳ ሳጥን ሄደ:: ካርዱን ከተተ ግን እንኳን ብሩ ሊወጣ ካርዱንም አስቀረው:: ያለው አማራጭ አዲስ አበባ ካሉ ወዳጆቹ በኪስ ስልክ ገንዘብ እንዲልኩለት መጠየቅ ነበር:: ወዲያው ልከውለት ብሩን ለሚፈልገው ተግባር አዋለው:: ካርዱን ማውጣት የቻለው ሰኞ ከሰዓት በኋላ ነበር::

እኔ የፈክሳን አገልግሎት አደንቃለሁ:: በተደጋጋሚ የማይሠሩ ፈክሳዎች በፍጥነት ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲበቁ ቢደረግ የተሻለ ነው:: እንደዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸውን ባንኮች ስም መጥራቱ አስፈላጊ አይደለም:: ባንኮች ግን ዘወትር ለስማቸው ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ይመስለኛል:: ፈክሳዎች በሚገባ ፍጥነት ሊጠግኑ የሚችሉ ባለሙያዎች በእረፍት ቀን ጭምር ቢመደቡም ደንበኛን ማክበር መሆኑ መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም ::

በቅርቡ የአንድ ባንክ ፈክሳን በአንድ መሥሪያ ቤት ደጃፍ ተተከለ:: ማሽኑ ጀማሪ ስለሆነ መሰለኝ፤ የተወሰነ ሰዓት ይሠራና ይበላሻል:: አንዳንዴም ይሠራና ብር መስጠት ይጀምራል:: ብሩን ሲሰጣችሁ ደግሞ ጎርዶ ጎምዶ ነው:: ማለትም ከፈለጋችሁት የብር መጠን ቆርጦ፤ ሁለት ሺህ ብር ጠይቃችሁ አንድ ሺህ አምስት መቶ ይሰጣችኋል:: ለማረጋገጫ ደግሞ ብሩን የወሰዳችሁበት ወረቀት ይሰጣችኋል:: ግን ወረቀቱ የሚናገረው ሌላ የሰጣችሁ ብር ደግሞ ተመኑ ሌላ ነው:: ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ እንደሚሉት:: እናም ብዙ ሰዎች የተወሰደባቸውን ብር ለማስመለስ ወደ ባንኩ ሁለት ሳምንት መመላለሳቸውን አስታውሳለሁ:: እዳ ከሜዳ ይሉት ብሂል ይሄ ነው::

ያለንበት ዘመን ብር ይዘን የምንቀሳቀስበት ዘመን አይደለም:: ‹‹ ብር ያልያዘ መንገደኛ አይፈራም ቀማኛ›› እንደሚባለው ብሂል ወደ ምናባዊ የገንዘብ ልውውጥ እንድንሄድ ከተፈለገ የኪስ ባንኩ አጠቃቀምም እየተጠናከረ፤ የፈክሳ ሳጥኖቹም እየተቀላጠፈ እና እየተስተካከሉ መሄድ አለባቸው:: ባንኮቹን ፈክሳዎቹ ከሚሠሩና ከሚጠግኑ አካላት ጋር ተመካክረው አገልግሎታቸውን ሊያቀላጥፉ ይገባል:: ይህ ሲሆን በኤቴኤም ማሽኖች ላይ የሚፈጠረው ምሬት ይቀንሳል፤ ማሽኖቹም የታሰበላቸውን አገልግሎት ለሕዝቡ መስጠት ይችላሉ::

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You