አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ገለጸ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በዘንድሮው የ2017 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በግብርናው፣ ኢንዱስትሪው፣ አገልግሎቱ ዘርፎች ዕድገት እንዳለ አመላካቾች ያሳያሉ።
ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ባሳለፍነው ወር ኅዳር ወደ 16 ነጥብ 9 በመቶ በመውረድ ካለፉት አምስት ዓመታት ዝቅተኛው አኃዝ ተመዝግቧል ያለው መግለጫው፤ ምርታማነትና ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበሩ ለዚህ በጅቷል ብሏል።
በ2017 በጀት ዓመቱ ጅማሮ ወዲህ በሁሉም የገንዘብ ዝውውር አመልካቾች ዘንድ በመጠኑ ከፍ ያለ ዕድገት እንደታየ ኮሚቴው አመልክቶ፤ ነገር ግን ከቅርብ ወራት ወዲህ የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ቢኖርም፤ ከኢኮኖሚው ስፋት አንጻር የገንዘብ ዝውውር አመልካቾች የመቀነስ አዝማሚያ ታይቶባቸዋል ነው ያለው፡፡
የባንክ ሥርዓት ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር፣ ከፍ ያለ የመጠባበቂያ ሂሳብና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ እንደሆነ በኮሚቴው ተገምግሟል። የበጀት እንቅስቃሴዎች ጥሩ አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ይህም በዘንድሮው በጀት ዓመት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወሰድ ያደረገና የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም በእጅጉ የሚደግፍ ሆኗል ሲል ገልጿል፡፡
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ለውጥ ለውጭ ንግድ ዘርፍ ትልቅ መሻሻል ለገቢ ንግድ ግን መጠነኛ ቅናሽ ታይቶበታል ያለው መግለጫው፤ የንግድ ባንኮችም ሆነ የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉንም አስረድቷል፡፡
የዓለም ኢኮኖሚ የሀገር ውስጥ ሁኔታዎችን የሚነካው በዋናነት በሸቀጦች ዋጋ አማካይነት ሲሆን፤ አሁን ያለው የሸቀጦች ዋጋ በጥቅሉ ለሀገራችን ምቹ ነው ሊባል እንደሚችል ኮሚቴው ጠቁሞ፤ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ የቅርብ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ አበረታችና በጥቅሉ የመርገብ አዝማሚያ ቢያሳይም፣ ጠበቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቧል። በዚህም ኮሚቴው የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል ሲል ጠቅሷል። የዋጋ ግሽበት ለመቀነስና የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመን መኖሩን ለማረጋገጥ ሲባል የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ ማድረግ አንደኛው ምክር ሃሳብ ነው ያለው መግለጫው፤ ሁለተኛው ምክረ ሃሳብ ደግሞ የባንክ ብድር ዕድገት ግብ የመጠቀም ሁኔታ እንዲቀጥል፤ ነገር ግን ለዚህ በጀት ዓመት የብድር ዕድገት ግቡ ከ14 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ነው ሲል አስታውቋል፡፡
በብሔራዊ ባንክ ለባንኮች በሚሰጣቸው የአንድ ቀን የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት፣ በአንድ ቀን የብድር አገልግሎት ላይ የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ እና ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሂሳብ በነበረበት እንዲቆይ ወስኗል ሲል መግለጫው አብራርቷል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም