‟ሰው ስትሆን ለሌሎች መኖርና መሥራት እንዳለብህ ለአፍታም መዘንጋት የለብህም”

አንድ አንድ ሰው ርዕዮተዓለም፣ ትውልድ፣ ዘመን፣ ማንነት፣ ወዘተረፈ የተሻገረ ስብዕና አለው። ከስንት አንድ እንደሚገኝ ዘመን አይሽሬ የኪነ ጥበብ ሥራ ዘመንም ትውልድም የሚሻገር ክላሲካል። አዎ እንደ ክቡር ሽመልስ አዱኛ ያለ። ሶስት አራት ትውልድ የተሻገረ አገልጋይነት። የሚያስቆጨው እንዲህ ያሉ ሰዎችን በሕይወት እያሉ በልካቸው እውቅና ከመስጠት ይልቅ የቀብር ላይ የሕይወት ታሪክ አንባቢ ሆነን ቀርተናል።

ትውልድ አርዓያ አድርጎ ሊከተላቸው ሲገባ አላስተዋወቅናቸውም። ቢተዋወቁ ነገ ሺህ ሽመልሶችን ማፍራት ያስችል ነበር። ሆኖም የሚዲያዎቻችን ብሔራዊ ጀግኖች ግን ከተወሰነ የሙያ ዘርፍ ፤ ከመዝናኛው ኢንዱስትሪ እና ከማኅበራዊ ሚዲያዎች የተዋሷቸው ናቸው። ሁሉንም የሙያ ዘርፍ በፍትሐዊነት ያማከሉ አይደለም።

ምልዕክቶቻችንና ጀግኖቻችንን በሕይወት እያሉ እውቅና መስጠት ላይ እንደ ሀገር ድክመት ቢኖርብንም ሰሞነኛ ይበል የሚያሰኝ አብነት ላንሳና ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ እመለሳለሁ። በሕይወት እያሉ እውቅና እየተቸራቸው ካሉ ጥቂት እድለኛ የሀገር ባለውታዎች አንዱ የትዝታው ንጉስ መሐሙድ አሕመድ ነው። ከተነሳሁበት ሀሳብ ጋር እንዳያናጥበኝ እንጂ እኔም ከትዝታው ንጉስ ጋር እንደ አቅሚቲ ትዝታ አለኝ።

ተመራቂ ተማሪ እያለሁ የመጽሔት ዝግጅት ኮሚቴ አባል ነበርሁ። ለመጽሔቱ ማሳተሚያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ደግሞ የሙዚቃ ድግስ ማዘጋጀት ነበረብን። ድምጻውያንንና ኮሜዲያውያንን እየዞርን እናግባባ ነበር። ጋሼ መሐሙድን ስናነጋግረው የሰጠን ምላሽ ግን ዛሬ ድረስ አይረሳኝም። በዝግጅቱ እንደሚገኝ ቃል ሲገባልን ከሌሎች አርቲስቶች ጋር እንዳደረግነው ስንት እንደምንከፍለው ስንጠይቀው እናንተ ልጆቼ ናችሁ። መክፈል አይጠበቅባችሁም ሲለን ማመን ነው ያቃተን።

በቃሉ መሰረት በዝግጅታችን ተገኝቶ እነዛን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹን አቀረበልን። በወቅቱ ታዋቂ የነበር ሌላ አንድ ድምጻዊ ግን በጣም ውድ ክፍያ ጠይቆን እንዲቀንስልን ስንጠይቀው ተፈናቃይ ስለሆንሁ አልቀንስም ብሎ ግግም አለ። ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ፤

ዛሬ ከአንድ የተዋጣለት የቀዶ ጥገና ሀኪም ወይም አርክቴክት አልያም መሐንዲስ ወይም ተመራማሪ አልያም የፈጠራ ባለሙያ ወይም ዳኛ አልያም ነገረ ፈጅም በላይ አንድ ቲክቶከር ይበልጥ ተከታይና እውቅና አለው። የሚያሳዝነው ማኅበራዊ ሚዲያው ወጣቱን ጭልጥ አርጎ መውሰዱ ሳያንስ፤ ወደ መደበኛው ሚዲያ ይመጣና የተረፈውን ታዳሚ ጠርጎ ይወስደዋል።

ዛሬ መደበኛ ሚዲያው ቲክቶክ ወይም ዩቲውብ ላይ “ታዋቂ” የሆነን ሰው ወይም ሁነት በእንግድነት በመጋበዝ ወይም እንዳለ በማቅረብ ፈቅዶ ቅኝ እየተገዛ ነው። ይህን ከማኅበራዊ ሚዲያዊ ምንም ረብ ያለው ነገር የለም እያልሁ አይደለም። የማኅበራዊ ሚዲያ ጀግና ወይም ሄሮ እና የመደበኛው ሚዲያ ጀግና ለየቅል ስለሆነ በሚል እንጂ። በእርግጥ የሚስማሙበት የጋራ ጀግና ካገኙ ቢጋሯቸው አይከፋም።

ሌላው ማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰጠን መረጃ የምንፈልገውን እንጂ የሚያስፈልገንን አይደለም። መደበኛው ሚዲያውም ትውልድ የሚፈልገውን መረጃ እንጂ የሚያስፈልገውን መረጃ መስጠት እየተወ ነው። በሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን የኳስ ዘገባዎችንና ቀጥታ ስርጭቶችን እንዲሁም የአይዶል ሾው ብዛታቸውን እዚህ ላይ ልብ ይሏል።

የቀድሞው የሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ኢትዮጵያን ያገለገሉት እና በበጎ ሥራቸው የሚታወቁት አቶ ሽመልስ አዱኛ በ1970ዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ያስከተለውን ረሃብ ለመቆጣጠር የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል፤ በጊዜው የእርዳታ ተግባራትን በማስተባበር አስከፊውን ጉዳት ለመቀነስ በተደረገው ርብርብ ይበልጥ የሚጠቀሱ ሰው ናቸው።

ከ1977 እስከ 1979 በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ፤ ከ1979 እስከ 1983 የሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ ዘርፈ ብዙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ላይም ስለመሳተፋቸው እና ልዩ ልዩ እውቅናዎችን ስለማግኘታቸው ታሪካቸውን ጠቅሶ ያስታውሳል። አቶ ሽመልስ አዱኛ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ በመሆን፣ የኢትዮጵያ የቤተሰብ መምሪያ መሥራች እና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በመሆን እንዲሁም በሌሎችም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ሀገራችውን አገልግለዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ፤ አቶ ሽመልስ አዱኛ በሀገር ባለውለታነታቸውና በበጎ ሥራቸው የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል::”ሰው ስትሆን ለሌሎች መኖርና መሥራት እንዳለብህ ለአፍታም መዘንጋት የለብህም::”ይህን ታላቅ ኃይለ ቃል ከዓመታት በፊት ለአንድ ሚዲያ የተናገሩት ሁለገቡ ባለሙያ፣ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ በመንግሥት ሹምነት፣ በሌሎች አገራዊና ዓለማዊ ተቋማት ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ ናቸው::

በ1960ዎቹም ሆነ በ1970ዎቹ አጋማሽ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ደርሶ የነበረውንና የብዙዎች ሕይወትን የቀጠፈው ድርቅና ረሃብ ለመግታት፣ ብዙኃኑን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ከሞተ ሕይወት ለመታደግ ተቋቁሞ የነበረውን የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽንን ባጭሩ ዕማማኮን በዋና ኮሚሽነርነት የመሩ አቶ ሽመልስ አዱኛ ነበሩ:: ለ1966ቱ አብዮት መፈንዳት አንዱ መንሥኤ የነበረው በ1965 ዓ.ም. በወሎ ጠቅላይ ግዛት የደረሰው ድርቅና ረሃብ ለመግታት፣ የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱ ብሔራዊ የዕርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሲያቋቁም በመሪነት የተሰየሙት የአገር ግዛት ምክትል ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ ነበሩ:: ድኅረ አብዮት ኮሚቴው ወደ ኮሚሽንነት ሲያድግ መሪነቱን ይዘው ቀጥለውበታል::

በኮሚሽነርነታቸው በዓለም አቀፍ መድረኮች በየአገሮቹ እየዞሩ ዓለም ድጋፉን እንዲሰጥ በዕንባ ጭምር በመታጀብ የድረሱልን ጥሪ ማሰማታቸው ተቀባይነትም አግኝተው ለወገኖች ዕርዳታው እንዲደርስ ማድረጋቸው ገጸ ታሪካቸው ያሳያል:: ዕማማኮን ለ10 ዓመት ያህል እስከ 1975 ዓ.ም. የመሩትና በ1976 ለሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ያስረከቡት አቶ ሽመልስ ዳግም በወሎ፣ በትግራይ፣ በኦጋዴንና አፋር የተከሰተው ድርቅ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ መጋለጡንና አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑን በ1975 ዓ.ም. ይፋ አድርገው ነበር::

“ተራበ አሉ ያ ገበሬ

“ምሰሶዋ የአገሬ” እየተባለ በሚነገርበት በዚያው ዘመን አፋጣኝ ምላሽ በአብዮታዊው መንግሥት ባለመገኘቱ ሚሊዮን የሚደርስ ሕይወትን ማሳጣቱ ይታወሳል::

የዕማማኮ ኮሚሽነርነታቸውን ካስረከቡ በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል የሕፃናት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሠርተዋል:: ባሕር ማዶ በመሻገርም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ባገኙባት ሕንድ ለሁለት ዓመት ያህል በአምባሳደርነት አገልግለዋል:: የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) በተመሠረተበት ዋዜማ በ1979 ዓ.ም. በዘውዳዊው ሥርዓት በመምሪያ ኃላፊነት በሠሩበት የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር (በደርግ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባለው) ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል::

‹‹በመልካም አስተዳደር ምስጉን ሰው›› እንደነበሩ፣ ‹‹ቢሯቸውን በዕለተ ረቡዕ ለሁሉም ክፍት አድርገው ችግር አለብኝ ለሚሉ የሚቀበሉ የሕዝብ አገልጋይ›› ነበሩ ብለው ምስክር የሰጡላቸው እንዳሉ በገጸ ታሪካቸው ተጠቅሷል:: ለመንግሥት ፈታኝ የነበረውና ሥልጣኑንም የነጠቀው ኢሕአዴግ በግንቦት 1983 ዓ.ም. መንበሩን ከመጨበጡ በፊት፣ ኢሕዲሪ ባደረገው ሹም ሽር ጠቅላይ ሚኒስትር የተደረጉት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ከሾሟቸው የካቢኔ አባላት መካከል አቶ ሽመልስ አዱኛን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማድረጋቸው ይታወሳል::

አቶ ሽመልስ ከመንግሥታዊ ከፍተኛ ኃላፊነት ጡረታ ከወጡ በኋላ ድሮም በነበሩበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰማራት በልማትና በሰላም፣ በሰብዓዊነት መስኮች የላቀ አገልግሎት መስጠታቸው ይነገርላቸዋል:: በ1950ዎቹ መሥራች የነበሩት የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ ኤችአይቪ ኤድስን ለመግታት የተቋቋመው ‹‹ኦሳ›› የተባለ አገር በቀል ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለማስጠበቅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር መሥራች ፕሬዚዳንት ነበሩ::

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ አማካሪ እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኃላፊነት አገልግለዋል:: በ2002 ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫም በግል ተወዳዳሪ ነበሩ::

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በቀድሞ አጠራር በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በጅግጅጋ ከተማ እሑድ ጥቅምት 2 ቀን 1928 ዓ.ም. (13 ኦክቶበር 1935) የተወለዱት አቶ ሽመልስ አዱኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረርጌ፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በአዲስ አበባ ጄኔራል ዊንጌት ተምረዋል:: የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሥነ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ ድኅረ ምረቃም ከሕንድ ቦምቤ (ሙምባይ) ታታ ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ አገልግሎት አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል::

በ1950ዎቹ አጋማሽ በሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር እየሠሩ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሶሺዮሎጂ ያስተምሩ ነበር:: በ1950ዎቹ መጨረሻና 60ዎቹ መጀመሪያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት በኃላፊነት የሠሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስፈላጊነትን ሲያስተጋቡ ኖረዋል:: እሳቸውም ማለት ብቻ ሳይሆን በተግባርም አሳይተውታል:: ‹‹የገባነውን ቃልና መግለጫ በተግባር ካላሳየን፣ ማድረግ ያለብንን ባለማድረጋችን የራሳችን ቃላት በእኛ ላይ ይፈርዱብናል፤›› ማለታቸውም ተመዝግቧል::

አቶ ሽመልስ በሕይወት ዘመናቸው ላበረከቱት የላቀ አገልግሎት ከተበረከቱላቸው ሽልማቶችና ዕውቅናዎች መካከል ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር የሄንሪ ዱናንት የላቀ የሰብዓዊ አገልግሎት ሜዳሊያና የጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ይገኙበታል:: ነፍስ ኄር አቶ ሽመልስ አዱኛ ዘመን ገትቷቸው በተወለዱ በ89 ዓመታቸው ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. አርፈው በማግሥቱ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል:: በሳቸው የሚኒስትርነት ዘመን ከእሳቸው ጋር የሠሩት አቶ ተስፋዬ ድረሴ ባንድ ወቅት በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ እንዲህ ከትበው ነበር::

‹‹ድሆች ናችሁ ያሉን

ድሆች ነን ወይ እኛ

በእጃችን እያለ ሺመልስ አዱኛ››

በአንድ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ አንዱ እንደተጻፈው፣ ‹‹አቶ ሽመልስ አዱኛን በጡረታ ዘመናቸው አግኝቶ ስለሠሩት ሁሉ መልካም አመስግኖ ሲጨዋወቱ የሰጡት ቃል እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰው ስትሆን ለሌሎች መኖርና መሥራት እንዳለብህ ለአፍታም መዘንጋት የለብህም:: እኔም ያን ከማድረግ ውጪ የተለየ ነገር አላደረግሁም:: የገዛ ቤተሰቤ እንደሆኑ አድርጌ መመልከቴ ይመስለኛል ከስሜት ውጪ ያደርገኝ የነበረው››

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You