አዲስ አበባ ፤ በአዲስ አበባ ከ404ሺህ በላይ ለሚሆኑ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ ማከናወኑንን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግፋ ወሰን ደሲሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የማረጋገጥ ሥራው የተከናወነው በ337 ቀጣናዎች ላይ ሲሆን በቁራሽ መሬት ከ219 ሺህ 722 በላይ፤ በጋራ መኖሪያ ቤት 173 ሺህ 136 በላይ የሚሆኑ ባለመብቶችን ማዳረስ ተችሏል። በዚህም ከከተማዋ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት 54 በመቶ መሸፈን ተችሏል።
ኤጀንሲው ባለፉት አምስት ዓመታት ከአገልግሎት 13 ቢሊዮን 739 ሚሊዮን 180 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማስገባት ችሏል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ገቢው የተገኘው በሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ለ414 ሺ 174 ባለጉዳዮች የካዳስተር አገልግሎት በመስጠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የካዳስተር ሥርዓትን በልደታ፣ ቂርቆስ፣ አራዳ፣ አዲስ ከተማ እና ጉለሌ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ትግበራው ኮልፌ ቀራኒዮ 82 በመቶ፣ ቦሌ 79 በመቶ፤ የካ 50 በመቶ፤ ንፋስ ስልክ 50 በመቶ፤ አቃቂ ቃሊቲ 47 በመቶ እንዲሁም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ 31 በመቶ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ጨምረው እንዳብራሩት፤ ኤጀንሲው የይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ከጀመረበት 2007 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 2016 ዓ.ም ድረስ ሰባት ጊዜ የይዞታ ማረጋገጥ እወጃ ተካሂዷል።
ከዚህ ውስጥ ሦስቱ የተካሄዱት ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ዓመታት ነው። በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ስምንተኛውን ዙር የይዞታ ማረጋገጥ እወጃ በማከናወን የሕጋዊ ካዳስተር ግንባታ ሥርዓት በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
በተጨማሪ በካዳስተር ሥርዓት የተመዘገቡት ከ370 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችንና ይዞታዎችን ማኅደር ወደ ዲጂታል በመቀየር በአርካይቭ ማኔጅመንት ሥርዓት ማደራጀት ተችሏል፡፡
ይህም ከዚህ ቀደም ይገጥም የነበረውን የፋይል መጥፋት፣ የጊዜ ብክነት፣ የባለጉዳይ እንግልትና ምልልስ እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪን ማስቀረት ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም