ኮሊውድ ላይ

ከቀናት በፊት ነበር አጋጣሚው:: እኔና ሁለት ወዳጆቼ ከአንደኛው ካፍቴሪያ ቁጭ ብለናል:: አብረን ቁጭ አልን እንጂ ለደቂቃዎች አብረን አልነበርንም:: በየፊናችን ስልክ ስልካችንን ነበር በዓይን የምናንተከትከው::

ድንገት ግን የአንደኛው ወዳጃችን መከረኛ ግርምትና የጩኸት ሳቁ ከገባንት አስፈንጥሮ ያስወጣን:: አመሉ ባይጠፋንም ሁለታችንም ግን እኩል ቀና ብለን ተመለከትነው:: “ምነው?” አልኩት በሁኔታው ተገርሜ:: ባያስቅም በሚስቀው ሳቁ ላይ ፌዝ አክሎበት “ትበላው የላት ምን አማራት አሉ…” አለና እንዳመሉ ያስገረመውን ነገር ሊያሰማን ከነወንበሩ ጠጋ ብሎ “ስሙኝማ…” አለን::

ከተገናኘንበት ሰዓት አንስቶ ይሄ ለሦስተኛ ጊዜው ቢሆንም ጆሯችን ክፍቱን እስከሆነ ድረስ ያለማድመጥ መብት አልነበረንምና ቀጥል አልነው:: ተመቻችቶ ተቀመጠና “ኢትዮ ኮሊውድ የተሰኘ ግዙፍ የፊልም መንደር በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው” የሚል የዜና አርዕስት ካነበበልን በኋላ መልከት አድርጎን እየሳቀም ዝርዝሩን ቀጠለልን “…ልክ እንደ ሆሊውድ፣ ቦሊውድ እና ሮሊውድ የፊልም መንደሮች ያለ… ኮሊውድ ኢትዮጵያ የተሰኘ…የ43 ሺህ ካሬ ካርታ በመረከብ አስገራሚ በሆነው የዘንባ ጫካ…” እያለ እስከመጨረሻው ካነበበልን በኋላ የምንለውን ለመስማት ጠበቀን::

ከጥቂት ዝምታ በኋላ “እኮ ታዲያ ያሳቀህ ነገር ምኑ ነው?” ሲል ሁለተኛው ወዳጄ በእርጋታ ጠየቀው:: “በዚህ ዜና ኮሜዲ ያልሳቅሁ በምን ልስቅ ነው…መቼም አያስቅም ካላችሁኝ ሙሉ ደቂቃ ሳነበንብ አልሰማችሁኝም ነበር ማለት ነው” ብሎ ጥቂት ተረቡን ከተራረበ በኋላ “ሊሆን የማይችል ተረት ተረት ነው::

ለአንድ ስቱዲዮ ጭንቁን የሚያይ የፊልም ኢንዱስትሪ ከሕልም ቅዠቱ ሳይነቃ ድንገት ብንን ብሎ፤ በ43 ሺህ ካሬ ላይ መንደር…የቅዠት ኮሊውድ ነው:: ይልቅስ ለኛ የሚያስፈልገን ሰላምና ጠግቦ መብላት ነው:: ቢሆን እንኳን በድህነት ውስጥ ይህን ማሰብ ቅንጦት ነው:: ሳንበላ ሆሊውድ ላይ መንጠራራት…” ነበር ያለን:: መሃላችን የገባው ክርክርና ፍጭት አብሮ ተቀምጦ፣ አብሮ ካለመሆን ቢታደገንም እርሱን ማሳመን ግን ጥቁር ግዙፍ ድንጋይ እንደመሸከም ነበር::

ለዛሬው ሀሳብ መነሻ ስለሆነኝ ብቻ ነበርና የኛው ውል አልባ ውሽንፍር፣ ከደረሰበት ቋጥረን በይለፍ እንዝለለው:: አጋጣሚውን ለማንሳት ያስፈለገኝ አንድም ወዳጄን መሰል በርካታ ተሳልቆ አሳላቂ የሚዲያ አዋቂዎችን በመመልከቴ፣ እነርሱንም ባካትት ብዬ ነው:: ከላይ ይኼው ወዳጃችን እንዳነበበልን ዜናው የእውነትና ሊሆን ያለም ነገር ነው:: ምናልባትም ብዙዎቻችን ሰምተን አሊያም ከሚዲዎች ተከታትለነውም ሊሆን ይችላል:: ይሁንና በዚህ ሀሳብ ዙሪያ ጥቂት ለመሽከርከር ወድጃለሁ:: እንዴት፣ ወዴትና ከወዴት… ከሚሉና መሰል ዲስኩሮች ጋር ብንደሰኩር መልካም ነው::

ሀሳቡን ማን ከወዴት አመጣው? ማንም ያምጣው… ብለን ከማለፍ በእግረ መንገድ ወጣቱንም ልናመሰግነው ይገባል:: የደቡብ ፈርጥ፣ የኢትዮጵያ እንቁጥ የሆነውን፣ አርቲስቱን ወንድዬ አበበን (ወንድዬ ኮንታ) ብዙዎቻችን በዋናነትም በባሕል ሙዚቃዎቹ እናውቀዋለን:: በለምለሟና አረንጓዴዋ፣ የገነት አጸድ መሳይ ተፈጥሮን በታደለችው፣ በኮንታ ጥቅጥቅ ደኖች መሃል ተገኝቶ ይህን የፊልም መንደር ስለመገንባት ለብዙ ጊዜያት ያብሰለስላል:: ግን እንኳንስ ለዚህ ለሌላም ድንቡሎ በኪሱ አልነበረውም::

አለመኖር ግን በኪስ ሞልቶ በጭንቅላት ባዶ መሆን ነው:: ጭንቅላትን በቆንጆ ሀሳብ ከሞሉት የዚያኔ የናጠጡ ቱጃር ከመሆን በላይ ነው:: ለብዙ ጊዜያት ሲያብሰለስል፣ ይህን ሀሳቡን እውን የሚያደርግበትን መንገድ ሲነድፍ ቆይቷል:: ከትልልቅ ባለ ሀብቶች እስከ ሙያው ባለቤቶች፣ ከኪነ ጥበብ አፍቃሪያን…ሁሉንም በመቅረብና በማቅረብ ተራራውን መውጣት ጀምሯል:: ወደላይ ለመውጣት ሲያስብ ከስር ድጋፍ ከሆኑት መካከል የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መኖራቸውም ታውቋል::

እኛም ሀሳቡ የሀሳብ መና ሊሆን ይችላል ብለን እንዳንሰጋ፣ እርሱም ወደኋላ እንዳይመለስና እኔም ይህቺን ቁንጽል እንድጽፍ ሞራል የሆነኝ የጅምር እርምጃው ነው:: በጅምሩም እንደመነሻ “ቶካ የፊልም መንደር እና ኢኮ ቱሪዝም ኃ/የተ/የግ/ማኅበር” በሚል ስያሜ ቦታውን ተረክቧል::

ወደቀጣይ ሥራዎች ስለመግባቱም ተነግሯል:: በውብ ተፈጥሮ ባሸበረቀችው በኮንታ ኤላ አንቻኖ ወረዳ፣ በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በ43 ሺህ ካሬ ላይ የሚያርፈው ይህ መንደር ግቡ የፊልም ኢንዱስትሪው ብቻ አይደለም:: ኢኮኖሚውንና ቱሪዝሙንም ያካተተ ነው:: በዚህ ሥፍራ ላይ በሚገኘውና እንደ አማዞን ጥቅጥቅ ባለው የዘንባ ጫካ መልካም ጅምሮች ይታያሉ::

“ኢትዮ ኮሊውድ” በተሰኘው ሀሳባዊ ምስል ውስጥ በዋናነት ሁለት ጣምራ ሰንደቆች የሚውለበለቡበት ነው:: አንደኛውና የመጀመሪያው ነገር አሁን የምናወራለት የፊልም መንደር ነው:: ሁለተኛው ደግሞ የኢኮ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ መንደር ነው:: በሁለቱም ሕብረ ቀለማት ውስጥ እንደሚኖሩበት በእቅድ ተነድፈው ከተካተቱባቸው ነገሮች መካከል አንደኛው የሥነ ጥበባት ትምህርት ቤት መገንባት ነው::

ሆስፒታልና የባሕላዊ ሕክምና መስጫ ተቋም ይኖርበታል:: ሙሉ የሲኒማ ስቱዲዮ፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያ፣ እንዲሁም ለአርቲስቶች የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች የሚገነባበትም ይሆናል:: የስዕል ጋለሪ፣ የመጽሐፍት መደብሮች፣ የባሕላዊ አልባሳት ማምረቻና የገበያ ማዕከልም ያካተተ ምሉዕ መንደር ለማድረግ፣ ስፖርትን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ዘርፎችም ይሠሩበታል::

ዓለም አቀፍ የቱሪስቶች መንደር ለማድረግም የሐይቅ ላይ የጀልባ መዝናኛዎች፣ የመናፈሻ ሎጅና የእንግዳ ማረፊያዎችን በመገንባት ጉዞ ወደ ታላቋ ኢትዮጵያ መሆኑ ነው:: እያንዳንዱ የሚሠሩ ነገሮችም፤ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ጥበቦችን በመጠቀምና ለመጠቀም እንጂ አሁን ያለንበትን በመድገም የበረሀ አውሎንፋስ ለመምሰል አይደለም::

“ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሀምሳ ሰው ጌጡ ነው::” የሀሳቡ ባለቤት የሆነው አርቲስት ወንድዬ ራሱን እንደ አንድ ሰው ቆጥሮ ሀምሳውንም ሎሚዎች ስለመሸከም ቢሆን ያሰበው፣ ቤሳ ቤስቲን የለውምና በእውን ቀርቶ በሕልሙ እንኳን ለማየት ባልተመኘው ነበር:: ግን ራሱን ሳይሆን ኢትዮጵያን፣ በኢትዮጵያ ውስጥም ኢትዮጵያዊውን ሁሉ ተመልክቶ ነው::

ከባለሀብቱ እስከ ተራው የቀን ሠራተኛ በዓባይ ግድብ ላይ የነበረውን ርብርብ ያውቀዋል:: ከፋሲለደስ እስከ አክሱም፣ ከጀጎል ግንብ እስከ ጢያ ትክል ድንጋይ የነበረውንም ጥበብ ሊዘነጋው አይችልም:: ትልቁ አድዋ ያለው ጭንቅላት ላይ ነውና ይህንን ድል ለማድረግ ከተቻለ ለኢትዮጵያዊ ቀሪው ሁሉ እዳው ገብስ ነው:: የኛ ችግር መቻልን መፍራት እንጂ አለመቻል አይደለም::

ለእንዲህ ያለው ነገር ማበረታቻ ስንፈልግ “ሮምም እኮ በአንድ ቀን አልተገነባችም” እንላለንና እኔም ይህቺን አባባል ልዋስ እወዳለሁ:: “ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል” የምትለዋን ደግሞ ለተስፋችን ብርሃን ልመርቃት:: ያኔ ገና ጥንቱን ላሊበላን የሠሩ እጆች ላይ ምን ነበር? የትኛውንም ቴክኖሎጂ፣ አንድም ዶላር ሳይዙ አልነበረም እንዴ የገነቡት:: ታዲያ ምነው ደርሶ አጋዥ፣ አመሃኝቶ ድህነት እግር ላይ የሙጥኝ ማለት…ትልቁና ዋናው ነገር ሁሉንም ሰበብ አስባቦች አርቆ አንድ ብሎ መጀመር ነው::

ለሁሉም ነገር፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ከባዱ ነገር መጀመር እንጂ ለፍጻሜው የሚሰለፍ ብዙ ነው:: እኛ ጀመረን ባንጨርሰው እንኳን ቀጣዩ ትውልድ መሠረቱን እየተመለከተ አይዘለውም:: ሳይሞክሩና ራስን ሳይፈትሹ አንችለውም ብሎ መደምደም፤ የችሎታ ማነስ ሳይሆን የአዕምሮ ሽንፈት ነው:: አድዋ የጭንቅላት እንጂ የመሳሪያና የቁሳቁስ ኃያልነት ያመጣው ድል አለመሆኑን አንዘንጋው::

እስከመቼ ነው ድህነታችንን ያለመቻላችን ሁሉ ሰበብ አድርገነው የምንኖረው? ያ ሲሞግተን የነበረው ወዳጃችን ብቻውን አይደለም:: መረጃው ከተሰራጨ በኋላ ሰዎች ምን ይላሉ የሚለውን ለማወቅ ፈለኩና ለዚህም ከማህበራ ሚዲያዎቻችን የተሻለ ሌላ ጆሮ መቀሰሪያ ቦታ አልነበረኝም:: የተቀደሰ ሀሳብና ጅምር መሆኑን እየገለጹ ይበል የሚያሰኝ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ የሚያንጓጥጡና እንደ ወዳጃችን በፌዝ የሚስቁም እልፍ ናቸው::

ልክ እንደ ወዳጃችን ሁሉም ለዚህ እንደምክንያት የሚያስቀምጡት ሁለት ነገሮችን ነው…በድህነትና ሰላም ማጣት ውስጥ ቆርፍዶ የምን የፊልም ኢንዱስትሪ ነው… ባለበት ትንሽዋ ነገር እንኳን ራሱን ችሎ ለመቆም ያልቻለን የፊልም ኢንዱስትሪ አሁን በአንድ ጊዜ በዚህ መጠን ማሰብ መቼም የማይሆን ነው መሰል ሀሳቦች ናቸው::

ብዙ ጊዜ ደጋግመን ብለነዋል፤ ፊልም አሊያም ኪነ ጥበብ የቅንጦት ኢንዱስትሪ አይደለም:: ቢሆንለትና ቢያረግለት ጥቅሙ ለዚህ ተራበ ተጠማ ብለን ሰበብ ለምናደርገው ሕዝብም ጭምር ነው:: የታሰበው ነገር ይሁንም አይሁንም ሀሳቡ ግን ሀገራዊ ኢኮኖሚን ከፍ የሚያደርግ እንጂ በራሱ ራሱን ብቻ በቅንጦት ዓለም የሚያንፏልልበት አይደለም::

የዚህ ፊልም መንደር እውን መሆን ከሰላም ጋር ምን አገናኘው? ኢንዱስትሪው ከፍ በማለቱ የተራበውን በምን ያስቆጨው ይሆን? ኢንዱስትሪውን ለመገንባት የታቀደው ለሕዝብ ከሚውል የመንግሥት በጀት ላይ ቢሆን ኖሮ ሀቅ ነው እንል ነበር፤ ግን አይደለም:: ባለሀብቱን አስተባብሮ መንደሩን መገንባት በየት በኩል አድርጎ ሰላም የሚያሳጣና በተራበው ላይ ማፌዝ እንደሆን በግሌ አይገባኝም:: ይህን ያመጣብን እኮ አለመሥራታችን ነው:: ምንም ይሁን ምን በመሥራት ውስጥ የሚጠቀም እንጂ የሚጎዳ ማኅበረሰብ የለም::

አይችልም! አይሆንም! የሚለውን ከብረት የከረረ፣ ከድንጋይ የጠነከረ ሀሳብ ከአዕምሯችን ፈንቅለን ማስወጣት ይኖርብናል:: ድህነት ካሉ አዎን ድሃ ነን:: ገና በእግሩ ያልቆመ የፊልም ኢንዱስትሪ ነው ወይ ያለን፤ አዎን ገና ውሃም ያልሞቀ የፊልም ኢንዱስትሪ ነው:: አሁን እንዲህ ነው ማለት ግን ቀጥሎ እንዲያ አይሆንም ማለት አይደለም::

ዓለም ላይ የማይሆንና የማይቀየር ታሪክ ምን አለ? ዛሬ እጅን በአፍ የምንጭንባቸው ነገሮች እኮ መነሻቸው አንድ ሰው ነው:: ቶማስ ኤድሰን ዛሬ ላይ እንዲህ የተጥለቀለቅንበትን መብራት ሲፈጥር ማናችን አብረነው ነበርን? ብቻውን አሳካዋለሁ ብሎ ሲጀምር ሽቦ ያቀበለው ማንም አልነበረም:: አንድ ሰው ብቻውን ለዓለም ሙሉ መትረፍ ከቻለ እኛ ተጋግዘን ለራሳችን ለመሆን የማንችልበት ምን ምክንያት ይኖራል?

ጅምሩ ላይ መላው የዓለም ማኅበረሰብ እርግጠኛ የሆነው ኢትዮጵያ የጣሊያን ግዛት እንደምትሆን ነበር:: ከመላው ዓለም እሳቤ በተቃራኒ ቆመው “እንችላለን!” ያሉ የኛ አባቶች ግን የአድዋን ታሪክ አጻፉ:: የእነርሱ ልጆች ሆነን ግን በራሳችን ላይ እናላግጣለን:: ከወደቅንበት እንዴት ለመነሳት እንደምንችል ከማሰብ ይልቅ በምን እንደወደቅን እናብራራለን::

ለመነሳት ከማሰብ የሚወድቀውንና የወደቅንበትን መቁጠር ደስታን ሳይሰጠን አይቀርም:: ቢሆንም ባይሆንም መልካም ሀሳቦች ሲገኙ በጄ! ማለትን መልመድ አለብን:: ያለንበትን ሳይሆን ልንሆን የምንችልበትን ነው ማሰብ የሚኖርብን:: ድሃ መሆናችን ሳይሆን ከድህነት መላቀቅን የምንፈራ ነው የሚመስለው:: “ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል” የምንለው ነገር፤ የእውነትም ሞቆን ይሆን?

“ልክ እንደ ሆሊውድና ቦሊውድ…” የምትለው ዐረፍተ ነገር ነበረች ወዳጃችንን በጣም ፈገግ ያሰኘቻቸው:: እውነቱን ለመናገር ያልጠረጠርነው አፍዝዝ አደንዝዝ ይዞን እንጂ የሆሊውድ በእኛ ታሪክና ቅርስ ተማርኮ ዛሬም ድረስ ዓይኖቹን አለመንቀሉን ብናውቅ መልካም ነበር:: በየዘመናቱም በቀጥታም በእጃ ዙርም የዘረፉንን እንዳያልቅባቸው እየቆጠቡ በየፊልሞቻቸው ውስጥ እየመነዘሩ ሲጠቀሙበት እንዳሉ ናቸው::

እንኳንስ ከፊልሞቻቸውና ቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ሳይቀር አለን:: ይህን ሁሉ ያመጣው ምን እንዳለን አለማወቃችንና የምናውቀውንም እንዴት መጠቀም እንዳለብን ግራ ግብት ስላለን ነው:: እንዲህ ያለውን ሀሳብ እልፍ ጊዜ አንስተነዋል፤ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በግለሰቦችና በተናጠል፣ በየፊናው የሚመራ ሲኒማ ሳይሆን፤ ልክ እንደ ሆሊውድ ወጥ በሆነ መንገድ ሁሉንም አንድ ላይ አሰባስቦ የሚይዝ ግዙፍ ተቋም ነው::

አሁን በታሰበው ዓይነት መንገድ ሲሆን ፊልሞችም ሆኑ ማንኛውም የኪነ ጥበብ ሥራዎች ግለሰቡ በተያዘውና በመሰለው ብቻ በዘፈቀደ አይሠሩም:: ጥልቅ የሆኑ ጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ አመቺና በግለሰብ ደረጃ ለማድረግ የማይቻለውን የሚያስችል ይሆናል:: ሌላው ደግሞ የባለሙያዎች ጥምረት ነው::

እስከዛሬ ድረስ እያስተዋልን ያለነው ትልቁ ችግር፤ እያንዳንዱ በግሉ በአንድ ነገር ላይ ድንቅ ብቃት የያዘ እንደሆን ራሱን ችሎ እንጂ ከሌላው ሥር ሆኖ በጥምረት መሥራትን አይፈልግም:: በዚህ ምክንያትም አንድ ላይ ሆነው ተአምር ለመሥራት የሚችሉ የሲኒማ ባለሙያዎች በተናጠል ሲሯሯጡ እንመለከታለን:: የኢትዮ ኮሊውድ ሀሳብ አንድም ይህን ችግር ለመገርሰስ ያስችላል:: ማንም የትኑም ያህል ጎበዝ ቢሆን በተናጠል ሙሉዕነት አይኖረውም:: ጎዶሎውን ለመሙላት ቢያንስ ሌላ አንድ ጎበዝ ከጎኑ ያስፈልገዋል::

ኮሊውድ ላይ…ይህ ሀሳብ እውን ሆኖ እንመለከተው ይሆን? በማኅበራዊ ሚዲያው፣ በዚህ ሀሳብ ላይ ሲያፌዙና ሲያላግጡ ከነበሩት አንዱ፣ ከላይ በምስሉ ከምንመለከተው ፎቶግራፍ ጋር አያይዞ እንዲህ አለ፤ “የኢትዮጵያን የፊልም መንደር ስሙን ማን አሉት “ኮሊውድ” ሲል ይሳለቃል:: አዎን ኮሊውድ ነው! እኛ መሥራት ካልቻልንና ካልመሰለን፣ ለመሥራት የሚቆመውን አናት ለመኮርኮም ጊዜ ረዘመንና ገዝፈን የምንቆመው ስለምንድነው?

እኛ ስላልፈለግንና ስላልመሰለን ፀሐይ ወጥታ መግባቷን አታቆምም:: አይሆንም ለጠላት ይሁንና ይሆናል ብለን እናስብ:: ቀሪውን የጥበብ አምላክ በጥበቡ፣ ሁሉንም ጊዜ ይፍታው:: ግራም ይንፈስ ቀኝ እኔ በግሌ ኮሊውድ ላይ፣ ኮሊውድን ለማየት እሻለሁና ምኞቴ ነው:: እውን ሆኖ ለመመልከት ከቻልኩ ደግሞ ኮሊውድ ላይ የማላየው ተአምር አይኖርም ማለት ነው:: “ላይ” አንድም ምኞት፣ አንድም ከፍታ ነው:: ማን ያውቃል ኮሊውድ ላይ ተቃጥረን እንገናኝ ይሆናል:: ለሁሉም ግን ጊዜ ለኩሉ፣ ጥበብ በኩሉ ኮሊውድ ላይ ትደር!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You