በተወዳጁ የአለማችን ስፖርት እግር ኳስ ደጋፊዎች ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ አላቸው። ደጋፊዎች የእግር ኳስ ውበትና የካምቦሎጆ ድምቀት ብቻ አይደሉም። የአንድ ክለብ ወይም ብሔራዊ ቡድን የጽናት፣ የአሸናፊነትና የስኬታማነት ሚስጥር ጭምር ናቸው።
ደጋፊዎች በሁሉም የአለማችን ክለቦችና ብሔራዊ ቡድኖች እንቅስቃሴ በገንዘብ፣ በማህበራዊና በስሜታዊነት የቆሙ በመሆናቸው በየትኛውም የዓለም ማእዘን ውስጥ ባሉ በማንኛውም የስፖርት ቡድን ውስጥ ቁልፍ ተጫዋች ተደርገው ይቆጠራሉ።
ደጋፊዎች በማንኛውም ግጥሚያ ላይ የቡድናቸውን ተጫዋቾች ካላስፈላጊ ጫና ሲከላከሉ፣ ሲያጀግኑ፣ በተፎካካሪዎቻቸው ላይ ሲጮሁ፣ አሸናፊዎቹንና አስተዳዳሪዎቻቸውን በማምለክና ከቡድናቸው ብሔራዊ መዝሙር ጋር በማመሳሰል አስደናቂ የሙዚቃ ቅኝት ሲያሰሙ ቡድናቸው ራሱ በተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ማንም ያውቃል።
ታማኝ ደጋፊዎች በማንኛውም ጨዋታ ስታዲየሞች ዋና ንጥረ ነገሮች በመሆናቸው የሚወዱት ክለብ እየተሸነፈም ማበረታታት በጭራሽ አያቆሙም። ቡድናቸው የቱንም ያህል ወደ ውጤት አዘቅጥ ውስጥ እየገባ ውብ ዝማሬ አይነጥፍባቸውም። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወደ 250 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ የእግር ኳስ ቡድኖች ወይም ክለቦች የታወቁ አድናቂዎች ወይም ደጋፊዎች በዓለም ዙሪያ ሊገኙ ይችላሉ፡፡
ቀንደኛ የእግር ኳስ ደጋፊዎች በየትኛውም አለም ሊገኙ ይችላሉ። ከነዚህ መካከል ጥቂቶች ቡድናቸው በየትኛውም አይነት ውጣ ውረድና ቀውስ ውስጥ ቢገባም ዘወትር ካምቦሎጆ ተገኝተው ከመደገፍ በዘለለ ርቀት ሳይገድባቸው ሌሎች ጉዳዮቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለቡድናቸው የትኛውንም መስዋዕትነት የሚከፍሉ ጥቂት አይደሉም። እንደነዚህ አይነት ደጋፊዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስም ውስጥ ይገኛሉ። ከአርባ አመታት በላይ የቀድሞውን መብራት ሃይል የአሁኑን ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመደገፍ በልዩነት የሚጠቀሱት በቀለ ሄኒ (ኮረንቲ) ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። እኚህ አንጋፋ ደጋፊ በቅርቡ ህይወታቸው እስካለፈበት እለት ድረስ ቡድናቸውን ከአራት አስርት አመታት በላይ በየትኛውም ሁኔታ በታማኝነት ከመደገፍ አልፈው በአንድ ወቅት የቡድናቸው ወሳኝ ተጫዋች ወደ ሌላ ክለብ እንዳይዘዋወር እቤታቸውን እስከ መሸጥ ውሳኔ ላይ የደረሱ ታማኝ ደጋፊ ሆነው በሌሎች ክለብ ደጋፊዎችም ይሁን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሁሌም በክብር ይታወሳሉ።
የዛሬው ስፖርት ማህደር አምዳችንም ወደ ስፔን አቅንቶ በአለም ዙሪያ በተለየ ሁኔታ የሚታወስ አስደናቂ የእግር ኳስ ደጋፊን ታሪክ ያወሳል። ይህ የተለየ ደጋፊ ማን እንደሆነ የስፖርቱ ቤተሰብ ከመንደርደሪያው በቀላሉ ሊገምት ይችላል። ቪሴንቴ ናቫራ አፓሪቺዮ – አይነ ስውሩ ደጋፊ! በአለም ዙሪያ ገናና ስም ያለው እግር ኳስ አፍቃሪ ነው።
አፓሪቺዮ የስፔኑን ክለብ ቫሌንሲያ የውጤት ከፍታና ዝቅታን የተመለከተ፣ በክፉውም በደጉም ዘመን ከክለቡ ጋር ሁሉንም ስሜቶች የተጋራ አንጋፋ ደጋፊ ነው። እግሮቹም ለዘመናት ወደ ሜስታላ ለማቅናት አልደከሙም።
በስታድየሙ ፊትለፊት “ትሪቡና ሴንትራል” በሚባለው በ 15ኛው ረድፍ በቁጥር 164 መቀመጫ ላይ የአመት ትኬት ስለሚገዛ የስፖርቱ ቤተሰብ በዚያ ቦታ ላይ ከአፓሪቺዮ ውጪ የተቀመጠ ደጋፊን ማስታወስ አይቻለውም።
ይህ ክለቡን በታማኝነት ከልቡ በመነጨ ስሜት ሲደግፍ የኖረ ሰው ከአርባ አመታት በፊት በህይወቱ ነገሮች መልካቸውን ቀየሩበት። አንጋፋው ደጋፊ የሚወደውን ክለብ በአይኑ እየተመለከተ እንዳይዝናና አይኑ ላይ የጤና እክል ገጠመው።
አፓሪቺዮ በአይኑ የኋላ ክፍል የምትገኝ ስስ አካሉ ነገር (Retina) ላይ ችግር መኖሩን ያወቀው አይኑ ከተጎዳ በኋላ ነበር። ህክምናው በመዘግየቱም የአይን ብርሀኑን መልሶ ለማግኘት ሳይታደል ቀረ። የሜስታላን ደጋፊን የስቴድየም ድባብ በአይኑ እየተመለከተ፣ በአፍንጫው እያሸተተና በእጁ እየዳሰሰ ልባዊ ድጋፉን ለክለቡ ሲቸር የነበረው መልካም ዘመን ግን አይኑ ቡድኑ ሲጫወት ማየት ባለመቻሉ ታሪክ ሆኖ አልቀረም።
ይህ ደጋፊ አይነስውር ሆኖም ለዘመናት ልባዊ ድጋፉን ሲሰጠው ከኖረው ክለቡ አላራራቀውም። የአይኑ ጨዋታዎችን አለማየት ከካምቦሎጆ ደጅ አላስቀረውም። የአመት የስቴድየም መግቢያ ትኬት እየቆረጠና ቦታው ላይ እየተቀመጠ በሜስታላ መታደሙን ቀጠለ። አይኑ ባያይም በሌሎች የስሜት ህዋሳቶቹ የስታድየሙን ድባብ በመካፈሉ ገፋበት።
አፓሪቾ እኤአ 2017 ላይ ባጋጠመው ህመም የሚወደውን ክለብ ትቶ ወደማይቀረው ሞት አመራ። ብዙዎቹ ደጋፊዎች ግን የሱን መቀመጫ ካለሱ ሲመለከቱ እንባቸው ይቀድማቸው ነበር። አንጋፋው ደጋፊ አጠገባቸው ባይኖርም እንኳን ፅናቱን ግን ተምረውበታል። ክለቡ ቫሌንሲያም ቢሆን የዚህን አስደናቂ ደጋፊ ታሪክ እንደ ቀላል አልተመለከተውም። ፅናቱን የሚያወድስ እንዲሁም የደጋፊዎችን ስሜት የሚመልስ ድንቅ ስራ ሰርቷል። ሁሌም የሚታወስበትን አስደናቂ ታሪክም መቼም እንዳይረሳ አድርጎ ለመጪው ትውልድ አኑሮለታል።
ቫሌንሲያ ክለብ የአንጋፋውን ደጋፊ ቪሴንቴ ናቫራ አፓሪቺዮ ሀውልት አሰርቶ እርሱ በሚታወቅበት በ”ትሪቡና ሴንትራል” በሚባለው በ 15ኛው ረድፍ በቁጥር 164 መቀመጫው ላይ አስቀምጦ የዘለአለም የክለቡ ጨዋታ ላይ እንዲታደም አድርጎታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም