የመጀመሪያው የብር ሜዳሊያ በበሪሁ አረጋዊ ተመዘገበ

በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ በወንዶች 10ሺ ሜትር ማግኘት ችላለች። ይህም ከ1972 ከምሩፅ ይፍጠር የነሐስ ሜዳሊያ ጀምሮ ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው ኦሊምፒኮች ሁሉ በ10ሺ ሜትር ከሜዳሊያ ውጪ እንዳትሆን ያስቻለ ነው።

በትናንት ምሽቱ ፍልሚያ ኢትዮጵያውያን ወርቁ ባይቀናቸውም ከውድድሩ መጀመሪያ እስከ መጨረሻ በመተጋገዝ ያሳዩት የቡድን ሥራ ብዙዎችን አስደስቷል። ያም ሆኖ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች የተሳሳተ የታክቲክ ስሌት የርቀቱን የሦስት ጊዜ የዓለም ቻምፒዮን ዑጋንዳዊውን ጆሽዋ ቺፕቴጌ ማስቆም አልቻለም። በዚህም ቺፕቴጌ 27:01.17 በሆነ ሰዓት 2008 ቤጂንግ ላይ በቀነኒሳ በቀለ የተመዘገበው የኦሊምፒክ ሪከርድ በማሻሻል በ26:43:14 ወርቁን አጥልቋል። ወጣቱ አትሌት በሪሁ አረጋዊ በአስደናቂ ጥረት በ26:43:44 የብር ሜዳሊያውን ወስዷል። ዮሚፍ ቀጄልቻና ያለፈው ኦሊምፒክ የርቀቱ አሸናፊ ሰለሞን ባረጋ ስድስተኛና ሰባተኛ ሆነው ፈጽመዋል። በውድድሩ ያደረጉት ጥረትና ያሳዩት የቡድን ሥራ ግን ትልቅ ዋጋ ነበረው።

በታሪካዊው አትሌት ማሞ ወልዴ የ1968 ሜክሲኮ ኦሊምፒክ በብር ሜዳሊያ የጀመረው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ወንዶች ድል በማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር የ1980 ሞስኮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያው አንድ ብሎ ጀምሯል። የርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ክብር በጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ከአትላንታ እስከ ሲድኒ፣ በአቦ ሸማኔው ድንቅ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከአቴንስ እስከ ቤጂንግ እንዲሁም በወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ገድል ጎልቶ መታየት ችሏል። ዘንድሮ ግን ዳግም የርቀቱ ክብር ከኢትዮጵያውያን አምልጧል።

በርቀቱ ትልቁ የኢትዮጵያ ውጤት አቴንስ 2004ና ቤጂንግ 2008 ቀነኒሳ በቀለና ስለሺ ስህን ተከታትለው በመግባት ወርቅና ብር ያጠለቁበት ነው። በአራት ተከታታይ ኦሊምፒኮች ከ1996- 2008 የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ናት። ስድስት ነሐስ በማግኘትም ቀዳሚ ስትሆን በብር ሜዳሊያም ከፊንላንድ በአንድ ዝቅ ብላ በ3 ሜዳሊያ ተከታይ ነች። በሪሁ አረጋዊ ትናንት ምሽት ያጠለቀው የብር ሜዳሊያ ከማሞ ወልዴና ስለሺ ስህን ጋር ታሪክ እንዲጋራ አድርጎታል።

ቺኮስላቫኪያዊው ኤሚል ዛቶፔክ በተከታታይ ወርቅ በማጥለቅ የመጀመሪያ ነው። ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለና በሞ ፋራህ ይህን ታሪክ ተጋርተዋል። ከኃይሌ ገብረሥላሴ 1996 የአትላንታ ድል ጀምሮም በርቀቱ አንዴ ያሸነፈ አትሌት በቀጣይ ኦሊምፒክ ሌላ ድል ደግሟል። ይህም በቀነኒሳና ሞ ፋራህ ወርቃማ ዘመንም ቀጥሏል። ሰለሞን ባረጋ በዚህ ረገድ ዘንድሮ ሊሳካለት አልቻለም።

ፊንላንድ በ10ሺ ሜትር ታሪክ 7 ወርቅ፣ 4 ብር፣ 4 ነሐስ በማስመዝገብ ቀዳሚ ስትሆን፣ ኢትዮጵያ በ6 ወርቅ፣ 4 ብር፣ 6 ነሐስ ትከተላለች።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You