አዲስ አበባ ፦ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታዎችን በስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለማከናወን መታቀዱን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በትላንትናው ዕለት የተከበረውን የዓለም የውሃ ቀንን ምክንያት በማድረግ በካፒታል ሆቴል በተደረገው ውይይት እንደተገለጸው፤ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎት ግንባታዎችን ለማከናወን ዕቅድ ተይዟል።
በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ምክትል ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት፤ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚካሄደው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ይሆናል። ይህን ዕቅድ በታሰበው መልኩ እውን ለማድረግ መንግሥት ከመደበው በጀት በተጨማሪ ከተለያዩ የልማት አጋሮች፣ ከህብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎና ከአበዳሪ ተቋማት የረጅም ጊዜ ብድርና አነስተኛ ወለድ ሀብት ለማሰባሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል።
በ ‹‹ዋን ዋሽ» (የአንድ ቋት) አካውንት የብሄራዊ ፕሮግራም እስካሁን አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ መቻሉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የተገኘው ገንዘብ ከሚቀጥለው የበጀት ዓመት ጀምሮ ወደሥራ ለመግባት መነሻ ይሆናል ብለዋል። በኢትዮጵያ የውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ችግሮች ነበሩ ያሉት ዶክተር ነጋሽ፤ ከነዚህ ተግዳሮቶች መሀልም የዘርፉ የማስፈጸም አቅም ዝቅተኛነት በዋንኛነት ይጠቀሳል ብለዋል።
ለዚህ አበይት ችግር መፍትሄ ለመስጠትም በአሁኑ ጊዜ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዲስ አደረጃጀት የውሀ ልማት ኮሚሽን የተቋቋመ ሲሆን፤ ዘርፉን ከአንድ ዳይሬክቶሬት ወደ ስድስት በማሳደግ ለሥራው ትኩረት መስጠቱንም አስታውሰዋል።
በዕለቱ በተካሄደው የውይይት መድረክ የሁለተኛው የአንድ ቋት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሳኒቴሽንና ሀይጂን ሰነድ ትውውቅ ይፋ ሆኗል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ በተከበረው ዓለም አቀፉ የውሃ ቀን «ንጹህ የመጠጥ ውሃና የሳኒተሪ አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ» የሚል መሪ ሃሳብ አለው። መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ የከተሞች መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፌዴሬሽንና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ትብብር የተዘጋጀ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
መልካምስራ አፈወርቅ